– ‹‹መድረክና ሰማያዊ ፓርቲዎች ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል›› ፕሮፌሰር መርጋ በቃና
– የጊምቦ ገዋታ የምርጫ ውጤት አልተካተተም
በመላው ኢትዮጵያ (ከጊምቦ ገዋታ ምርጫ ጣቢያ በስተቀር) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደውን የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አገራዊ ምርጫ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸውን፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እንደገለጹት፣ ቦርዱ በአዋጅ ቁጥር 532/99 አንቀጽ 77 መሠረት አጠቃላይ የምርጫውን ውጤት ይፋ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ለአምስተኛው አገራዊ ምርጫ 36,851,461 ሕዝብ በመራጭነት ተመዝግቦ፣ 34,351,444 ሕዝብ ድምፁን ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 334 ወንዶችና 212 ሴቶች በዕጩነት አቅርበው አሸናፊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ ካለው 547 መቀመጫዎች 546ቱን ሲያሸንፉ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ብቸኛው የግል የፓርላማ አባል የነበሩት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስና የኢሕአዴግ ዕጩ ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም (የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት) የሚወዳደሩበት የቦንጋ ጊምቦ ገዋታ ምርጫ ክልል ውጤት ይፋ ባለመደረጉ፣ ከተገለጸው ውጤት ጋር አለመካተቱን ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡
ለክልል ምክር ቤቶች ኢሕአዴግና አጋሮቹ፣ 1187 ወንዶችና 800 ሴቶች በድምሩ 1,987 አባላት በዕጩነት አቅርበው ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸውን ፕሮፌሰሩ አክለዋል፡፡
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 52 የፖለቲካና ዘጠኝ የግል ዕጩዎች ለ547 መቀመጫዎች የተወዳደሩ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ በአምስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሐረሪ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች 27,347,332 ድምፅ በማግኘት 500 መቀመጫዎችን ያለምንም ተቀናቃኝ ማሸነፉን ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡
ለሁለቱ ምክር ቤቶች 40,536,607 የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መቅረቡን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ 1,130,390 ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ዋጋ አልባ መሆናቸውንና 520,379 ድምፅ መስጫዎች መበላሸታቸውን ተናግረዋል፡፡
በምርጫ ውድድሩ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲዎች ሁለተኛና ሦስተኛ መውጣታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር መርጋ፣ የምክር ቤቶቹን መቀመጫዎች የሚያስገኝ ድምፅ ባለማግኘታቸው ተሸናፊ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ቦርዱ የሕዝብ ድምፅ ማስከበር እንዳለበት የተናገሩት ሰብሳቢው፣ ይኽንኑ ተግባራዊ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ በደቡብ ክልል የጊምቦ ገዋታ ምርጫ ክልል የምርጫ ውጤት ለቦርዱ መድረሱን ጠቁመው፣ ቦርዱ ውጤቱን ባለማፅደቁ በዕለቱ በገለጹት ውጤት ላይ አለመካተቱን፣ ነገር ግን በቅርቡ ፀድቆ በቦርዱ ድረ ገጽ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በጊምቦ ገዋታ ምርጫ ክልል በተካሄደው ምርጫ፣ የኢሕአዴግ ዕጩ ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም የግል ዕጩውን ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስን በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸውን ከምርጫ ጣቢያዎቹ ከተገኘው መረጃ መረጋገጡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡