ሰሞኑን የተሰማው የሁለት ፖለቲከኞች ግድያ ጉዳይ በጣም ያሳስባል፡፡ በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ ከተማና በትግራይ ክልል በሁመራ በሰማያዊ ፓርቲና በዓረና ለትግራይ ሉዓላዊነት ፓርቲ አባላት ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ የሚወገዝ ከመሆኑም በላይ የገዳዮቹ ማንነት በአስቸኳይ ተጣርቶ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ የምርጫው ከፊል ውጤት ተነግሮ ዜጎች ወደ መደበኛ ተግባራቸው በተመለሱ ማግሥት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ግድያ ሲሰማ፣ ከማንም በላይ መንግሥትን ሊያሳስብ ይገባል፡፡ በዚህም ምክንያት የፖለቲከኞቹ ገዳዮች በአስቸኳይ መታወቅ አለባቸው፡፡ ለፍርድም ይቅረቡ፡፡
መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የማስጠበቅ፣ ድንገተኛ አደጋ ከደረሰም ተከታትሎ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ኃላፊነት አለበት፡፡ ለሕዝብም የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባልና በደብረ ማርቆስ ከተማ ፓርቲውን ወክሎ ለምርጫ የተወዳደረው አቶ ሳሙኤል አወቀ፣ ከጥብቅና ሥራው ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ችግር በደንበኞቹ ግድያ እንደተፈጸመበት የደብረ ማርቆስ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ እነዚህ ደንበኞች የተባሉት ተጠርጣሪዎች እነማን ናቸው? ይኼ ግልጽ መሆን አለበት፡፡
ሟች ሳሙኤል በሕይወት በነበረበት ወቅት በተደጋጋሚ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ድብደባ ይፈጸምበት እንደነበርና ከዚያም አልፎ ተርፎ የመግደል ሙከራ እንደተካሄደበት ማስረጃ እንዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በፌስቡክ ገጹ ላይም ሕይወቱ አደጋ ላይ መውደቁን ገልጾ እንደነበር ፓርቲው አስታውቋል፡፡ መንግሥት ኃላፊነት ተሰምቶት ጥበቃ እንዳላደረገለትና ለሕልፈቱ የመንግሥት አካላት ተባባሪ ነበሩ በማለት ወንጅሏል፡፡ ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ በማለት እንደማያላዝንም አስታውቋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የአባሉን ገዳዮች ማንነት ማጣራትም ሆነ ለፍርድ መቅረብን ችላ ቢለውም፣ መንግሥት ግን ኃላፊነት ስላለበት ገዳዮቹን ለሕዝብ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ለፍርድ ማቅረብም አለበት፡፡
በትግራይ ክልል የምዕራብ ዞን የአረና/መድረክ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ታደሰ አብረሃ፣ ማንነታቸው ባልታወቀ ግለሰቦች አሰቃቂ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ተሰምቷል፡፡ መድረክ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት በኢሕአዴግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ድብደባ ተፈጽሞባቸው እንደነበር፣ ሰሞኑን በደረሰባቸው ድብደባም ሕክምና እንዳያገኙ ተደርገው መሞታቸውን፣ ተጠርጣሪ ገዳዮችም ሆን ተብሎ እንዲያመልጡ መደረጉን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ መንግሥት የአቶ ታደሰን ገዳዮች ማንነት አጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
ምርጫው በሰላም ተጠናቆ ሕዝቡ ወደ ዕለት ተዕለት ተግባሩ ከተመለሰ በኋላ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለት አባላት በቀናት ልዩነት ተገደሉ ሲባል ያስደነግጣል፡፡ የፖለቲካው ጽንፍ ጫፍና ጫፍ በረገጠበት በዚህ ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለት አባላት መገደል ሲሰማ ሰላማዊውን ድባብ ይረብሻል፡፡ የምርጫውን ውጤት ያልተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ቅሬታዎችንና ተቃውሞዎችን ቢያሰሙም፣ ለብጥብጥና ለሁከት የሚዳርጉ ክስተቶች አልተስተዋሉም፡፡ በዚህ መሀል ግን የተቃዋሚ ፓርቲ ሁለት አባላት ሲገደሉ መንግሥት ከማንም በላይ ሥራዬ ብሎ በአስቸኳይ አጣርቶ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የተቀሰሩ ጣቶች ወደ ራሱ ይጠቁማሉ፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየታዩ ያሉ እሰጥ አገባዎችም ከሚገባው በላይ ይህንን ሥጋት እያመለከቱ ናቸው፡፡
ሁሌም እንደምንለው ዜጎች ከምንም ነገር በላይ የሚተማመኑት በሕግ የበላይነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት የሚታየው ሥርዓት አልበኝነት ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ሲንሠራፋ የሕግ የበላይነትን የሚጋፋው ሕገወጥነት ይነግሣል፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት ዜጎችን ከሕገወጦችና ከአጥቂዎች መከላከል ነው፡፡ ሕገወጦች ተገቢ ያልሆነ ተግባር ሲፈጽሙም ለሕግ መቅረብ አለባቸው፡፡ ተጎጂዎችም ፍትሕ ሊያገኙ ይገባል፡፡ የሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዳዮች ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች በሚገባ ተጣርተው ለፍርድ መቅረብ የሚኖርባቸው፣ ሕገወጦች ከሕግ በታች እንደሆኑ ማሳየት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡
የሁለቱ ዜጎች ሕልፈት አላስፈላጊ ከሆነ የፖለቲካ ፍጆታነት ወጥቶ በትክክለኛው ሕጋዊ መንገድ ሊያዝ ይገባዋል፡፡ አሁን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ከመጠን በላይ ተለጥጦ የማያስፈልግ አቅጣጫ እንዲይዝ የሚፈለገው የሁለቱ ሟቾች ጉዳይ ፍትሕ ያስፈልገዋል፡፡ አገር የሚያስተዳድር መንግሥት እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ውጤታማና ትክክለኛ ፍትሕ እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ሲዘገይ ግን ቀንበሩ እየከበደ የሚመጣው በራሱ ላይ ነው፡፡ ፕሮፓጋንዳውም ከባድ ነው፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሞቱባቸው አባላቶቻቸው መንግሥትን ተጠያቂ እያደረጉ ነው፡፡ መንግሥት የተፈጸሙትን ግድያዎች እንዳላየ ሆኖ አልፏል እያሉ ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ የማወቅ መብት ስላለው እውነቱ ሊነገረው ይገባል፡፡ እውነቱ የሚነገረው ደግሞ የገዳዮቹ ትክክለኛ ማንነት ተገልጾ ለፍርድ ሲቀርቡ ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳ በሕግ ፊት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን ወንጀለኝነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን የማቅረብ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ መንግሥት ግን ለሕዝብ የተጠርጣሪዎቹን ማንነት በአስቸኳይ አጣርቶ ለፍርድ ማቅረብ አለበት፡፡ በአስቸኳይ፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ የሚወቀስበት የፖለቲካ ምኅዳር መጣበብና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ ነው፡፡ በምርጫው ማግሥት ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫውን በአፈና ውስጥ ማካሄዳቸውን ሲናገሩ ነበር፡፡ ከዚያም በፊት የፖለቲካው ምኅዳር መጣበብ በተደጋጋሚ የተነሳ አጀንዳ ነው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ የግድያ ዜናዎች ሲሰሙ ግን የብዙዎችን ጆሮ ያቆማሉ፡፡ በአገሪቱ ላይ ጥርጣሬን ይፈጥራሉ፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመተማመን ያሰፍናሉ፡፡ ዜጎች በሕግ የበላይነት ላይ መተማመን እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት የፖለቲከኞቹን ገዳዮች ማንነት በአስቸኳይ አጣርቶ ለፍርድ ያቅርብ!
በአቶ ሳሙኤል አወቀና በአቶ ታደሰ አብርሃ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ጥልቅ ሐዘናችንን እየገለጽን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡