Friday, March 24, 2023

የሽብርተኞችና የፀረ ሽብርተኝነት አዲሱ ትርክት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በቁጥር በርከት ያሉት የኮሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ተገናኝተዋል፡፡ ለተሳታፊዎች መድረኩ የተዘጋጀው በምርጫ ማግሥት ቢሆንም በሽብርና በምርጫ ላይ ለመምከር ነው፡፡ በአዳማው ቲታስ ሆቴል አዳራሽ በቅርቡ በተጠራው የውይይት መድረክ ላይ የተሰየሙት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ በሁለቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ የኒዮ ሊበራሊዝም አስተሳሰብ አራማጆች፣ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነትና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጆች፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትና የፀረ ሽብርተኝነት ትግል ምን እንደሚመስሉ ጉዳዮቹን በማገናኘት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ያለምሕረት መነጋገር አለብን?››

አቶ ሬድዋን በሽብርተኝነት ላይ በምዕራቡ ዓለምና በኢትዮጵያ መንግሥት አተያይ መካከል ያለው ልዩነት ላይ በማተኮር ሐሳባቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የቀድሞ የአውራምባ ጋዜጣ ባለቤትና የሲፒጄ ተሸላሚ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ሁለት ዓይነት የምዘና (Double Standard) አሠራሮች አቅርቧል፡፡ አቶ ሬድዋንም የኢትዮጵያ ፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ከምዕራባውያን፣ በተለይ ደግሞ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ የተቀዳ ነው የሚለውን የተለመደ አስተያየት ሰንዝረው፣ ለምን አዋጁ ላይ ተቃውሞ እንደሚያሰሙ አብራርተዋል፡፡ ‹‹አሜሪካ ውስጥ አንድ ጥቁር 20 ዓመት ከታሰረ በኋላ ነፃ ነው ተብሎ ይለቀቃል፡፡ ነጭ ቢሆን ግን በጥርጣሬ አይታሰርም ነበር፤›› በማለት እዚያ አለ ያሉትን የዘረኝነት ገጽታ አንፀባርቀዋል፡፡ ‹‹በነገራችን ላይ በዚያ አገር እስር ቤቶች የግል ናቸው፡፡ ሰው ካልታሰረ ይከስራሉ፣ ይዘጋሉ፡፡ እንዲያተርፉ ሰው መታሰር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር ሲያነፃፅሩም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ በሽብር ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው በአራት ወራት ውስጥ ክስ ይመሠረትበታል፡፡ አልያም ይፈታል፡፡ እነሱ ዘንድ ግን ምንም የጊዜ ውሱንነት የለውም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በሽብር ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው ዓቃቤ ሕግ (ከሳሽ) ወንጀለኛ መሆኑን የማረጋገጥ (Burden of Proof) ግዴታ አለበት፡፡ አሜሪካ ውስጥ በሽብር የተከሰሰ ሰው ወንጀለኛ አለመሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት ራሱ ነው፤›› ብለው፣ የኢትዮጵያ አዋጅ ከአሜሪካ የተለየበትንና ኢትዮጵያ ያልተቀበለቻቸውን አንቀጾች ጠቁመዋል፡፡

በቅርቡ በባልቲሞርና በቴክሳስ የተፈጸሙትን ክስተቶች በምሳሌነት አንስተው፣ ‹‹ክስተቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆኑ ዘረኝነቱ የሥርዓቱ ተደርጎ ነበር የሚዘገበው፡፡ አሜሪካ ውስጥ ግን የግለሰብ ተደርጎ ይወሰዳል፤›› ብለዋል፡፡ እንዲሁም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጋዜጠኛ በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ ሲከሰስ በእነሱ ጀግና ተብሎ ይሸለማል፡፡ እስቲ አስቡት አሜሪካ ውስጥ ቢን ላደንን ጀግና ብሎ የጻፈ ሰው ዕጣ ፈንታው ምን እንደሚሆን?›› ያሉት አቶ ሬድዋን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የእኛ ጀግና›› ብለው የሚጽፉ ጋዜጦች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በተመሳሳይ የሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሰ ሰው ጀግና ተብሎ ሲነገር ‹ምነው?› ብለን ስንጠይቅ ነው በእነሱ የምንወቀሰው፤›› በማለትም ተቃርኖውን አመልክተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ስምም በመጥቀስ (አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሲፒጄ፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች) በተመሳሳይ ተችተዋል፡፡ ጋዜጠኛ ዳዊት በራሱ ላይ ደርሰዋል ያላቸውን ጉዳዮች እንደ አብነት በማቅረብ ገለጻ አድርጓል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት የሁለት ዓይነት ምዘና (Double Standard) ችግር እንዳለባቸው በማንሳት፣ ‹‹ከንቀት ስለሚጀምሩ የእኛን እውነታ ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ችግራችንን ሳይሆን የሚነግሩን ጥንካሬያችንን ነው የሚያጨልሙብን፡፡ የእኛን ችግር በተመለከተ ያለምሕረት መነጋገር አለብን፤›› በማለት የአተያይ ችግር እንዳለ አስረድቷል፡፡

‹‹ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ፍጥጫው እስከ መቼ ነው? በቅርበት የምትነጋገሩበት ሁኔታ የለም ወይ? በመጨረሻ እነሱ [ምዕራባውያን] የደረሱበት ለመድረስ አይደለም ወይ የምንሮጠው?›› ከውይይቱ ተሳታፊዎች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ አቶ ሬድዋን በኢትዮጵያና በምዕራባውያን መካከል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት እንዳለ፣ እንዲሁም አንዱ ሌላው ላይ ለመጫን የሚያደርጉትን ጥረት ካላቆሙ የሚደረጉ ውይይቶችና መግባባቶች ፍሬያማ እንደማይሆኑ አስረድተዋል፡፡

ዋና ዋና ‹‹የሰለፊ›› አመለካከቶች

በዚሁ የሽብርተኝነት ጉዳይ ላይ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ለሽብርተኝነት የተመቹ የባህል እሴቶች፣ በሽብርተኝነት ፍቺ ላይ ያለው አለመግባባት፣ የሽብርተኝንት ምንጭና የሽብርተኞችን ሥነ ልቦና በተመለከተ አስረድተው፣ ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አምርተዋል፡፡

ከሽብርተኝንት ጋር የተያያዙት ፅንፈኝነትና አክራሪነትን የመሳሰሉ ጽንሰ ሐሳቦችም ጋር ያለውን ግንኙነትና ርቀትም አቅርበዋል፡፡ ‹‹ከፅንፈኝነት ወደ ሽብርተኝነት ያለው የሽግግር ሒደት (Pupa) ወደ ሙሉዕ አካል (Larva) ካለው ዕድገት›› ጋር አመሳስለውታል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ፅንፈኛና አክራሪ ሳይሆን ሽብርተኛ መሆን አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ራሱን አክራሪ እስኪያደርግ ድረስ የሽብር ተግባር እንዲፈጽምም አይፈቅድለትም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ማናቸውም ቤተ እምነቶች ከባህል ውጪ አይደሉም፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ የሃይማኖት ሽብርተኞች የአገሪቱን ባህላዊ እሴት የሚቀበለውንና እንግዳ ያልሆነውን የሱፊዝም አመለካከት በማግለል፣ የ‹‹መቻቻል ፀር›› ያሉትን የሰለፊዝም አስተሳሰቦች እንዴት የሙጥኝ እንዳሉ እያነፃፀሩ አመላክተዋል፡፡

የሰለፊስቶቹ የጋራ ባህሪያት ያሉዋቸውን፣ ‹‹ቅዱሳን መጻሕፍት ተራክሰዋል፣ ሊቃውንት ተረስተዋል…›› በማለት፣ አስተሳሰቡ የእስልምና እምነት ትልቅ የሃይማኖት ዝቅጠት አጋጥሞታል ከሚል ድምዳሜ እንደሚነሳም ተናግረዋል፡፡

‹‹የሰለፊ አመለካከት ባለበት ቦታ ሁሉ ጦርነት፣ ግጭትና ማኅበራዊ ቀውስ አለ፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ አይኤስአይኤስ በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሰውና በተለይ በተለያዩ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ያሉትን ጥንታዊ ቅርሶች የሚያወድመውና በሰው ልጆች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን የሚፈጽመው ከዚሁ አስተሳሰብ በመነሳት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዓለማዊ (Secular) መንግሥት አይቀበልም፡፡ የተለያዩ እምነቶችና አስተሳሰቦች እንዲኖሩ አይፈቅድም፡፡ በመጨረሻም አንድ በሸሪዓ የሚመራ የዓለም መንግሥት እንዲቋቋም ይፈልጋል፤›› በማለትም የመጨረሻ ዕቅዱንና ግቡን አመልክተዋል፡፡

‹‹ሰለፊዝም ጥግ የያዘ የፖለቲካ ንቅናቄ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹ለሰለፊስቶች ዓለማዊ መንግሥት መቀበልም ሆነ ከሌላ ማኅበረሰብ ባህል ጋር ተቻችሎ መኖር ዝቅጠት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ዓመት በፊት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ መንግሥት ጣልቃ ገብቷል በመባሉ፣ ከመንግሥት ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህም ጋር በተያያዘ የአስተባባሪው የኮሚቴው አባላት ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ወሃቢያ በመባል የሚታወቀው አስተምህሮ የሰለፊስቶች አስተሳሰብ አራማጅ ነው በማለት የተናገሩት አቶ ሽመልስ፣ ‹‹በአካሄድ ላይ ብቻ ልዩነት አላቸው፡፡ አሸዋ ውስጥ አንገቷን እንደቀበረች ሰጎን ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ቀስ በቀስ ጉልበት እያገኙ በሄዱ ቁጥር በናይጄሪያ ብዙ ጥፋት እየፈጸመ ካለው ቦኮ ሐራም ጋር በማነፃፀር በእንጭጩ ካልተቀጩ ወደዚያ ማደጋቸው አይቀሬ ነውም ብለዋል፡፡ በናይጄሪያ ችግሩ በመንግሥት አመራር ውስጥ ዘልቆ መግባቱንም አስታውሰዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶች ጋር ተቻችሎ ይኖራል ያሉት የሱፊ ሙስሊሞች እምነት፣ ያለፉት ገዢዎች ከሃይማኖት ጋር በነበራቸው የመጣበቅ ምክንያት ደካማ ተቋማዊ አቅም እንዳለውና ራሱን መቋቋም በማይችልበት ደረጃ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሱፊዎች ለዘብተኞች በመሆናቸውም ወጥተው መታገል አልቻሉም፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ዕርዳታ እንደሚያሻቸውም ጠቁመዋል፡፡ ሱፊዝምን የሚያስተምሩ አባቶችን ስም የማጥፋትና የመሰወር ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሰለፊዝም የፖለቲካ ንቅናቄ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የዋሃቢስቶችን እንቅስቃሴ የዘረዘሩ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ውስጥም የራሳቸው ግዛት እየፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡ አንዳንድ ተነጥለው የሚኖሩባቸውን ቦታዎችንም እንደ (አየር ጤናና ኮልፌ) የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡

ለአቶ ሽመልስ በተሳታፊዎች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፣ ‹‹የመንግሥት አመራር በጉዳዩ ላይ በበቂ ደረጃ ዕውቀት አለው ወይ?››፣ ‹‹በመንግሥት ውስጥ ይህ አስተሳሰብ ሰርጎ ላለመግባቱ ምን ማረጋገጫ አለ?››፣ ‹‹የሽብርተኝነት ኔትወርኩ በውል ተጠንቷል ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

አንድ ከግል ሚዲያ የተወከለ ጋዜጠኛ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን የሚይዝበት አኳኋን አግባብነት እንደሌለውና በመንግሥት ይፈጸማሉ ያላቸውን ተዛማጅ ጥያቄዎች አንስቷል፡፡ ሌላ አስተያየት ሰጪ ግን፣ ‹‹እንዲያውም መንግሥት ከመጠን በላይ ትዕግሥት አድርጓል፡፡ እነሱ በገንዘብ የትና የት ደርሰዋል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡

ሌላ አስተያየት ሰጪም፣ ‹‹እነሱን ከማውገዝና ደጋግመን ስለነሱ ከማውራት ይልቅ ምን ቢደረግ ይሻላል? እያንዳንዱ ዜጋ ምን መሥራት አለበት? በሚለው ላይ ብንነጋገር ይሻላል፤›› በማለት ሐሳባቸውን ያንፀባረቁ ሲሆን፣ አሸባሪዎች ዘመኑ የሰጣቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በተራቀቀ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

አቶ ሽመልስ የተነሱ አስተያየቶችን እንደሚቀበሉና በቀጣዩ ሥራቸው ላይ አካተው እንደሚሠሩ በመግለጽ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት ሽብርተኞች በሚላቸው አካላት ላይ ስለሚወስደው ዕርምጃ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የሽብርተኝነት ድርጊት መስዋዕትነት እየተከፈለበት መጥቷል፡፡ የትዕግሥትና የጥንቃቄ ዕርምጃ ብቻ ሲወሰድ ቆይቷል፤›› ብለው፣ ፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የተረቀቀበት ምክንያት የተጠናከረ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ተቀናቃኝ የሆኑ አክራሪ የፖለቲካ ድርጀቶችን (ኦነግና ኦብነግ) የመታገል እንጂ፣ የሃይማኖት አክራሪነትን የመታገል ልምድ የለንም፡፡ ለችግሩ ደንታ ቢስ ሆነን ግን አልነበረም፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ችግሩ ግልጽ ሆኖ እርቃኑን ወጥቷል፤›› በማለት ግልጽ የሆነ የማታገያ ስትራቴጂ መቅረፅ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ እስካሁን የነበረው አካሄድ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ሁለት ዕርምጃ ወደኋላ እንደነበር ጠቅሰው፣ ‹‹ቅድሚያ የምንሰጠው አስተሳሰብን በአስተሳሰብ ለመመከት ነው፡፡ ብቅ ሲሉ የምንረባረብበት፣ ዝም ሲሉ የምናንቀላፋበት ጉዳይ አይደለም፤›› በማለት አጠቃለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -