Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በርካታ የቻይና ፋብሪካዎች ነቅለው ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቻይና መንግሥት ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ትኩረት እንዲደረግ፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረጉ ፋብሪካዎች ደግሞ ተነቅለው ወደ አፍሪካ እንዲሄዱ ማዘዙ ተሰማ፡፡ ከአፍሪካ አገሮች በተለይ ግብፅና ኢትዮጵያ ተመርጠዋል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዕድገት ይበጃሉ ያላቸውን ፋብሪካዎች ለመቀበል፣ ከቻይና ናሽናል ዴቨሎፕመንትና ሪፎርም ኮሚሽን ጋር ለመደራደር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የቻይና መንግሥት ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከአገር ወጥተው እንዲሠሩ ውሳኔ ያሳለፈው፣ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል በማለቱ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በቻይና የአገልግሎት ዘርፍን ለማሳደግና ከዚህ ቀደም ርካሽ የነበረው የሰው ኃይል በአሁኑ ጊዜ እየተወደደ በመምጣቱ፣ ፋብሪካዎቹ ከአገር ወጥተው በማደግ ላይ ባሉት ኢትዮጵያና ግብፅ እንዲተከሉ መመርያ ማስተላለፉ ተነግሯል፡፡

ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ የተመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለአገሪቱ ዕድገት ወሳኝ የሚባሉ ፋብሪካዎችን በመምረጥና የቻይና መንግሥት ሊያቀርብ ስለሚችለው የፋይናንስ ሁኔታ ድርድር እንዲያደርግ፣ ኃላፊነቱን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መስጠቱ ታውቋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ የሚመሩት የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደ ቻይና ተጉዞ፣ ከቻይና ብሔራዊ ዴቨሎፕመንትና ሪፎርም ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር የመጀርያውን ድርድር ማካሄድ እንደሚጀምር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና በማላቀቅ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መሠረት ላይ ለማሳረፍ ያቀደው የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ለቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ ለስኳር ልማትና ለኬሚካል ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡

ይህንን ዕቅድ ለማሳካትም በዶ/ር አርከበ እቁባይ የሚመራው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ በአሥር ቢሊዮን ዶላር ወጪ በተለያዩ ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም ላይ ይገኛል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ የሚመረጡት የቻይና ፋብሪካዎች በእነዚህ የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ወይም ራሳቸው በሚያቋቁሟቸው የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ፋብሪካዎቻቸውን እንዲተክሉ እንደሚደረግ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት አመቺ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት ኢንቨስትመንት በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተዋናዮችን ለማረበታታት ያወጣቸው በርካታ ሕጎችና ማበረታቻዎች፣ እንዲሁም በአገሪቱ ያለው የሰው ኃይል አገሪቱን ተመራጭ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች