ከአሥራ ሦስት ዓመት በፊት በአንድ የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ የሆነ ነው፡፡ የፋብሪካው ሠራተኞች በቀን አልያም በማታ ፈረቃ ይሠራሉ፡፡ ከፋብሪካው ማሽኖች በአንዱ ሦስት ሠራተኞች እየተቀያየሩ በፈረቃ ይሠራሉ፡፡ ተረኛው ማሽኑን ሲዘውር የተቀሩት ይጨዋወታሉ፡፡ አንዳንዴም ያሸልባሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለዓመታት ከቆዩ በኋላ አንዱ ባልደረባ ‹‹ማሽን ላይ ስንሠራ የባጥ የቆጡን ከማውራት ለምን መጻሕፍት እያነበብን አንወያይም?›› የሚል ሐሳብ ይሰነዝራል፡፡ ይስማሙና እያንዳንዳቸው በወር 30 ብር እያዋጡ መጻሕፍት መግዛት ይጀምራሉ፡፡ በተዋጣው ገንዘብ መጻሕፍት ተገዝቶ ዕጣ ለደረሰው ሠራተኛ ይሰጣል፡፡ እስከ ቀጣዩ ወር ድረስ መጻሕፍቱን እየተዋዋሱ ያነባሉ፡፡ ሥራ ላይ ሲሆኑ ስላነበቧቸው መጻሕፍት ይወያዩ ጀመር፡፡
በሦስት ተጀምሮ ከፋብሪካው ሠራተኞች ስምንቱን ያካተተ የመጻሕፍት ዕቁብ ሆነ፡፡ አብዛኞቹ ሠራተኞች ድርጅቱን ለቀው እስኪወጡ ድረስ ዕቁቡ ቀጥሏል፡፡ ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን የሰጠን ዕቁቡን ከመሠረቱት አንዱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በንባብ ላይ ያተኮረ የሬድዮ መርሀ ግብር አዘጋጅ ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን አኗኗር ማኅበረሰባዊ ትስስር ከሚገለጹባቸው መንገዶች ዕድርና ዕቁብን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሥራ ባልደረቦች፣ የአንድ ቀዬ ነዋሪዎች ወይም ጓደኛሞች መካከል በተሰወነ ጊዜ ልዩነት ገንዘብ እየተዋጣ ለባለዕድል የሚሰጥበት የመጻሕፍት ዕቁብ በመጠኑ መልኩን የቀየረ ይመስላል፡፡ በመጻሕፍት ዕቁብ ባለዕድል የሚያገኘው ጠቅም ያለ ገንዘብ ሳይሆን መጽሐፍ ነው፡፡ በመጻሕፍት ዕቁብ፣ መጻሕፍት ከመግዛት ባሻገር ስለ መጻሕፍቱ መወያያ መድረክ መፍጠር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣ ነገር ነው፡፡ የዕቁቦቹ አባላት ከሚያዘወትሯቸው የመጻሕፍት መደብሮች ከ20 እስከ 25 በመቶ ቅናሽም ይደረግላቸዋል፡፡
በመግቢያው የጠቀስነው ጋዜጠኛ ከፋብሪካው ከወጣ በኋላ ዕቁቡን መቀጠል ባይችልም በሕይወቱ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ወቅቶች አንዱ መሆኑን ይናገራል፡፡ ዛሬ ላለበት ሙያ መሠረቱም በወቅቱ የነበረው የመጻሕፍት ዕቁብ ተሞክሮ እንደሆነ ያምናል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የዕቁቡ አባላት የተለየ መቀራረብ ነበራቸው፡፡ ‹‹የፋብሪካ ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ የመጻሕፍት ዕቁብ ስንጀምር ግን እርስ በርስ የምንለዋወጣቸው ሐሳቦች ለበርካታ የሕይወት ፈተናዎች መፍትሔ አመላክተውናል፤›› ይላል፡፡
በየወሩ ለዕቁቡ የሚጣለው ገንዘብ አነስተኛ ሊባል ቢችልም ቀላል እንዳልነበረ ይናገራል፡፡ በወቅቱ ተሰባስበው ስለመጻሕፍት መወያየታቸውን አለቆቻቸው አልወደዱትም ነበር፡፡ ‹‹አምፀዋል›› የሚል ደብዳቤ እንደተጻፈባቸው ያስታውሳል፡፡ በተደጋጋሚም ደመወዛቸው ተቆርጦባቸዋል፡፡ ከሥራው ጋር በተያያዘ የመጻሕፍት ዕቁብ ያላቸው ሰዎች አጋጥመውታል፡፡ ይህም ለንባብ በመጠኑም ቢሆን ትኩረት እየተቸረው እንደመጣ ያሳያል ብሎ ያምናል፡፡ ከተሞክሮው በመነሳት አሠሪዎች ዕቁቦችን ቢደግፉ መልካም ነው ይላል፡፡ ሠራተኞቻቸውን አሰባስበው ዕቁብ የሚያስጥሉ አንዳንዴም መጠነኛ የገንዘብ ድጎማ የሚያደርጉ መሥሪያ ቤቶችን እንደምሳሌ ይጠቅሳል፡፡
ኤልያስ ደግነት በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአራተኛ ዓመት የውጪ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ የማታ ክፍለ ጊዜ ተማሪ ነው፡፡ በብራና ማተሚያ ቤት የግራፊክስ ዲዛይንና ለቀማ፣ ኤዲቲንግና ፐብሊሺንግ ባለሙያ ነው፡፡ እሱና አሥር የክፍል ጓደኞቹ የመጻሕፍት ዕቁብ ከመሠረቱ አንድ ዓመት ሆኗል፡፡ ሲጀምሩ በወር 50 ብር ያዋጡ ነበር፡፡ በቂ ስላልነበረ 100 ብር አደረጉት፡፡ አባላቱ መጻሕፍት ለማግኘት ወራት ከሚጠብቁ በሚል አሁን በየ15 ቀኑ 150 ብር ያዋጣሉ፡፡ ‹‹ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር ገንዘቡ ብዙ ነው፤ ቢሆንም ለመጻሕፍት የሚወጣ ስለሆነ ግድ የለም፤›› ይላል፡፡
ኤልያስ እንደሚለው፣ አብዛኛው ሰው አዘውትሮ መጻሕፍት የመግዛት ልማድ የለውም፡፡ ዕቁብ ከጀመሩ በኋላ ግን የአባላቱ ልማድ እንደተለወጠ ያምናል፡፡ ዕጣ ለደረሰው ሰው የሚፈልገው መጻሕፍት ይገዛለታል፡፡ አባላቱ መጻሕፍቱን እየተቀባበሉ ያነቡና በመጨረሻ ለባለዕጣው ይሰጣል፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሊለያዩ ስለሚችሉ በየመጻሕፍቱ ጀርባ ስማቸውንና ፊርማቸውን እንደማስታወሻ ያሰፍራሉ፡፡
በተለያየ ምክንያት ገንዘብ ማውጣት አይቀርም የሚለው ኤልያስ፣ ከወጪ መካከል መጻሕፍትን ማካተት ላልለመደ ሰው ዕቁቡ ሁነኛ መንገድ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት ውድ በመሆናቸው ለመግዛት የሚያቅማሙ ግለሰቦች በዕቁብ ሲሆን፣ ቀለል እንደሚልላቸው ይናገራል፡፡ ‹‹አንድ ሰው መጽሐፍ ሲገዛ ደራሲውንም እያበረታታ ነው፤ በርካታ መጻሕፍት ሲኖሩት ደግሞ ከራሱ አልፎ ቤቱ ለሚመጡ ሰዎችም መጽሐፍ ጋባዥ ይሆናል፤›› ይላል፡፡
አለባቸው ግርማ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሺፍት ሱፐርቫይዘር ነው፡፡ የሚኖረው ቃሊቲ አካባቢ ሲሆን፣ የመጻሕፍት ዕቁብ የገባው እዛው ሰፈር ከሚኖሩ አሥር ጓደኞቹ ጋር ነው፡፡ ዕቁባቸው ከ20 እስከ 26 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተማሪ፣ ሾፌር፣ ነጋዴና በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ አባላትን ያካተተ ነው፡፡ በወር 50 ብር ያዋጣሉ፡፡ ባለዕጣ መጻሕፍቱን ከገዛ በኋላ የሚተርፈውን ገንዘብ ይወስዳል፡፡ እየተዋዋሱ ስለሚያነቡ አንድ አባል የገዛውን መጽሐፍ ሌላው በድጋሚ አይገዛም፡፡
አለባቸው እንደሚናገረው፣ አብዛኞቹ አባላት በተለያየ አጋጣሚ ሰፈር ውስጥ ቢገናኙም፣ የመጻሕፍት ዕቁብ በተለየ መልኩ ያቀራረባቸዋል፡፡ ለየት ያለ ይዘት ያለው መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ሁሉም በአንድ ላይ ባይገናኙም ሁለትና ሦስት እየሆኑ ሰፈር ውስጥ ይነጋገሩበታል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ መጽሐፍ በየጊዜው ላይገዛ ይችላል፤ እቁብ ሲሆን ግን ግዴታም ነው፤›› ይላል፡፡ አባላቱ መጻሕፍትን በማዋስ ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች የሰፈር ወዳጆቻቸው እንደተረፉም ያክላል፡፡ ‹‹መጻሕፍት ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩ ቅርሶች ናቸው፤›› የሚለው አለባቸው፣ ተመሳሳይ ዝንባሌ ያላቸው ግለሰቦች የመጻሕፍት ዕቁብ ቢገቡ መልካም እንደሆነ ያመለክታል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ እንዳለ እፋጢፋኖስ በክሩዝ ስኩል የእንግሊዝኛ መምህር ነው፡፡ ከትምህርት ቤቱ መምህራን ጋር የመጻሕፍት ዕቁብ ከጀመሩ አራት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ በየሳምንቱ ዓርብ ስለመጻሕፍት የሚያወያዩበት የ‹‹ቡና ጠጡ›› ዝግጅት አላቸው፡፡ በዕቁቡ እስካሁን ወደ 40 መጻሕፍት እንዳገኘ ይናገራል፡፡
መምህራኑ በተለይ ክረምት መግቢያ ላይ ለተማሪዎቻቸው የመጻሕፍት ጥቆማ ይሰጣሉ፡፡ አባላቱ በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች እንደሚገኙም ይናገራል፡፡ ‹‹መጽሐፍ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው፤›› የሚለው መምህሩ፣ ተሞክሯቸውን በሌሎች የክሩዝ ትምህርት ቤት ቅርንጫፎች ለማስፋፋት እንደሚፈልጉ ይናገራል፡፡ በመጻሕፍት ላይ በሚያደርጉት ውይይት የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ይናገራል፡፡
ሳምሶን ሰለሞን የሕግ ባለሙያ ሲሆን፣ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ይሠራል፡፡ አሁን በሚሠራበት ቢሮ ካቋቋመው ዕቁብ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በሠራባቸው መሥሪያ ቤቶችም በርካታ ዕቁቦች መሥርቷል፡፡ ዕቁብ የጀመረው ከሁለት አሠርታት በፊት ጥበቃ ሆኖ በሚሠራበት ወቅት ነው፡፡ ያኔ የ200 ብር ደመወዝተኛ ቢሆንም በየጊዜው መጻሕፍት ይገዛ ነበር፡፡ ብዙ ጓደኞቹ መጽሐፍ እንዲያውሳቸው ይጠይቁት ነበር፡፡ እሱ ግን እያንዳንዱ ሰው መጽሐፍ መግዛት እንዳለበት ስለሚያምን አያውስም፡፡ ‹‹መጻሕፍት የማንበብ ፍላጎት ካላችሁ ገዝታችሁ አንብቡ፤›› ይል ነበር፡፡ ወጥ በሆነ መንገድ መጻሕፍት እንዲገዙ በሚል በወር 20 ብር እንዲያዋጡም ይጠይቃቸው ነበር፡፡
በዚህ መልኩ የጀመረው ዕቁብ አሁን በወር 50 ብር እየተዋጣ ቀጥሏል፡፡ ተራ ደርሶት መጻሕፍት የሚገዛ ሰው ከዕቁቡ የሚተርፈው ገንዘብ አይመለስለትም፡፡ ቀሪው ለነዳያን ይሰጣል፡፡ አባላት ማንበብ የሚፈልጉትን መጽሐፍ የመግዛት መብት ቢኖራቸውም ዕቁቡ የሚከለክላቸው መጻሕፍት እንዳሉ ይናገራል፡፡ እንደ ሳምሶን ገለጻ፣ በዕቁቡ በሚዋጣው ገንዘብ የሚገዙ መጻሕፍት አባላት ትምህርት እንደሚያገኙባቸው የታመነባቸው መሆን አለባቸው፡፡ በዕቁቡ አባላት መካከል መጽሐፍ መዋዋስም አይፈቀድም፡፡ እያንዳንዱ ሰው የመጽሐፍ ባለቤት እንዲሆን የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ይናገራል፡፡
በያዝነው ወር ዕቁብ የሚደርሰው ለሳምሶን ነው፡፡ የመጻሕፍት መደብሮች የሚያደርጉት ቅናሽ በርካታ መጻሕፍት እንዲገዙ አስችሏቸዋል፡፡ በግሉ የሚገዛቸውና ከዕቁቡ የሚያገኛቸው ተደማምረው የመጻሕፍት ስብስቡ ከ1,400 በላይ መሆኑን ይናገራል፡፡ የመጻሕፍት ዕቁብ ሁሌም ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲሰላቹ ወይም የመክፈል ፍላጎት ሳይኖራቸው ሲቀር ኃላፊነት ወስዶ የሚከታተል ሰው ያስፈልጋል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ መሰል ዕቁቦች አንባቢ ትውልድ የመፍጠር ሚና ስላለቸው መበራከት አለባቸው፡፡ ‹‹አንባቢ ትውልድ ለራሱ፣ ለሕዝብና ለአገርም ይጠቅማል፤›› ሲል ይናገራል፡፡
ለመጻሕፍት ዕቁቦች የዋጋ ቅናሽ ከሚያደርጉ መደብሮች አንዱ ጃፋር የመጻሕፍት መደብር ነው፡፡ የመደብሩ ባለቤት ጃፋር ሽፋ እንደሚናገረው፣ በይበልጥ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የመጻሕፍት ዕቁቦች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ አብዛኞቹ ባለዕቁቦች የመንግሥት ሠራተኞች ሲሆኑ፣ የባንክ ቤት ሠራተኞችና በግል የሚሠሩም ይገኙበታል፡፡ በሕክምና፣ ምሕንድስናና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ያሉ ግለሰቦች የተሰባሰቡባቸው ዕቁቦች ጥቂት እንደሆኑ ይገልጻል፡፡
ለመጻሕፍት የዋጋ ቅናሽ ሲደረግ በርካታ ደንበኞች በመሳብ የተሻለ ትርፋማ መሆን እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ በወር እስከ 4,000 ብር አውጥተው መጻሕፍት የሚገዙ የዕቁብ ደንበኞች አሉት፡፡ የታሪክ መጻሕፍት፣ ልብወለድና የግጥም መድብሎች በብዛት ይሸጣሉ፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ከሚያገኘው ገቢ ባሻገር መጻሕፍት ለመግዛት ተሰባስበው ወደ መደብሩ በየወሩ የሚሄዱ ሰዎች ማየት ያስደስተዋል፡፡
መሰል ስብስቦች እንዳይቋረጡ መበረታታት እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ አንባቢ ተበራክቷል ብሎ ለመናገር ባያስደፍርም ከጊዜ ወደጊዜ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ያምናል፡፡ ብዙዎች መጻሕፍት ሸመታን የሚያስቡት ገንዘብ ሲተርፋቸው እንደሆነ በመጥቀስ፣ የመጻሕፍት ዕቁቦች የተሻለ አማራጭ ይዘው እንደመጡ ይናገራል፡፡
አስተያየቱን የሰጠን ደራሲ ይታገሱ ጌትነት እንደሚናገረው፣ የመጻሕፍት ዕቁቦች ደራስያንን፣ አንባቢዎችንና ነጋዴዎችንም ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡ የመጻሕፍት ዕቁብ የሚገቡ አንባቢዎች መጻሕፍት በመግዛት የተሻለ ልማድ ያላቸው በመሆናቸው ደራስያን ይጠቀማሉ፡፡ ሻጮችም በአንድ ጊዜ በርካታ መጻሕፍት የሚገዙ ደንበኞችና ቀጣይነት ያለው ገቢ ያገኛሉ፡፡ አንባቢዎች በቡድን ሲሆኑ መጻሕፍት የመግዛት ተነሳሽነታቸው ይጨምራል፡፡ የመጻሕፍት ወጪ ሳይከብዳቸው እንዲገዙም ያበረታታቸዋል፡፡ ዕቁቦች አንባቢዎች ሒሳዊ ንባብ እያደረጉ ስለመጻሕፍት በጥልቀት እንዲወያዩ መንገድ ይከፍታሉ ሲል ይገልጻል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ የመጻሕፍት ዕቁብ ያላቸው ግለሰቦች ባጠቃላይ ያነባሉ ለማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ የውይይት መድረክ መፍጠር አጋዥ ይሆናል፡፡ ዕቁቦች በደራስያን እንዲሁም በሻጮችም መደገፍ አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ አባላት ደራስያንን ወይም ሌሎች ባለሙያዎችን ለውይይት ቢጋብዙ የተሻለ ዕውቀት ያገኛሉ ይላል፡፡ ዕቁብ ያላቸው እርስ በርስ ተዋውቀው ልምድ የሚለዋወጡበት መንገድ ቢፈጠር ዘለቄታቸው አስተማማኝ ይሆናል፡፡ የመሰል ዕቁቦች መስፋፋት በአገር ደረጃ የንባብ ባህል እንዲዳብር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ያምናል፡፡