ከተመሠረተ 199 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በአሜሪካ በደቡብ ካሮላይና በባርነት ቀንበር ሥር የነበሩትን ነፃ ለማውጣት በነበረው አስተዋጽኦ ታሪክ ዘግቦታል፡፡ በ1960ዎቹ ለተጠነሰሱት ‹‹ሲቪል ራይትስ ሙቭመንት›› እንዲሁም ‹‹ብላክ ላይቭስ ማተር ሙቭመንት›› የነበረው ሚና በጥቁር አሜሪካውያን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ አይዘነጋም፡፡ ከደቡብ ካሮላይና በተጨማሪም የደቡብ ባልቲሞር ጥቁር አሜሪካውያን የክርስትና እምነት ተከታይ ምዕመናንም መሰባሰቢያ ነው፡፡ ነጮች ሊያቃጥሉት ቢሞክሩም ሙሉ ለሙሉ ከታሪክ ማጥፋት አልቻሉም፡፡
ከተመሠረተ እ.ኤ.አ. ከ1816 ጀምሮ ስለሰላም፣ ስለፍቅር፣ ስለነፃነት ሲሰበክበት የቆየው በአማኑኤል የአፍሪካውያን ሜተዲስት ቤተ ክርስቲያን በ199 ዓመቱ በምዕመኑ ላይ ገጥሞት የማያውቅ የግድያ ወንጀል፣ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ተፈጽሟል፡፡
በአሜሪካ ቻርልስተን በደቡብ ካሮላይና በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በመማር ላይ ከነበሩ 13 ጥቁር አሜሪካዊ ምዕመናንን መካከል ዘጠኙን ተኩሶ የገደለው ደግሞ የ21 ዓመቱ ነጭ ዳይላን ሩፍ ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ራሳቸውን የሞቱ አስመስለው ሕይወታቸውን ያተረፉ የዓይን እማኞች ለሮይተርስ እንደተናገሩት፣ ወጣቱ ሩፍ በቤተ ክርስቲያኑ የሚሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመማር አስፈቅዶ ነበር የገባው፡፡ ሆኖም በትምህርቱ መሀል የማይስማማባቸውን ነጥቦች እያነሳ ይከራከርም ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ከቦርሳው ውስጥ መሣሪያ በማውጣት በመጀመሪያ በቤተ ክርስቲያኑ አንጋፋ ምዕመን፣ ቀጥሎም በመማር ላይ በነበሩ ሴቶችና ወንዶች ላይ ተኮሰ፡፡
ግድያውን ከመፈጸሙ አንድ ሰዓት ቀድሞ ‹‹የቤተ ክርስቲያኑን ትምህርት መማር እፈልጋለሁ፤›› ብሎ የገባው ባለ1.75 ሴንቲ ሜትር ቁመቱ ሩፍ፣ ጥቁር አሜሪካውያን የሆኑ ስድስት ሴቶችንና ሦስት ወንዶችን ገድሎ ቢያመልጥም፣ ከ16 ሰዓታት በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
የመጀመሪያ ጥይቶቹን ያሳረፈባቸውን የ87 ዓመቷን ሱዚ ጃክሰን ከጣለ በኋላ፣ ከምዕመናን ለቀረበለት ‹‹ለምን የቤተ ክርስቲያን ተከታዮችን ታጠቃለህ?›› ጥያቄ መልሱ፣ ‹‹ይህን ማድረግ አለብኝ፡፡ እናንተ የእኛን ሴቶች ትደፍራላችሁ፡፡ አገራችንንም እየወሰዳችሁ ነው፡፡ ከዚህ መሄድ አለባችሁ፤›› ነበር፡፡
21 ዓመቱን ሲያከብር ከአባቱ በተበረከተለት መሣሪያ ዘጠኝ ንፁኃንን የገደለው ሩፍ፣ አሜሪካ የዘረኝነትና የጥላቻ አድማሷ እየሰፋ ለመሄዱ መገለጫ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም 20 ሕፃናት ተማሪዎችን ጨምሮ 26 ሰዎች በትምህርት ቤት ውስጥ በመሣሪያ መገደላቸው፣ አንድ ጥቁር ወጣት በነጭ ፖሊስ በመገደሉ ምክንያት፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ በመሣሪያ ንግድ ላይ ገደብና ማዕቀብ እንዲጣል ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት አለማግኘቱ በአሜሪካ ዘርን ዒላማ አድርጐ የሚፈጸም ግድያን አፋፍሞታል፡፡
አሜሪካ ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ብትባልም ዜጐቿ ግን ሰላምን ማጣጣም አልቻሉም፡፡ በዘር ጥላቻ ሳቢያም ሞት በየጊዜው ይከሰታል፡፡ ጥቁሮች በነጭ ፖሊሶች ያልተገባ በደል ይፈጸምባቸዋል፡፡
በአሜሪካ ዘረኝነት ላይ ያነጣጠሩት ግድያዎች ሲከሰቱ ቁጣ ቢቀሰቀስም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን አሜሪካውያን ከዚህ ቀደም አንስተው የነበረውንና ምላሽ ያላገኘውን የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ በአሜሪካ ከመውለብለብ እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡አሜሪካን ለዘረኝነት ዳርጓታል ሲሉም ኮንነዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1861 እስከ 1865 በደቡብ ዩናይትድ ስቴትስ፣ በሰሜን ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ፣ በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም በአትላንቲክ ኦሽን አካባቢ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል የተደረገው ጦርነት የአንድነት ምክንያት ሆኖ ዛሬ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ተብላ የምትጠራውን አገር ለመመሥረት ቢያስችልም፣ ዘረኝነቱን ግን ማስቆም አልተቻለም፡፡ በወቅቱ የተደረገው ጦርነት ጥቁሮችን ከባርነት ቀንበር ያላቀቀ፣ አካባቢዎችን በማቀላቀል ድንበር ያስከበረ፣ አሜሪካ መልሳ እንድትቋቋም ዕድል የፈጠረ ቢሆንም፣ ቀድሞውንም የነበረውን የነጮች የበላይነትና የጥቁሮች ተገዥነት አጥርቶ ሊቆይ አልቻለም፡፡ ጥቁሮች በአሜሪካ የሚገለሉ፣ የሚናቁ፣ በነጭ ፖሊሶች የሚረገጡም ናቸው፡፡ በአፀፋው ጥቁሮች ብሶታቸውን ወንጀል በመሥራት ይመልሱታል፡፡ በጥቁረታቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው ግፍና በደል እንዲሁም ግድያ አፀፋውን ግድያ ያደርጉታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ሥልጣን ከያዙ እ.ኤ.አ. ከ2008 ወዲህ እንኳን ከስድስት ያላነሱ በዘረኝነት ላይ የተመሠረቱ ግድያዎች ተፈጽመዋል፡፡
በአሜሪካ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እያለ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ መውለብለቡ፣ ዛሬም ክፍፍሉ እንዳለ ያሳያል፣ የዘረኝነት መገለጫ ነው፣ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ አሜሪካውያን ለአምስት ዓመታት ባደረጉት ውጊያና በከፈሉት መስዋዕትነት ተሽሯል የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ ታሪካችን ነው በሚሉት ሳቢያ ሰንደቅ ዓላማው ዛሬም በአሜሪካ ይውለበለባል፡፡ በየሱቆቹም በልብሶች ላይ ታትሞ አልያም ብቻውን እንደ አሜሪካ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሁሉ ይቸበቸባል፡፡ ይህ ግን በተለይ በአማኑኤል የጥቁር አሜሪካውያን ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ላይ ጥቃት ከተፈጸመ ወዲህ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ዘጠኝ ንፁኃን በነጭ መገደላቸውን ተከትሎም በተደረገ ሰላማዊ ሠልፍ፣ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ በአሜሪካ ከመውለብለብ እንዲታገድ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ገዳይ ሩፍ ምዕመኑን ከመግደሉ አስቀድሞ በድረ ገጽ በለቀቀው ምሥሉ የአሜሪካ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን ሲያቃጥል መታየቱ፣ ግድያ ከመፈጸሙ ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ ያለበትን ልብስ ማዘውተር መጀመሩ፣ ሠልፍ የወጡ አሜሪካውያንን የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ የዘረኝነት መገለጫ ነው እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡
ዩኤስ ኤ ቱዴይ እንደዘገበው፣ የደቡብ ካሮላይና አገረ ገዢ ኒኪ ሃሌይ፣ የአሜሪካ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ በስቴት ሐውስ ከመውለብለብ እንዲወገድ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ሰንደቅ ዓላማውን ከካፒቶል ግራውንድስ የማንሻው ጊዜ አሁን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ግድያው በተፈጸመ በሦስተኛው ቀን በካይሮላይና የተገኙት ኦባማም፣ ሰንደቅ ዓላማው ተነስቶ ሙዚየም መቀመጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ተደርጐ ስቴቶች ወደ አንድ ቢመጡም የአሸናፊና ተሸናፊነት ስሜት ከአሜሪካውያን ልብ አልወጣም፡፡ በጦርነቱ ያሸነፈው አንድነት እንጂ በተለያዩ አቅጣጫ ሲዋጉ የነበሩ ስቴቶች አይደሉም ብለዋል፡፡ አገሪቷም ሁሉም የሰው ዘሮች የሚኖሩባት፣ የተለያዩ ሐሳቦች የሚገለጽባት አንድ አገር መሆኗን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የቻርልስተን ከንቲባ ዴሞክራቱ ጆሴፍ ሪሌይ እንደ ኦባማ ሁሉ ሰንደቅ ዓላማው በሙዚየም ሊቀመጥ እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹ሰንደቅ ዓላማው ሰዎች በጥላቻና በዘረኝነት እንዲሞሉ እያደረገ ነው፤›› የሚል ነው፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እያለ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን የሚያሳይ በመሆኑ ይነሳ ያሉም አሉ፡፡
የአሜሪካ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ በአሜሪካ እያንሰራራ ለመጣው የነጮች የበላይነትና የጥቁሮች የበታችነት ምክንያት ሊሆን አይችሉም የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ ሰንደቅ ዓላማው በአደባባይ ከመውለብለብ እንዲነሳ ከሪፐብሊካኖች ጭምር ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ምን ውሳኔ እንደሚያስተላልፉ ባይታወቅም፣ የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማው የታተመባቸውን አልባሳትና ዕቃዎች የሚሸጡና የሚያመርቱ ከገበያው ላይ ምርቱን እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡
ግዙፉ የዎልማርት ኩባንያም የኮንፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማ ያለባቸውን አልባሳትም ሆነ ምርቶች በየትኛውም መደብሮቹ መሸጥ እንደሚያቆም አሳውቋል፡፡ አሜሪካውያን የኮፌዴሬት ሰንደቅ ዓላማን ከማውለብለብ ቢቆጠቡ በአገሪቱ ያለው ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ ወንጀል ይቆም ይሆን የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡