Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ለማዳበሪያ ትራንስፖርት ተስፋ ተጥሎበታል

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአሁኑ ወቅት 85 በመቶ የተጠናቀቀው ከአዲስ አበባ-ጂቡቲ ድረስ እየተገነባ ያለው የባቡር መስመር በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት ይስጣል ተባለ፡፡ በሎስጂቲክስ ችግሮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ከማምጣቱም በላይ፣ ከውጭ ለሚገባ ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያ ትራንስፖርት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

  የኢትዮጵያ ግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ በየነ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባቡሩ ሥራ የሚጀምር ከሆነ ማዳበሪያው ታሽጎ ወይም በብትን ይግባ የሚለው ይታያል፡፡ ነገር ግን ባቡሩ ሥራ ከጀመረ በብትን ማስገባቱ አዋጭ ይሆናል ሲሉ አቶ በየነ አስረድተዋል፡፡

  ለሚቀጥለው ምርት ዘመን የሚፈለገውን ማዳበሪያ መጠን ለማወቅ ግብርና ሚኒስቴር ቅኝት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ዘርፉ የሚፈለገውን የማዳበሪያ መጠንና ዓይነት ከክልሎች እየሰበሰበ ሲሆን፣ በይደር የሚቆየውን ማዳበሪያ መጠን በመገምገም ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

  የአገሪቱ ግብርና ዘርፍ የሚፈለገውን የማዳበሪያ መጠን እንደታወቀ፣ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ጨረታ አውጥቶ ግዥ እንደሚፈጽም ተጠቁሟል፡፡

  ለ2007 ዓ.ም. ምርት ዘመን 894 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ዩርያና ኤንፒኤስ ማዳበሪያዎች ግዥ ተፈጽሞ፣ አብዛኛው አገር ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ አገር ውስጥ የገባው ማዳበሪያ በኩንታል 1,200 ብር አካባቢ በመሸጥ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

  ነገር ግን በ2007 ዓ.ም. ግዥ ከተፈጸመው ማዳበሪያ ውስጥ አንድ መርከብ ማዳበሪያ በአሁኑ ወቅት በጂቡቲ ወደብ በመራገፍ ላይ ይገኛል፡፡ አቶ በየነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግብርና ሚኒስቴር አገሪቱ የምትፈልገውን የማዳበሪያ መጠንና ዓይነት እንዳሳወቃቸው ግዥ ለመፈጸም ወደ ገበያ ይወጣሉ፡፡

  የግብርና ሚኒስቴር ግብርና ግብዓት ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ላቀው በበኩላቸው፣ ክልሎች የማዳበሪያ ፍላጎታቸውን በነሐሴ ወር እንደሚያሳውቁና በጥቅምት ወር ወደ ግዥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

  በዚህ የምርት ዘመን ግዥ የተፈጸመው 894 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ሲሆን፣ አንዱ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ከ412 ዶላር እስከ 480 ዶላር ግዥ ተፈጽሟል፡፡ በምርት ዘመኑ ለማዳበሪያ ዘርፍ አስቸጋሪ ጉዳይ የነበረው የትራንስፖርት ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም የሆነው ማዳበሪያን በዝቅተኛ ዋጋ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ሲባል በትራንስፖርት ሒሳብ ላይ ተመን በመውጣቱ ነበር፡፡

  ይህም የትራንስፖርት ድርጅቶችን ትኩረት መሳብ ባለመቻሉና በወቅቱ በርካታ ዕቃዎች ጂቡቲ ወደብ ደርሰው የነበረ በመሆኑ፣ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማጓጓዝ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡

  አቶ በየነ እንዳሉት፣ በሚቀጥለው ዓመት ይህንን ችግር ለመፍታት ከወዲሁ ከባህር ትራንስፖርትና ከሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ጋር ንግግር ይጀመራል፡፡ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ድረስ በሚገነባው የባቡር መስመር ችግሩ ሊቀረፍ እንደሚችል አቶ በየነ ያላቸውን እምነት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

  የዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ዋጋም በዚህ የምርት ዘመን ከተገዛበት ዋጋ ቅናሽ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚናገሩት አቶ በየነ፣ በሚቀጥለው ምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ የሚቀርበው ማዳበሪያ የዋጋ ቅናሽ ሊኖረው ይችላል ብለዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚፈልገው ማዳበሪያ መጠን እያደገ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ አፈሩ የሚፈልገው ማዳበሪያ ዓይነትም ተለይቶ እንደታወቀ ተገልጿል፡፡ በግብርና ዘርፍ ውስጥ ብዙም  የማይታወቀው ኤንፒኤስ ማዳበሪያ፣ የአገሪቱን ግብርና የተቀላቀለ በመሆኑ በአገሪቱ አምስት ማዳበሪያ ፋብሪካዎችም አፈሩ የሚፈልገውን ማዳበሪያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች