Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየሴት ጋዜጠኞችና ጸሐፍት ውጣ ውረድ የበዛበት ተሳትፎ

የሴት ጋዜጠኞችና ጸሐፍት ውጣ ውረድ የበዛበት ተሳትፎ

ቀን:

ውድ አንባቢያን፣ በቅድሚያ በቅርቡ ስለፕሬስ በቀረበው ጽሑፍ በተለይም የኢትዮጵያን የፕሬስ ታሪክ የሚዳስሰው የጊዜ ሥሌት ግድፈት እንዳለበት ለማስታወስና ስህተቱን የፕሬስ አካላቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በማስላት ትክክለኛውን ማወቅ እንደሚቻል በመጠቆም፣ ለተፈጠረው ስህተት ጸሐፊው አንባቢያንን ይቅርታ ይጠይቃል፡፡

ሴቶችና መገናኛ ብዙኃን ስንል በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በመጽሐፍ፣ በካርቱን ሥዕል፣ በሕዝብ ግንኙነትና በማስታወቂያ ሥራ ያላቸው ተሳትፎ ማለታችን ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በሪፖርተር ጋዜጣ (የአማርኛና የእንግሊዘኛ) ዝግጅት ክፍል ስንት ሴቶች አሉ? ብለን ብንጠይቅ ከ50 በመቶ በላዩ ሴቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ስለዚህ በዚህ የጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከሌሎች ጋዜጦችና መጽሔቶች አንፃር ሲታይ በጣም በርካታ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ጋዜጠኞችንና ከጋዜጠኝነት ተግባር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሴቶች በርከት ብለው የምናገኛቸው በአዲስ አድማስና በአዲስ ዘመን ነው፡፡ ሆኖም በአዲስ ዘመን ውስጥ የአዘጋጆች፣ የሪፖርተሮችና የሌሎች ከጋዜጠኝነት ሥራ ጋር የተያያዘ ሙያ የሚያከናውኑት በፕሬስ ሕጉ መሠረት ከዋና አዘጋጆቹ ጋር ስላልቀረበ እንጂ ብዙ ሴት ጋዜጠኞች፣ ዲዛይነሮች፣ ፎቶግራፈሮችና ፕሩፍ ሪደሮች እንዳሉ አዘጋጁ በግል ያውቃል፡፡ የዘመን መጽሔት ዋና አዘጋጅም ሴት ስትሆን እርሷም የመጀመሪያዋ ሴት ዋና አዘጋጅ ልትሆን ትችላለች፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሥራ አስኪያጅ ሴት ሲሆኑ፣ የንግሥት መጽሔት ባለቤትም ሴት መሆናቸው በመጽሔቱ ውስጥ ተገልጿል፡፡ ከተጠቀሱት ጋዜጦችና መጽሔቶች በተጨማሪ ዛሬ በገበያ ላይ ቢሆኑም እንደ ምንሊክ፣ ሳሌም፣ ዕፎይታ፣ ጦቢያ፣ ሚዛን፣ አፍሪካ ቀንድ፣ ሙዳይ፣ አዕምሮ ያሉት በቋሚ በቅጥርም ሆነ በፍሪላንሰርነት ሴቶችን በጋዜጠኝነትና ከጋዜጠኝነት ጋር በተያያዘ ሙያ ያሳትፉ ነበር፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ዘርፉም፣ በተለይም በሬዲዮና በቴሌቪዥን ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ጀምሮ የሚያደርጉት ተሳትፎ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ዓላማ ሴቶችንም የመገናኛ ብዙኃንን በአጭሩም ቢሆን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት ሲሆን፣ በመጀመሪያ የመገናኛ ብዙኃንን ምንነት፣ የሴቶች ተሳትፎ በልዩ ልዩ የዓላማችን ክፍሎች፣ በአገራችን ያለው የሴቶች ተሳትፎ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ችግሮቻችን ምን ያህል ግዙፎች እንደሆኑ ለማመልከት ነው፡፡ እዚህ ላይ የውጭ አገር ልምድ የተጨመረው የአገራችን ሴቶች ተሳትፎ ከምን መጀመር እንዳለበት ለማሳየት ሲል ታስቦ እንደሆነ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

  • አቀፋዊ የሴቶች ተሳትፎ  በመገናኛ ብዙኃን

ሴቶችና መገናኛ ብዙኃን ስንል ሴቶች በመጽሐፍ፣ በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በካርቱን ሥዕል፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በሕዝብ ግንኙነት፣ በማስታወቂያ ሥራ ያላቸው ተሳትፎ ማለታችን ሲሆን፣ ቀዳሚው መጽሐፍ፣ መጽሔትና ጋዜጣ በመሆናቸው በመጀመሪያ ከመጽሐፍ ሥራ እንጀምራለን፡፡ ሴቶች በመጻሕፍት ማለትም በግጥም፣ በአጭር ልቦለድና በረጅም ልቦለድ ታሪክ ጸሐፊነት መሳተፍ ከጀመሩ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ ስለሴት ደራሲያን የተጻፉ በርካታ መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ እንዲያውም ከድርሰት ዘርፎች አንዱ በሆነው ግጥም ያላቸው ተሳትፎ ከራሱ ግጥም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ሊዛ ቱትል ‹‹ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ፌሚኒዝም›› በተሰኘው መጽፋቸው (እ.ኤ.አ 1986) ያስረዳሉ፡፡ እኚህ ባለ 400 ገጽ ዓውደ ጥበብ ያዘጋጁ ሴት ‹‹ስለሴቶች እኩልነት እንደ ዛሬ በሰፊውና በጥልቀት ትግል ከመደረጉ አስቀድሞ ይልቁንም የሴቶች ፍላጎት፣ አመለካከት፣ ሐሳብ፣ በወንዶች አመለካከት፣ ሐሳብና ፍላጎት ከመጣመሙ፣ ወይም ትክክለኛ ያልሆነ ትርጓሜ እየተሰጠው እንዲገለል በሚደረግበት ጊዜ፣ ይልቁንም ወንዶች በመሠረቱት የበላይነት ስሜት ሴቶች ምን ማለት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው በሚቆጣጠሩበት ጠባብ ጉሮሮ ከመፈጠራቸው በፊት ከእነሱ እንደማያንሱ ያሳዩበት ወቅት ነበር፤›› በማለት በተለይም ስለግጥምና ስለገጣሚያን ባወሱት ክፍል ያስረዳሉ፡፡

- Advertisement -

ብሎምስበሪ የተባለው ድርጅት ‹‹ውሜንስ ሊትሬቸር›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1992 ባሳተመው መጽሐፍ በ1172 ገጾች በሰፊውና በጥልቀት እንዳሰፈረው፣ በጥንታዊት ግሪክ ሮም፣ ከ15ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን በነበረችውና ባለችው ብሪታኒያ፣ በተለያዩ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ፣ የአውስትራሊያና የእስያ እንዲሁም የሰሜንና የደቡብ አሜሪካ አገሮች በርካታ ሴት ደራሲያን በልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ዘርፎች እንደሚሳተፉ እንረዳለን፡፡ ከመጽሐፉ እንደምንረዳው ከክርስቶስ ልደት በፊት አምስተኛው ክፍለ ዘመን እስከሆነበት ጊዜ ወንዶች ብቻ ይጽፉ ነበር፡፡ ከአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ ግን ሴቶች በተለይም እንደ ዘፈን ግጥሞች ባሉት ላይ ከፍተኛ ችሎታ እንዳላቸው እየተስተዋለ መጣ፡፡ ከአምስተኛው እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ዓመተ ዓለም) ባለው ጊዜ ሴቶች በቤት አስተዳደር ትምህርት ሲሠለጥኑ የሥነ ጽሑፍ መጻሕፍትንም ለማንበብ ዕድል አገኙ፡፡ ይህም በዚህ መስክ የመሳተፋቸውን ዕድል ከፍ አደረገው፡፡ ከአራተኛው መቶ እስከ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ዓ.ዓ) እንዲያውም የፍቅር ግጥም የሴቶች ዋነኛ የስሜት መግለጫ መግቢያ ተደርጎ የሚቆጠርበት ወቅት ሆነ፡፡ ተሳትፎው በግሪክ ብቻ ሳይሆን በጥንታዊት ሮምም ተስፋፋ፡፡

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ አምስተኛው መቶ ዓመተ ምሕረት ባለው ጊዜም በሮማውያን ዘንድ በርካታ የሴት ጸሐፍት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከቀደምት ሮማውያን ሴት ጸሐፍት መካከልም ቀዳማቂትና ዳግማዊት ሱልፒሺያ የሚባሉ ይገኙበታል፡፡ ቀዳማዊት ሱልፒሺያ ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅድመ ክርስቶስ እስከ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድኅረ ክርስቶስ የነበረች ስትሆን፣ በልዩ ልዩ አርዕስቶች ግጥሞችን ደርሳለች፡፡ እንደ ሱልፒሺያ ሁሉ ሆር ቴሽያ፣ ሳይሲያና ኮርኔሊያ የመሳሰሉ ሴት ጸሐፍት የነበሩ ሲሆን፣ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን (ዓ.ዓ.) መገባደጃ ላይም በፖለቲካና በኢኮኖሚው የነበራቸው ተሳትፎ ከፍ እያለ በመሄዱ በሥነ ጽሑፍም የነበራቸው ተሳትፎ ከፍ ማለቱ አልቀረም፡፡ በአውሮፓ ከክርስቶስ ልደት በፊት ሴቶች በሥነ ጽሑፍ መስክ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ፣ በእስያ ውስጥ በተለይም በእስራኤል፣ በህንድ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች፣ በጃፓንና በቻይናም ያደርጉ ነበር፡፡ የአውሮፓና የእስያ ሴት ደራስያን ከጥንት ጀምሮ በሥነ ጽሑፍ መስክ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው የሚነገር ቢሆንም፣ አውሮፓውያን አጥኝዎች እንደሚሉን አፍሪካውያንና ሥነ ጽሑፍ የሚተዋወቁት ከቅኝ አገዛዝ በተያያዘ ሁኔታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በኢትዮጵያና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ለሠርግ፣ ለሐዘን፣ ለጦርነትና ለሌሎችም ማኅበራዊ ጉዳዮች ሴቶች እናቶቻችን ግጥም እንደሚደረድሩ እናውቃለን፡፡

ስለ ሴቶች በሥነ ጽሑፍ የመሳተፍ ታሪክ ሲወሳ ከኅትመት መሣሪያ መፈጠር ወዲህ እየተጠናከረ መምጣቱን ማስታወስ ይገባል፡፡ ይሁንና ዓለማችን የወንድም የሴትም ሆና እያለች ለምን የሴቶች ጸሐፍት አነስተኛ ሆነ? ቨርጂኒያ ውልፍ በ1928 (እ.ኤ.አ) ‹‹ኤሩም ኦቭ ዋንስ ኦውን›› በሚል ርዕስ በጻፈችው መጣጥፍ ሴቶች ከወንዶች እኩል ለመጻፍ የራሳቸው ገቢና የራሳቸው ክፍል (ቤት) ሊኖራቸው እንደሚገባ ፍርጥርጥ አድርጋ አስረድታለች፡፡ ቨርጂኒያ ውልፍ ሴት ገጸ ባሕርያትን ደካሞች፣ መከራ የማይችሉ፣ መዝናናትና ክብካቤ ብቻ የሚፈልጉ፣ ለወሲብ ብቻ የተፈጠሩ አድርገው የመሳላቸው ጉዳይም ተፅዕኖ እንዳደረገ ወደኋላ ሳትል ገልጻለች፡፡ ከቨርጂኒያ ውልፍ ቀደም ብሎ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የማየት አስተሳሰብ እንዲወገድና ሴቶች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው እንዲከበር በእንግሊዝ አገር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይደረግ እንደነበረ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከታወቁት ግንባር ቀደም መሪዎች መካከልም የፕሮፌሰር ፓንክረስት አያት ኢመሊን ፓንክረስት (1858-1928) እናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት (1882-1960)፣ ከ1830-1921 የነበረችው ኤሚሊ ዴቪስ፣ ኤልሳቤጥ ጋሬት አንደርሰን (1836-1917)፣ ሊዲያ መከር (1827-90)፣ ይገኙበታል፡፡ እዚህ ላይ መጠቀስ የሚገባው በ18ኛው እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን አንዳንድ የሴት ጸሐፍት በወንዶች ስም ይጽፉ እንደነበር ነው፡፡ ሴቶች በመጻሕፍት ሥራ ምን ያህል ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው ስንገልጽ በሌላ በኩል ከጋዜጣ ሥራ ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ እንደሚያሳየን ሳይናገሩት የሚሄድ ሀቅ ነው፡፡

በኮሌጅ ደረጃ ለማስተማር አገልግሎት እንዲውል ‹‹ኒው ሰርቬይ ቱ ጆርናሊዝም›› በሚል ርዕስ ዶ/ር ፎክስ መቻ እ.ኤ.አ በ1965 ለስድስተኛ ጊዜ ባሳተሙት መጽሐፍ እንደ አሜሪካዊቷ ማርጋሬት ፉለር (1810-1850)፣ ኤልዛቤጥ ኮክሬን ሲማን በሚል የብዕር ስም ስትታወቅ የነበረችው ሄሊ ብለይ (1867-1922) ያሉ ግንባር ቀደም ጋዜጠኞች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም አንጋፋ ጋዜጠኞች እንደ ዶ/ር ቶምሰን፣ አይሽቤል ሮዝና አንአሐር ማክከርሚክ ያሉት ጋዜጠኞች እንዲፈጠሩ መንገድ ከፍተዋል፡፡ እነዚህ ግንባር ቀደም ጋዜጠኞች በዘመናቸው ወንዳ ወንድ፣ መጢቃዎች፣ የማያዛልቅ ጸሎት ለቅስፈት የሚል አሽሙር ነክ አስተያየት ይሰነዘርባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይልቁንም በዘመናቸው የነበሩ ሴቶች ባልትና ወይም ሥነ ጥበብ ግፋ ቢልም ስለቁጠባ እንዲማሩ እንጂ፣ በቀለም በወዛው የጋዜጠኝነት ጎዳና ጥልቅ ብሎ መጓዝ አደጋ እንደሚያደርስ ይነገራቸው ስለነበር በዚህ አዳላጭ መንገድ መጓዝ የዋዛ አልነበረም፡፡ የዋዛ ስላልነበረም ከባዱን ሥራ ወንዶች፣ እንደ ማስታወቂያ ያሉትን ብልጭልጭ ነገር የሞላባቸውን ተግባራት ሴቶች ግንባር ቀደም ሆነው እንዲሠሩ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ የወንዶች ተፈላጊነት በሁለተኛ ደረጃ እንደነበረም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ደግነቱ ማስታወቂያ መሥራት ደረጃ በደረጃ ወደ ጸሐፊነት የሚመራ በመሆኑ ግን፣ የንግድ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ለማዘጋጀት እንዲችሉ አበቃቸው፡፡ በኋላም በአብዛኛዎቹ ዕለታዊ ጋዜጦች (ትልቅም ሆኑ ትናንሽ) ስለልብስ ፋሽን፣ በሐኪም ሊታዘዙ ስለሚችሉ መድኃኒቶች፣ ፍቅረኞቻቸውን ስለተነጠቁ ወጣቶች፣ ሕፃናትን አርሞና ኮትኩቶ ስለማሳደግ፣ ስለቤተሰብና ማኅበረሰብ፣ ስለቤት ማሳመር፣ ስለጓሮ አትክልት አያያዝና ስለመሳሰሉት ያቀርቡ ጀመር፡፡

ከ1943-44 (እ.ኤ.አ) በኦሐዩ ዩኒቨርሲቲ የጆርናሊዝም ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ፍሬድሪክ ደብሊዩ ማጉየር ‹‹ጆርናሊዝም ኤንድ ስቱደንት ጆርናሊዝም›› በሚል ርዕስ እ.አ.አ በ1951 ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣ የተማሪዎች ጋዜጣ ማቋቋም በዚህ የሕይወት አቅጣጫ ለሚጓዙ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡ ወጣቶችን ከለጋ ዕድሜያቸው አንስቶ በዚህ ሙያ ማሠልጠን የሕዝብን ፍላጎት ለማድላትና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያስችል በአጽንኦት በጋዜጣና በመጽሔት ሴቶች ስለሚያደርጉት ተሳትፎ ሲወሳ፣ የጋዜጦችንና የመጽሔቶችን ተነባቢነትና ተፈላጊነት ከፍ ማድረጉ ሳይጠቀስ መታለፍ የለበትም፡፡ ተፈላጊነቱና ተነባቢነቱም ከተራ ተሳትፎና በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል፡፡ የዛሬውን ትተን የዛሬ ሃምሳ ዓመቱን ብንመለከት በአሜሪካ ይታተሙ ከነበሩት 131 ዕለታዊ ጋዜጦች ውስጥ የ121 ጋዜጦች አሳታሚዎች፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ዋና ሥራ አስኪያጆች ወይም ዋና አዘጋጆች ሴቶች እንደነበሩ የዶ/ር ፎክስሞት የኮሌጅ ማስተማርያ መጽሐፍ ያረጋግጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ፣ በእስያም ሆነ በአፍሪካ ሴቶች የማይሳተፉበት ጋዜጣ ይኖራል ብሎ መገመት በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሴቶች ለብዙ ዓመታት ከመገናኛ ብዙኃን ተገልለው ቢኖሩም፣ ዛሬ ግን ያለሴቶች ተሳትፎ የጋዜጦችና የመጽሔቶች ዓላማ ግቡን ሊመታ እንደማይቻል ተቀባይነትን ያገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ስለኅትመት መገናኛ ብዙኃንና ስለሴቶች ተሳትፎ አጠቃለን ወደ ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን ከመሸጋገራችን በፊት ግን እነ ሬይ ኤልደን ሄይበርት ‹‹ማስ ሚዲያ›› በሚል ርዕስ በ1992 (እ.ኤ.አ) ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ‹‹የሴቶች እኩልነት ንቅናቄ ከኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ይልቅ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ባለቤት በመሆን የበለጠ መጠቀሙን፣ ከኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ይልቅ የኅትመት ሚዲያ በዋጋ አነስተኛ መሆኑ፣ ከሬዲዮና ከቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ይልቅ በኅትመት ጋዜጠኝነት በይበልጥ ሠልጥነዋል፤›› ተብሎ መጠቀሱን ማውሳት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ በተለይም ሬዲዮ፣ ለሕዝብ አገልግሎት መዋል ከጀመረበት ከ1920 አንስቶ ስላለው የሴቶች ተሳትፎ ስንመለከት ከጋዜጦችና ከመጽሔቶች ተሳትፎ አኳያ የምናስተውለው ነው፡፡ ሴቶች በጋዜጣና በመጽሔት ሐሳባቸውን የመግለጽ ልምድ አካብተው ስለነበር የሬዲዮ ፕሮግራሞች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲስፋፉ እነሱም በማስታወቂያና በድራማ፣ ከዚያም ለቤት እመቤቶች ይቀርቡ በነበሩ ፕሮግራሞች፣ በፕሮግራም አስተዋዋቂነትና በመሳሰሉት መሳተፍ ጀምረዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ የሴቶች ተሳትፎ በሬዲዮ ከፍ ማለት የጀመረው ግለሰቦች በርካታ ሬዲዮ ጣቢዎችን ማቋቋም ከጀመሩበት ከ1930 በኋላ መሆኑንም ለመጠቆም እንወዳለሁ፡፡

የሬዲዮ ፕሮግራም በ1940ዎቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ቴሌቪዥን ደግሞ ያኔ በዕድገት ላይ ነበር፡፡ በዚህ የመገናኛ ብዙኃን የሴቶች ተሳትፎ እምብዛም የሚጋነን አልነበረም፡፡ ከ1948 በኋላ ግን በርካታ ቴሌቪዥን ጣቢዎች ለመቋቋም ችለዋልና በርካታ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ለመሳተፍ በቅተዋል፡፡ እነፕሮፌሰር ሬይ ኤልደን ሂበርት ‹‹ማስ ሚዲያ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ እንደገለጹት በእርግጥ ለሰብዓዊ መብት መረጋገጥ ይደረግ የነበረውን ያህል አልነበረም፡፡ ከ1960ዎቹ በኋላ በተለይም ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከተስፋፉ በኋላ ግን በአዘጋጅነት ብቻ ሳይሆን በኃላፊነትም በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ስለሬዲዮና ቴሌቪዥን ካወሳን ዘንድ ስለተንቀሳቃሽ ፊልምና ስለሴቶች ተሳትፎም ማውሳት በተገባን ነበር፡፡ ሬዲዮንና ቴሌቪዥንን የሚገባውን ያህል ሳንሄድባቸው ወደዚህ ማተኮሩ እምብዛም አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም የመገናኛ ብዙኃን አካልና በዚህም መስክ በርካታ ሴቶች መሳተፋቸውን ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡

  • ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ያላቸው ተሳትፎ

ስለኢትዮጵያውያን ሴቶችና መገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ ስንገልጽ ሴቶች መሳተፍ የጀመሩበት ጊዜ መቼ ነው? የምንቆጥረውስ በየትኛው የመገናኛ ብዙኃን ዘዴ ከተጠቀሙበት ጊዜ አንስቶ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ ታሪክ የሚያስተምርበትና ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ‹‹አጭር የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ›› በሚል ርዕስ በ1976 ዓ.ም. ያዘጋጁት ሥራም፣ ስለወንዶቹ ጸሐፊዎች እንጂ ስለሴቶቹ የሚያወሳው ነገር የለም፡፡ አንዲት ግጥም ብትሆን የጻፈች ሴት ብትኖር መጻፏ በሚታወቅላት ዓለማችን ለምን የአንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት የሥነ ጽሑፍ ሥራ ከኢትዮጵያ የሥነ ጽፍ ታሪክ ገጽ ጠፋ? ለመሆኑ ሴቶች ግጥም፣ አጭር ልቦለድ፣ መጣጥፍ፣ ረጅም ልቦለድ፣ ወይም ትንሽም ብትሆን በጋዜጣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ጽፈው ያውቃሉ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ዓባይነሽ ብሩ ‹‹የሴቶች ጉዳይ በመገናኛ ብዙኃን›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀችው ጽሑፍ እንዳለችው የኅትመት ሥራ ከተጀመረ፣ በተለይም መጻሕፍትና ጋዜጦች መታተም ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የተጠናቀሩ ሪፖርቶች ቢታወቁም ዮናስ አድማሱ፣ ሀብተ ማርያም ማርቆስ፣ ዮሐንስ አድማሱና ኃይሉ ፉላስ ‹‹አማርኛ በኮሌጅ ደረጃ የተዘጋጀ›› በሚል በ1966 ዓ.ም. በተባዛው የማስተማሪያ ጽሑፍ ስለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ አስፍረዋል፡፡ ደብተራ ዘነብንም የቴዎድሮስ ዘመን ሰው እንደነበሩ አልረሱም፡፡ ዳሩ ግን፣

‹‹አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፣

እንዶድ ለብልቦ አቃጥሎ ይፍጃችሁ፡፡

ሺሕ ፈረስ ከኋላው ሺሕ ፈረስ ከፊቱ

ሺሕ ብረት ከኋላው ሺሕ ብረት ከፊቱ

ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሻጭ እናቱ፡፡

ይህንን ሲሰማ ያጓራል ላመሉ

ማን ናትም ቢሏችሁ ምንትዋብ ናት በሉ፡፡››

የተቀኘችው ምንትዋብ ቸኮል (1857 ዓ.ም.) ግጥም እንደዋዛ ጣል ከመደረጉ በቀር፣ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ ሊኖራት እንደሚገባ አልተጠቀሰችም፡፡ የጥንታዊ ግሪካውያን፣ ሮማውያንና ሩቅ ምሥራቃውያን ታሪክ የሚያስታውሳቸው ግን ተዋበች ቸኮል የመሳሰሉትን እንደሆነ ከሥነ ጽሑፍ ታሪካቸው እንማራለን፡፡ ነገር ግን የጥንቱ ጥንት እንደቀረ ቆጥረን የአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ሴቶች ከመጻፋቸው በፊት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከ1941 ዓ.ም. ጀምሮ ይጽፉ እንደነበር ሁለቱም የዩኒቨርሲቲ ሥነ ጽሑፍ መማሪያዎች ሳይጠቅሱት ‹‹ዚ ኦክስፎርድ ካምፓኒየን ቱ ቴአትር›› በሚል ርዕስ ለሦስተኛ ጊዜ በታተመው መጽሐፍ ግን ‹‹ከሴት ተውኔት ጸሐፊዎች መካከል ከስንዱ ገብሩ ሌላ በ1974 ሮማንወርቅ ካሳሁን ማህቶተ ጥበብ በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ ደርሳለች›› የሚል ሠፍሮ እናገኛለን፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ምናልባት ለዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያነት ብቃት የላቸውም ቢባል እንኳን፣ ባለው ሁኔታ እንደ ግንባር ቀደም ጸሐፊነታቸው ለምን ሳይጠቀሱ እንደሚታለፉ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ከሁለቱ ጸሐፍት ሌላ አቶ መንግሥቱ መኰንን መምህር አብራራው እየተባሉ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ዘወትር ቅዳሜ ማታ የጥያቄና መልስ አዘጋጅ የነበሩት ጋዜጠኛ ባለቤት ወይዘሮ መሠረት መንገሻም፣ ‹‹የአልቤርጎው ፈላስፋ›› በሚል ርዕስ ባለትዳሮች ዝሙት መፈጸም እንደሌለባቸው የሚመክር መጽሐፍ (በ1950ዎቹ) ማሳተማቸው ይታወቃል፡፡

በዘመናችንም አጫጭር ልቦለድ ታሪኮችን፣ ግጥሞችንና ረጅም ልቦለድ ታሪኮችን የጻፉ እንዲሁም የተረጎሙ ሴቶች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ከእነዚህም ጸሐፍት መካከል ‹‹እንጉዝና›› ‹‹ቃሳ›› የጻፈችው ፀሐይ መላኩ፣ ከገጣሚዎችና ትልልቅ መጽሐፍ ከተረጎሙት ወይንሸት ማስረሻን፣ አዜብ ግርማ ወልዴን፣ ከሕፃናት መጻሕፍት ደራስያን እነ ሜሪ ጃፋርሰ፣ ከግጥም ጸሐፍት እነዓለም ፀሐይ ወዳጆን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በርካታ አጫጭር ልቦለድ ታሪኮችንና ግጥሞችን በጋዜጣ፣ በመጽሔትና በመጻሕፍት ላይ እየጻፉ የሚያስነብቡን አሉ፡፡ ስለኢትዮጵያውያት ሴት ደራስያን አጋረደች ጀማነህ ለመጀመሪያ ዲግሪዋ ያቀረበች ከመሆኗም በላይ ሌላም ሰው በዚህ መስክ የማስተርስ ዲግሪውን ለማግኘት ያደረገው ጥናት አለ፡፡ ስለዚህም ስለሴቶች ጸሐፍት ጥናት ለማድረግ የሚፈልግ ቢኖር እነዚህን ሥራዎች በማየት ሐሳብ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡

  • በጋዜጦች ያላቸው ተሳትፎ

በአገራችን ውስጥ ጋዜጣ መታተም የጀመረው ወይም ከጋዜጣ ኅትመት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መተዋወቅ የጀመረው ጣሊያኖች ምጽዋ ላይ በ1874 በቋንቋቸው ማተም ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ ከ1893 ጀምሮ ሐረር ውስጥ በፈረንሳይኛና በአማርኛ ይታተም የነበረው ‹‹ለ ሰሚር ዳ ኢትዮጵያ›› ለንባብ በቅቷል፡፡ ከዚያም ከ1895 ጀምሮ መታተም የጀመረው ‹‹አዕምሮ›› የተባለው ጋዜጣ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከ1920 በኋላም ‹‹ብርሃንና ሰላም››፣ ‹‹ከሣቴ ብርሃን››፣ ‹‹አጥቢያ ኮከብ›› የተባሉ ጋዜጦች ታትመዋል፡፡ በጣሊያን ወረራ ዘመን አርበኞች ‹‹ባንዲራችን›› የተባለ ጋዜጣ ሲኖራቸው ጣሊያኖች ደግሞ ‹‹የሮማ ብርሃን›› የተባለ ጋዜጣ ነበራቸው፡፡ ከ1933 ዓ.ም. ወዲህም ‹‹ባንዲራችን›› የተባለው ጋዜጣ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› በሚል በዓረብኛና በአማርኛ በሚታተም ጋዜጣ ተተክቷል፡፡ ከዚያም አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ድምፅ፣ ኅብረት የተባሉ ጋዜጦች እንዲሁም መነን፣ ሚረር፣ ኢትዮጵያን ኦብዘርቨር፣ አዲስ ሪፖርተር፣ አብዮታዊት ኢትዮጵያ፣ የካቲት፣ ሰንደቅ የተባሉ መጽሔቶች ለንባብ በቅተዋል፡፡ በእነዚህም ጋዜጦችና መጽሔቶች በርካታ ሴቶች በጽሑፍም በማስታወቂያም ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህም ሌላ በየመንግሥታዊ መሥሪያ ቤት የሚታተሙ መጽሔቶች አሉ፡፡ ከእነዚሁ መጽሔቶች ብዙዎቹ ብልጭ ድርግም የሚሉ በመሆናቸው ማጥናቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ፖሊስና ዕርምጃው፣ ታጠቅ፣ ዜና ቱሪዝም፣ ፈለገ ብርሃን የመሳሰሉትን ግን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሴቶች በጋዜጣና በመጽሔት መሳተፍ የጀመሩበትን በአጠቃላይ ስንዳስሰው ግን የ70 ዓመት ዕድሜ እንዳለው እንረዳለን፡፡ ይኸውም ሰንደቅ ዓላማችን የተባለው ጋዜጣ በተለይም በ1940 ዕትሙ የወ/ሮ መቅደስ ወርቅ አጭር የሕይወት ታሪክ ማቅረቡ ነው፡፡ እኚህ ሴት ‹‹የሙያ ምንጭ›› የተባለ መጽሐፍ ደራሲ እንደሆኑም ይኼው ጋዜጣ ያስረዳል፡፡ የ1940 መረጃን አገኘኝ እንጂ አዲስ ዘመንና ሰንደቅ ዓላማችን የተባሉት ጋዜጦች መታተም ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተከታታይ እንኳን ባይሆን አልፎ አልፎም ቢሆን የሴቶች ጉዳይ ሊጠቀስ አይችልም ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ በ1945 ዓ.ም. የተማሪዎች ዓምድ ላይ የሺ እመቤት፣ በ1946 ሚስ ካሌብ አስመራ፣ በ1945 ሮማን ወርቅ ካሳሁን በ1948 ‹‹የቆነጃጅት ማታ›› የሚል ሥነ ግጥም የሚያቀርቡበት ጊዜ ነበር፡፡ ምናልባት ሴቶች ስንል ኢትዮጵያዊ ማለትም ጠቢብ ብቻ ካላልን በስተቀር ወለተ ሥላሴ ወይም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የክርስትና ስም የነበራቸው ሲልቪያ ፓንክረስትም፣ ኢትዮጵያን ሔራልድ መዘጋጀት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተካፋይ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ እኚህ ሴት ከዘራቸው ማለትም ከእናት ከአያታቸው ጀምሮ ለሴቶች እኩልነት ሲታገሉ የነበሩ በመሆናቸውም የሴቶችን ጉዳይ ወደጎን ይተውታል የሚል ግምት አይኖረንም፡፡

ከዚህ በተረፈ መነንና ሚረር የተባሉት መጽሔቶች ስለሴቶች ፋሽን፣ ሙዚቀኛ ሴቶች፣ ሕዝባችን የሚሉ የፎቶግራፍ ሪፖርቶች፣ ማስታወቂያዎች ይዘው ይወጡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህልም በ1942 ዓ.ም. በታተመው መነን ውስጥ የሴቶች መስተዋት፣ በ1954 ዓ.ም. መነን ላይ የሴቶች ገጽ እናገኛለን፡፡ በዚሁ የ1954 ዕትም ሴት የሬዲዮ ጋዜጠኞችን ተሳትፎ የሚያወሳ ጽሑፍ ወጥቷል፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያን፣ የኢትዮጵያ ድምፅን፣ ኅብረትን፣ ሠርቶ አደርን፣ አብዮታዊት ኢትዮጵያን፣ የካቲትንና ሰንደቅን እንዲሁም ከ1983 ወዲህ መታተም የጀመሩ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ስንመለከት ደግሞ በርካታ ሴቶችን እናገኛለን፡፡ በጅምር ቀሩ እንጂ ገነትና ሔዋን የሚባሉ መጽሔቶች ነበሩ፡፡    

  • በሬዲዮ ተሳትፎ

ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሬዲዮ መሳተፍ የጀመሩበት ጊዜ አባይነሽ ብሩ በ1984 ዓ.ም. ባቀረበችው ጥናቷ መሠረት አይታወቅም፡፡ በእሷ ግምት መሠረት ግን ከ1959 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሳምንታዊ ፕሮግራም የሚያሳየውና ከጥር እስከ ነሐሴ 1957 ዓ.ም. የነበረው ሮስተር እንደሚያረጋግጠው ሰኞ ጠዋት የሴት ባልትና፣ ቅዳሜ ጠዋት የቤተሰብ ኑሮና የሕፃናት አስተዳደግ ምክር፣ ሕመም፣ ሴቶችና ሙያቸው የተሰኙ ፕሮግራሞች እንደነበሩ እንገነዘባለን፡፡ ከዚህም ሌላ በ1954 ዓ.ም. የታተመ መጽሔት የሬዲዮ ጋዜጦችን ሲያስተዋውቅ ሴት አዘጋጆችም እንደነበሩ እንገነዘባለን፡፡ ይህም የሴቶች ፕሮግራም ከ1957 ዓ.ም. በፊት መጀመሩን የሚያመለክት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ይኼው ሮስተር ‹‹አስቴር ሞገስ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ማሠልጠኛ ክፍል ተማሪ›› ሲል ፎቶግራፏን እያነበበች አውጥቷል፡፡ ይሁንና ሴቶች በሬዲዮ የመሳተፋቸው ታሪክ የሚጀምረው ዜና ማንበብና ፕሮግራም ማቅረብ ከተጀመረበት ጊዜ ሳይሆን፣ በየትኛውም የሬዲዮና የቴሌቪዥን ታሪክ እንደተጻፈው ሁሉ ሙዚቃና ድራማ በማቅረብ እንዲሁም ማስታወቂያ በመስማት ተሳታፊ መሆን ከጀመሩበት ጊዜ በመሆኑ፣ የአገር ፍቅር ቴአትር የመጀመሪያዎቹ አርቲስቶች በዚህ ረገድ ግንባር ቀደሙን ታሪክ ምዕራፍ እንደሚይዙ መገመት ይቻላል፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋዜጦች ታሪክ ሲወሳ ግን የራሱ የጣቢያው ታሪክም መታየት ይኖርበታል፡፡ ‹‹ልሳነ ማስታወቂያ›› የተሰኘው መጽሔት አንደኛ ዓመት ቁጥር 1 በመጋቢት 1987 ዕትም እንዳሰፈረው፣ የሬዲዮ ሥርጭት የተጀመረው በ1928 ዓ.ም. ነው፡፡ ጣሊያን አገራችንን በወረረችበት ጊዜም የራሷን ፕሮግራም የምታሰራጭበት የሬዲዮ ጣቢያ አቋቁማ ነበር፡፡ በ1933 ዓ.ም. አገራችን ነፃነቷን ከተጎናጸፈች በኋላም የሬዲዮ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ተደራጅቷል፡፡ ይህም የማደራጀት ተግባር በ1946፣ በ1949፣ በ1952፣ በ1955 እናም ከዚያ ወዲህ ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል፡፡ በ1928 ዓ.ም. አገራችን በጣሊያን ስትወረር እቴጌይቱ ንግግር አድርገው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የሴቶች ተሳትፎ ከእቴጌይቱ የማይጀመርበት ምክንያት ከቶ ለምን ይሆን? ለነገሩ የሚጠቀሰው ግን የንጉሡ ንግግር ነው፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት በ1957 በሰጡት መግለጫ የሬዲዮ ጣቢያው ሲያስተላልፍ በነበረው ፕሮግራም በተለይም ‹‹መወያየት መልካም›› በተሰኘው ፕሮግራም ይሳተፉ እንደነበረ በፎቶግራፍ የተደገፉ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላም ሆነ የዚያን ጊዜ ሴቶችን የሚመለከቱ ብቻ ሳይሆኑ የሴት ፕሮግራም አዘጋጆች መኖራቸውን ከእነወ/ሮ ሮማን ወርቅ ካሳሁንና ከነወ/ሮ እሌኒ ፈጠነ ጋዜጠኝነት ከነሶፍያ ይልማ፣ ታቦቷ ወልደ ሚካኤል፣ እሌኒ መኩሪያ፣ ወዘተ ተሳትፎ እንረዳለን፡፡    

  • ተሳትፎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም. እንደ ተቋቋመ በሦስት ወር ውስጥ በወጣው ሳምንታዊ ፕሮግራም እንደሚመለክተው ዘወትር ሐሙስ ከ2፡15 እስከ 2፡45 ሰዓት ሴቶችና ሙያቸው የተሰኘው ፕሮግራም ነበረው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሴቶች ተሳትፎ ወዲያውኑ መጀመሩን ያረጋግጣል፡፡ ዓባይነሽ ብሩ ያቀረበችው ጥናት ግን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሴቶች ፕሮግራም ትውስታዎችን የሚጀምረው ከ1966 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ነው፤›› ይላል፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ እንደ እሌኒ መኩሪያ ያሉት ዜና አንባቢዎች ከ1966 ዓ.ም. በፊት እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ በዚህ ጊዜ በውጭ ማስታወቂያዎችና ፊልሞች ሴቶች ተሳታፊ ሆነው ይታዩ ስለነበረም፣ ሴቶቻችን በዚህ ረገድ እንዲሳተፉ የበኩሉን ቅስቀሳ ማድረጉ አልቀረም፡፡ በወቅቱ ይካሄዱ የነበሩት ቁንጅና ውድድሮች፣ ሐኪሞች፣ ባለሥልጣናትና ወታደሮች በቴሌቪዥን ሲታዩም እንደ ገነት በርሃ፣ ሙሉ ፀሐይ ቦጋለ፣ ብዙ ወንድማገኘሁ፣ ሳህለ ማርያም በየነ ያሉትን ለአቅራቢነትና ለአስተዋዋቂነት መሳቡ አልቀረም፡፡ በተለይም ከ1970 ዓ.ም. በኋላ አንፃራዊ በሆነ መልኩ በፕሮግራም አዘጋጅነት፣ በሪፖርተርነት፣ በአስተዋዋቂነትና በፊልም ኤዲተርነት በመቅጠሩ የሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ሌላ የኦሮሚኛ፣ የትግርኛ፣ የአፋርኛ፣ የሱማሊኛ፣ ወዘተ ፕሮግራሞች በመጀመራቸው ለእነዚህ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ተፈታኞች ቁጥር በሺሕ የሚቆጠር ሆኗል፡፡ ይህም ሴት ሪፖርተሮችን፣ አዘጋጆችንና አስተዋዋቂዎችን ማግኘት እጅግ ችግር ከነበረበት ከሃያ ዓመት አንፃር ሲታይ የሚበረታታ መሆኑን ነው፡፡

  • የሕዝብ ግንኙነት

በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው የሕዝብ ግንኙነት የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ነው፡፡ በመሆኑም በሕዝብ ግንኙነት ውስጥ የሚያገለግሉ ሴቶች ሁሉ ለጋዜጣ፣ ለሬዲዮ፣ ለቴሌቪዥን፣ ለመጽሔት፣ ለበራሪ ጽሑፎች የሚሆን ጽሑፍ ያዘጋጃሉ፡፡ የፊልምና የፎቶግራፍ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ ፕሬስ ኮንፈረንስ ወይም የቃለ መጠይቅ ተግባራት እንዲከናወኑ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡ ከሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛነት በተጨማሪም በውጭ ዜናዎች ወኪልነት የሚሠሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡

  •  

የአሁኖቹ ማስረጃዎች እንደሚጠቀሙት እስከ ቅርብ ጊዜ (1983) በልዩ ልዩ የፕሬስ መስኮች የተሳተፉት ሴቶች አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት ያጠናቀቁ ሲሆኑ፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁት ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ ከ1991 ዓ.ም. በኋላ ባለው ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነትና ጋዜጣ ነክ የሆኑ ትምህርቶች መሰጠት ከጀመሩ ወዲህ ግን በርካታ ሴት ጋዜጠኞች በሙያው እየተካኑ በመውጣት ላይ ናቸው፡፡ በልዩ ልዩ የፕሬስ ውጤቶች የሚታየው ተሳትፎም የሚያበረታታ ነው፡፡ ይሁንና ሴቶች በግልና በመንግሥት ጋዜጦች፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በማስታወቂያ ሥራ፣ በፊልም ሥራ፣ በአማተር ጋዜጦችና ደራስያን ክበብ፣ በየመሥሪያ ቤቶቹ ባሉ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ በማጥናትና ለመጪው ትውልድ የሚያረካ መረጃ ለማቆየት የሚደረገው ጥረት መጀመር አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ለመመረቂያ ወይም ለዲግሪ ማሟያ የሚጻፉት ጥናቶች ለጋዜጣ፣ ለመጽሔትና ለመጽሐፍ በሚያመች መንገድ እየተዘጋጁ ለአንባቢያን ቢቀርቡ ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም፡፡ ምንም እንኳን የመገናኛ ብዙኃን ዕድገት ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ብልጭ ድርግም እያለም ቢሆን ቀጥሏል፡፡ አሁን ትልቁ ችግር የፕሬስ ሕግ አለመኖር ወይም የሳንሱር ችግር አይደለም፡፡ የፕሬስ ሕጉ ይሻሻል፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተዘረጋው የፕሬስ ነፃነት በሰበብ አስባቡ አይደናቀፍ፣ ሰዎች ይጻፉ፣ ይናገሩ፣ ሳይሸማቀቁ ሐሳባቸውን ለመግለጽ ይቻሉ የሚል ነው፡፡ ይልቁንም ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት የሚያስፈልግበት መሠረታዊ ምክንያት ፕሬስ የመንግሥትና የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ስለሚያገለግል ነው፡፡ በእርግጥም ፕሬስ ብዙውን ጊዜ መንግሥት የሚሠራቸውን ጉድለቶች ስለሚያጋልጡ ምናልባት ላንዳንዶቹ መንግሥትንና ሕዝብን የሚጎዳ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ያላቸውና ያልተገነዘባቸው ግድፈቶች ቢኖሩ ስህተቱን በወቅቱ እንዲያርም ይረዳዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ ስለዚህ ፕሬስ ሕዝብንና መንግሥት አጥብቆ የሚተችና የሚኮንን እንኳን ቢሆን፣ የሚያቀርበው ትችትና ኩነና ትክክል ከሆነ መቀበል ለዕድገት እንጂ ለውድቀት አይዳርግም፡፡ ይህም ሆኖ ፕሬስ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ምን ያህል ገንቢ በሆነና የዴሞክራሲን ባህል በሚያዳብር ሁኔታ ተጠቅሞበታል?

እንደ እውነቱ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ትልቁ ችግር በአንዳንድ የግል ፕሬሶች አካባቢ ዜናንና ልቦለድ ድርሰትን ለያይቶ ለማየት ያለመቻል ችግር አለ፡፡ ልቦለድ ድርሰት በዜና መልኩ መቅረብ ከጀመረ ነፃ ፕሬስ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ማበብ ሊያገለግል አይችልም፡፡ ፕሬስና በአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አካባቢ የሚታየው ችግር ይህም እነዚህ ክፍሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖረውን ሚና፣ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ውስጥ በሚኖረው ለመለካት በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ መቻል አለበት፡፡ ፕሬሱ ተሰሚነት እንዲኖረው ከተፈለገ ብቸኛው አማራጭ በኅብረተሰቡ ውስጥ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የትም ቦታ የሚገባው ማመልከቻ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ፋይዳ ያለውን ሚና እንዲጫወት አያስችለውም፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ እስካላከበረና የመጨረሻ የፍትሕ ጥያቄ አቅራቢዎች የውጭ አገር ታዋቂ ግለሰቦች ወይም የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ድርጅቶች እስከሆኑ ድረስ ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም፡፡ ሊሆን የሚችለው ለየት ያለ ቅኝ አገዛዝ ምኞት ነው፡፡ አንዳንድ የግል ፕሬሶች ይህንን ባለመገንዘባቸው ገንቢ ሚና መጫወት ሲችሉ ባለፉት ዓመታት ሳይጫወቱ ቀርተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ወደፊት የሚጠብቀን ብሩህ ተስፋ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሕጉን መሠረት በማድረግ ገንቢ በሆነ አቅጣጫ መራመድ የፕሬሱ ፈንታ መሆኑን የሚገነዘብ ትውልድ ሲመጣ ለፈጠራ ወሬ፣ ለፀረ ሰላምና ለፀረ ልማት ዓላማ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚፈልጉ ግለሰቦች በሞኖፖል የያዙት መሆኑ ይቀርና ገንቢ በሆነ መንገድ መንግሥትን ተሚተቹም ሆኑ የሚቃወሙ የፕሬስ ውጤቶች ይመጣሉ፡፡ የሴቶች ተሳትፎም ከፍ ይላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...