ዘርፈ ብዙ ግልጋሎትና ልዩ ልዩ መረጃዎችን ዘወትር ለ24 ሰዓት የሚሰጥ የመረጃ ማዕከል የተገነባ ሲሆን፣ ከጳጉሜን 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ‹‹ታላቋ ኢትዮጵያ 24›› የተሰኘው ማዕከሉ በኢትዮጵያ ውስጥና በውጪ አገር ባሉ መገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጩ መረጃዎችን አሰባስቦ የሚያቀርብ ድረ ገጽም አለው፡፡ ከጋዜጣ፣ ከሬዲዮ፣ ከቴሌዥንና ከመጽሔት የሚገኙ መረጃዎችን ለግለሰቦችና መሥሪያ ቤቶች የሚያቀርብ ሶፍት ዌርም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ማዕከሉ የተዘጋጀው በኢሚሪባስክ ኢንፎ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንትስ እና በኤፍ ስቶፕ ፕሮዳክሽን ሲሆን፣ ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ፕሮጀክት ዳይሬክተሩ ታምራት ፍቃደ እንደተናገረው፣ ማዕከሉ ስለ ኢትዮጵያ የተጻፉ መጻሕፍት፣ ፊልሞች፣ የጥናትና ምርምር ጽሑፎችና የእደ ጥበባት ውጤቶች የሚገኙበት ዲጂታል ላይብረሪ አለው፡፡
እንደ ታምራት ገለጻ፣ ማዕከሉ በስልክ፣ በፋክስ፣ በማኅበረሰብ ድረ ገጽና በሌላም መንገድ ጥያቄዎችን ለሚያቀርቡ ደንበኞቹ ለ24 ሰዓት መረጃ ይሰጣል፡፡ የሚሰጠው ምላሽ ከአገር ውስጥና ከውጪ በርካታ ተናጋሪ ባላቸው ዋና ዋና 12 ቋንቋዎች ይሆናል፡፡ ማዕከሉ ጥናት ለሚያካሂዱ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ተማሪዎች በነጻ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግሯል፡፡
ማዕከሉ ስለ አንጋፋ ኢትዮጵያውን የሕይወት ታሪክ መረጃ የሚገኝበት መንገድ የዘረጋ ሲሆን፣ ሲኒማ ቤትም አለው፡፡ ለጥንዶች የተዘጋጀውን ሲኒማ ቤቱ ከረፋዱ 3፡00 እስከ ምሽቱ 6፡00 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡ በየዓመቱ ታላላቅ ሥራዎች የከወኑ ኢትዮጵያውያን የሚሸለሙበት መድረክ እንዳመቻቹም አክሏል፡፡
የማዕከሉን መከፈት ምክንያት በማድረግ ከጳጉሜ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. እስከ መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. የተለያዩ መርሐ ግብሮች ይካሄዳሉ፡፡ የሙዚቃ ኮንሰርትና በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚገኙ ግለሰቦችን መጎብኘት ይገኙበታል፡፡
ታምራት እንደተናገረው፣ ‹‹ቅድሚያ ለኢትዮጵያውያን›› በሚል መሪ ቃል የሚንቀሳቀው ማዕከሉ፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል ላሉና በልዩ ልዩ ሙያ መስክ ለተሰማሩ ግለሰቦች መረጃ ለመስጠትና ስለ አገሪቱ የታሪክ፣ የባህልና ሌሎችም ሁነቶች ለማሳወቅ ያለመ ነው፡፡