‹‹ሳድግ ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ፤›› በርካታ ሕፃናት ወደፊት ምን መሆን እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ የሚሰጡት የተለመደ ምላሽ ነው፡፡ ዶክተርነት በማኅበረሰቡ ዘንድ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ለዚህም የሕፃናቱን ምላሽ እንደ አንድ ምስክር መውሰድ ይቻላል፡፡
አልፎ አልፎም በልዩ ሙያ መሰማራት የሚፈልጉ ነገር ግን ሳያስቡት ወደ ሙያው የገቡ ግለሰቦች አልጠፉም፡፡ የ28 ዓመቱ ዶ/ር አሚን ሱልጣንም ወደ ሙያው በአጋጣሚ ከገቡ ሰዎች መካከል ነው፡፡ ዶ/ር አሚን ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ በትምህርቱ ብርቱና በደረጃ ከሚወጡት መካከል ቢሆንም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እስኪጀምር ድረስ በሕክምና ትምህርት የመሰማራት ህልም አልነበረውም፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጀመረ በኋላ የባዮሎጂ ትምህርት ከሌላው በተለየ ይስበው ጀመር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም ከሌላው ለይቶ ያተኩርበት ጀመር፡፡ በሌሎቹ የትምህርት ዓይነቶችም አይታማም፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግበው በባዮሎጂ የትምህርት ዓይነት ነበር፡፡ ሳያስበውም ከሕክምና ሙያ ጋር ይቆራኝ ጀመር፡፡
ዩኒቨርሲቲ በተቀላቀለበት ጊዜም ምርጫው የሕክምና ትምህርት ነበር፡፡ የከፍተኛ ተቋም ትምህርቱን የተከታተለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ሲሆን፣ 86.3 በመቶ ነጥብ በማስመዝገብ የጊዜው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኖ ትምህርቱን አጠናቅቋል፡፡
ዶ/ር አሚን በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ይልቁኑ የጨጓራ፣ የአንጀትና የጉበት ክፍል ስፔሻሊስት ሐኪም ለመሆን ችሏል፡፡ ስፔሻላይዝድ ባደረገባቸውም የሕመም ዓይነቶችም ካሉት ተማሪዎች ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገቡ የኢትዮጵያ የውስጥ ደዌ የሕክምና ማኅበር ባለፈው ቅዳሜ በግሎባል ሆቴል ባዘጋጀው የአንደኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ዕውቅና ከሰጣቸው ሦስት የሕክምና ባለሙያዎች መካከል ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ የውስጥ ደዌ ሕክምና ማኅበር ዶ/ር አሚንን ጨምሮ ከጐንደርና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሁለት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቶችን ሸልሟል፡፡ ማኅበሩ ካበረከተላቸው የላፕቶፕ ሽልማት ጎን ለጎን የተለያዩ የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትን፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በኮንፈረንሶች የሚሳተፉበትን ዕድል እናመቻቻለን ያሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንግሥቱ ዕርቄ ናቸው፡፡
በሕክምናው አገልግሎት ላይ የሚነሱትን ቅሬታዎች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት መቅረፍ እንደሚቻል፣ የተሸለሙት ባለሙያዎችም ለሌሎቹ ተምሳሌት እንደሚሆኑ፣ ተመራቂ ተማሪዎች በሥራ ከተሰማሩ በኋላ ተከታታይ ሥልጠናዎች እንደሚያስፈልጉና ይህ ካልሆነ የተማሩትን መዘንጋት እንደሚጀምሩም ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ ባደረገው ዳሰሳ በስኳር፣ በግፊት፣ በጉበት፣ በኩላሊት ሕመሞች የሕክምና አሰጣጥ፣ ክፍተት እንደሚታዩ፣ ይህንንም ለመቅረፍ በቅርቡ ሞጁል ተዘጋጅቶ ሥልጠና መስጠት መጀመራቸውን ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በሕክምናው ጥራት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል፡፡ ማኅበሩም የአባላትን መብት ከማስከበር ባሻገር በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት መሻሻሎችን መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ ስለሚታዩ የአተገባበርና የዕውቀት ክፍተቶች ሰፊ ጥናት በማድረግ ክፍተቱን ለይቶ የእምቅ ዕውቀት ግንባታ ሥልጠናዎች የሚሰጡ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ‹‹በአገር አቀፍ የጤና ሥነ ምግባር ኮሚቴ የራሳችንን ሚና መጫወት አለብን፤›› የሚሉት ዶ/ር መንግሥቱ፣ በሌላው ዓለም የሙያ ማኅበራት የሙያ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ለሚፈጽሙ የሥራ ፈቃድ ይነጥቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን በመጀመርያ ሕግ ፊት ይቀርባሉ፡፡ ማኅበሩም በጉዳዩ ጣልቃ የመግባት አቅም የለውም በማለት ሁኔታውን ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡
ማኅበሩ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሙያ ፈቃድ ጋር አያይዞ ያወጣውን አዋጅ በማስፈጸም ረገድ አንድ ሰው የሙያ ፈቃድ ለማደስ በዓመት የሚማራቸውን ትምህርቶች ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ጠብቆ ተከታታይ የሙያ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት እንዲማሩ የሚያደርግ ይሆናል፡፡