[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ የብሔራዊ ፈተና ተፈትና ቤት ስትገባ አባቷን አገኘቻቸው]
- ደህና ዋልክ አባዬ?
- ደህና ነኝ፤ አንቺ እንዴት ዋልሽ?
- እኔ በጣም ደህና ነኝ፡፡
- ከትምህርት ቤት እየገባሽ ነው?
- አዎን፡፡
- ትምህርት እንዴት ነበር?
- ሰሞኑን እኮ ፈተና ላይ ነን፡፡
- እንዴ እና አሁን ተፈትነሽ ነው የምትመጪው?
- አዎን፡፡
- በእጅሽ ምንድነው የያዝሽው?
- ዛሬ የተፈተነው የፈተና ሽት ነው፡፡
- እስቲ አምጪው፡፡
- እሺ እንካ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ የፈተና ሽቱ ላይ መልሶቿን አክብባ ስለነበር ማረም ጀመሩ]
- በጣም ደስ ይላል፡፡
- ምኑ አባዬ?
- እስካሁን እኮ ኤክስ አላገኘሁብሽም፡፡
- የአባቷ ልጅ እኮ ነኝ፡፡
- ጐበዝ፤ እውነትም በእኔ ነው የወጣሽው፡፡
- የደፈንኩት ይመስለኛል፡፡
- መድፈን እኮ ከዘራችን ነው፡፡
- አንተም ትደፍናለህ እንዴ?
- መድፈን ቢሉሽ መድፈን ነው?
- አባዬ ግን አንተ ትማራለህ እንዴ?
- ኧረ አልማርም፡፡
- ታዲያ ምንድነው የምትደፍነው?
- ምን የማልደፍነው ነገር አለ ብለሽ ነው?
- መንግሥት ጋ ቀዳዳ አለ እንዴ?
- የምን ቀዳዳ?
- የሚደፈን ቀዳዳ፡፡
- አንቺ ልጅ አይደለሽ እንዴ?
- ብሆንስ ታዲያ?
- እንዲህ ዓይነት አሽሙር ማነው ያስተማረሽ?
- ትምህርት ቤት እኮ ብዙ ነገር ሲሉ እሰማለሁ፡፡
- ምን ይላሉ?
- እሱን ሌላ ጊዜ እነግርሃለሁ፡፡
- እንዴ የዚህን ጥያቄ መልስ ምንድነው ያልሽው?
- ቢ ነዋ፡፡
- ወይኔ!
- ምነው አባዬ?
- መልሱ ኤ ነበራ፡፡
- ስንተኛው ጥያቄ ላይ ነህ?
- የመጨረሻው ላይ ነኝ፡፡
- እኮ ስንት ኤክስ አገኘህብኝ?
- አንድ ኤክስ፡፡
- አሪፍ ነዋ አባዬ፡፡
- አሪፍ አይደለም፡፡
- ለምን?
- መድፈን ነበረብሽ?
- አንድ ኤክስ ስለሆነ እንደ ደፈንኩት ይቆጠራል እኮ፡፡
- እኔማ በእኔ እንድትወጪ ፈልጌ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- እኔ ፈተናዬን ደፍኘዋለኋ፡፡
- አልማርም አላልከኝም እንዴ?
- ሌላ ፈተና ነበረብኝ፡፡
- እና ደፈንከው?
- አዎን ደፈንኩት፡፡
- በዚህ ዘመን ግን የሚደፍን ሰው ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡
- እኔ አለሁ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- አነበቡት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑን?
- ጋዜጣው ይዞ የወጣውን፡፡
- ምን ይዞ ወጣ?
- ኦባማ እኮ ኢትዮጵያ ሊመጣ ነው፡፡
- አታውቅም ነበር እንዴ?
- እርስዎ ያውቁ ነበር እንዴ?
- ባለፈው እንግዳ ይመጣል አላልኩህም ነበር እንዴ?
- እኮ እንግዳ ይመጣል ነው ያሉኝ እንጂ መቼ ኦባማ አሉኝ?
- ለሴኩዩሪቲ ጉዳይ ብዬ ነዋ፡፡
- ለምን ይዋሻል?
- ምን አልከኝ?
- በጣም ደስ ይላል፡፡
- ምኑ ነው ደስ የሚለው?
- ኦባማ መምጣቱ፡፡
- ገና ብዙዎች ወደ ኢትዮጵያ ይጐርፋሉ፡፡
- ምን ሊያደርጉ?
- ሊማሩ ነዋ፡፡
- ከእኛ?
- አዎና፡፡
- ከእኛ ደግሞ ምን ይማራሉ?
- አንተ ኢትዮጵያ እኮ ትልቅ አገር ናት፡፡
- እንዴት?
- የሰው ልጅ መገኛ ናት፡፡
- እሱን አውቃለሁ፡፡
- የሥልጣኔ መገኛ ናት፡፡
- እሱማ ትክክል ነው፡፡
- የቡናም መገኛ ናት፡፡
- እሱንም አውቃለሁ፡፡
- አሁን ደግሞ የአንድ አዲስ ነገር መገኛ ሆናለች፡፡
- የምን?
- የዲሞክራሲ፡፡
- ምን አሉኝ?
- የዲሞክራሲ መገኛ አልኩህ፡፡
- እኛን ነው አሜሪካንን ነው የሚሉኝ?
- እኛ ነን እንጂ፡፡
- እኮ እንዴት ሆኖ?
- ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂደን መቶ በመቶ ማሸነፍ ችለናል፡፡
- ምን አሉኝ?
- ስለዚህ ቻይና ያሉ ወንድሞቻችን ከዚህ መማር ይፈልጋሉ፡፡
- ምንድነው የሚማሩት?
- እነሱ እኮ ምርጫ ሳያካሂዱ ነው ማሸነፍ የቻሉት፡፡
- እሱማ ይታወቃል፡፡
- እኛ ደግሞ ምርጫ አካሂደን መቶ በመቶ ማሸነፍ ችለናል፡፡
- አሃሃ…
- ስለዚህ ገና ሌሎች በርካቶች እኛን ይጐበኙናል፡፡
- እነማን ናቸው?
- እነ ሳዑዲ ዓረቢያና ሰሜን ኮሪያ የመሳሰሉ፡፡
- እነዚህ አገሮች እኮ ምርጫ አካሂደው አያውቁም፡፡
- ለዛ እኮ ነው የምልህ?
- እንዴት?
- ምርጫ ባለማካሄዳቸው ስለሚወቀሱ፣ ምርጫ አድርገው ማሸነፍ እንደሚችሉ እናስተምራቸዋለን፡፡
- በጣም የሚገርም ሐሳብ ነው፡፡
- ከዚህ በኋላ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ ማተኮር አለብን፡፡
- ለምን?
- ዓለም ሁሉ ወደ እኛ ይጐርፋላ፡፡
- እኮ ለምን?
- ከእኛ ለመማር፡፡
- እና ኦባማም የሚመጡት ለዚህ ነው?
- እንዴታ?
- ከእኛ ሊማሩ?
- አሜሪካ እኮ በቅርቡ ምርጫ ታካሂዳለች፡፡
- እውነትም የእኛ ዕድገት የኢኮኖሚ ብቻ አይደለም ማለት ነው?
- ምን ነካህ? በኢኮኖሚ ብቻ አድገህ በዲሞክራሲ ካላደግህ እኮ ዋጋ የለውም፡፡
- እና በዲሞክራሲውም ልክ እንደ ኢኮኖሚው 11 ፐርሰንት አድገናል ማለት ነው?
- የዲሞክራሲው ከዛም ከፍ ይላል፡፡
- ስንት ፐርሰንት?
- መቶ ፐርሰንት፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ከውጭ ደወለ]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- እንኳን ደስ አለዎት፡፡
- ለምኑ?
- ያው ውጤቱ መቶ ፐርሰንት መሆኑን ሰምቼ ነው፡፡
- የሥራችን ውጤት ነው፡፡
- የእስራችን ውጤት ነው ያሉኝ?
- የለም የለም፤ የሥራችን ውጤት ነው፡፡
- ለነገሩ ልክ ብለዋል፡፡
- ከለፋህ ሁሌም ያልፍልሃል፡፡
- ካለፉ ግን ሊያልፍብዎት ይችላል፡፡
- ሥራህ በግልጽ ከታየ ዓለምም ያደንቅሃል፡፡
- ዓለም መቼ አደነቀን ታዲያ?
- ከዚህ በላይ መደነቅን በምን እንለካው?
- ዓለም መደነቁን በምን አወቁ?
- ይኸው ሊጐበኘን እኮ ነው፡፡
- ማን ነው የሚጐበኘን?
- የዓለም መሪው ኦባማ ሊጐበኘን ነው እኮ፡፡
- ታዲያ እንዳደነቀን በምን አወቁ?
- ስለሚጐበኘን ነዋ፡፡
- የሚጐበኘን በሌላ ምክንያት ቢሆንስ?
- ተደንቆብን ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?
- ታዝቦን፡፡
- ምን?
- ምርጫውን እንዲታዘቡ መንግሥት ስላልጋበዛቸው ከውጤቱ በኋላ ራሱ ሊታዘበን እየመጣ ቢሆንስ?
- ተቃዋሚ ሆንክ እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ችግርዎት እኮ ይኼ ነው፡፡
- ምንድነው ችግሬ?
- ከእርስዎ አመለካከት ውጪ የሆነ ሁሉ ተቃዋሚ ይመስልዎታል፡፡
- ታዲያ ይህ የተቃዋሚ እንጂ የደጋፊ ሐሳብ ነው?
- ድጋፋችን ጭፍን መሆን የለበትም፡፡
- ዓይንህን ካልጨፈንክ እኛን መደገፍ እንዴት ትችላለህ?
- ለነገሩ እውነትዎትን ነው፡፡
- እና አሁን ዓይንህን ገልጠሃል?
- ሁለቱንም ባይሆን አንዱን ገልጫለሁ፡፡
- እየተጣቀስክ ነዋ?
- ሁለቱንም ከመግለጤ በፊት መስተካከል ያለበትን አስተካክሉ፡፡
- እሺ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
- መቼም ሰሞኑን ጉራህ አይቻልም?
- ለምኑ?
- ኦባማ ሊመጣ መሆኑን ሰምቼ ነዋ፡፡
- ሥራችን ገና ብዙዎችን ያስመጣል፡፡
- ጀመረህ ጉራህ፡፡
- ጠንክረን እየሠራን ስለሆነ በርካታ መሪዎች ገና ይመጣሉ፡፡
- የመጀመሪያ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆኑ ነው ኢትዮጵያን ሲጐበኝ?
- የለም የለም፤ ከዚህ በፊት ሌሎችም ጐብኝተውናል፡፡
- እነማን?
- ቡሽ ብትይ፣ ክሊንተን ብትይ፣ ካርተር ብትይ፡፡
- ይኼ እኮ ነው ችግርህ፡፡
- እንዴት?
- እነሱ እኮ የመጡት ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ነው፡፡
- ቢወርዱስ?
- እንደ እናንተ ከወረዱም በኋላ አገሪቱን የሚገዙ ይመስልሃል አይደል?
- ምነው ወሬ አበዛሽ?
- ለመሆኑ ለምንድነው የሚመጣው?
- ለሁለት ነገር ነው፡፡
- ለምንና ለምንድነው?
- በመጀመሪያ ከእኛ ለመማር ነው፡፡
- እንዴት?
- በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መቶ ፐርሰንት እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ለመማር ነው፡፡
- ሁለተኛውስ?
- በዓለም መሪዎች ፊት ለዚህ የምርጫ ውጤት ሽልማት ሊሰጠን ነው፡፡
- ለምን ይሸልማችኋል?
- ስለደፈነው፡፡
- ሙገሳ ስትጠብቅ ሌላ እንዳይገጥምህ፡፡
- ሌላ ምን?
- ሙለጫ!