Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየኢትዮጵያና የኢንተርፖል አጋርነት ያፈራው ምንድነው?

የኢትዮጵያና የኢንተርፖል አጋርነት ያፈራው ምንድነው?

ቀን:

በሒሩት ደበበ

ኢንተርፖል የተባለው ዓለም አቀፍ የፀረ ወንጀል የጋራ ፖሊሳዊ ጥምረት፣ በአሁኑ ወቅት 191 የሚደርሱ የዓለም አገሮችን በአባልነት የያዘ ማኅበር ነው፡፡ ይህ በየነ መንግሥታዊ ድርጅት በቀደሙት ጊዜያት በታዳጊ አገሮች ተጠርጣሪዎች መያዝ ላይ የነበረው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው እየተባለ ሲተች ኖሯል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዘርፈ ብዙ መሻሻሎችን እንዳመጣ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 በወጣ መረጃ የዓመት በጀቱ ከተናጠል የአገሮች ድጋፍ ውጪ 70 ሚሊዮን ዩሮ ይደርሳል፡፡ 700 የሚደርሱ የሠለጠኑና የነቁ ፖሊሶችና መርማሪዎችም አሉት፡፡ በየዓመቱም ከ100 በላይ የሚሆኑ ከፍተኛ ወንጀለኞች ሕግ ፊት እንዲቀርቡ እያደረገ ነው፡፡

ኢንተርፖል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀጥሎ ከፍተኛ የአባል አገሮች ብዛት እንዳለውም ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1923 ቪየና ውስጥ የተቋቋመው ይኼ የጋራ ደኅንነትና ፀረ ዓለም አቀፍ ወንጀል በርካታ የጋራና የተናጠል የወንጀል ተጠርጣሪዎችን በመያዝ፣ ለሰው ልጆች ደኅንነት አስተዋጽኦ በማድረጉም ይወሳል፡፡

- Advertisement -

የተቋሙ ዋነኛ ሥራ በተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይ መረጃ ማፈላለግ፣ ማግኘት፣ ማደራጀት፣ ማከማቸትና ማሰራጨት ብቻ ሳይሆን ቢያንስ ተጠርጣሪን በመያዝ አሳልፎ የመስጠት ሚናም አለው፡፡ እስካሁንም በሰብዓዊ መብት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ በሽብር፣ በሙስና፣ በዓለም አቀፍ አጭበርባሪነት፣ በተደራጁ ወንጀሎች፣ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር፣ የዕፅ ዝውውር፣ የኮምፒዩተርና ሳይበር ወንጀሎች፣ ወዘተ በተጠርጣሪዎች ላይ የወሰዳቸው ውጤታማ ሥራዎች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡

አገራችን የኢንተርፖል አባል አገር ከሆነች በርካታ ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ አኅጉራዊ የፖሊሲ ጥምረት እንዲፈጠርም ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ መንግሥታት ተርታ ትሠለፋለች፡፡ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የአገሪቷንና የሕዝቦቿን ጥቅም ጎድተው ከአገር የወጡ የእኛው ፍጥረቶች ቁጥራቸው ትንሽ ባይሆንም፣ የኢንተርፖል አጋርነት መታየት የጀመረው ግን ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በቀዳሚነት በርካታ ኢትዮጵያውያንን (በተለይ ከሃድያና ከከምባታ አካባቢዎች ዜጎችን) በማጭበርበር ወደ ደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ለመመልከት ልውሰድ ብሎ ያጭበረበረ ወንጀለኛ፣ በርካታ ሚሊዮኖችን ከደሃና እንጀራ ፈላጊዎች ላይ መዝረፉን ሰምተን ተቆጭተን ቀርተን ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥትና ኢንተርፖል ባደረጉት ጥምረት ተደብቆ በመንደላቀቅ ከሚኖርበት ጀርመን መዘው አምጥተውታል፡፡ ፍርዱ ምንም ይሁን ምን ወንጀለኛው ከሕግ በታች እንደሆነ በሚያሳይ ሁኔታ እጁን ታስሮ ወደ አገር ሲገባ ብዙዎችን አስደምሟል፡፡

በያዝነው ዓመት የመጀመርያ ወራት ላይ ከዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ተይዞ የመጣ በዱባይ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ያፈራ ተጠርጣሪም፣ በሕገወጥ ተግባር ተሰማርቶ የአገር ሀብት የዘረፈ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከሕገወጥ ስደት ጋር በተያያዘ በዜጎች ላይ ሲነግዱ የነበሩ ሕገወጥ ደላሎችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢንተርፖል ድጋፍ ከጎረቤት አገሮች መያዝ እንደተቻለ ሰምተናል፡፡

የኢንተርፖል አፈላልጎና የመያዝ አቅምን ተከትሎ በአክሲዮን ሽያጭ የሕዝብ ገንዘብ ይዘው ተሰወሩ የተባሉ አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ‹‹ላናመልጥ›› በሚል እሳቤ፣ በመደራደር ወደ አገር ቤት እንደመጡም እየታየ ነው፡፡ እነዚህ በጎ ጅምሮች ባሉበትም ሁኔታ ቢሆን ግን አሁንም የአገራችንን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ፣ በፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የብዙዎችን ልብ ያደሙም ሆነ፣ በሙስናና በከፋ ምዝበራ ተጠርጥረው ከአገር ውጭ የሚኖሩ ሰዎችን በመያዝ ረገድ ሥራው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ብሎ መገምገም ያስፈልጋል፡፡

ባለፈው ዓመት መጀመርያ (እ.ኤ.አ. በ2014) አንድ ዓለም አቀፍ የአገሮችን የፋይናንስ ዝውውር የሚያጠና ተቋም ባለፉት አሥር ዓመታት ከኢትዮጵያ 11 ቢሊዮን ዶላር (ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ) ወደ ውጭ ወጥቶ አልተመለሰም ሲል፣ ደረቅ እውነቱን ተናግሯል፡፡ ይህንኑ መረጃ እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያሉ ተቋማት ተቀብለው በአንዳንድ ሪፖርታቸው ከማካተታቸውም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይፋዊ የማስተባበያ መረጃ ሲሰጥ አልታየም፡፡ አልተደመጠም፡፡

ይልቁንም በተለያዩ ኢመደበኛ ‹‹ወሬዎች›› ይኼን ያህል ገንዘብ ከአገር ወጣ ሲባል፣ ከሙስና ጋር ብቻ ሊያያዝ አይገባም የሚሉ ተከራካሪዎች ተደምጠዋል፡፡ በአስመጭና በላኪነት መስክ ከተሰማሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደላቸው አሠራሮችና ባለሀብቶች ጋር የሚያያዘው ይበዛል፡፡ ከውጭ የመጡ አንዳንድ ሕገወጥ ‹‹ኢንቨስተሮችም›› በገንዘብ ማሸሹ ተግባር ላይ ተዋናይ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡ ከሁሉ በላይ በቻይና ሕገወጥ ንግድ አስፋፊዎችና በእኛው አገር ኮንትሮባንዲስቶች፣ እንዲሁም የግብር አጭበርካሪዎች ከውስጥ ወደ ውጭ የተሰደደ የአገር ሀብት አገራችን የጀመረችውን ፈጣን ዕድገት ምን ያህል በደገፈ ነበር? ብሎ መቆጨት ይገባል፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት መሠረታዊ ጉዳይ ታዲያ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታና የደኅንነት ኃይል በዋናነት፣ በመቀጠልም ኢንተርፖል ሊፈልጋቸው የሚገቡ የሙስናና የንግድ አጭበርባሪዎች የሉምን? መባል አለበት፡፡ ነው ወይስ የተመረጡ ወንጀለኞች ብቻ ናቸው ተይዘው የሚገቡት የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡፡

አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚያስረዱት በኢትዮጵያ ፖሊስ አማካይነት ጥያቄ ቀርቦላቸው ለመተባበር ዝግጅት ተደርጎ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች አሉ፡፡ ኢንተርፖል በራሱ መመዘኛ የፖለቲካ ልዩነትና ውዝግብን መሥፈርት የሚያደርጉ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ በኩልም ‹‹እግር መጓተት›› ይታይበታል ይላሉ፡፡ በርካታ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች (የእኛኑ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን) ጨምሮ በሰብዓዊ መብት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተጠርጣሪ ለመያዝ ድፍረት አላሳየም በሚል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በብዙዎቹ የቀይ ሽብር ተጠርጣሪዎች ላይ አስተማሪ ዕርምት ለመውሰድ የሄደበት ርቀትና በኋላም ከሞት በመለስ በችሎት ፊት አስቀጥቶ የቋጨው ፋይል ለብዙዎች አገሮች ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹አልተሳካም›› የሚባለው ጉዳይ ብዙዎች በከረረ ወንጀል የሚፈለጉ የሥርዓቱ ግንባር ቀደም ተጠርጣሪዎችን ከየአገሩ ለመያዝ አለመቻሉ ነው፡፡ ዛሬ አንዳንዶቹ ከተሳካላቸው ባለሀብቶች፣ ምሁራንና ዳያስፖራ ጎራ ተሰልፈው በሰላም የሚኖሩት የንፁኃን ደምና የአገር ሀብት ዕዳ ሳይኖርባቸው ሳይሆን ስላልተያዙ ብቻ ነው፡፡

ባለፉት 24 ዓመታት ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲያስተዳድር የሕዝብ መሬት እንደ ቅርጫ ሥጋ ቸብችበው፣ በከፍተኛ የመንግሥት ግዢና ሽያጭ ሙስና ተጠርጥረው፣ ወይም ዓይን ባወጣ የግብርና ታክስ ማጭበርበርም ሆነ ሙስና ወንጀል ተሳትፈው የተሰወሩ የሉምን?! የመመዝበራቸው ማረጋገጫስ በደርባን፣ በጆሃንስበርግ፣ በጁባ፣ በጂቡቲ፣ በካርቱም፣ በማላቦ ብቻ ሳይሆን በዱባይና በቤይሩት ሳይቀር ቤትና ድርጅት የከፈቱት ሁሉ ዕውን በላባቸው ነው? በአውሮፓና በአሜሪካ ለሚሠራ የሐበሻ ድርጅትና ኩባንያ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ አንጡራ ሀብትስ የለን ይሆን!?

በቅርቡ በአገራችን አንድ ታዋቂ ከሆነ ኮሌጅ ባለቤት ጋር ተያይዞ በመዲናችን የተሰማው ወሬ እንደ አገር የተደቀነብንን አደጋ ያሳያል፡፡ ‹‹ባለሀብቱ›› የድርጅቶቻቸውን የግብርና የታክስ አሠራር ለሚከታተሉና ‹‹ለሚታመኑ›› የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሙያዎች መምነሽነሻ ገንዘብ ሲሰጡ ኖረዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ይኼ እውነታ በግል ድርጅቱ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች እያወቁ ዘልቀዋል፡፡ ይሁንና ከግብር ማጭበርበሩ ባሻገር ተቋሙ ከትምህርት ጥራትና ብቃት መመዘኛ አንፃር መቀጠል ሲሳነው ለመዝጋት በቅቷል፡፡ ባለሀብቱም የቀራቸውን ንብረት ሸጠው ከአገር ተሰደዋል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የዘገየ መረጃ ግን ‹‹የአሥር ዓመታት ግብር ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ አለባቸው›› የሚል ያረፈደ ወሬ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ሰውየው ከአገር ከጠፋ በኋላም ፈልጉልኝ ሲል መረጃ ለጠፈ፡፡

ይህና ሌሎቹ አንዳንድ ማሳያዎች በአገር ውስጥ የተሸከምናቸው የሙስናና የሕዝብ ሀብት ምዝበራ ተባባሪ ወንጀለኞችን መመንጠር ዋና ሥራ ሆኖ፣ ከሚሰደደው ገንዘብ ጀርባ ያሉ ተጠርጣሪዎችን መያዝና ፍርድ መስጠት ዋና ሥራ ሊሆን ግድ ነው፡፡ የኢንተርፖል አጋርነታችን በተጨባጭ ፍሬ አፍርቷል ሊባል የሚችለውም በጥቂት ማሳያዎች ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡ በሚያውቃቸው የፈጠጡ እውነታዎችም ሊሆን ግድ ነው፡፡ እርግጥ ዋናው ድርሻ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኝነትና ‹‹አጥፊን ያዙልኝ›› ሊሆንም ግድ ነው፡፡

በኢንተርፖል ታሪክ ከሚጠቀሱ መልካም ተግባሮች ጎን ለጎን፣ በራሱ በተቋሙ ውስጥ የሚጠቀሱ መድልኦዎችና ሙስናዎችም በሕዝብ ጥቅም ላይ ደባ የፈጸሙትን ሁሉ ለቅሞ ለመጋለጥ አውኳል፡፡ ለምሳሌ የቅርብ ጊዜውን ብንወስድ እ.ኤ.አ. በ2010 የኢንተርፖል ፕሬዚዳንት የነበሩት ጃኪ ሴሌቤ ከአንድ ዕፅ አዘዋዋሪ ወንጀለኛ 150 ሺሕ ዩሮ ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተከሰው ጉዳዩ እስኪጣራ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡ ሌሎች ከአፍሪካ አገሮች የከፋ ምዝበራ ፈጽመው በሕግ ፊት ላልቀረቡ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ተድበስብሶ መቅረት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ይጠቀሳል፡፡

‹‹ኢንተርፖል አገር አቀፍ በሆኑ ጥቃቶች፣ ጉዳቶችና ዓለም አቀፍ ወንጀሎች እንጂ በእያንዳንዱ ግለሰብ ወንጀል እየገባ ለመሥራት አቅሙም ሆነ መብቱ የለውም፤›› የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ያጋጥማሉ፡፡ ይሁን በቻይና በአንዳንድ የግል ኩባንያዎች ላይ ሳይቀር ተፈጽመው በመንግሥት የእስር ዋራንት በተቆረጠባቸው ተጠርጣሪዎች መያዝ ላይ ኢንተርፖል ያለውን ሚና ማየት ይቻላል፡፡ በቅርቡ በህንድ፣ በብራዚልና በቺሊ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በዚሁ የፀረ ወንጀል ማኅበር ድጋፍ በችሎት አደባባይ ፊት የቀረቡ ወንጀለኞች ድርጊትና የመዘበሩት ገንዘብ ሲታይ፣ በእኛም አገር ተደጋግመው ከሚጠቀሱት ዝርፊያዎች የበለጠ የሚባል አይደለም፡፡

ኢንተርፖልና የፖለቲካ ወንጀለኞች (እንደ ዘር ማጥፋት) ያለውን በተመለከተ፣ ሁለት ዓይነት ክርክሮች ይደመጣሉ፡፡ አንዳንዶች ማኅበሩ በአገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የመመርመር ሥልጣንም ሆነ ተጠርጣሪ የተባሉትን የመያዝ ሥልጣን የለውም ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ1980 ወዲህ ኢንተርፖል በፖለቲካ ጉዳይ ገብቶ ዕርምጃ እንደማይወስድ የሚከለክለው የሕግ ደንቡ አንቀጽ 3 ተሻሽሏል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና በፖለቲካ መዘዝ በንፁኃን ዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱና በአገር ሀብት ላይ ምዝበራ ፈጽመዋል የሚባሉ ወገኖችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በርካታ ፖለቲካዊ ፈተናዎች ይኖራሉ፡፡

አንደኛው ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ዝምድና፣ ከዘረኝነትና ማግለል ጋር የሚያያዘው እውነታ ነው፡፡ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት) በተባለው ተቋም ላይ እንደሚታየው፣ አፍሪካውያን መሪዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ የሚመስል ጥቃት ብዙዎች ፍትሐዊነቱን እንዲጠራጠሩት ያደርጋል፡፡ የገለልተኝነት ጥያቄንም ያስነሳል፡፡

ሁለተኛው ከኃያላን መንግሥታት ፍላጎትና ከሙስናም ጋር ይያያዛል የሚሉ አልታጡም፡፡ ምዕራባውያን ‹‹አሸባሪ›› ያላሉትን ሌላው ዓለም በተናጠል እየጮኸ ‹‹ሽብርተኛ ነው›› ቢል፣ እንደ ኢንተርፖል ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመንቀሳቀስ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ የማኅበሩ መሪዎች መድልኦና ሙስና የሚያሳድረው ተፅዕኖም ቀላል እንዳልነበር በማኅበሩ ታሪክ ውስጥ ኢንተርፖል የናዚ የጦር ወንጀለኞችን ሕግ ፊት ለማቅረብ ጥረት ሳያደርግ፣ ድርጅቱን እ.ኤ.አ. ከ1938 እስከ 1945 የመሩት አራቱም ጄኔራሎች የጀርመን ፋሽስት ሠራዊት አዛዦች ስለበሩ አንድ ዕርምጃ ማስኬድ እንዳልተቻለ የተጠቀሰው መረጃ ያስረዳል፡፡

ለሁሉም ኢንተርፖል ብቻ ሳይሆን አፍሪካፖልም ሆነ የቀጣና የፀጥታና የደኅንነት ኃይል መጠናከሩ ዋነኛ ተጠቃሚ አገራችን መሆኗ ላይ እንግባባ፡፡ በማኅበራቱ መቋቋምም ሆነ መጠናከር ላይ የነቃ ተሳትፎ የማድረግ ጉዳይም ለነገ መባል የሌለበት ነው፡፡ እዚህ ላይ በሰላም ማስከበር ሥራና በፀረ ሽብር የጋራ ግብረ ኃይል ረገድ የተጀመረው ሥራም ተሳስሮ ሊታይ ይችላል፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን በአገር ውስጥ ሕዝብና መንግሥት አጥብቆ የሚታገላቸው ወንጀሎች የትኞቹ ናቸው? የሚለው ጥያቄ ግልጽ ትግል ይፈልጋሉ፡፡ ሙስና፣ ሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ ስደት፣ የመሣሪያ ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ ወይስ ሌላ? በእነዚህ ድርጊቶች ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊዎች እነማን ናቸው? እንዴት ማጋለጥስ ይቻላል? የሚሉ ተጠየቆችን ሁሉ መመለስ ግድ ይላል፡፡ ከዚያ በኋላ የትኞቹ ወንጀለኞች ከአገር ወጥተው በሌላው ዓለም ይኖራሉ? የኢንተርፖል ድጋፍስ ይጠይቅባቸዋል? የሚለው ነጥብ ይከተላል፡፡ ምናልባት ጥያቄና የትብብር ጥረት እንዲደረግ ሐሳብ ቀርቦ የዘገየ አፈጻጸም ካለም እንዴትና ለምን ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

ኢንተርፖልንም ሆነ ሌሎች የጎረቤት አገሮችን የትብብር ማኅበሮች (ለምሳሌ ኢጋድን) የማይደግፉና የማይተባበሩ መንግሥታት (ለምሳሌ የኤርትራ መንግሥት) ሲያጋጥምስ ምን ዓይነት የመፍትሔ አማራጭ ለመውሰድ ይቻላል ማለትም ተገቢ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ አገርና ሕዝብን በመበደል ከአገር ወጥተው የሚኖሩ ሰዎች መያዝና ለፍርድ ማቅረብ እንደ ቀላል የሚታይ ስላልሆነ መዘናጋት አይገባም፡፡ በሕዝብ ሞራልና በሕግ የበላይነት ልዕልና ላይ ያለውን ፋይዳ አጤኖ መትጋትም ያስፈልጋል እንላለን፡፡ የኢንተርፖል ትኩረትን መሳብ የሚቻለውም በውስጥም ሆነ በውጭ ወንጀለኞችን ለመመንጠር የሚያስችል የመንግሥት ቁርጠኝነት ሲኖር ነውና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...