Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየእነ አቶ መላኩ ፈንታ ክስ ለሁለተኛ ጊዜ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አስነሳ

የእነ አቶ መላኩ ፈንታ ክስ ለሁለተኛ ጊዜ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

በቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ በከባድ ሙስና የተከሰሱ ነጋዴዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የጉምሩክ አዋጅ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል ወይስ አይገባም በሚለው ጉዳይ ላይ ለመወሰን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉዳዩን መራለት፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክሱን መሠረት ያደረገው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 411 (የመንግሥት ሥራን ለማያመች አኳኋን መምራት) እና በተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 ላይ ነው፡፡ ይሁንና አዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 በቀድሞው ሕግ በወንጀልነት የተፈረጁ ድርጊቶችን የሚሽር ነው፡፡ ተከሳሾቹም ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ጥያቄ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 22(2) ላይ የወንጀል ክስ የቀረበበት ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ፣ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚ እንደሚሆን ስለሚደነግግና የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5(3)ም በተመሳሳይ ይኼንኑ የሚደነግግ በመሆኑ፣ በአዲሱ ሕግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተሻሩት አንቀጾች ነፃ እንዲወጡ ነው፡፡

ይኼን ጥያቄ ካቀረቡት ተከሳሾቹ መካከል አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ (የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር)፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር (የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት)፣ አቶ ስማቸው ከበደ (የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት) እና ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ (የአዲስ ካርዲያክ ሆስፒታል መሥራችና ባለድርሻ) ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ፍቅር ማሩ የተከሰሱት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር የሕክምና ዕቃዎችን በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ አስገብተዋል ተብለው ነው፡፡ በአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ይኼ ድርጊት በገንዘብ የሚያስቀጣ እንጂ፣ የወንጀል ድርጊት ባለመሆኑ ነፃ መውጣት እንዳለባቸው ተከራክረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ግን ድርጊቱ ኮንትሮባንድ በመሆኑ ይኼ ድርጊት ግለሰቡን በወንጀል ከመጠየቅ አያድናቸውም ሲል ተከራክሯል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል  ሕግ አንቀጽ 411 አሁንም እንዳልተሻረ አስታውሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ፍርድ ቤቱ የተከራካሪ ወገኖችን ክርክር ከሰማ በኋላ አዲሱ አዋጅ ተከሳሾቹን ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለውን ጭብጥ መርምሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ በቀድሞው አዋጅ ወንጀል የነበሩ ድርጊቶች መሻራቸውን ማረጋጡን ገልጿል፡፡ ይሁንና በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 182 ላይ ‹‹በሌሎች ሕጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ይኼ አዋጅ ከፀናበት ቀን በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረው ሕግ መሠረት ፍፃሜ ያኛሉ፤›› ተብሎ መደንገጉ ልዩ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስገንዝቧል፡፡ የወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ሕግ በመሆኑና የጉምሩክ አዋጅ ደግሞ ልዩ ሕግ በመሆኑ፣ በመርህ ደረጃ ልዩ ሕግ ከጠቅላላ ሕግ ቅድሚያ ተሰጥቶት ተግባራዊ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ሕግ በሕግነት ፀንቶ የማይቆም በመሆኑ፣ አዲሱ ሕግ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑ መመርመር እንደሚያስፈልግ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በፍርድ ቤቱ ዕይታ የአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ አንቀጽ 182 በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጡት አንቀጽ 9፣ 13 (ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሕግ ስለመሆኑና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚፃረር ማንኛውም ሕግና ውሳኔ እንደማይፀና ይደነግጋሉ) እና 22 ጋር የሚጣጣም ባይሆንም፣ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የሌለው በመሆኑ የዚሁ ሥልጣን ባለቤት የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን መርምሮ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም፣ ውሳኔውን ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲያቀርብ መርቶታል፡፡

ይኼው ክስ ከዚህ ቀደም ባስነሳው ሌላ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመርያ ደረጃ ሥልጣን እንዲታይ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8(1)፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ይግባኝ የመጠየቅ መብት የሚጥስ ነው ተብሎ እንዲሻር ማድረጉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...