Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ግማሽ ሙሉ ግማሽ ጎዶሎ?

ሰላም! ሰላም! ‹‹እስኪ እንጨዋወት ጨዋታ ምን ከፋ፣ የሆድን በሆድ እያልን ግዜ ከምንገፋ፤›› ያለው ዘፋኝ ይናፍቀኛል። ዘፋኙ ይሆን ጀምሮ የተወው የጨዋታ ርዕስ? በእውነቱ ማንኛቸው እንደሚወሰውሱኝ እርግጠኛ አይደለሁም። ለመሆኑ እርግጠኛ ሆነን እናውቃለን? ብንሆንስ በምን? እንዳትሉኝና የጨዋታው ርዕስ መፍታታት እንዳይጀምር። እንዲያ ነው እንጂ! ነገር ካነሳን አይቀር ታዲያ ቀብረን እንለፍ። አይመስላችሁም? የቆመን እንጂ የሞተን መቅበር እርግፍ አድርገን በተውንበት፣ ጨዋነታችንና ወጋችን አጥንቱ ሰጎ በወጣበት በዚህ ዘመን፣ ለወደቀ ሞራል ምስክር ከመሆን ያድነን ነው የሚባል። ሌላ ምን ይባላል? እናም ወደታኮሰኝ ነገር ስታጠፍ፣ እርግጠኛ መሆን የቻልንባቸውን ወይም መሆን የምንችልባቸውን ነገሮች ቆጠራ መጀመሬ ነበር። አይዟችሁ ምንም እንኳ ድምፅ የመስጠት ዘመን ቢሆን እዚህ ላይ ‹ፒክኒክ› መውጣት ይቻላል። በዚያው እንዳትቀሩ እንጂ። አላምናችሁም እኮ እናንተን!

በዚህች በአፈራችን ሲለን በምናፍርባት ሲለን በምንኮራባት፣ ‹ሁለት ሞት ሙቱ› ሲለን ደግሞ ‹አያሳየን› ብለን በምንርቃት ምስኪኗ አገራችን እርግጠኛ መሆን ብሎ ነገር መዝገበ ቃላታችን እንዳይጓደል ያለ ቃል እንጂ፣ በበኩሌ የሚቀሰር ምሳሌ ያለው አይመስለኝም። የታየው እንግዲህ ማሳየት ነው። በልዩነት ማመን ከእኔና ከእናንተ ካልጀመረ ከላይ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አላዋጣም። ለነገሩ በዚህም እርግጠኛ አይደለንም። አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳይቀር፣ በነፈሰው ነፍሶ በነደደበት ስለሚያነደን ኑሯችን ስንጫወት፣ ‹‹እኔ አንዳንዴ ሳስበው እንኳን ስለርምጃችን፣ በልተን ስለማደራችን፣ ስለኢኮኖሚ ዕድገታችን ቀርቶ ስለድህነታችንም እርግጠኞች ነን ብዬ አላስብም። ዓይናችን ስለማየቱ፣ ጆሯችን ስለመስማቱ፣ በማሰባችን ከእንስሳት የምንለይ የዓላማ ፍጡራን መሆናችንን ማመን ብሎ ነገርማ እርሳው፤›› አለኝ። ከሁሉ ደሃ ስለመሆናችንም እርግጠኞች አይደለንም አባባሉ አስደንግጦኝ ትንሽ ቆይቶ (የምሁር ነገር ምን ይታወቃል) ‹ድህነታችን በጥናት ይረጋገጥ› እንዳይለኝ ፈርቼ ዞር አልኩ። ዞር ስል ለስንት አሥርት ዓመታት በኖርኩበት ሠፈር ያለን ፎቶ ቤት አንዱ ቢጠይቀኝ፣ ‹‹ወደ ቀኝ ታጥፈህ መሰለኝ›› ብዬ መመለስ። በዚህ ዓይነት አልኩ ወዲያው፣ በዚህ ዓይነት ‹የረገጥከው አፈር የማን ነው?› ቢለኝ ‹የእኛ መሰለኝ› ልለው ይሆን? ሆሆ!

እንዲህ የኖርኩትን ሁሉ በዜሮ የሚያጣፋ ግራ መጋባት ሲጠናወተኝ ታዲያ መድኃኒቴን አውቀዋለሁ። እሱም በሥራ መወጠር ነው። መድኃኒት በመግዛትና መድኃኒት በማሠራት ያዳከምነው ወኔ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን . . . አቤት ዛሬ እኛን ነበር ማየት። ለነገሩ አድርገነው ቢሆን ዛሬ የያዝነውን ይዘን እንዳለነው፣ ቢሆን የምንለው ዕድሜ ይመርበት ይክፋት እርግጠኛ መሆን አንችልም። ነገርኳችሁ እኮ። መራገጥ እንጂ ማረጋገጥ የእኛ አይደለም ስላችሁ? እኔን ካላመናችሁ ባሻዬ አንድ የሚሉት አባባል አለ። ‹‹ላለፈው ዕድሜ ከመቆጨት ለሚመጣው አስብ›› ይላሉ። ይህቺ የባሻዬ አባባል ‹ከዚህ በፊት የሰማናት ስለመሰለን የራሳቸው ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አንችልም› ካላችሁ ደግሞ እንደፈቀዳችሁ። የመጠርጠር መብታችሁ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በጎዳናው ተምኔት የተፈቀደ ነው። ግን አደራ ባሻዬን በኩረጃ ስማቸውን ስታጠፉ እንዳልሰማና እንዳንጣላ። የምሬን ነው! ፍራሽ ማደስ በእሳቸው አልተጀመረም። ስንቱ ብርሁነቱን ንቆ፣ ትኩስ ኃይሉን በመምሰልና በማስመስል አምክኖ በሰው ወርቅ እየደመቀ እያየን፣ አንድ የአገር አንጡራ ሀብት አረጋዊ ያለችውን ቢያሽሞነሙንና ቢጥፍ ነውር አይመስለኝም። አያችሁ ሰው መጠየቅ ያለበት ባለው አቅም ዕውቀት ልክ መሆን አለበት። አልተሳሳትኩም መቼም። ‹‹ጥሬ እፈጭ ነው ብለሽ ዱቄት አታፍሺ›› ሲባል የሰማሁበት ግዜ ለምን እንደሆነ እንጃ እሩቅ ይመስለኛል። እናንተ ሰዓቱ ነው ትውስታችን ነው እየፈጠነ ያስቸገረን ግን? በ40 ሳንጨማደድ እንደባለ 80 ምርኩዝ ምርኩዝ ማለት አበዛንና!

አዲስ አበባችን ይዝነብ አይዝነብ እርግጠኛ መሆን ባቃታት ሰዓት አንድ ያሻሻጥኩትን ቤት ‹ኮሚሽን› ልቀበል ጉዞ ጀመርኩ። ያሻሸጥኩት ቤት ስደርስ መጠነኛ ስለላ ለማድረግ ዕርምጃዬን ገታሁ። ስለላ የምትለዋ ቃል በአንጎሌ መስቀለኛ መንገድ መብራት ጥሳ ስታቋርጥ ዓይኔን ወደ ሰማይ አቀናሁ። ወተቱን መግምጎ ሲያበቃ ቁንጣን ይዞት እንደሚያጎላጅ ሕፃን የተደበረ ወፍራም ደመና ብቻ ይታየኛል። ግን ተጠራጠርኩ። ይህቺን ለዕለት እንጀራ ለቀማ የምትረዳኝን የድለላ አሰሳ ትታችሁ ወጪ ወራጁን ዝንብ ትንኙን በሰው አልባ አውሮፕላኖቻቸው ሲያጠኑ የሚውሉ እንዳሉ ስታስቡ፣ እናንተም እንደኔው ማንጋጠጣችሁ አይቀርም። አንዴ ለባሻዬ ልጅ ስለነዚህ ምዕራባውያን በእጅጉ ለስለላ ተግባር ስለሚጠቀሙባቸው አጅግ ዘመናዊ፣ እንደገለባ የቀለሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አንስቼበት ብዙ ካስረዳኝና ካስተማረኝ በኋላ፣ ‹‹አይዞህ ከእኛ ጉዳይ የላቸውም። ለእኛ የሚታያቸው ያው ድህነታችንና አልሞት ባይ ተጋዳይነታችን ነው፤›› ብሎ ሊያፅናናኝ ሞክሯል። ዳሩ ከአክሱምና ከላሊበላ ወዲህ በቀላሉ መፅናናት፣ ማነፅና መታነፅ አልሆን ስላለን ነው መሰለኝ አልተፅናናሁም፡፡ በአይዞሁም አልፀናሁም። ለወትሮው የዕለት እንጀራዬን ወደሚሰጠኝ አምላክ ‹ደህና ዋልክ?› ብዬ የማንጋጥጥ ሰውዬ፣ ‹ድሮን› አሰሳ ላይ ስተከል በራሴ አዘንኩ። ብለው ብለው በሰማይ መጡብን አትሉም? ‹የምድሩንስ ነገር እኛ ችለነዋል፣ ከፍ በል ጌታዬ ወዳንተ መጥተዋል› ያለችው ሴት ማን ነበረች? ወይ ነዶ ዘመኑ ራቀ እኮ እናንተ!

ወዲያው በቆምኩበት አንድ ደቃቃ ውስጥ የሊስትሮ ዕቃ የያዘ ልጅ መጣና ‹‹ይጠረግ?›› አለኝ። ‹‹ምኑን?›› አልኩት። ‹‹ጫማውን›› አለኝ። ‹‹ዛሬ ይለፈው። ካፈር መጥቼ አፈር ልሆን ሁሌ እሱን ሳሳምር። ተወው አንዳንድ ቀን ጫማችንም ወደ አፈር ይመለስ፤›› ብዬ ግራ ሳጋባው፣ ‹‹ገብጋባ›› ሲለኝ ሰማሁት። ልጅ ሆኘ እንዳላደግኩ ልጅነትን ሊያስረግመኝ እየተፈታተነኝ ‹‹ምን አልክ?›› ብለው ‹‹ጫማ አላስጠርግም የምትል መኪና አትዩብኝ ልትል ነው?›› ብሎ ቀረቀረልኝ። በምንንቀው ባሰን እኮ ተግሳፁና ስድቡ። ጉድ። የሊስትሮው ዕቃ ግማሽ አካሉን ከሚያጥፈው ጩጬ ጋር ስሯሯጥ ታይቼ ደግሞ ሌላ ስም ከማወጣ ብዬ፣ ‹‹ና እሺ ጥረግ›› ብዬ ጫማዬን አስጠረግኩ። ከለማኝ እርግማንና ከላብ አደር ሽሙጥ ይሰውራችሁ እንጂ ሌላ ምን ይባላል? ምርቃትማ ከሰው አፍ ከጠፋ ዝንት ዘመኑ?

ጫማዬን እያስጠረግኩ አንድ ‹አይሱዙ› ከተፍ አለ። ደንበኞቼ ዕቃቸውን ጭነው ቤቱን ሊገቡበት መምጣታቸው ነበር። ከመቅፅበት ሠፈሩ በጠብደል ጎረምሶች ተወረረ። ሌሎች የማላውቃቸው ሰዎችም ካደፈጡበት ብቅ በቅ አሉ። ደላሎች ኖረዋል። ደንበኛዬ ግራ ተጋብቶ ከአውቶሞቢሉ ወረደ። አንዴ ወደ ጎረምሶቹ አንዴ ወደተሰባሰቡት የሠፈሩ ደላሎች እያየ ጤና የማይታይበትን አቀባበል ሲያጠና፣ ‹‹ይኼ ዕቃ የሚወርደው የድለላችን ከተከፈለን በኋላ ነው፤›› አለ አንዱ ከደላሎች መሀል። ከጎረምሶች አንዱ ደግሞ፣ ‹‹በቤተሰብ ተደራጅቼ አወርዳለሁ ማለት ልማታዊ ካለመሆኑም በላይ ማግለልና መድልኦ ያለበት አስተሳሰብ በመሆኑ በቀላሉ አንላቀቅም፤›› ብለው ተገተሩ። የጎረምሶቹ አልገረምኝም። ምንም እንኳ የልብ ማበጥን ዛሬ ዕድሜ ሳትለይ መገኘት በማይገባት ቦታ እየተገኘች ብታስቸግረንም ያስተንፍስልን ብሎ ማለፍ ነው። ደላሎቹ ግን ቤቱ እንደሚሸጥ ያውቁ ስለነበር ብቻ ‹በሠፈራችን እንዴት የሩቅ  ደላላ ቤት ያሸጣል?› ማለታቸው ክልላዊነት፣ ጠባብነትና ዘረኝነት ምን ያህል ወሰን እየተሻጋረ እንደሆነ አስታውሶኝ ከልቤ አዘንኩ። በቃ ሠፈሩ አልኳችሁ . . . ድብልቅልቁ ወጣ። ኋላ ለውዷ ማንጠግቦሽ ስለውሎዬ በአጭሩ የተጠናቀረ ዘገባ አቅርቤ ይኼን ነግሬያት፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው። ውሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር በፈሳሹ ድንበር የሚከልል። ለካ ሰው መፀዳጃ ቤት ሄዶ ፊኛውን የማስተንፈስ ‹ፎብያ› ያለበት፣ ቅጥርና ድንበር የማስከበር ጥኑ ሥውር ፍላጎት ስላለው ጭምር ነው፤›› ብላ እንባ እስኪረግፈኝ አሳቀችኝ። እንግዲህ ይኼን ሰምተው ብረት የራቃቸው አገሩን በፊኛቸው ጎርፍ እንዳያጥቡት ብዬ ለማንም ሳልናገር ቀረሁ። አደራ እናንተም!

በሉ እንሰነባበት። ከስንት ግብግብ በኋላ ‹ኮሚሽኔን› ተቀብዬ እዚያ ሠፈር እንዳልደርስ ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝ ስመለስ ሆድ ስለባሰኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ደወልኩ። የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተገናኝተን አንድ አንድ ስንል አመሸን። ብርዱ በአጥንት ይገባል። ብንጠጣ ብንበላ አልሞቀን ብሏል። ‹‹የዘንድሮ ክረምት ደግሞ በንፋስ ሊያጥበን ነው መሰል ሐሳቡ›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ይኼን ሲል አንዱ ከሩቅ ሰምቶት ‹‹ንፋስ ምን አለን? ከሕግ በላይ የሚወበራው፣ አላስቆም አላስቀምጥ ያለን አልጠግብ ባይ ጉቦኛ የሚያጥበን አይብስም?›› አለው። ‹‹ነገር መጣልህ›› አልኩና የካፖርቴን ኮሌታ ወደ ላይ ቀስቼ ጠንቀቅ ብዬ ተቀመጥኩ። ተጠንቅቀንም መዳናችንን እርግጠኛ አይደለንም እንዳትሉ ብቻ። ወይ እናንተ!

‹‹እና ምን ይሻላል?›› አለው አንዱ ተናግሮ አናጋሪ ወዲያ የተቀመጠ። ‹‹ማጥራት ነዋ። ማፅዳት ነው መፍትሔው። ሳይታክቱ መጥረግ፤›› አለው። እኔ ብርዱን አልቻልኩም። የባሻዬን ልጅ ተሰናብቼ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ስደርስ ቤቱ ተተራምሷል። ‹‹ምንድነው እሱ?›› ብዬ ማንጠግቦሽን ብጠይቅ ‹‹ቤት እያፀዳሁ›› አለችኝ። ወገቧ እስኪቆረጥ ጎንበስ ቀና ትላለች። ‹‹በዚህ በሌሊት እንደ ዕብድ? ደግሞስ ከላይ ከላይ አፅድተሽ ሲነጋ በደንብ አታፀጂም?›› ብላት ‹‹ ‹ሱፐርፊሺያል› ፅዳትና ሥራ ነው፡፡ አንድ ወደፊት አስኪዶ ሦስት ወደኋላ እየሳበ ያስቸገረን፤›› ብላኝ እርፍ። ብርዱ ላይ የማንጠግቦሽ እንግሊዝኛ አጠቃቀም ሲጨመርበት አዞረኝ። ዘልዬ አልጋዬ ላይ ወጣሁ። ለማለት የፈለገችው ግን ገብቶኛል። የታይታ ሥራ፣ ከአንገት በላይ ፅዳት፣ ዛሬ ከትላንት እንደማይሻል ሁሉ አንገት እያስደፋን እባቡን፣ ጊንጡን፣ አይጡን፣ ምስጡን አደላድሎ አስተኝቶብናል። እኮ እስከ መቼ በታይታ ሥራ፣ በአገም ጠቀም አካሄድ እንታሻለን? እስከ መቼስ ከላይ ከላይ? ኧረ ለመሆኑ ጠርሙሱ ሙሉ ነው ጎዶሎ እያልን የምንነታረከውስ እስከ መቼ ይሆን? በግማሽና በሙሉ ክርክር የባከነው ጊዜ ሲታሰብ በራሱ ያማል፡፡ ለጊዜው ሁሉን ረስቼ እኔ ተኝቻለሁ። መልካም ሰንበት!        

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት