Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርአዱኛ ብላሽ ካቲካላ እንደ ‹‹ባሪያ›› ፈንጋይ

አዱኛ ብላሽ ካቲካላ እንደ ‹‹ባሪያ›› ፈንጋይ

ቀን:

በፍቃዱ በቀለ

ወጣትነት ጣጣው ብዙ ነው፡፡ በተፈጥሮ  ከሚመጣው ለውጥ በተጨማሪ ከአካባቢ በሚደርስ ተፅዕኖ ወጣቶች ለአላስፈላጊ ነገሮች ይዳረጋሉ፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሱስ አምጪ ስለሆኑ ነገሮችና በሕዝባችን በተለይም በወጣቱ ላይ እየደረሱ ስላሉት ጥፋቶች ተደጋግሞ ቢወሳም፣ አገርኛ መጠጥ ስለሆነችውና በተለያየ ስም ስለምናውቃት ካቲካላ እየደረሰ ስላለው ጥፋት ብዙም ሲወሳ አልተሰማም፡፡ ይህን ጽሑፍ የማቀርበው አዳማ ውስጥ ከምኖርበት አካባቢ በተጨባጭ ለዓመታት ያደረግኩትን ምልከታ ዋቢ በማድረግ ሲሆን፣ ዓላማውም የአሳሳቢነቱን ደረጃ በመረዳት በጋራ መፍትሔ ለመሻት ነው፡፡

ካቲካላ በሌላ ስሟ ‹‹የአንበሳ ወተት››፣ ‹‹ሽላቦ››፣ ‹‹ካክሻ››፣ ‹‹ወሳኝ››፣ ‹‹የሐበሻ አረቄ››፣ ‹‹ቁንዲፍቱ››፣ ‹‹ካት ስፒር››፣ ‹‹ኋይት ስፒር››፣ ‹‹ሃይቴክ››፣ በመባል ትጠራለች፡፡  በመላው አገራችን፣ በገጠርም ሆነ በከተማ በሰፊው የሚዘወተር አገር በቀል ምርት ስትሆን፣ የመጠጥ ፍላጎትን ለማርካት ብቻ ሳይሆን ለአምሮትና በባህላዊ መንገድ ከሆድ ሕመም ፈውስ ለማግኘትም በሚል ሰበብ ትወሰዳለች፡፡ የምርቷ ዓይነት ከጊዜ ወደጊዜ እየበዛ፣ የተጠቃሚዋም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ግልጽ ነው፡፡

- Advertisement -

‹‹ኋይት ስፒር›› ስትጠጣ ምቾት አትሰጥም፡፡ እንደ መልኳ ሳይሆን ጣዕሟ ይሰነፍጣል፣ ወደ ምላስህ ስታስጠጋት ዓይንህን ጨፍነህ፣ ፊትህን አጨፍግገህ፣ ስትውጣት ደግሞ በግራ እጅህ ደረትህን ይዘህ አንገትህን ሰበር እንድታደርግ ታስገድዳለች፡፡ ከጉሮሮ እንደወረደችም ወዲያው መድኃኒት እንደሚውጥ ሰው ውኃ ቸልሰህባት ነው ጊዜያዊ ሰላም የምትሰጥህ፡፡ እሳት የላሱ ጠጪዎች ካልሆኑ በስተቀር ዛሬ መሸታ ቤት አረቄ ሲታዘዝ አብሮ ውኃ በብርጭቆ ተከትሎ ይቀርባል፡፡ ካክሻን ሲጎነጩ ከማቃጠሏ የተነሳ ወዲያው በላዩ ላይ ውኃ መጠጣት ግድ ሆኗል፡፡ አብዛኛዎቹ የአረቄ ሱሰኞች እንደ ጤና ክሊኒክ ተመላላሽ ታካሚ ሰዓታቸውን ጠብቀው በየዕለቱ በመሸታ ቤቶች የሚታደሙ ሲሆን፣ ብዙዎቹ የተጎሳቆለ ሕይወት የሚመሩ፣ በወጣትነት ዕድሜ ያሉና ቅብጥብ ወንዶች ናቸው፡፡

ሳይንሳዊ ማብራሪያ መስጠት ባልችልም በብዙ ተጠቃሚዎች ላይ እንዳየሁት (ወንድም ሴትም) የአረቄ ሱሷ በጣም ኃይለኛ ነው፡፡ ወዳጅነት ከጀመረች አትለቅህም፣ አብራህ ዘመን ትሻገራለች፡፡ ራስነትህን አስጥላ የእሷ ተገዢ ታደርግሃለች፡፡ ብዙ የአረቄ ሱሰኞች ከእሷ ለመላቀቅ ሲጥሩ ቢስተዋልም፣ አብዛኛዎቹ ከልባቸው ባለመሆኑና የመውጪያ መንገድ (‹‹ስትራቴጂ››) ስለማያዘጋጁ ከውስን ቀናት በኋላ ተመልሰው ሲዋኙበት ይታያሉ፡፡ አረቄ ሱሷ አምጣ አምጣ ብቻ ሳይሆን እጅና እግርን ታንቀጠቅጣለች፣ ዓይንን ትይዛለች፣ የምግብ ፍላጎትን ትቆልፋለች፣ የንግግር ዘይቤንም ታበላሻለች፡፡ አወሳሰዷም እንዳስለመዷት ነው፡፡ የለመዱት ጠዋት ከሆነ ከእንቅልፍ እንደነቁ በባዶ አንጀት ኳ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ወዳጅነትዎ አመሻሽ ላይ ከሆነ ደግሞ ጀንበር እንዳዘቀዘቀች ወደ ካቲካላው ቤት ለመብረር ትራኩ ላይ ማኮብኮብ ይገደዳሉ፡፡ አሃ ሱስ ነዋ!

አዳማ/ናዝሬት ከተማ ውስጥ በተለይም ቀበሌ 01፣ 06፣ 07፣ እና 08፣ ውስጥ በርካታ ‹‹ዕውቅናን›› ያተረፉና ‹‹አንቱ›› የተሰኙ አረቄ ቤቶች ይገኙባቸዋል፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ አረቄ እንደ ጠጅ በማንቆርቆሪያ የሚንደቀደቅባቸው ቤቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በሞንታርቦ በታገዘ የሙዚቃ አጀብና የዲኤስቲቪ አገልግሎትም በመስጠት ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡ አግዳሚ ወንበር በሚዘወተርባቸው የመጠጥ ክፍሎቻቸው ግድግዳ ላይ የአረቄን መልካምነት፣ ጤና ሰጪነትና አዋጭነት (ትንሽ ዋጋ) የሚገልጹ ጽሑፎች በአራቱም ማዕዘናት ለጥፈው ደንበኞቻቸውን እያነቃቁ ያስኮመኩማሉ፡፡ ‹‹ታካሚዎቹም›› ከሙዚቃው በተጨማሪ ከግል ጉዳያቸው ጀምሮ ፖለቲካዊና ስፖርታዊ ወጎችን እያወሩ ቁንዲፍቱን ፉት ይላሉ፡፡

አዱኛ በቅርብ ካለ ገጠር አካባቢ ተወልዶ አዳማ ያደገ ሲሆን በልጅነቱ ፈጣን፣ ትምርቱንም በፍላጎትና በብቃት ይከታተል የነበረና ከብዙዎች ጋርም ተግባብቶ መኖር መቻሉ፣ ቤተሰቦቹ ያሳደጉት እንደማኛውም የሠፈሩ እኩዮቹ ያለውን ተቃምሶ ራሱንም እየረዳ ይኖር እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ምን ያደርጋል ጣፋጭ ግን ጠመዝማዛ በሆነው ወጣትነት ዕድሜው ላይ ትንንሽ ሳንቲምና ሱሶች እግር ተወርች አስረውት ትምህርቱን እንደ ኤቬሬዲ ድመት ተይዞ 9ኛ ክፍል ላይ ‹‹አጠናቋል››፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሰው ለዓመታት በተለያዩ ሱሶች ቢዋጥም እንደ ካክሻ ዘላቂ ወዳጅ አላገኘም፡፡ ይኼው 15 ዓመታት በወዳጅነት ዘልቀዋል፡፡ ቀላል ፍቅር ነው!

ይህ ከተፎ ወጣት ቀድሞ ለሥራ ይታትር የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ዛሬ በሌሊት ሲነቃ የሚያስበው የዕለቱ ተረኛ ባለጠላ ማን እንደሆነች በማስላት ነው፡፡ አቅም ከፈቀደና ጥንካሬው ከተገኘ ጠዋት ወገግ ሲል ጀምሮ መጠጣቱን የሚያቆመው ገንዘብ ከኪሱ ሲሟጠጥና ውድቅት ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ኑሮው መሠረት የለውም፡፡ ከልመና ትንሽ ከፍ ያለ ቢመስልም አብዛኛውን የመጠጥ ኮታውን የሚያሟላው በቅፈላ ነው፡፡ ለቅፈላ ያመቸው ዘንድ ዘወትር በአረቄ/ጠላ መሸጫ ቤቶች መስቀለኛ መንገድ ላይ አገጩን ይዞ በመቆም ለአላፊ አግዳሚው ሰላምታ ያቀርባል፡፡ ከቀናው አንዱ ጠጪ ሲገባ እንዴት ነው አንድ በይኛ ብሎ እግሩን ያስገባል፡፡ ጨዋታው ደርቶ የሚቀባበል ሰው ከተገኘ ሁለት ሦስት ሊደጋግም ይችላል፡፡ ቁርስ፣ ምሳና እራት የሚባሉ ነገሮች ለእሱ እምብዛም ምቾት አይሰጡትም፡፡ አንጀቱ አይቀበለውማ!

ይህ ምንዱባን በሱስ ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜያት ታማኝነትን አጉድሏል፡፡ የራሱንና የቤተሰቡን ንብረት አውጥቶ ሸጧል፡፡ ሙሉ ራሱን ጥሏል፡፡ ለሱሱ ሲል ክብሩን ዝቅ አድርጓል፡፡ ከበረንዳ አዳሪነትም በተጨማሪ በተለያዩ ተውሳኮች ተጠቂ ሆኗል፡፡ ጊዜያዊ ምክር የሰማ መስሎ መሃላ ቢደረድርም በማግሥቱ የአረቄ ጥሪን አሜን ብሎ ከመቀበል ወደኋላ አይልም፣ መልሶ ይዘፈቃል፡፡ የአካባቢው ተፅዕኖ ነው በሚል እሳቤ ቤተሰቦቹ በተደጋጋሚ ጊዜ ከሚኖርበት አዳማ ከተማ ይዘውት ወደ ሌላ ቦታ ቢወስዱትምና ሥራ ቢጀምርም፣ ከሳምንታት በኋላ የያዘውን ይዞ ወደ አዳማ አረቄ ቤቶች ይመለሳል፡፡ ይህን ሲያደርግ ለዓመታት ቢያስቆጥርም ዕድሜ አስተምሮትና ፀፅቶት፣ ሱሱም ምሮት ከአረቄ ዛሬም ድረስ አልተፋታም፡፡ ክፉ ፍቅር!

እነሆ ዛሬ አዱኛ በአረቄ መዘዝ ቤት አልባ ነው፡፡ ቢደክመው የሚያርፍበት ቢታመም ጋደም የሚልበት ጎጆ የለውም፡፡ በራስ የመተማመን ስሜቱ ደብዛው ጠፍቷል፡፡ ብዙ በመሥሪያውና ሀብት በማፍሪያ ዕድሜው መደበኛ የገንዘብ ምንጩ የሰው እጅ ማየት ከሆነ ሰነባበተ፡፡ መረን የለቀቀ ሱሰኝነት ክብርን ይነካል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚሰጥህ ቦታም የወረደ ይሆናል፡፡ ካክሻ ለአዱኛና መሰሎቹ አሳዳሪ ጌታ ሆናለች፡፡ እነሱም ተገዢ ባሪያዎቿ፡፡ እሷን ለማግኘት ሲባል ሰብዓዊ ክብርን በገዛ ፈቃድ ማዋረድ እጅግ ዘግናኝ ተግባር ነው፡፡

ታዲያ አዱኛ ብላሽ ማለት ይኼ አይደለም ትላላችሁ? ካቲካላስ ‹‹ባሪያ›› አላሳደረችም? ይህ እውነታ በብዙ ከተሞቻችን ውስጥ እየተዘወተረና እየሰፋ ያለ፣ ግን እንደ ዘበት በቸልታ የታየ፣ ውሎ አድሮ ይዞት እየመጣ ያለው መዘዝ ከቤተሰብና ከአካባቢ አልፎ ለአገርም ፀር እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ተግባር ላይ ተሳታፊ እየሆኑ ያሉት ስብጥራቸው ብዙ ገጽታ ያለው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የሁለተኛና የዩኒቨርሲቲ/ኮሌጅ ትምህርታቸውን ያቋረጡ፣ ከዩኒቨርሲቲ/ኮሌጅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁና ሥራ ያልያዙ፣ በግል ወይም በቅጥር ሥራ ተሰማርተው በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ስኬት ያላገኙ፣ ወይም ያቋረጡ እንዲሁም ከቤተሰብ የተጣሉና ከቤት የወጡ ይገኙበታል፡፡ 

የችግሩ አሳሳቢነት የከፋ የሚያደርገው ሱስን ለመሙላት ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል ወጣቶች እጅ ላይ ሳንቲም ሲጠፋ ከቤት፣ ከጎረቤት ወይም ከሌላ ሥፍራ ዕቃዎችን በመስረቅ ‘ይጀውራሉ’፡፡ የራሳቸውን ሞባይል ብቻ ሳይሆን ልብስና ጫማ ጭምር አውልቀው ‘ሲጠግሩ’ ማየት የተለመደ ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ተሰርቀው የሚመጡ ዕቃዎችን በወደቀ ዋጋ መደበኛ ሥራቸው በማድረግ የሚሸምቱ በየቦታው ብዙ ናቸው፡፡ ጫት ቤትና ሺሻ ቤቶች ዋና ዋና የመገበያያ ሥፍራዎች ሲሆኑ፣ ቁንዲፍቱ ቤቶችም የወረዱ ዕቃዎችን ማራገፊያ ወደቦች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ እውነቱ ከሁላችንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም አልመሸም፡፡ ተስፋ ሰንቀን በጋራ መክረን፣ በየቤቱ ያለውን ጉድ በግልጽ አውጥተን፣ የችግሮቹን መነሻ በመለየት ወጣቶቹን መታደግ ይኖርብናል፡፡

አዱኛ የአብዛኛውን የአረቄ ሱሰኞች የሚወክል፣ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው አዱኛ ይሆናሉ የተባሉ ወጣቶችን የሚወክል ገጸ ባህሪ ነው፡፡ እኔ የጠቀስኩት ትንሽ ነው፡፡ እውነታው ከዚህ የገዘፈና ምርምር ጭምር የሚያሻው ችግር ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...