Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልለግድቡ ገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ አልበም ሊታተም ነው

ለግድቡ ገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ አልበም ሊታተም ነው

ቀን:

–  ዳሽን ቢራ 1.5 ሚሊዮን ብር ለአልበሙ ለግሷል

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል የሙዚቃ አልበም   የተዘጋጀ ሲሆን፣ በቅርቡ ለኅትመት እንደሚበቃ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ከሚያስተባብራቸው በርካታ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው አልበሙ ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ በሲዲ ገበያ ላይ ለማዋል አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹ኅብር ሙዚቃ ለህዳሴያችን›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው አልበሙ፣ የ14 ብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ ያካተተ ነው፡፡ ዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ለሙዚቃ ክሊፖቹ ኅትመት እንዲሁም ለአልበሙ ምርቃት የሚውል 1,540,000 ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

ድርጅቱ ድጋፉን የለገሰው ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አጠገብ በሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በተካሄደ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛዲግ አብርሃ እንደተናገሩት፣ በአልበሙ የተካተቱት ዘፈኖች በግድቡ ግንባታ ሕዝቡ ስለሚያደርገው ተሳትፎ የሚያወሱ ናቸው፡፡

‹‹ግድቡ የሚገነባው በመላው የአገሪቱ ዜጎች የጋራ ተሳትፎና የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ በአልበሙ የ14 ብሔር ብሔረሰቦች ዘፈን መካተቱ ሥራውን ልዩ ያደርገዋል፤›› ብለዋል፡፡ አልበሙ ታትሞ ለሕዝብ እንዲደርስ ድጋፍ ያደረገውን ዳሸን ቢራንም አመስግነዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ድርጅቱ የ14 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ መፈጸሙን አስታውሰው፣ ‹‹ድርጅቱ ዳግም ድጋፉን አሳይቷል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዛዲግ በተለያየ የኪነ ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ባሙያዎች ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡን የሚያነሳሱ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ቀርበዋል፡፡፡ ሕዝቡ ‹‹ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ እንዲያደርግ ለማነቃቃትና ለማነሳሳት በምናደርገው ጥረት አርቲስቶች ከጎናችን ዘልቀዋል፡፡ ያለ አገራችን ብርቅዬ አርቲስቶች ድጋፍ ሕዝባችን በግድቡ ዙሪያ ያደረገውን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ከባድ ይሆን ነበር፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ በቦንድ ግዥ፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና የአካባቢ ጥበቃ ክንውኖች ሕዝቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ሕዝቡ መረጃ ማግኘት እንዲችል አርቲስቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ሥራዎቻቸው በተለይም ለቦንድ ግዥ ሕዝቡን በማነሳሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ገልጸዋል፡፡

‹‹የግንባታው ገንዘብ በዋነኛነት የሚሰባሰበው በቦንድ ሽያጭ ነው፡፡ የቦንድ ግዥውን የሚያነሳሱ ሥራዎችም ያስፈልጋሉ፤ ሕዝቡ ቦንድ ስለመግዛት እንዲያስብ የሚያደርጉና ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎች ተሠርተዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከነዚህ አንዱ 8100፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ገንዘብ በማሰባሰብና ለቦንድ ግዥ በማነሳሳት ተጠቃሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዛይድ በተመሳሳይ መልኩ ገቢ እንደሚያስገኝ የሚጠበቀው አልበም ለገበያ ሲበቃ ሕዝቡ ኦሪጅናል ሲዲውን በመግዛት ግድቡን እንዲሁም ሥነ ጥበቡን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሙዚቃ አልበሙ ዝግጅት ከ120 በላይ በጎ ፈቃደኛ አርቲስቶች የተሳተፉበት ነው፡፡

በአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ምክንያት ስለግድቡ ጉዳዮች የሚቀርቡ ዘገባዎች በመጠኑ መቀዛቀዛቸውን አክለው፣ የግድቡ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እየተከናወነ እንደሆነና ቅስቀሳው እንደሚጠናከር ተናግረዋል፡፡ የ8100 ሁለተኛው ዙር በቅርቡ  እንደሚጀመርም ጠቁመዋል፡፡

የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አቶ መክብብ ዓለሙ በርክክቡ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ‹‹ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተዜሙ ዘፈኖችን ለሕዝብ የማድረስ ግዴታ አለብን፡፡ ግድቡ ታሪካዊ ነውና ስለግድቡ የተዜሙትን አሳትሞ ለሕዝብ ማድረስ በመቻላችን ደስታና ኩራት ይሰማናል፤›› ብለዋል፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞች ቦንድ በመግዛትና ከወርኃዊ ደመወዛቸው ላይ ተቆራጭ በማድረግ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ የሐምሌ ወር ሙሉ ደመወዛቸውን ለግድቡ ግንባታ እንደሚለግሱ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በግደቡ ዙሪያ ከተካሄዱ ክንውኖች ‹‹የዓባይ ዘመን ጥበብ›› የሥዕል ዐውደ ርዕይ ይጠቀሳል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ከወራት በፊት የግድቡን መጋመስ ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሒልተን ባደረገው የምስጋና ሥነ ሥርዓት ላይ ሽልማት ካገኙ መካከል የተለያዩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...