የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ በሐምሌ ወር አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ከአፍሪካ ኅብረት አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ፣ ዋይት ሀውስ አስታወቀ፡፡ በሥራ ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ጎብኝቶ አያውቅም፡፡
የበርካታ አገሮች መሪዎች ይታደሙታል ተብሎ የሚጠበቀው ከሐምሌ 5 እስከ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ጉባዔ ባራክ ኦባማ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይሁንና የዋይት ሀውስ መግለጫ ፕሬዚዳንቱ ለዚሁ ጉባዔ ስለመምጣታቸው የሚያወሳው ነገር የለም፡፡
ጉባዔው በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብን ይተካል የተባለለት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለመተግበር የሚያስችሉ የፋይናንስ ምንጮች ላይ ይመክራል፡፡ ይህንኑ ጉባዔ ለመከታተል ከ5,000 በላይ የአገር መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የግል ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራትና የሚዲያ ተወካዮች አዲስ አበባ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡
የዋይት ሀውስ የፕሬስ ጉዳዮች ኃላፊ ጆሽ ኧርነስት የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት አሜሪካ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከርና በአፍሪካ ኢንቨስት የማድረግ ቁርጠኝነት ያላት መሆኑን ለማሳየት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮችና ዜጎች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያመጡ፣ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲገቡና የደኅንነት ይዞታቸውን እንዲያጠናክሩ አሜሪካ የምታደርገው ጥረት አካል እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ በኬንያ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ጉባዔ ከተከታተሉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ታውቋል፡፡ የባራክ ኦባማ አባት ኬንያዊ ቢሆኑም ይህ ጉዟቸው እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ነው፡፡