Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ቅድሚያ ለማን?

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹ቀይ ጭብጨባ?››

‹‹…የባህል ልብስህ ነጭ ነው፡፡ በዓል በሆነ ቁጥር ሕዝቡ ነጭ ሲለብስ መንግሥት ይሸበራል፡፡ በወር ሠላሳ ቀን፣ ያውም ጠዋትና ማታ ነጠላውን አጣፍቶ፣ ጋቢውን ደርቦ ቤተ ክርስቲያን የሚስም ሕዝብ ያለባት አገር ከነጭ ቀለመ ጋር የጠበቀ ዝምድና ነው ያላት፡፡ ነጭ ነገር ውልብ ባለ ቁጥር ካድሬው ሁሉ ነፍሱ በድንጋጤ ይውለበለባል፡፡ ነጭ እርግብ ሳይቀር ያስደነብረዋል፡፡ ጓድ ሊቀመንበር ታዲያ ሽብሩ ሳይሆን የሽብሩ ቀለም ገናናነት አሸበራቸው፤ የሕዝባቸው ልብ ነጭ ሽብር ተቀባ!››

‹‹ደርጉን ሰበሰቡና በቁጣ፣ ‘ጓዶች ካሁን ጀምሮ ማንም ነጭ ልብስ እንዳይለብስ፣ ሽሮ ሜዳ ያሉ ሸማኔዎችም ነጭ ነጠላ እንዳይሠሩ፣ ነጭ እጀ ጠባብ እንዳይሸምኑ ለማወጅ አስቤያለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ነጭን አሸንፎ ሕዝቡ ሕሊና ውስጥ የሚቀመጥ ቀለም ካለ እስቲ ተናገሩ! ሕዝባችን ከነጭ ቀለም ሌላ ምን ዓይነት ቀለም ይወዳል? ይህች አገር አብዮታዊ ቀለም ያስፈልጋታል!’ ሲሉ ጠየቁ፤ በቀለሙ ላይ እንቢ የሚል ሌላ ቀለም ፈለጉ!››

‹‹…ጌታዬ ያው ጀግና ሕዝብ የደም ቀለም ራሰመለከት ደሙ ይፈላል…በዚያ ላይ የጀግንነት ምልክትም ነው፡፡ የመስዋዕትነት ምልክት ነው፡፡ ባንዲራችን ላይ ሁሉ ቀይ ቀለም አለ፡፡ ነጭ እኮ ባንዲራችን ላይ የለም፤ ከየት አባታቸው እንዳመጡት እንጃላቸው…›› ሲል የቀይ ቀለምን ገናናነትና የነጭን ቀለም ኮሳሳነት አንድ የደርግ አባል አጋንነው ተናገሩ፡፡››

ሌላው ቀጠለ፣

‹‹…አሁን የተናገሩት ጓድ ጥሩ አስቀምጠውታል፡፡ እውነት ነው ቀይ ቀለም ግተሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መሠረት አለው፡፡ በተጨማሪም ቀይ የአሳት፣ የነበልባል ምልክት ነው፡፡ ጓድ ሊቀመንበር፣ ቀይ ደግሞ ባህላዊ ቀለማችን ነው … ከጥሬ ሥጋ ጋር ይያያዛል፡፡ ሕዝቡ መቼስ ለበዓላት ነጭ ለብሶ፣ ያለው ጥሬ ሥጋ፣ የሌለው ቀይ ወጥ መብላቱ አይቀርም፡፡ ቀይና ነጭ አይነጣጠሉም፤ ወንድማማች ናቸው!›› ሲል አብራራ፡፡

‹‹…ጓድ መንግሥቱ ታዲያ አሰብ አደረጉና ‘መልካም ጓዶች፣ አብዮት አደባባይ ሕዝቡን በነቂስ አስወጥታችሁ ሰብስቡልኝ!’ አሉ፡፡ ሕዝቡ እንደተሰበሰበ ጓድ መንግሥቱ ድንገት መዥረጥ አደረጉና በጠርሙስ የተሞላ ቀይ ቀለም ሕዝቡ ፊት ሲያፈጉት ወላ ነጭ ሽብሮች፣ ወላ አገር ሊሰልሉ የመጡ ነጫጭ ‘ቱሪስቶች’ ከራማቸው ተገፈፈ፡፡ መቼስ ያኔ ቀለሙን ለተመለከተው ሊቀመንበሩ አስፋልቱን የፈነከቱት ነበር የሚመስለው፡፡ ሕዝቡ ቀዩ ቀለም መንገዱን አልብሶት ሲመለከት አፉን ደም ደም እያለው ቀይ ጭብጨባውን ለሊቀመንበሩ ለገሳቸው፡፡››

‹‹ቀይ ጭብጨባ?›› አልኩ ግራ ገብቶኝ፡፡

‹‹አዎና! ደም ያሰከረውን ሰው ፈርተህም ይሁን ተሳስተህ ‘አይዞህ በርታ!’ የምትልበት ደመኛ ጭብጨባ አለኮ፡፡ እሱን ነው የምልህ፡፡ በተለይ በአገራችን ታላላቅ የሚባሉት ጥፋቶች ቀደም ሲል የሕዝብ ቀይ ጭብጨባ ያበረታታቸው ነበሩ፡፡ ቀይ ሽብር ራሱ የቀይ ጭብጨባ ውጤት ነው፡፡›› አለና ወደ ሌላኛው ግድግዳ ተሻገረ፡፡

‹‹…እናልህ ያንን ደም የመሰለ ቀለም ሊቀመንበሩ ሕዝቡ ፊት ሲያንቧቹት ሕዝቡ ደነገጠ፡፡ ምን ሕዝቡ ብቻ ይኼው ቴሌቪዥኑም ምኑም እስከዛሬ ድንጋጤው አልለቀው ብሎ የሊቀመንበሩን ቀይ ቀለም የተሞላ ጠርሙስ እና አሰባበሩን እንደ ድንቅ ትርዒት በየቀኑ ያሳየዋል፡፡ ታዲያ ከአብዮት አደባባይ የተፈነጠቀው ቀይ ቀለም ኢትዮጵያን ከዳር እስከ ዳር ቀይ አለበሳት፡፡ ቀለም ያመጣው መዘዝ ሰይፍ አማዘዘ፡፡ ነጭ እና ቀይ የሚሉትን የቀለም ሽፋኖች ብትተዋቸው ያም ሽብር ይኼም ሽብር ነበር፡፡ እና ይኼ ባለ ኅብረ ቀለም ሽብር ስንቱን ንፁኃን በላ ወዳጄ፡፡ ሕዝቡ እንደሆነ በዚያም በዚህም ነጭ አይታየው ቀይ አይታየው … ባጭር ለቀረ ልጁ፣ ቤተሰብና ወዳጁ ጥቁር የታሪክ ማቁን በልቡ ለብሶ እህህ ተረፈው፡፡›› አለ ቀለም ቀቢው፤ ሁለተኛውን ግድግዳ አጋምሶ ነበር፡፡

  • አሌክስ አብርሃም ‹‹ዙቤይዳ›› (2007)

*******************

 

ያቺ አለላ ሙዳይ….

ያች አለላ ሙዳይ….

ከሩቅ ተቀምጣ-ከቅርብ የምትታይ

ወዲህ ማዶ ሆና-አድማስ ምትታይ

ያቺ አለላ ሙዳይ…

አላት ብዙ ጉዳይ

ሰው አዳኝ-ሰው ገዳይ

ያች አለላ ሙዳይ…

አላት ብዙ ሚስጥር

ለበጎ ሚኳትን-መጥፎ ሚመሰጥር

ያች አለላ ሙዳይ….

እያየኋት በዓይኔ-አላስተውላትም

ድምጻEን እየሰማሁ-አላደምጣትም

ያች አለላ ሙዳይ…

አፍ አላት እንደሰው-አታወራበትም

ነፍስ አላት እንደ እኛ-እሷ ግን አትሞትም!

ያች

አለላ

ሙዳይ…

  • ደመቀ ከበደ ‹‹አንድ ክንፍ›› (2003)

*************

ግጥም ምንድነው?

ማንኛውም ዝርው ቤት እየመታ በስንኝ ተሳክቶ ሲነገር ግጥም ይባላል፡፡ ይህም ቤት እየመቱ የመጽሐፍ ዘዴ እንጂ የንግግር ስልት አይደለም፡፡ ግጥም ከዝርው የሚለይበት ቤት በመምታት እንጂ በንግግር ስልት ግን አንድ ነው፡፡ ቤት እየመታ የሚናገርና የሚጽፍ ሰው ገጣሚ ይባላል፡፡ ገጠመ ካለው የመጣ ዘር ስለሆነ ቤት እየመቱ የመጽሐፍ ዘዴ እንጂ የንግግር ስልት አይደለም ቢባል ውሸት አይሆንም፡፡ ግጥሙ ግን ምሥጢር ያለው ከዝርው ከፍ ያለ የሰምና ወርቅ ጣጣ ግን የሌለበት የሆነ እንደሆነ ዘይቤ (ስለምን) ይባላል፡፡ ሰውዬውም ባለዘይቤ (ባለስለምን) ወይም ዘይቤ አዋቂ (ስለምን ዐዋቂ) ይባላል፡፡ ሰምና ወርቅ ከነጓዙ በጽሑፉ ውስጥ የተገኘበት እንደሆነ ቅኔ ሠሪውም ባለቅኔ (ቅኔ ዐዋቂ) የተቀኘ ይባላል፡፡

ም ጎመጀሁ ጎመጀሁ አንጎሌ ተሰየ

ናላዬ ዞረብኝ ልቤም ተሠቃየ

አፌን ምራቅ ሞላው ሆዴን ራበኝ

የሲሳዩን ዜና እመ! ብትነግሪኝ፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ስንኞች ወደ ስድ ንባብ ሲለወጡ የሚጨምሩት ነገር ስለሌለ ሁሉም ግጥም ናቸው፡፡

እመ! የሲሳዩን ዜና ብትነግሪኝ አንጎሌ ተሰየ ናላዬ ዞረብኝ አፌን ምራቅ ሞላው ልቤ ተሰቃየ ሆዴንም ራበኝና በጣም ጎመጀሁ፡፡ ይህ እንደሚያሳየን ግጥሙ እንዲስማማ ስንኙ እንዲያምር ተብለው ከገቡት ቃላት በቀር በስተ ተርጉም በኩል የጨመረውም የቀነሰውም የለ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ያለ ቅኔና ስለምን ያልያዘ ጽሑፍና ንግግር ሁሉ ግጥም ይባላል፡፡

(ዓለማየሁ ሞገስ፤ የአማረኛ ግጥምና ቅኔ ማስተማሪያ፣ 1954)

************

የትምህርት መንገድ ይህ ነው

እንጀራ በጨው ተምትመህ ብላ፤

ውኃ በመለኪያ ጠጣ፤

ከመሬት ላይ ተኛ፤ ትምህርት በምትማርበት ጊዜ ሁሉ የችግር ኑሮ ኑር፤

ይህንን ካደረግህ ዕድለኛ መሆንህን አትጠራጠር፤ ለራስህ ትልቅነትን አትፈልግ፡፡

ራስህንም አታክብር፤ ከትምህርትህ ሥራህ ይብለጥ፤ ጠረጴዛህ ከጠረጴዛቸው፤ ዘውድህም ከዘውዳቸው ይበልጣልና የመኳንንት ጠረጴዛ አያጓጓህ፡፡

አሠሪህና የሚያሠራህ ጌታ የድካምህን ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጁ ናቸው፡፡

**************

ምሳሌና ንግግር

ትምህርትና ውኃ ይመሳሰላሉ ይባላል፡፡ ውኃ ለምድር ዓለም ሕይወቱ ነው፤ ትምህርትም ለምድር ዓለም ሕይወቱ ነው፡፡ ለውኃ ዋጋ አነሰው ይባላል፤ ለትምህርትም ሁልጊዜ ዋጋ ሲያንሰው ነው፡፡

ውኃ ከላይ ይወርዳል፤ ትምህርትም የሚመጣው ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡

ውኃ እድፍን ያጠፋል፤ ትምህርትም ነውርን ያስወግዳል፡፡

ውኃ በጠብታ ተከማችቶ ትልቅ ወንዝ ይሆናል፤ ትምህርትም ጥቂት በጥቂት ተከማችቶ ሰፊ ዕውቀት ይሆናል፡፡

ውኃ በዝቅተኛ ቦታ ይሔዳል፤ ትምህርትም ትሕትና የሌለበትን ሰው አይጠጋውም፡፡

በትምህርቱ የሚኮራ ካደባባይ ላይ የወደቀ ጥንብን ይመስላል፤ ሰው ሲያልፍ አፍንጫውን ካልያዘ አይሆንለትም፡፡

  • ካንዲት ኢትዮጵያዊት የተጻፈ ‹‹ምክርና ምሳሌ›› (1947 ዓ.ም.)

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች