የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ አዲስ አበባ እስከ አዳማ የተገነባው የፍጥነት መንገድ አካል የሆኑ ሁለት መንገዶች በከፊል ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሊሆኑ ነው፡፡ ከአቃቂ ለቡና ከአቃቂ የረር በመገንባት ላይ ያሉት መንገዶች አንደኛው መስመራቸው ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን፣ ግንባታቸው በፍጥነት እንዲካሄድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ሁለቱ መንገዶች ግንባታቸው በየካቲት 2008 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀድም፣ በአካባቢው እየተፈጠረ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ በጣም እየጨመረ በመምጣቱ ትራንስፖርት ሚኒስቴር በሰጠው መመርያ፣ አንደኛው ረድፍ በአፋጣኝ ተገንብቶ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በዚህ መሠረት የቻይናው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሲሲሲ ግንባታው በማገባዳደድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጠን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የፍጥነት መንገዱ መጨረሻ ከሆነው አቃቂ ተነስቶ ለቡ ድረስ ያለው 13.6 ኪሎ ሜትር እና ከአቃቂ ተነስቶ አይሲቲ ፓርክ (የረር ጎሮ) ድረስ የሚገነቡት መንገዶች ናቸው ለትራፊክ ክፍት የሚሆኑት፡፡
እነዚህ መንገዶች በአጠቃላይ ስድስት መኪኖችን በአንድ ጊዜ የሚያስተላልፉ ሲሆን፣ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት የሚሆነው አንደኛው ረድፍ ሦስት መኪኖችን በአንድ ጊዜ ያስተላልፋል ተብሏል፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች 4.6 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸው ሲሆኑ፣ ከአጠቃላይ ወጪ 75 በመቶ የቻይና ኤግዚም ባንክ ቀሪውን 25 በመቶ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ይሸፍናሉ፡፡
የመንገዶቹ ግንባታ ባለፈው 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ነው የተጀመረው፡፡ በሁለት ዓመት ከስምንት ወር ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ ነገር ግን አንዱ ረድፍ የግድ ማለቅ አለበት በመባሉ ግንባታው እየተፋጠነ በመሆኑ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል፡፡
እነዚህ ሁለት መንገዶች ከአዲስ አበባ-አዳማ ድረስ የተገነባው ግዙፍ የፍጥነት መንገድ አካል ናቸው፡፡ የአዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድ 84.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው 12.2 ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ሁለቱ መንገዶች እንደተጠናቀቁ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከቃሊቲ እስከ አቃቂ ድረስ ያለውን መንገድ ደረጃ የሚያሻሽል መሆኑ ታውቋል፡፡
ይኼ መንገድ ብቸኛው የአገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ የሚከናወንበት በመሆኑ ተለዋጭ መንገድ ሳይገነባ የመንገዱን ደረጃው ማሻሻል አይቻልም ተብሎ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የፍጥነት መንገዱ በሁለት አቅጣጫዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመዘርጋቱ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ወደ ግንባታ ይገባል በማለት ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ አገር ውስጥ ባለመኖራቸው አስተያየታቸውን ማካተት ሳይቻል ቀርቷል፡፡