Tuesday, June 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመገንጠል ጥያቄ በሎግያ

በሐናንያ መሐመድ (ከአፋር)

ከሰው መንጋ እንገንጠል፣

ለአንድ አፍታ እንኳ እንገለል፣

በዕፎይታ ጥላ እንጠለል…

መገንጠል ለዕፎይታ፣ ለነፃነትና ራስን ለመቻል ወዘተ… ካለ ከፍተኛ ጉጉትና ምኞት የሚፈጠር ከውስጥ የሚመነጭ ስሜት ነው፡፡ ቢሆንም ግን መገንጠልን አንዳንድ ጊዜ ተገንጣይም አስገንጣይም ሲፈሩት ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በየዕለቱና በየሰዓቱ የመገንጠል ጥያቄዎችና የአብሮነት (አንድነት) ጥያቄዎች በየትኛውም የምድር ማዕዘናት ይነሳሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ተገንጣዮች አለመመቸት፣ መሰላቸት፣ ጥላቻ፣ ጭቆና፣ ሰቆቃ፣ አለመግባባት፣ መከራና አፈና የእንገንጠል ጥያቄያቸው ዋና ዋና እርሾዎች መሆናቸውን ሲያስረዱ፣ አስገንጣዮችም በበኩላቸው ተገንጣዮች ቢገነጠሉ የሚደርስባቸውን የከፋ ችግር በማስረዳት፣ አለዚያም ለመወደድ በመፍገምገም የመገንጠል ጥያቄን አብዝተው ሲሸሹ ይስተዋላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ጥያቄው መቆሚያ የለውም፡፡ አስገንጣዮችም ላለማስገንጠል የሚያደርጉት ጥረት ይቀጥላል፡፡ ተገንጣዮችም ለመገንጠል የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡ ለእኔ ግን ትልቁ ጥያቄ ተጎጂው አካል ተገንጣይ ነው? አስገንጣይ ነው? ወይስ ሁለቱም ተጎጂዎች ናቸው የሚለው ነው፡፡

አንተ ወዳጄ! እንግዲህ የጀመርነው ወግ ነውና የማወራህ እንደተመቸኝ ነው፡፡ ታላቁ ገጣሚያችን ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን እነኚህን ስንኞች ሲቋጥር በምንም መልኩ አስቦ ቢሆን ለዚህ ወሬዬ አይገደኝም፡፡ በራሴ መንገድ እፈታቸዋለሁ፣ እንዲሁም ጨማምሬ በራሴ መንገድ አሰነኛቸዋለሁና፡፡ ደጋግመህ ስታነባቸው በአንተ ዕውቀትና አረዳድ ልክ የየራሳቸው ትርጉም የሚሰጡ ስንኞች መሆናቸውን ብቻ እመንልኝ፡፡ ቀድሜ ይህን የነገርኩህ ከጉምጉምታ ላድንህ ፈልጌ ነው፡፡ በየጓዳው ማጉመትመት ባህላችን እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ብትታዘበኝ ምን ያደርግልሃል? እኔ የማወራህ በማውቀው ልክ ነው፡፡ ‹‹ከሰው መንጋ እንገንጠል…..›› አሉ ይገርማል አይደል?፡

 በመዲናችንና በመጽናኛችን ሎግያ ከተማ ተገንጣዮችም አስገንጣዮችም ይኖሩባታል፡፡ አስገንጣዮቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ ተገንጣዮቹ ደግሞ ውሻዎችና ፍየሎች ናቸው፡፡ በእርግጥ እስካሁን የፍየሎች የመገንጠል ጥያቄ በነዋሪዎቹ  ዕውቅና አልተሰጠውም፡፡ ፍየሎችም ቢሆኑ ጨክነው አልተገነጠሉም፡፡ ውሻዎች ግን ከሰው ልጆች ድንጋይና ብትር በመሸሽ  ለዓመታት ተገንጥለው በነፃነት በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ባለቤት ወይም አሳዳሪ የሌላቸው ውሻዎች ኑሮን መግፋት አይቻላቸውም፡፡ በዚህ ግን አሳዳሪም ሆነ ባለቤት ያለው ውሻ አታገኝም፡፡ ‹‹ከሰው መንጋ መገንጠል…›› ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡

ምን ትዝ አለኝ መሰለህ አንተ ወዳጄ! የሎግያን የሜዳ ውሻዎች ሳስብ ከዘመናት በፊት የሜዳ አህያዎችም ተገንጥለው እንደወጡ እንዳስብ አስገድዶኛል፡፡ ታውቃለህ? የሜዳ አህያዎችና የቤት አህያዎች የሚለያዩት በነፃነታቸው ብቻ ነው፡፡ የሜዳ አህያዎች ራሳቸውን ከጅብ፣ ከአንበሳና ከተለያዩ የዱር አራዊቶች በመጠበቅ በራሳቸው ነፃነትና ነፃ ፈቃድ መኖር ሲችሉ፣ አህያዎች ደግሞ ከባለቤታቸው እጅ ከወጡ አንድ ቀንም ዱር ማደር የማይችሉ ፈሪዎችና ልፍስፍስ መሆናቸውን እናስተውላለን፡፡ የሜዳ ፍየልና የቤት ፍየል፣ የቤት ድመትና የዱር ፈንግል አውሬ፣ የቤት ዶሮና የዱር ቆቅ፣ የቤት እንስሳ ከብትና የዱር እንስሳ ሳላ፣ የቤት እንስሳ ግመልና የዱር እንስሳ ቀጭኔ፣ ወዘተ… መዘርዘር እንችላለን፡፡

አንተ ወዳጄ! እነዚህና መሰል እንስሳት መቼ የዱር እንስሳ መቼ የቤት እንስሳ እንደሆኑ ታውቅ ይሆን? የእንስሳት ሪፈረንደም ነበር እንዴ? ወይስ በሐሳብና በዓላማ ተለያይተው ይሆን አብሮነታቸው ያልቀጠለው? ይህ ነገር በእርግጥም ጥናት ይጠይቃል፡፡ ሳስበው ገና አደከመኝ፡፡ አዕምሮ ሊረዳው ይከብዳል፡፡ እኛ እንደ ቀልድ ችላ የምንለው የእንስሳት ዓለም የተዓምራት ጉራንጉር ነው፡፡ የእንስሳት የጋብቻ ታማኝነት፣ ወስላታነት፣ ሌብነት፣ ተንኮል አጃኢብ የሚያሰኝ ክስተት ነው፡፡ የፍጥረታት አፈጣጠርና የአኗኗር መርህ እጅህን አፍህ ላይ ጭነህ ተፈጥሮን አርፈህ እንድታደንቅ ያስገድድሃል፡፡

እናም ውሻዎች ከዓመታት በኋላ የቤት ውሻና የዱር ውሻ ተብለው እንደ ሜዳ አህያዎችና እንደ ሜዳ ፍየሎች በዓለም አቀፍ የዱር እንስሳት መዝገብ ላይ ስማቸውን ማስፈራቸው አይቀርም፡፡ ያኔ የሎግያ ውሻዎች ለዚህ ነፃነት ውሻዎችን ሁሉ እንዳበቋቸው በውሻኛ ቋንቋ ለውሻዎች መናገራቸው አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ሎግያ መጥተህ የውሻዎችን ነፃነት በደንብ ማየት ትችላለህ፡፡ ከሰው መንጋ እንገንጠል፣ በዕፎይታ ጥላ እንጠለል… ብለው መገንጠላቸው አብዝቶ ያስገርመሃል፡፡

በሰውም ዘንድ ሆነ በእንስሳት ዓለም መገንጠል አስፈሪ ይመስላል፡፡ አስገንጣዮችና ተገንጣዮች ለዘመናት አብረው ተሳስበው እንዳልኖሩ በመገንጠል ማግሥት ጠላትነት ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡ ተለያይተው ያልተጣሉ አገሮችም ሆነ ባልና ሚስቶች፣ ሸሪኮችም ሆነ ጓደኛሞች አታገኝም፡፡ መለያያት ባለበት በዚያ ጥል አለ፡፡ ስለዚህ ራስን መቻል እስከ መገንጠል የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ለፍጥረት ሁሉ የማይዋጥ መራራ ሀቅ መሆኑን ትረዳለህ፡፡

ለሎግያ ውሻዎች ከፍተኛ ጠላታቸውም የሰው ልጆች ሲሆኑ፣ ዘመዳቸውም የሰው ልጆች ናቸው፡፡ በመገንጠል ከጥል እስከ ብዙ ኪሳራና መከራ ይከሰታል፡፡ አብዛኛዎቹ እንስሳት በመንጋ የሚሄዱት የልዩነት ጉዳት ስለገባቸው ይመስለኛል፡፡ እንኳን አንድ ዝርያ ሆነው ይቅርና የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችም ሲደጋገፉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ አዕዋፋትን ተመልከት፡፡ በከተማችንም ቢሆን አሊኳዳ የሚባለው አሞራና ውሻ ተስማምተው አብረው ጥንብ በመብላት ኑሯቸውን ሲገፉ ስታይ የማይስማሙም እንደሚስማሙ ትገነዘባለህ፡፡ ይገርማል እኮ በዚህ ዘመን ብዙ ነገር እየተቀየረ ነው፡፡ ውሻና ድመት አብረው መመገብ ጀምረዋል እኮ፡፡ አንድነትን፣ አለመገንጠልንና ኅብረትን የሚሰብኩ ትክክል መሆናቸውን በዚህ ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡ ነገር ግን የአብሮነትም ሆነ የመለያየት ጥያቄ አንፃራዊ በመሆናቸው መቼና እንዴት እንደሚነሱ አይታወቁም፡፡ ምናልባት ‹‹ለአንድ አፍታ እንኳ እንገለል›› በማለትም ሊጀመሩ ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ተገነጠለ›› የሚለውን ተዘነጠፈ፣ ተዘነጠለ፣ ተለያየ፣ ተላቀቀና ብቻውን መተዳደር ጀመረ… በማለት ይተረጉመዋል፡፡ በዚህም መሠረት በየዕለቱ በቆሎዎች ሲዘነጠሉ፣ ቅርንጫፎች ሲገነጠሉ፣ የተፋቀሩ ሲለያዩ፣ አስተዳዳሪና ተዳዳሪ የጎሪጥ ሲተያዩና ባልና ሚስት ለመገነጣጠል ፍርድ ቤት ሲመላለሱ  ይውላሉ፣ ያድራሉ፡፡  ያም ሆነ ይህ መገንጠል አዲስ ነገር የለውም፡፡ የመገንጠል ጉዳትና ጥቅም ግን እንደ ሁኔታዎቹ  ይለያያል፡፡

ሕፃናት ቤተሰቦቻቸውን ሲያጡ እንጂ የሚያለቅሱት አንዲት አገር ስትገነጠል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አይገባቸውማ፡፡ መጫወቻቸው ቢገነጠልባቸው ግን አብዝተው ያነባሉ፡፡ ለአሞራዎችና ለዱር አራዊት የሚኖሩበት ጫካና ዋሻ እስካለ ድረስ የአገሮች መገነጣጠል አያሳስባቸውም፡፡ አሞራዎች የኢትዮጵያና የኤርትራን፣ የሶማሌና የኬንያን፣ የአፍሪካና የአውሮፓን፣ የአንድ አገርና የሌላን አገር ድንበር አያውቁም፡፡ ፓስፖርትም ሆነ የመኖሪያ ፈቃድ አይጠየቁም፡፡ ይህ ከሆነ ለአሞራዎች መገንጠል ሌላ አንድምታ አለው ማለት ነው፡፡ ጓደኞቻችን ከፍቅረኛቸው ጋር ሲለያዩ ስቃዩ ብዙም አይሰማንም፡፡ አንዲት ቅጠል ከቅርንጫፉ ተገንጥላ መሬት ስታርፍ ትሞታለች፡፡ የሰው ልጆች ግን የቅርንጫፍ ተገጥሎ መሞት አያሳስበንም፡፡ እናትን ከልጅ ነጥለን አርደን እንበላለን፡፡ ለእኛ ቀላል ነገር ለሌላው ከባድ ነው፡፡ የምንኖረው በምድር ላይ ነውና መገንጠልም ማስገንጠልም በውድም በግድም ይቀጥላሉ፡፡ ‹‹በዕፎይታ ጥላ እንጠለል…›› በማለት፡፡

በውቧ ከተማችን በሎግያ ፍየሎች የእንገንጠል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸው የሚል ጭምጭምታ አለ፡፡  ከሰው ልጆች ተገንጥለውም ከሜዳ ፍየሎች ጋር ስምምነት መፍጠር ይፈልጋሉ ይባላል፡፡ ያው ከሚታየው ነገር ለመገመት እንደሚቻለው ፍየሎች የውሻዎችን ነፃነት ሰምተው ይሆናል  ብዬ እገምታለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የሜዳ ፍየሎች ነፃ ሲወጡ ያኔ እኛስ የቤት ፍየል መሆን ይሻለናል ብለው ምናልባት ይቀሩ ይሆናሉ፡፡ ምንም እንኳን በድንቃድንቅ ታሪክ መዝገብ ላይ ባይሰፍሩም በሎግያ ከተማ የሚገኙ ፍየሎች ሌሎች አስገራሚ የክፍለ ዘመናችን ተፈጥሯዊ ክስተቶች ይመስሉኛል፡፡ አፈጣጠራቸውና ሥነ ባህሪያቸው አስገራሚ ነው፡፡ ፍየል እንዳትላቸው እንደ ሥጋ በል እንስሳ አጥንት ሳይቀር ይቆረጥማሉ፡፡ ቤት ከፍተው ይመገባሉ፡፡ ፍየል አይደሉም እንዳትል ደግሞ ፍየልነታቸውን አምነው እስካሁን በመታረድ ላይ ናቸው፡፡

ምናልባት አንተ የምታውቀው ፍየሎች ቅጠል ሲመገቡ ይሆናል፡፡ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ፍየሎች ግን ፌስታል፣ አጥንት፣ ካርቶን፣ ወረቀት፣ ጫት… ማንኛውንም ሊበላ የሚችል ነገር ሁሉ ሲበሉ ከቢራ እስከ አረቄ ይጠጣሉ፡፡ ድንገት የቤትህ ካርታ ወይም የትምህርት መረጃህ ከጠፋብህ ፍየል በልቶብሃል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ የቤት ፍየሎች ከሜዳ ውሾች የሚለዩት ታርደው ሲለሚበሉና የመገንጠል ጥያቄያቸውን የሰው ልጆች ስላልተረዷቸው ወይም ስላልተቀበሏቸው ብቻ ነው፡፡

ቢላ ከሚያፏጭብን፣ ከሚገተግተን የሰው ነብር፣

ለማንም ምንም ሳናዋይ፣ ሳንናገር ሳንጋገር፣

እንጨክን እንገንጠል፣ አዋሽ ማዶ እንግባ ከዱር፣ በማለት ፍየሎች የፍየልኛ ፉከራ ላይ ይመስሉኛል፡፡ ፍየሎችን ያማረራቸው ትልቅ ነገር ሰርክ መጨፍጨፋቸው ነው፡፡ ይባስ ብሎ ከተወለደች ሳምንት ያልሞላት የፍየል ግልገል የምትበላው በከተማችን ነው፡፡ የበከል ሥጋ ይባላል፡፡ ፍየሎች ምንም ቢያስቡ፣ የትኛውንም ዕርምጃ ለመውሰድ ቢዘጋጁ የሰው ልጆችም ግን ‹‹ለእኛ አይደል የተፈጠራችሁት?›› ብለው ሐሳባቸውን ከቁብ ያልቆጠሩት ይመስላሉ፡፡

አንተ የምታውቀው በሌላ አገር ከብት፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ… የመሳሰሉትን ለምግብነት ሲውሉ ሲሆን፣ በአካባቢያችን ግን ፍየሎች ብቻ ናቸው በየሆቴሎቹ የሚረፈረፉት፡፡ የበግ ሥጋ ወይም የከብት ሥጋ የሚያርድ ሆቴል አታገኝም፡፡ በፍየሎች ላይ የሰው ልጆች የዘመቱ እስኪመስልህ ድረስ በየዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍየሎች ለምግብነት ይጨፈጨፋሉ፡፡ ስለዚህ በየተራ ከሚታረዱ እንደ ሜዳ ፍየል ለመኖር ልምምድ ላይ ይመስሉኛል፡፡ መቼ ተገንጠልው እንደ ውሻዎች ጫካ እንደሚገቡ ባላውቅም፣ ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ በውድም በግድም መገንጠላቸው እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ ለማንም ምንም ሳናዋይ፣ ሳንናገር ሳንጋገር፣ እንጨክን እንገንጠል አዋሽ ማዶ እንግባ ከዱር… ፡፡

በነገራችን ላይ የበረሃ ፍየል አይታሰርም፡፡ ጉሮኖ አይገባም፡፡ ሌሊት ብትወጣ ብዙ የፍየሎች መንጋ እየተቦጣቦጡ በደረቅ ሌሊት ታገኛቸዋለህ፡፡ ሰውም በረንዳ ያድራል፡፡ ፍየሎችም ውጭ ያድራሉ፡፡ እንዲያውም ሰው ሲተኛ ፍየሎች በጨረቃ ‹‹ወክ›› ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዴ ሮንድ ተረኛ ይመስሉሃል፡፡ በሌላ ጊዜ በአሳቻ ሰዓት አዋሽ ማዶ ለመሰደድ ሰዓት የሚያጠኑ ይመስላሉ፡፡ ወይም ሲገነጠሉ እንዴት መኖር እንዳለባቸውና ከዱር አራዊት ራሳቸውን እንዴት መከላከል እንዳለባቸው እየተለማመዱ ይሆናል፡፡ ምናልባትም የሜዳ ፍየሎች ከእኛ ጋር መኖር ትችላላችሁ የሚል የይሁንታ መልስ እስከሚሰጧቸው እየጠበቁም ሊሆን ይችላል፡፡ ከሰው ልጆች ተገንጥለው ከሜዳ ፍየሎች ጋር ኅብረት ለመፍጠር ማለት ነው፡፡ መገንጠልና አንድነት የማይቀሩ ጥያቄዎች ናቸው ያልኩህ ለዚህ ነው፡፡ ከአንዱ ትገነጠላለህ ከሌላው ጋር ትስማማለህ፡፡ ብዙዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን የሚስማሙት ፍየሎች ሌሊት የማይተኙት የጫት ቀርጥ (ገረባ) ስለሚበሉ ስለሚመረቅኑ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ራሳቸውን እያደራጁና የሰው ልጆችን እያዘናጉ ይሆናል የሚል መላምት ይሰነዝራሉ፡፡ አንድ ቀን በደረቅ ሌሊት ፍየሎች በሙሉ ጥርግ ብለው የሜዳ ፍየሎች መሆናቸው እንደማይቀር ሁኔታዎች ይጠቁማሉ፡፡ የበከል ሥጋ እያሉ ልጆቻችንን ከሚቀረጥፉብን፣ በየማለዳው ከሚዘምቱብን፣ እንገንጠል ከዚህ የባሰ መቼም አይመጣብን፡፡ ብብብእእ… ይላሉ በደረቅ ሌሊት በፍየልኛ፡፡

ፍየሎችም በሌሊት ሲንቀሳቀሱ ትንሽ የሚበረግጉት የሜዳ ውሻዎች ተሰብስበው ሲመጡባቸው ብቻ ነው፡፡ ያን ያህል በውሻ የሚደፈሩም አይደሉም፡፡ ራሳቸውን መከላከል ያውቁበታል፡፡ በብልጠትም ቢሆንም የተካኑ ናቸው፡፡ የተዘጋ ቤት በማንገጫገጭ አላልተው ከፍተው የሚገቡ ናቸው፡፡ ምን እንደሚያደርጉና ምን ማድረግ እንዳለባቸው መለየታቸው ፍየልነታቸውን እንድትጠራጠር ያስገድድሃል፡፡ ብንስማማም  ባንስማማም ከሜዳ ፍየል በምንም አያንሱም፡፡ ማንም ዕውቅና ባይሰጣቸው የራሳቸውን ኑሮ በራሳቸው ሥልጣን የወሰኑ ናቸው፡፡ አብዝቶ የሚያሳዝነው ነገር ግን ድርጊታቸውም ሆነ ትብብራቸው እስካሁን ድረስ ከመታረድ አላዳናቸውም፡፡

እናም ወዳጄ መገንጠልና ማስገንጠል፣ አንድነትና  ልዩነት በሁሉም የዓለም ጥግ የየዕለት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከዱር እንስሳት የቤት እንስሳ ለመሆን የሚጥሩ ሞልተዋል እኮ፡፡ በዘመናት መካከል ያለ አንድ ጥቁር ሀቅ ሁሉም ቀን የየራሱን ጉድ አስከትሎ መገስገሱ ነው፡፡ ዛሬን እንጂ ነገን በድፍረት ለመናገር የሚሆን ዕውቀትም ሆነ መገለጥ በፍጥረታት መካከል አለመኖሩ ለመገንጠልና ለመስማማት ዋናው ምክንያት ይመስለኛል፡፡ አምላክ ራሱ ብቻ ጠቢብ እንዲሆን አስቦ የከወነው ድንግል እውነት ነው፡፡ የሰው ልጅ ነገ የሚሆነውን ቢያውቅ ምን እንደሚፈጠር አስበው፡፡ ማን ከማን ጋር እንደሚለያይና እንደሚስማማ ገምት፡፡ ይኼም ባለመሆኑ የተነሳ ቃል ኪዳን አፍሮ ሲኮሰምንና ባለውለታ ሲከዳ፣ እውነትን ውሸት በዝረራ ሲያሸንፈው ስታይ የፍጥረታት ጥያቄ ማለቂያ እንደለሌለው ያኔ ግልጽ ይሆንልሃል፡፡ እንለያይ፣ እንገንጠልና አብረን መኖር አንችልም፣ ወዘተ…. ይቀጥላሉ፡፡ በተቃራኒው አንድነት፣ ውህደት፣ ፍቅር፣ ቃል ኪዳን፣ ስምምነትና ጋብቻ ወዘተ… ይቀጥላሉ፡፡

ሌላው አስደናቂ ድባብ በከተማዋ በሁሉም ጫፍ እንደ ከባቢ አየር (አቶምስፈር) የከበቧት ውሻዎች ለሎግያ ከተማ ንፅህና ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ ከከተማዋ የሚደፉውን ቆሻሻ በነፃ ድራሹን ያጠፉታል፡፡ በሎግያ ውሻ ያለው ወይም ውሻ የሚያረባ ሰው አታገኝም፡፡ ምናልባት ብታገኝም ውሻ የሚያረባ መስሎት ተሸውዶ ይሆናል፡፡ ትንሽ ካደጉ በኋላ ውሻዎችም በራሳቸው ጊዜ ተገንጥለው ከዘመዶቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ፡፡

እናም ወዳጄ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ቀለል አድርጌ ሳስረዳህ በሎግያ ከተማ እንደ ውሻ የሚያስቡ ውሻዎችን አታገኝም፡፡ ከከተማዋ አቅም በላይ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ውሻ መሳዮች ግን ይኖራሉ፡፡  ግን የውሻ  ባህሪም ሆነ ሥነ ምግባር የላቸውም፡፡ ሌባ ሲመጣ እንዲጮህ፣ እንዲያነቃህ፣ ንብረትህን ከአደጋ እንዲጠብቅልህ፣ ግቢህን እንዲያስከብርልህ የበረሃ ውሻን ፈጽሞ አትመኘውም፡፡ ጅብ እንዳትለው ውሻ ነው፡፡ ውሻ እንዳትለው ዱር ውሎ ዱር የሚያድር ነው፡፡ ለዚህም ነው የሜዳ ውሻ ብዬ ልጠራቸው የተገደድኩት፡፡ ምናልባት የስንፍና ተፅዕኖ እንዳይሆን ብዬ እሠጋለሁ፡፡

በዚህ አካባቢ የሚገኙ ውሻዎች ብቸኛ ጎረቤታቸው አለዚያም በመረዳዳት የሚኖሩት አሊኳዳ ከሚባል ትልቅ አሞራ ጋር ነው፡፡ ይህ አሞራ ለከተማዋ አድባር ነው፡፡ አንተ ወደ ከተማዋ ዳር ከሄድክ ለመብረር ብዙ ሜትሮችን ተንደርድሮ ሲነሳ ስታየው ትንሽ አውሮፕላን ይመስልሃል፡፡ ውሾችም ሆኑ አሊኳዳዎች የሚመገቡት ከከተማው የሚወጡ የምግብ ቤት አጥንትና ቅንጭላት ነው፡፡ በሎግያ ከተማ የሚሸት ነገር አታገኝም፡፡ በንፅህና በኩል የሚከሰት በሽታም የለም፡፡ ትልቁ ችግር የእብድ ውሻ በሽታ የተከሰተ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ቢታሰብበት እላለሁ፡፡ ካልታሰበበት ደግሞ ክስተቱን ላለማየት መጸለይ ነው፡፡

ለውሻዎች መገንጠል ዋና ምክንያት ጥጋብ ይሆናል የሚል የቆሻሻ ደፊዎች  መላምት አለ፡፡ ምክንያቱም  በዚህ አካባቢ የሚኖሩ  የማንኛውንም እንስሳት ጭንቅላት አይመገቡም፡፡ መሀል አገር ቴስታታ ቀለቡ የነበረ ሰው ሎግያ ሲገባ ይረሰዋል፡፡ ተወላጁም ቢሆን ጭንቅላት አይበላም፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ቅንጭላትና የተለያዩ የማይበሉ ክፍሎች የውሻና የአሊኳዳ አሞራ ቀለብ ናቸው፡፡ ምናልባት አንተ የምታውቀው ውሻ ፍርፋሪ ሲጠብቅ ከሆነ እዚህ ግን እስከሚተርፈው ሥጋ የሚበላ ውሻ ነው፡፡ በሰው ልጆች ከመታዘዝ፣ ከመመታት፣ ታማኝ ሆነ ለመጠበቅ ከመታከት፣ ራሳቸውን ችለው መገንጠል አማራጭ እንደሆነ ተረድተውት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡  ከሰው መንጋ ተለይተን፣ ከጠረኑ ተነጥለን፣ ከጉምጉምታው ተገንጥለን…  ጨረቃን መስክሪ ሳንል ሳናውቅባት ሳታውቅብን፣ ማስተዳደር እንችላለን ራሳችንን በራሳችን… የሚለውን ቅኔ በራሳቸው ዓውድ ተርጉመው ተረድተውት ይሆናል፡፡

አንተ ግን ምን አሰብክ? ለመገንጠል ብዙ ጊዜ ሞክረሃል አይደል? ቢያንስ ቢያንስ ከራስህ ጋር የተለያየህባቸውና የተጣላህባቸው ጊዜያት ብዙ ይሆናሉ፡፡ ከጓደኞችህ፤ ከፍቅረኛህ፣ ከቤተሰብህ፣ ከማኅበርህ፣ ከሚወዱህና ከሚፈልጉህ ሰዎች ብዙ ጊዜ ተገንጥለህ ይሆናል፡፡ ምናልባት አሁንም ከሚስትህ ወይም ከፍቅረኛህ ሌላ ውሽማ ለመያዝ እያሰብክ እንዳይሆን፡፡ ቅር እንዳይልህ አዲስ ስምምነት ለመፍጠር እየጣርክ ነው ማለቴ ነው፡፡ ወይም ከመሥሪያ ቤትህ ተገንጥለህ ከሌላ መሥሪያ ቤት ጋር ተዋውለህ ለመሥራት፣ የሚበላ ያለበት የሥራ መደብ በመምረጥ ላይ ትሆናለህ፡፡ ሚስትህ ድብቅነቷ እየደበረህ ነው… ቤተሰቦችህ ጥሪት እንዳትይዝ እያደረጉህ ይሆናል… ኃላፊህ ጥቅም ያለው ሲሆን ሌላ ሰው፣ ልፋትና ድካም ያለውን ሥራ ላንተ እያስታቀፈ አስቸግሮሃል? የንግድ ሸሪክህ ቅሸባ እንደጀመረህ እየተጠራጠርክ ነው? ፍቅረኛህ ሰሞኑን ብር የመውደድ አባዜ ተጠናውቷታል…? በቃ እንደዚህ መሰላቸት ከተሰማህ መለያየት የሚባል ሐሳብ በውስጥህ እያቆጠቆጠ ነው ማለት ነው፡፡ በቃ ተገንጥለህ ራስህን መቻል እያሰብክ ነው፡፡

አለዚያም የሆነ ብር አገጫችታችሁ ንግድ እንድትጀምሩ፣ ፊልም እንድትሠሩ፣ ወይም ወደ ውጭ እንድተኮበልሉ ሰዎች ጋር እየተመካከርክም ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ከሌላ ክልል መጥቶ  በአንተ ክልል አለቃ ሆኖብሃል፡፡ ይህ ቦታ ለኔ ነው የሚገባው ብለህ ብታስብስ? ዞንህ ወይንም ወረዳህ አሪፍ በጀት እንዲኖራት ለምን ተገንጥላ ልዩ ዞን ወይም ወረዳ አናደርጋትም ብለህ እያሰብክም  ይሆናል፡፡ አለዚያም ያላትን ጠብሰው ሀብታም ለመሆን ዕቅድ እየነደፍክ እንዳይሆን? ከእምነትህ፣ ከሃይማኖትህና ከሰብዕናህ ተገንጥለህ አጭበርብረህ ለመክበር እያሰብክም ሊሆን ይችላል፡፡ ማንም አይከለክልህም፣ ግን መገንጠል ገባህ አይደል?

ምንም አስብ ምንም ግን በህሊናህ አስብ፡፡ ለሆድህና ለከርስህ ያሰብክ ቀን ያኔ ተሸንፍሃል፡፡ በመለየትህም በመስማማትህም አንድ ቀን ትፀፀታለህ፡፡ ለሆድህ አስበህ የምታደርገው ሁሉ ትክክል ቢሆንም አንድ ቀን በአዕምሮህ መወቀስህ አይቀርም፡፡ በዚህች ምድር ደግሞ ከአዕምሮ የከፋ ወቃሽ የለም፡፡ በኋላ ከራስህ ጋር ለዘለዓለም ተለያይተህ ሰላምህን ከምታጣ፤ መገንጠልም ሆነ መስማማት ስታስብ አዕምሮህን ተጠቀምበት፡፡ ለሆድህ ብለህ አትገንጠል፣ ለጥቅም ብለህ ሰውን አትፈንግል፣ በክፉ ምኞትህ ምክንያት ታማኝነትህን አትቅበር፡፡ በአጠቃላይ  ሰው ሆነህ እንደ ሰው ለመሞት ትጋ፡፡ ደግሞም የሰው መጠቀሚያ አትሁን፡፡ ባንተ ደም፣ ባንተ ላብና ባንተ…. በሆኑ ብዙ ነገሮች ለሚንተገተጉ ጩልሌዎች ራስህን አታጋልጥ፡፡ ሁሉም ቀናት የየራሳቸው  መልካምነትም ክፋትም አላቸው፡፡ አንተ ግን በቀናት መካከል መልካም ሁን፡፡ የሚለይ ምኞቱን ይከተላል ይላልና አስብበት፡፡

ሳላጫውትህ የማላልፈው ነገር በአካባቢያችን የሚገኙ አሞራዎች ማንም ሰው ያልተረዳላቸው ነገር ቢኖር በዚህ ሰዓት በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ ከተማዋ ስታድግና ስትስፋፋ የቆሻሻ መድፊያ ሜዳዎች (ጋንጋዎች) በሙሉ ቤት እየተሠራባቸው ይገኛል፡፡ እንዚህ የከተማዋ ማዘጋጃ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ አሞራዎች ማረፊያ ስላላገኙ ወደ የመን ይሁን ወደ ሊቢያ እርግጠኛ ባልሆንም እየተሰደዱ መሆናቸውን  እኔን መሰልና ቆሻሻ ደፊዎች ይገባናል፡፡ የአሞራዎቹ ስደት ምክንያት የመኖሪያ ማጣት፣ ቦታቸውን በሰው ልጆች መወረስ መሆኑ በውል ቢገባኝም  የውሾች  ለሰው ልጆች አንገዛም ብለው ማመፃቸው ግን ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ ነፃነታቸውን በራሳቸው ያወጁ ውሾች በዚህ አሉ፡፡ ነፃነት የሁሉም ፍጥረት መሻት በመሆኑ ነፃነታቸውን ወደድኩት፡፡ የፍየሎችን የእንገንጠል ጥያቄ ግን እንጃ የወደድኩት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ጥቅሜ ይነካላ! እኔ ምንም ባስብ ማንም ምንም ቢገምት፣ ቢጠቅማቸውም ቢጎዳቸውም ፍየሎች ግን እንዲህ በማለት ላይ ይመስሉኛል፡፡

ቢለዋ ከሚያፏጭብን፣ ከሚገተግተን የሰው ነብር

ለማንም ምንም ሳናዋይ፣ ሳንናገር ሳንጋገር፣

እንጨክን እንገንጠል፣ አዋሽ ማዶ እንግባ ከዱር

የሜዳ ፍዬል እንሁን፣ እንስማማ  እንተባበር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles