Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፈላጊና አፋላጊ!

እነሆ መንገድ። ከቄራ ወደ ወሎ ሠፈር ልንጓዝ ነው። “እውነት ኢትዮጵያ አበበ በቂላን አምጣለች? እውነት ምሩፅ ይፍጠር የእኛ ነው?” ሠልፈኛውን ፈንጠር ብሎ እንደ ጥጃ ጠባቂ እየተገላመጠ ወፈፍ ያደረገው ሰው ይለፈልፋል። “ምን አድርጉ ነው ደግሞ ዛሬ? እነሱ በደህናው ጊዜ ያልተዳቀለ እህል አሳድጓቸው ሮጠው አይደክሙ። እኛ የበላነው እንኳን ጉልበት ሊሆነን መቼ ይረጋል?” ሠልፈኞች መሀል ደከም ያሉ ወይዘሮ ያጉተመትማሉ። በዚህ መስመር ይመላለሳሉ መሰል ይኼን የአዕምሮ ታማሚ ያውቁታል። ሰውየው ሰማቸው መሰል፣ ‹‹እርስዎስ ይቅር አይችሉም። ሌሎቻችሁ ግን እዚህ ተሠልፋችሁ ታክሲ ስትጠብቁ አታፍሩም? አበበ በቂላ ባዕድ አገር በባዶ እግሩ ሮጦ ባንዲራችንን አውለብልቦ ታሪክ ሠርቶ አልፏል፡፡ እናንተ ግን በአገራችሁ የሰው አገር ጫማ ተጫምታችሁ ቆማችሁ ታክሲ ትጠብቃላችሁ? አትሮጡም? ሩጡ!” ይል ጀመር። “ካንጀቱ ነው?” አለች ጠይም ደርባባ። “ካንጀቱ ነው እንጂ። እሱ ምን አለበት በደህናው ጊዜ ለይቶለታል፤” ከኋላ የቆመ ወጣት የለዘዘች ቀልድ ለትውስታ ጣል ያደርጋል።

“ዝም በይው እባክሽ። እንኳን ለሩጫ የሚሆን ትንፋሽ ሊኖረን ካልጋ ስንወርድ እንዴት እንደምናለከልክ መቼ አየን። ለራሱ አልጋ የለው ትራስ የለው፤” ከደርባባዋ ሁለት ሰው አለፍ ብሎ ቦርሳ ያነገተ ጎልማሳ ተሳለቀ። ወፈፍ የሚያደርገው ሰውዬ ይኼን ሰማ። “አልጋ? አልጋማ አለኝ፤” አለ ዓይኑን አጉረጥርጦ ጎልማሳው ላይ እያፈጠጠ። “ምናለበት ዝም ብትል? ደህና የሚሄደውን መለስከው። ሰው ነገር ረስቶ ማረሳሳት እንዲህ ይክበድ? ምነው ይኼን ያህል የነገረኝነታችን ጥበብ ድሩ ሳሳ?” አሉ ወይዘሮዋ። “አልጋማ አለኝ። ይኼው ይህች መሬት አልጋዬ! ይኼው ይኼ አፈር ትራሴ! እንዲያውም አንተን ይመስላል ሰውዬው። ‘መሬት ላራሹ’ን ስፎክር ጩኸትህ በዛ ብሎ ቤቴ ገብቶ ከእነ አልጋዬ ከአውጥቶ እዚህ መሬት ላይ የጣለኝ  . . . ሰውዬው ይኼው። ራሱ ነው . . . ተጫምታችሁ መሮጥ እየፈራችሁ ትራስ አይንተራስም ብላችሁ ህልሜን ታማላችሁ እናንተ? አትሮጡም የራሳችሁን? ሩጡ!” አለና ራሱ ቀደደው። ሠልፈኛው ተነፈሰ። ተረኞች ታክሲያችን ውስጥ ገብተን ቦታ ቦታ ያዝን። እግራችንን ሳናፍታታ ክንፍ ካልገጠሙልን የምንል ሁላ!

ጉዟችን ተጀመረ። ወያላው ያጣድፈናል። “ወጣ ወጣ፣ ታክሲ ውስጥ የለም ሽምጠጣ እ? መንግሥትና ሕዝብ ማጭበርበር ተክኛለሁ ብለሽ የተማመንሽ እዚያው የለመድሽበት። እዚያ እጅ ከፍንጅ አለመያዝና እዚህ እጅ በእጅ መረካከብ የሳዳምና የቡሽ ያህል ልዩነት አለው፤” ይላል። በራሱ ንግግር ብቻውን ፍንድቅድቅ ይላል። “ተወን አቦ። ለራሳችን አመዳችንን ሳናራግፍ ሳዳም ሳዳም አትበልብን፤” ጋቢና የተሰየመ ወጣት ሁሉም እየሰማው ተናገረው። “እሺ እዚህ ጋ እሙቲ! ከቻልሽ አብዬ ኦባማ ሲመጡ አዲስ ልብስ ለብሼ እንድቀበላቸው ‘ቲፕ’ ጣል አድርጊበት እ።” ደርባባዋን ወጣት ለከፋት። “ኧረ እባክህ? የማነው?” ብላ ፊት ልትነሳው ስትል፣ “ካላመንሽ ይኼውልሽ እዚህ ጋ አንበቢ። ቅዱስ ቃሉ ነው የሚለው እኔ አይደለሁም፤” ብሎ፣ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትለጉመው” ወደ ሚል ጥቅስ ጠቆማት።

“እና አንተን ነው ይኼ የሚገልጸው? በሕግ ተርጓሚውና አውጪው ስንገረም ቅዱስ ቃሉን አጣማሚው ባሰን እኮ እናንተ?” ብላ ነገር ነገር ሲላት “ጨርሽዋ ማንበቡን። ወይ ጉድ፣ እውነትም ሰዎች ‘ኢሕአዴግ ርዕስ ብቻ የሚያነብ ትውልድ ፈጠረብን’ ብለው የሚነጫነጩት ወደው አይደለም፤” ብሎ ወደ መሀል መቀመጫ ጎራ አለ። አንድም ከሚታማው ትውልድ መሀል ላለመቆጠር፣ አንድም የሚታማውን መንግሥታችንን ላለማስቆጣት ጽሑፉን ስንጨርሰው፣ “ከታሪፉ ውጪ ገንዘብ ከኪስ አውጥቶ በማቁለጭለጭ የወያላውን ሞራል መንካት ከአሸባሪነት ድርጊት ተለይቶ አይታይም፤” ይላል። በቅንፍ ‘ቲፕ’ ለመስጠት ካልሆነ’ ብሎ ይዘጋል። ይኼ የኮረኮረው አንድ ስክነት የራቀው አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት፣ “ቲፑ ቀርቶብኝ ደመወዜ በተብቃቃልኝ’ አለች ኪሴ። ተቀምጠን ስንጓዝ ሲያዩን ተኝተን የምናድር የሚመስላቸው ወያሎች አልባሱብንም ትላለህ?” ይለኛል ጠጋ ብሎ። ያሻውን መናገሩ ላይቀር ሹክሹክታው ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም። እስኪ የገባው?

አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ውስጡ ያለውን ከማለቱ ከኋላችን፣ መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙ ተሳፋሪዎች አንዷ ሰምታው፣ “አንተ የወያሎች ይገርምሃል? ናሳ አንድ ‘ፕላኔት’ አገኘሁ ብሎ ሲፈነድቅ እኮ ነው እኔ የምስቀው። እኛ ኪሳችን ባዶ መሆኑን እያወቅን በጭፍን እምነት እንዴት ለዕለት ጉርስ የምትበቃ ሳንቲም በየቀኑ ስናገኝ እንደምንውል አላወቀ። ህዋ ህዋ ነው። መቼም አንድ ነገር አይጠፋም ብለህ ለፍለጋ ብትነሳ ያስኬዳል። ዘቅዝቀን፣ አራግፈንና ፈትሸን ያጠብነውን ልብስ ውለድ ብለን ፆም ሳንውል ማደር ግን ምን ይባላል? ‘ዲስከቨሪ ቻናል’ ያልቀረፀው አሰሳ ሆኖ እንጂ፣ የተዓምራት ኑሯችን ከጠፈር ጥበብ አይበልጥም?” ብላ ሒሳቧን አወጣች።

በወዲያ ጥግ የተቀመጠ መነጽር ያረገ ተሳፋሪ፣ “ኧረ ተይ ዝም በይ በሏት። በፈለጣ የቤት ኪራይ እየከፈልን፣ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት በአብሮ አደጎች ቸርነት እየታለፈ፣ በጨበጣ ተመርቅኖ በጨበጣ እየተጨበሰ ተዓምራት ትላለች እንዴ? ባይሆን ናሳ ባዶ ኳስ ባገኘ ቁጥር የዳቦ ስም ማውጣቱን ትቶ እዚህ መሬት ላይ የሚኖሩ ያልፈለጋቸው ፕላኔቶች አሉ ብትይ ያምርብሻል። አይደል እንዴ?” ሲል አጠገቡ ወደ ተቀመጠ ተሳፋሪ ዞሮ ‘ኮሜንቴን’ በግድ ‘ላይክ’ ካላደረክልኝ ይላል። ዝም ሲለው “የመቶ ብር ዝርዝር አለህ?” ብሎ ወያላውን ይጠይቃል። “የመቶ ብር ማምከኛ አለህ አትልም? ምን ዝርዝር ትላለህ?” አጠገቤ የተሰየመው ቁንጥንጥ ልጅ እየሳቀ ጣልቃ ገባ። ባለመነጽሩ አፍንጫው ላይ የሚንሸራተት መነጽሩን በሌባ ጣቱ ከፍ እያረገ ዓይቶ እንዳላየ ሲያልፈው ወደኔ ተጠማዞ፣ “አይደል እንዴ? ልጅነትህ ካለፈና መቶ ብር ከተዘረዘረ እኮ በቃ አጠፋፍተኸው አኗኗርህ ጣዕም ያጣል። ‹Am Telling You!› ወራጅ!” ብሎ ወረደ። የገንዘቡስ እሺ። ምነው ቀልቡ ሳይዘረዘር የሚጠፋበት ሰው በዛ?

አጠገቤ ተቀምጦ በነበረው ቁንጥንጥ ምትክ አንድ ጎልማሳ በስልኩ እየተነጋገረ ገብቶ ተሳፈረ። “ስማ! ስማ! ልነገርህ አንድ ጨዋታ። ስማኝ ስልህ?!” ይላል እየጮኸ። “አንድ ደፋርና ፈሪ ምሽግ የመስበር ‘ጌም’ በሞባይላቸው ይጫወታሉ። ፈሪው እየደጋገመ ውጤት ሲያስመዘግብ ደፋሩ አንድም ጊዜ አልተሳካለትም። እናም ይጠይቀዋል። ‘ይኼን ሁሉ ጊዜ ስሞክር ውጤት የለኝም። እንዴት አንተ ጨዋታውን ቻልክበት?’ ቢለው፣ ‘አንተ ከልብህ እኔ ከአንገት በላይ ስለምንጫወት ነዋ’ አለው እልሃለሁ። እናም ላንተም የምመክርህ በዚህ ‘አርቲፊሻል’ ዘመን ለሀቅ ልሙት ማለቱን ትተህ ‘ጌሙ’ ን ካንገት በላይ ተጫወተው። አለበለዚያ ዝንብና ድህነት ናቸው የሚጦሩህ፤” ይላል። መሀል መቀመጫ ተሰይመው ከገቡ ጀምረው የስልክ ስክሪን ፅዳት የተቀጠሩ የሚመስሉ ይጠያየቃሉ። “የምታረጅ ይመስልሃል?” ይለዋል አንደኛው። ኧረ ሲነጋልኝ እንደገረመኝ ነው። ምንም ቢሆን ነገን አላምነውም። ገንዘብ ሳይኖርህ ማርጀት ግን ‘ሙድ’ የለውም። ቆይ እንዲያውም ‹Mony is Power› ብዬ  ልፖስትና የፌስቡክን ቀበሌዬን ትንሽ ላንጫጫው፤” የወዲያኛው ወደ ስልኩ አደፈጠ።

  ወያላችን አዲስ ወደገባው ጎልማሳ ተሳፋሪ ቀርቦ ሒሳብ ጠየቀ። የጎልማሳውን የተፈታ ፊት አተኩሮ ሲያጠና ቆየና ሒሳቡን ሲቀበል፣ “በቅርቡ ኦባማን ደግሰን ለመቀበል መዋጮ ስለምንጀምር ያለህን ለመርጠብ ተዘጋጅ፤” አለው። ጎልማሳው ፈገግ ብሎ፣ “ሌላ ግድብ ብንጀምር አይቀልም? ምዕራባውያን እኮ አንድ ጎርሰው እንደኛ በቃኝ አይሉም፤” አለው። ቢጤውን ያገኘው ወያላ ጥርስ በጥርሶ ሆኖ፣ “ሞኝ ነን እንዴ እኛ? ኦባማ በአንድ ጎናቸው አፍሪካዊ ስለሆኑ እኮ እንደግስ ያልነው። ከአሜሪካውያን ቀድሞ የሰውዬው ‘ሼፒነት’ ሳይገባን፣ ሆዳቸው ትንሽ ለምዶ ትንሽ እንደሚችል ሳናረጋግጥ፣ ልንደግስ?” አለው። ይኼኔ ሁላችንም በግድ ፈገግን። ተርፎ የሚነሳውን ማዕድ አሥልተን እንግዳ የምንቀበልበት ዘመን መጣብና። ወይ ሐበሻና ብሉ ጠጡ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ተራቸውን ከደርባባዋ ወጣት አጠገብ የተቀመጡት ወይዘሮ ስልክ ይዘዋል። “እንኳን ደስ አለሽ የእኔ ልጅ። ደህና ነሽ ወይ ለመሆኑ? ወይ ጉድ ድምፅሽ ሁሉ የሌላ ሰው። ይገርማል እኮ እናንተ? ይኼ ማዳበሪያ እያፋፋችሁ መለየት ተሳነን። በይ አሁን ቶሎ ብለሽ ባል ማግባት ነው። አዎ! ቶሎ አግብተሽ ቶሎ ውለጂ። ልጅ በልጅነት ነው። ቀስ ብዬ አግብቼ እወልዳለሁ ብለሽ ኋላ በመቁረቢያሽ ምኑም ሳይገባቸው ገብቶናል ከሚሉ የዘመኑ ልጆች ጋር ስትዳረቂ እንዳትኖሪ። ዋናው ‘ኢንሹራንስ’  ልጅ ነው። ስትታመሚ ‘ዲግሪ’ አይደርስልሽም። ልጅ ነው የሚያስታምምሽ። ስትሞቺ ‘ዲግሪ’ አያለቅስልሽም ልጅ ነው አልቅሶ አላቅሶ የሚቀብርሽ። ነግሬሻለሁ፤” ይላሉ። ወዲያው ወደ መጨረሻ ወንበር ጫጫታ ተነሳ። “የዲግሪው ምጥ ሳይበርድ፣ ቁስሉ ሳይሽር ሌላ የወገብ ስብራት? እንዴት የፈረደባት ናት?” ሲል ባለመነጽሩ ናሳን ያጣጣለችው ወጣት በተቀራኒ፣ “ምነው አመራረቁንም አቀዳደሱንም እያወቅነው?” ትላለች።

መሀላቸው የተቀመጠ ተሳፋሪ የሁለቱ ተቃርኖ እንዳይባባስ አስቦ ይመስላል፣ “ዲግሪ አስታሞ አይቀብርም አሉ። አይ የድሮ ሰው ‘ኖሮ ኖሮ ከመሬት’ መሆኑን መቼም ልቦናው አይስትም፤” አለ። “እባክህ እየኖረ እንደማይኖር ስለሚያውቀው ነው ቀብሩ የሚያስጨንቀው። ሳልደምቅ መኖሬ ካልቀረ ቢያንስ ሽኝቴ ይድመቅ ነው ጨዋታው፤” አለችው ወጣቷ። ወዲያው ታክሲያችን ጥግ ይዛ ስትቆም ወያላችን “መጨረሻ!” ብሎ በሩን ከፈተው። ስንወርድ በየት እንደመጣ አናውቅም ያ ወፈፌ እንደ ቅድሙ ሠልፈኞች ፊት ለፊት ቆሞ፣ “አበበ በቂላ በሰው አገር ባዶ እግሩን ሮጦ እናንተ ተጫምታችሁ ትሠለፋላችሁ?” እያለ ይጮሃል። “አንዳንድ ድምፀት ሲደጋገም ያስፈራል” እያለ ተሳፋሪው በየፊናው ተበታተነ። ግን የሚያስፈራን፣ ርቀቱን በፅናት ሮጠን እንዳንጨረስ እያሳነፈንና እያዳከመን ያለው እውነት ጫማው ነው መንገዱ? ማምለጥ ይኼኔ ነው ያለው ማን ነው ብለን ጥያቄ ብንጀምር፣ ፈላጊም አፋላጊም አይገናኙም፡፡ ፈላጊና አፋላጊ ስናፈላልግ ደግሞ ቀኑ መሽቶ ይነጋል፡፡ መልካም ጉዞ!                 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት