ለአካል ጉዳተኞች ጭምር አገልግሎት የሚሰጡና ለሌሎች እንደማሳያ የሚያገለግሉ ሞዴል መፀዳጃ ቤቶች በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤቶች ውስጥ ተገንብተው በአገልግሎት ላይ ዋሉ፡፡
ከኬንያና ከኡጋንዳ የተገኘውን ተሞክሮ በመጠቀም ሞዴል መፀዳጃ ቤቶቹ የተቋቋሙት፣ በጉለሌ ክፈለ ከተማ በላይ ዘለቀ፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ተስፋ ኮከብ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ህዳሴ፣ በካራቆሬ እውቀት ለፍሬ፣ እና አዲስ ተስፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲሆን፣ ያሠራውም ቼሻየር ፋውንዴሽን ኦክሽን ፎር ኢንክሉዥን አዲስ አበባ ፕሮጀክት ነው፡፡
ወይዘሪት ገነት ስንሻው የፕሮጀክቱ የሃይጂን ባለሙያ እንደገለጹት፣ በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የተሠሩት ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶች፣ ለመዋዕለ ሕፃናት፣ ለመጀመሪያ ደረጃ የወንድና የልጃገረድ ተማሪዎች አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡
እያንዳንዱ መፀዳጃ ቤት በነፍስ ወከፍ ስምንት ክፍሎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ክፍል ለአካል ጉዳተኞች መጠቀሚያ ብቻ እንዲውል ተደርጎ የተሠራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ገላ መታጠቢያ ነው፡፡ ተማሪዎች ተፀዳድተው ከወጡ በኋላ እጃቸውን የሚታጠቡበት ከመፀዳጃ ቤቱ ጋር ተያይዞ የተሠራ የውኃ ቧንቧም አለው፡፡
ፕሮጀክቱ መፀዳጃ ቤቶቹን የሚያሠራው መምህራንን፣ ተማሪዎችንና ወላጆችን ያካተተ ኮሚቴ ካቋቋመና ከየወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች፣ እና ከትምህርት ቤቶች ጋር የሦስትዮሽ ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ መፀዳጃ ቤቶቹ ተገንብተው ከተጠናቁቁ በኋላ ለትምህርት ቤቱ የሚያስረክበው፣ 15 ወንዶችና 15 ሴቶች ያሉበት የወሽ ክለብ ካቋቋመ በኋላ ነው፡፡ ክለቡም ተማሪዎች በመፀዳጃ ቤቱ በጥንቃቄ እንዲጠቀሙና በእንክብካቤ እንዲይዙት ያግዛል፡፡
ፕሮጀክቱም በመጪው ዓመት በሌሎች የመጀመሪያ ደረጀ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
አቶ ዮሴፍ አድማሱ የፕሮጀክቱ የኮንስትራክሽን ሱፐርቫይዘር እንደገለጹት፣ መፀዳጃ ቤቶቹ ለአካል ጉዳተኞች መጠቀሚያ እና የገላ መታጠቢያ እንዲኖራቸው ያስፈለገበት ምክንያት ለአካለ መጠን የደረሱ ልጃገረዶች የወር አበባቸው በመጣ ቁጥር በመታጠቢያ እጦት የተነሳ እየተጉላሉና አካል ጉዳተኞችም በየጊዜው እየተቸገሩ መሆናቸውን በመገንዘብ ነው፡፡
ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት ከተሠራላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሰባት የሚገኘው አዲስ ተስፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡ ወይዘሮ ፀሐይ መንግሥቱ የዚሁ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት፣ የቀድሞው መፀዳጃ ቤት ደረጃውን ያልጠበቀ፣ መጥፎ ሽታ ያለው፣ ወንድና ልጃገረድ ተማሪዎች ተጨናንቀው የሚጠቀሙበት፣ ይህም ሁኔታ በተለይም በልጃገዶቹ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን በዚህም የተነሳ የወር አበባቸውም ሲመጣ ከትምህርታቸው ይስተጓጎሎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኞችን ያገናዘቡ መፀዳጃ ቤቶች አለመኖርን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፕላን ኃላፊ፣ በማንኛውም የትምህርት ተቋማት የሚገነቡ ሕንፃዎችና መፀዳጃ ቤቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው በሕግ የተደነገገ ቢሆንም፣ በትክክል ተግባራዊ ሆኗል ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ አገላለጽ፣ በአሁኑ ጊዜ የእያንዳንዱ ትምህርት ተቋም መፀዳጃ ቤት አካል ጉዳተኞችን ያካተተ መሆኑን የሚከታተልና እንዲስተካከል የሚያደርግ ባለሙያ በቢሮ ደረጃ ተመድቧል፡፡
አቶ ደረሰ ታደሰ የካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሸን የሕዝብ ግንኙት ባለሙያ፣ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሚገኙ መፀዳጃ ቤቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንደሚገባቸው ጉዳዩ ከሚመለከተታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር ውይይት ቢደረግም የተስተካከለ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡