Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልተስፋ የተጣለበት ‹‹የፊልም ዝግጅት››

ተስፋ የተጣለበት ‹‹የፊልም ዝግጅት››

ቀን:

‹‹የፊልም ዝግጅት፤ ቴክኒክና ጥበብ›› ቅጽ አንድ፣ በቅርቡ ገበያ ላይ የዋለ መጸሐፍ ነው፡፡ በሰሎሞን በቀለ ወያ የተጻፈው ‹‹የፊልም ዝግጅት›› ስለፊልም ሥራ ጥልቅ መረጃ የሚያስጨብጥ ሲሆን፣ ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በጎተ ኢንስቲትዩት በርካታ የፊልም ባለሙያዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡

መጽሐፉ ስለፊልም አሠራር አቅጣጫ በማመላከት ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያ ሲኒማ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ባለሙያዎች አንዱ በሆነው ሰሎሞን የተሰናዳውን መጽሐፍ ምርቃት ከታደሙት ባለሙያዎች መካከል ብርሃኑ ሽብሩ፣ ሰለሞን ማሞ፣ አብርሃም ኃይሌ ብሩና አበበ በየነ ይጠቀሳሉ፡፡ መጽሐፉ ለንባብ መብቃቱ በኢትዮጵያ ሲኒማ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሰሎሞን ማሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ሲኒማ በዕውቀት ለመምራት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች የተሻለ ደረጃ መድረሳቸውን ከሚያሳዩ አንዱ የመጽሐፉ መታተም ነው፤›› ብሏል፡፡ ብርሃኑ በበኩሉ በተለይ ወጣት ፊልም ሠሪዎች ከመጽሐፉ በሰፊው እንደሚጠቀሙ ጠቅሷል፡፡

አብርሃም መጽሐፉ ለፊልም ሥራ ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጠው ተናግሮ፣ ‹‹የሰሎሞንን ዕውቀት በበቂ እየተጠቀምንበት አይደለም፤›› ብሏል፡፡ ሐሳቡን የተጋራው አበበ፣ መጽሐፉ ባለሙያው ለዘርፉ ማበርከት ከሚችለው ትንሹ እንደሆነና በቀጣይ ለዘርፉ ጠቃሚ እውነታዎች የያዙ መጻሕፍት እንደሚያበረክት ያለውን እምነት ገልጿል፡፡

መጽሐፉን የመረቁት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ፣ መጽሐፉ በዘርፉ የሚጫወተውን የጎላ ሚና በአጽንኦት ገልጸው፣ በቅርቡ የተረቀቀው የፊልም ፖሊሲ እንዲሁም ሌሎች መሰል እንቅስቃሴዎች ለሲኒማው ዕድገት እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡

ከተማሪዎቹና ከሙያ አጋሮቹ በተደጋጋሚ የሚቀርብለትን ጥያቄ ተመርኩዞ መጽሐፉን እንዳዘጋጀው የገለጸው ሰለሞን፣ ፊልም ሠሪዎች እንደሚጠቀሙበት ያምናል፡፡  በርካቶች ‹‹አስቴር›› በተሰኘው ፊልሙ የበለጠ የሚያውቁት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጪ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ሰሎሞን ጽፎ ያዘጋጀው ባለ 35 ሚሊ ሜትሩ አስቴር ፊልም ለረዥም ወራት በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች የታየ ተወዳጅ ፊልም ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት የሦስተኛ ዓመት ተማሪዎችን የፊልም ድርሰት አጻጻፍና አዘገጃጀት አስተምሯል፡፡ በሥነ ጥበባት ኮሌጅ ሥር በሚገኘው ‹‹ዲጂታል አርትስ›› በተመሳሳይ ዘርፍ በድኅረ ምረቃ ያስተምራል፡፡

በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱንና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ተምሯል፡፡ የጀርመኑ ሹለ ሽሎሥ ዛሌም፣ የእንግሊዙ ሞልብራ ኮሌጅና የፈረንሣዩ ዩኒቨርሲቲ ድ ፓሪሶ ሴት ይጠቀሳሉ፡፡

ፈረንሣይ በሚገኘውና በእውቁ ፊልም ሠሪ ሉይ ሊምየር በተሰየመው ኮሌጅ የፊልም ድርሰትና ዝግጅት ተምሯል፡፡ በቀደሙት የፊልም ማዕከልና የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን የፕሮዳክሽን ኃላፊና ሲኒየር የፊልም ዳይሬክተር ሆኖ ለ11 ዓመታት ሠርቷል፡፡

 በወቅቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወረ ልዩ ልዩ ዘጋቢ ፊልሞች ሠርቷል፡፡ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ካገኙ ዘጋቢ ፊልሞቹ መካከል ‹‹ከድርቅ ጋር ትግል›› እና ‹‹ክዌንች›› ይጠቀሳሉ፡፡ በታዋቂና ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ በዳኝነት ሠርቷል፡፡ ፊልሞቹ በዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎችም ታይተዋል፡፡ በእውቅ መገናኛ ብዙኃንም ሽፋን አግኝተዋል፡፡ በቱኒዚያ፣ በሴኔጋልና በቡርኪናፋሶ የሠራቸው ዘጋቢ ፊልሞች ከነዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የምዕራብ አውሮፓ የፓን አፍሪካ ፊልም ሠሪዎች ፌዴሬሽን ወኪል ሆኖ በሠራበት ወቅት፣ ትውልደ አፍሪካውያን ፊልም ሠሪዎችን አደራጅቷል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የፖን አፍሪካ ፊልም ሠሪዎች ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ሆኖ ሲሠራ፣ የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር እንዲጠናከርና የፓን አፍሪካ ፊልም ሠሪዎች ፌዴሬሽን አባል እንዲሆን አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥና በውጪ አገር በሚያዘጋጃቸው ወርክሾፖችም ብዙዎችን አስተምሯል፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባዘጋጀው ወርክሾፕ ተሳታፊ የነበሩ ወጣት የፊልም ባለሙያዎች ‹‹የማይታይ ብክለት›› የተሰኘ አጭር ፊልም አዘጋጅተዋል፡፡ ፊልሙ በምርቃቱ ዕለት የቀረበ ሲሆን፣ ስለ ሰሎሞን ሥራዎች የሚያወሳ ዘጋቢ ፊልምም ታይቷል፡፡ ፊልሙ ከሰሎሞን የፊልም ሥራዎች በተጨማሪ ስለፎቶግራፍ ሥራዎቹና  ከዚህ ቀደም ያዘጋጀውን የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ዳሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...