Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትልቁ ሥጋት ሙስና ነው

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትልቁ ሥጋት ሙስና ነው

ቀን:

በፍሰሐ በዕደ ማርያም

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአምስትና በአሥርም ዓመት እየታቀደ የአንድ አገር ሽግግራዊ ለውጥን ማምጣት የጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ ወይም በኢትዮጵያ አልጀመረም፡፡ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ህንድና ብራዚል ባለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት ተጉዘውበታል፡፡ ምዕራባውያኑም ቢሆኑ ስሙ ይቀያየር እንደሆን እንጂ፣ በስትራቴጂካዊ ፕላን በመመራት የችግርን ድሪቶ እያራገፉ የዕድገትና የብልዕግናን ጎዳና መጎናፀፍ ችለዋል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለዕቅድ ማውራት ባይሆንም አገራችን አንደኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) ዕቅድ አጠናቃ ሁለተኛውን ለመጀመር ጫፍ ላይ እንደመገኘቱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ለማስታወስ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ከፍተኛ በጀት፣ ዕውቀት፣ አመራርና የሰው ኃይል የሚፈልግ ዕቅድ መነደፍ ስለሚገባው፣ ለሚመረተውና ወደ ውጭ ለሚላከው ዕቃ ብቻ መጨነቅ አይገባም፡፡ ወይም በትምህርት፣ በጤናም ሆነ ሌሎች ዘርፎች ስለሚከናወኑ ተግባራት ብቻ ትኩረት ሰጥቶ መቆም ያስቸግራል፡፡

ይልቁንም ለተነደፉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ማሳኪያ የሚሆን ፋይናንስ ከየት ይገኛል? እንዴትስ ጥቅም ላይ ይውላል? የሚል ኮርኳሪ ነጥብ ማንሳት ግድ ነው፡፡ ለዚህም የዜጎች የቁጠባ ባህል እንዴት ይዳብር? የሕዝብ ሀብት እንዴት ይጠበቅ?  ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይንሰራፋ ምን ይደረግ? የሚሉ ጭንቀቶችም የመንግሥትን ቀልብ ሊገዙ ግድ ይላል፡፡

በዓለም ብልፅግናን የተቀዳጁ አገሮችም ሆኑ ዛሬም ድረስ በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ከራሳቸው አልፈው የዓለምን ስደተኞች በመሰብሰብ ማኖር የቻሉት፣ ከላይ በተነሱ ተጠየቆች ላይ ተገቢ መልስ እየሰጡ በመምጣታቸው ነው፡፡ በተለይ የአገር ጠላት የሆነውን ሙስናን የመከላከል ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ባይሠሩ ኖሩ፣ የሚያንቀሳቅሱን ሀብት ያህል ከፍተኛ አደጋ ሊገጥማቸው የሚችሉ አገሮች እጅግ ብዙና በርካታ ናቸው፡፡

በዘንድሮው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ጊዜ የተከበረው የፀረ ሙስና ቀን መሪ ቃል ‹‹የሙስናን ሰንሰለት እንበጥስ›› (Break the Corruption Chain) የሚል የሆነበትን ምክንያት ለተመለከተ፣ አደጋው ከአገር አልፎ የሚተሳሰር የመሆኑ ተጨባጭ እውነት እየነገሠ በመምጣቱ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተጎነጎነ ሙስና ቻይና፣ ቱርክ ወይም አሜሪካ የሚተሳሰሩበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ግዙፍ የመሠረተ ልማትና የማዕድን ማምረት ጨረታው ጦፏል፡፡ ሌላው ዓለም አሮጌ ኢንዱስትሪዎቹን በመንቀል ‹‹ሰላምና ገበያ አለ›› ባለበት አገር ሁሉ እንደ ችግኝ ሊተክል አሰፍስፏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ መድረክ ‹‹የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት›› እንኳን የሚከፈለውን ጉቦና ሙስና እንደ ጉድ እየሰማን ነው፡፡ ሙስና አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ገጽታ አለው ሲባል፣ ከፖሊሲ አውጪዎች አንስቶ እስከ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች የሚደርሱ ሰዎች ሊበከሉ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ለማሳየት እንደሆነ፣ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በመሪ ቃሉ ላይ የሰጠው ትንተና አስረድቷል፡፡ ስለሆነም ሙስናን በፅናት ለመታገል በአገር ውስጥ ሁሉን አቀፍ (Multi Disciplinary) የሆነ ርብርብ ከማድረግ ባሻገር፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ባህል እንዲጎለብት መሥራትና ሕዝቡን ማነቃቃት ለነገ ሊባል የማይገባው ሥራ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አትኩሮት ትሪሊዮን ብሮችን የሚፈልገው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የፀረ ሙስና ትግሉ እንዴት ይተሳሰሩ የሚል ሒሳዊ መላምቶችን መሰንዘር ነው፡፡ ስለሆነም በምጠቃቅሳቸው ዋና ዋና መስኮች ላይ የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችን በመለየት ፈጥኖ የዕርምት ዕርምጃ ይወሰድ ዘንድ ለመማፀንም ነው፡፡ በመሆኑም በየርዕሰ ጉዳዮቹ ነጥብ ነጥብ ለማንሳት እሻለሁ፡፡

ወሳኙ ገቢዎችና ጉምሩክ

ባለፉት አምስት ዓመታት አገሪቱ ላስመዘገበችው ፈጣን ዕድገትም ሆነ የመሠረተ ልማት እመርታ በብድርና በዕርዳታ ከተገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ከአራት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባት መቻሉ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ብቻ ይህ መሥሪያ ቤት 170 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲሰበስብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት አካል ጠንካራ ሥነ ምግባር፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሠራር ግልጽነትና ጠበቅ ያለ ተጠያቂነትን ማስፈን የግድ ይለዋል፡፡

ከወራት በፊት ‹‹ሥነ ምግባር›› ከተበሻሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መጽሔት ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌም ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ይስማሙበታል፡፡ በዚሁ መሠረት በግንቦት 2005 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በአገሪቱ አንዳንድ ቱባ ነጋዴዎች ላይ የተገኘው የሙስና ‹‹ሚስጥር›› እና ከእነርሱ ጋር የተያያዘው ሕገወጥ ኔትወርክ መጋለጡ፣ በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ አንድ ዕርምጃ ለመራመድ አስችሏል ይላሉ፡፡ ቀስ በቀስም ሠራተኛው ከመረበሽ ወጥቶ ወደ ተረጋጋ ሥራ በመግባቱ ሥራው ያለቀለት ባይሆንም፣ እንደ አገር በገቢ አሰባሰቡ ላይም ሆነ በሕዝብ አገልጋዩነት ላይ መሻሻል ታይቷል፡፡

ከኃላፊው ገለጻ በተቃራኒው የሚነሳው ሥጋት ግን መንግሥት በወቅቱ ከወሰደው ዕርምጃ ጋር ተያይዞ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም፣ የዘገየ መሆኑን ነው፡፡ ክሱ ብቻ ሳይሆን በተጠርጣሪዎች የተዘረፈውን ሀብት ምን ያህል ነው? የትኛው ለሕዝብ ጥቅም ዋለ? የትኛውን በላባቸው ያገኙት ነው? ፈጥኖ መመለስ አለበት፡፡ በውሳኔ መዘግየት ለአገር የሚጠቅም ንብረት ለብክነትና ለጉዳት ሲጋለጥ ታይቷልና፡፡ ሁለተኛው መከራከሪያ አሁንስ በባለሥልጣኑ የሚታይ የሙስና ችግር የለም? የሚለው ነው፡፡ የአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መተላለፊያው በዚህ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም መሻሻል ቢኖርም በአካል ንክኪ፣ በሰው ግምትና በመስተንግዶ ላይ የተመሠረተ የግብር ሥርዓት ላይ ያለን እንደመሆኑ መጠን ለሙስና መደራደርና ለመድልኦ የተጋለጠ ዘርፍ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ የግብርና የጉምሩክ ሥርዓትን በማበላሸት የግል ጥቅምን ለማባረርና ሕገወጥ ሀብት ለማካበት ለሚባዝኑ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች እንዳሉ፣ ሕዝቡ በተለያየ ሁኔታ እየገለጸ ይገኛል፡፡  

እንግዲህ ደጋግሞ ችግሩን ማውራቱ አይደለም መድኃኒቱ፡፡ መፍትሔው ምን ይሆን ብሎ መሥራት ነው ዋናው?! አንደኛው በየሥራ ክፍሉ በአብዛኛው ሴቶች   ታማኝና ሥነ ምግባር ያላቸውን ዜጎች ማሰማራት ያስፈልጋል፡፡ በፌዴራል ተቋማት በፈጻሚውም ሆነ በሥራ መሪው መካከል የብሔርና የሃይማኖት ፍትሐዊ ስብጥር መዘርጋት፡፡ የቼክና ባላንስ አሠራርን ማጥበቅ ይገባል ይገባል፡፡ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በማስፋት ዜጎች የገቢ መረጃቸው እንዲታወቅ፣ የሚጣልባቸውን ግብር በግልጽ እንዲረዱ፣ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ (እንደተች ስክሪን) የጉምሩክ ሥርዓቱን በማሳለጥ ረገድ እንቅልፍ ሊወስድ አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ ከአፍሪካ እነ ጋና፣ ቦትስዋና፣ አልጄሪያና ግብፅ የደረሱበት ደረጃ እንኳን ቀላል አይደለም፡፡

ሌላው መፍትሔ አሁንም የሕዝቡን ግንዛቤ በአግባቡ ማሳደግ ላይ መሥራት ነው፡፡ ሕዝቡ መረጃ እንዲሰጥ፣ ሙሰኞችን እንዲያጋልጥ፣ በማጋለጡ እንደማይጠቃ ዋስትና በመስጠትና በመሸለም፣ በሙስና አጥፊነት ላይ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ግድ ይላል፡፡ ይህን በተመለከተ አቶ በከረም ለመጽሔቱ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ግብር ከፋዩን የፀረ ሙስና ትግል አካልና ባለቤት ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ በተደረገው ጥረት፣ ግብር ከፋዩ ችግር ያለባቸውን ሠራተኞች እንዲጠቁምና እጅ ከፍንጅ ጭምር እንዲያዙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ከተቆጣጣሪ አካላትና ከኮሚሽኑ ጋር ተቀናጅቶ መሥራትና መረጃ መለዋወጥ ተችሏል፡፡ ቢሆንም አገር አቀፍ ሁኔታው ሲታይ በሕዝቡ ተሳትፎ ላይ ገና ብዙ ሥራ ይጠይቀናል፤›› ብለዋል፡፡

የጉምሩክ ዘርፉም መሻሻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የቀጠሮ ማስረዘም፣ የቀረጥ ነፃ ጉዳይ ግልጽነት አለመላበስና ከተቆጣጠሪዎች ጋር የመሞዳሞድ አደጋው መፈተሽ አለበት፡፡ ለመሆኑ በየከተሞች ሜዳውን የሞላው ልባሽ ጨርቅ፣ አዲስና አሮጌ ዕቃዎች በየት የገቡ ናቸው? ማን አመጣቸው? በየት አለፉ? መባል አለበት፡፡ ጥቂት ትራንዚተሮች የመፈተሸና የጉምሩክ ሥራን በማቀላጠፍ ‹‹ጉዳይ ገዳይነት›› ገብተው የሚገኙት ማን ፈቅዶላቸው ነው? በቀረጥ ነፃ ስም የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ምን እየሠሩ ነው? በሕንፃ ግንባታ ዕቃዎች ስም በገፍ እየገባ ያለው የተለያየ ሸቀጥ ገበያውን እየሞላ አይደለም? በአንድ ሆቴል ግንባታ ስም ለስንት ሆቴል የሚገባ ሕገወጥ ዕቃ ከቀረጥ ነፃ እንደሚገባ አይታወቅም፣ ወዘተ እነዚህና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ቀጣዩን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚመጥን ልክ ሊዘመትባቸው የግድ ነው፡፡

ደረጃ ማውጣት፣ ምዘናና ልኬት አዲስ የሙስና በሮች

የሙስና መጥፎ ጎን አዲስ ጉዳይ በተከፈተ ቁጥር እንደሚያፈስ ጋን እየተሸነቆረ የአገርን ጥቅም የሚያሳጣ መሆኑ ነው፡፡ በአገራችን የምዘና፣ ደረጃ የማውጣትም ሆነ የስታንዳርድ ባህል አዲስ ቢሆንም፣ ሙስና እንደ ወረርሽኝ ገብቶ እያጠቃው እንደሆነ ከብዙዎች የሚሰወር አይደለም፡፡

በትምህርት መስክ (ከግል ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች) የብቃት ደረጃ አሰጣጥ ጋር የደራ ሌብነት አለ፡፡ መዛኙ፣ ማረጋገጫ ሰጪው፣ ሱፐርቫይዘሩ ሳይቀሩ በብዛት እንደ ብክነትና ወደ ተራ ጥቅም ፈላጊነት እንዲወርድ እየሠሩ ያሉ ‹‹ባለሀብቶች›› ዋነኛ የወንጀሉ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በመካከለኛ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና ቡና ቤቶች የደረጃ ምደባና ፈቃድ መስጠት ላይ የተሰማሩ የባህልና ቱሪዝም ወይም የንግድ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ያለ እጅ መንሻ የማይነቃነቁ ሆነዋል፡፡ ክፍተቱ የአሠራርም ጭምር እንደሆነ መረዳት የሚቻለው የምዘና ፈጻሚዎች በተናጠል በየግል ተቋማቱ እንዲሄዱ መደረጋቸው ለመደራደር በር ከፋች በመሆኑ ነው፡፡ አንዱ ያየውን ሌላው የሚያረጋግጥበት አሠራር ያለመኖሩና ባለጉዳዩም በጥራትና በስታንዳርዱ መሠረት ተዘጋጅቶ ከመጠባበቅ ይልቅ፣ ተዝረክርኮ በእጄ እሄዳለሁ ማለት መለመዱ እንደ አገር በመንግሥት ላይ እምነት እያሳጣ ነው፡፡

የምዘና ነገር ከተነሳ ከሰሞኑ ለውጭ ገበያ የሚመረቱ ቡናና ሰሊጥ የሚገበዩበት ሥፍራ የታዘብኩትን ላውጋችሁ፡፡ በቡና ቦርድ ግቢ በርካታ ከባድ ካሚዮኖች ከየአቅጣጫው ቡና ጭነው ይገባሉ፡፡ የቡና ደረጃ የሚያወጣ (በመውጊያ ዓይቶ የሚመረምረው) ሸራውን ገልጦ ከላይ ይወጣል፡፡ የቡናውን ዓይነት በመውጊያ ከየኩንታሉ እየመረመረም በተቀመጠው ደረጃ አንደኛ፣ ሁለተኛና ልዩ እያለ ለገዢዎች ያሳውቃል፡፡ ታዲያ የቡና አቅራቢው በአሽከርካሪው በኩል ተገቢውን ‹‹እጅ መንሻ›› ካላቀረበ አንደኛ ቡና መጨረሻ የማይሆንበት ዋስትና የለም፡፡ ዝቅተኛ ደረጃውም ከፍ ተደርጎ እንዲጠራ ያረጋል፡፡ ያሳዘነኝ እውነት ወጊውና ከታች ያለው የቡና ወኪል በጣት ምልክት የጉቦውን መጠን በሺሕ ብሮች በመደራደር ያውም ለውጭ ገበያ የሚቀርብን ትልቅ የአገር ሰጪ ምርት ሲሞዳሞዱበት ማየቴ ነው፡፡ ይህን የተዝረከረከ አካሄድ ቴክኖሎጂ ወይም የዘመኑ አሠራር ሊፈታው አይችልም? ሌላ የቁጥጥርና ሙሰኛን የመመንጠሪያ ዘዴስ ጠፍቶ ይሆን?

ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በአዲስ አበባ መግቢያ ያሉ የከባድ ጭነት ሚዛን ተቆጣጣሪዎች አሠራርን ማንሳት ይቻላል፡፡ በዱከም፣ በሱሉልታና መሰል ሥፍራዎች ያሉ ልኬቶች ዋነኛ የሌብነት ሥፍራዎች ሆነዋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ሚዛኑ እንኳን ተበላሽቶ እንደሚሠራ በማስመሰል መንግሥት ማግኘት ካለበት በአምስትና በአሥር እጥፍ ጉቦ የሚቀበሉ ተቆጣጣሪዎች ሥራውን ‹‹የግል እርሻ›› ካደረጉት ሰነባብተዋል፡፡ ‹በዚያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የተመደቡ ደመወዝተኞችስ ያላቸው ሀብት ይታወቅ ይሆን?› ሲል ያጫወተኝ አንድ አሽከርካሪ ከፈጣኑ ዕድገትና ምልልስ እኩል በሙስና እየተንበሸበሹ ነው ሲል ይቆጫል፡፡ እዚህ ላይ ልክ እንደ ፍጥነት መንገድ በኤቲኤም የክፍያ ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ የምዘናና ክፍያ ሥርዓት መበጀት አይቻልም ይሆን?

ለማሳያ ያህል ያነሳናቸው የምዘናና የልኬት ሙስናዎች ቀላል ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ሒደትና የገንዘብ ዝውውር ላይ ብዙውን ዜጋ የሚያማርሩና የሚያበላሹ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንዴት ቀዳዳ እንድፈን? የሕዝብ ሀብትስ በምን መልክ ይጠበቅ? ብሎ ዕቅድ መንደፍ የግድ ይላል፡፡

ጣጠኛው መሬትና የሕዝብ ሀብትነቱ

‹‹መሬት መሸጥ መለወጥ የማይቻል የሕዝብ ሀብት ነው›› ቢባልም አሁን ባለው ሁኔታ እንደ መሬት በከፍተኛ ዋጋ የሚሸጥ የጋራ ሀብት ጠፍቷል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባና ዙሪያዋን ባሉ ከተሞች ቱባ የመሬት ደላሎች በየደረጃው ካሉ የማዘጋጃ ቤት ሹመኞችና ሙያተኞች ጋር ያላቸው ትስስር ተለይቷል? ተበጥሷል? እርግጥ ነው በአዲስ አበባ ዕድሜ ‹‹ለመሬት ባንክ›› ሀብቱ ተለይቶ በመረጃ ተሰናድቷል፡፡ መሬት በሊዝ ጨረታ ካልሆነ በሌላ መንገድ መተላለፍም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ምናልባት እንደ ችግር የሚነሳው ነባሩን ይዞታ ሕጋዊ በማድረግ ሒደት፣ እንዲሁም ‹‹በኢንቨስትመንት›› ስም ክፍት ጎረቤት ቦታዎችን በማስማሚያ የመስጠት ተግባር ነው፡፡ ሊዝም ተከፍሎ ካለ ጨረታ መሬት ለማግኘት የሚደረግ ሽሚያ አለ፡፡ ይህን የሚያስፈጽም፣ መረጃ የሚሰጥና የሚያስወስን ሹመኛ (ባለሙያ) ደግሞ በማማለያ መያዙ የዘወትር ተግባር ሆኗል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው የአገር ሀብት አያያዝም መላ የሚያስፈልገው መሆኑ ሊታበል አይገባም፡፡ በአንድ በኩል በካርታ አሰጣጥና ሰነድ ማስተላለፍ ረገድ የሚታይ ሙስና አለ፡፡ በሌላ በኩል አንድን መሬት ሁለትና ሦስት ጊዜ በማስተላለፍ (መሸጥ) ዜጎችን ለጉዳት የሚያጋልጥ ሕገወጥ ድርጊት ላይ መሰማራት፣ በተለይ ከቀበሌ አንስቶ ባሉ የመንግሥት አካላት እየተስተዋለ ነው፡፡ እንዲያውም ‹‹ሕጋዊ›› እየመሰለ የመጣው ከፍተኛ ጉቦ ከፍሎ የካርታውን ሕጋዊነት ማረጋገጥ ወይም ከራሱ ከአንዳንዱ ሕገወጥ የሥራ መሪ ቦታን መግዛት ሆኗል፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ማስተር ፕላን ከዋና ከተማዋ ጋር አስተሳስሮ አገርና ሕዝብ የሚጠቀምበትን መላ በመዘየድ ረገድ የተጀመረውን የሠለጠነ አሠራርና የብዙ ዓለም አቀፍ ከተሞች ባህሪ የተቃወመው ማን ነበር? ብሎ መጠየቅ የሚገባው ይኼኔ ነው፡፡ መሬትን በፖለቲካ መሣሪያነት ስም ለግል ጥቅም የማዋሉ ሩጫስ የነማን ፍላጎት ያለበት ነው?  ተብሎ ሊመረመር ይገባዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሕገወጥ ወረራ አሁን የሕዝብ መሬትን ማጠር አለ፡፡ በአንዳንድ ሕገወጥ የመንግሥት ኃላፊዎች ‹‹አይዞህ ባይነት›› ሌላው ቀርቶ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዳርቻ እንኳን እየታየ ነው፡፡ በጀሞ ቁጥር ሁለትና ሦስት ባሉ ሰፋፊ ቦታዎች ያን ሁሉ አጣና ሻጭ፣ ሕገወጥ ከሰል አዘዋዋሪና በጊዜያዊ ሱቆች የግንባታ ዕቃዎች ሽያጭ ማን ነው ያሰፈረው? ተደራጅቶ በመሥራት ስም የተሽከርካሪ ማጠቢያ፣ መጠገኛ፣ የብረታ ብረት መሥሪያና እንጨት ሥራ፣ ወዘተ ቦታዎች በመያዝ ‹‹የዘለዓለም ሀብቴ ነው›› ለማለት የሚያቋምጥ ጥገኛስ እውን እንዲታረም እየተደረገ ነው?

መሬት የሕዝብ ሀብት ነው ሲባል በፍፁም ጥቂቶች እንዲበለፅጉበት አይደለም፡፡ በመንግሥት ኃላፊነት ስም ሕዝብ አደራ ብሎ የሾማቸው እንዲባልጉበትም ሊሆን አይገባም፡፡ ራሱ መንግሥትም ቢሆን ያለቅጥ የመሬትን ዋጋ እያናረና የሕዝብነቱን ባህሪ እንዲያሳጠው አይደለም፡፡ ምንም እንኳን መሬት የተሸጠበት ሀብት ለልማት የሚውል መሆኑ ባይዘነጋም፣ መሬት በግልጽነትና በተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን በፍትሐዊነት የሕዝብ እሴት (Value) መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባዋል፡፡ በዚህ ረገድ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብር አንዱ መልካም ጅምር ሆኖ በሁሉም መስክ ተሳስሮ ሊታይ የግድ ነው፡፡

ለማጠቃለል ሲሞከር

የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወደ መጠቃለሉ ገደማ ነው፡፡ ግምገማው ተጠናቆ ይፋ ባይደረግም አብዛኛው የፕሮጀክት አፈጻጸም (መንገድ፣ ባቡር፣ ግብርና፣ ትምህርትና ጤና) በከፊል የተሳኩ ይመስላሉ፡፡ ግፋ ቢል የአንዳንድ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መዘግየት ቢኖርም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የስኳር፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የመስኖ ፕሮጀክቶች፣ ወዘተ ጥሩ ሄደዋል፡፡

የእነዚህን ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከሙስናና ብልሹ አሠራርስ ምን ያህል ተከላክለናል?  በዘርፉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲዳብር ምን ተሠራ?  እንዴት ባለ ሁኔታስ ለቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትምህርት ወስደን እንቀጥላለን? መባልም አለበት፡፡ ትልቅ ልማትና ዕድገት ሲታቀድ ተከትሎ የሚመጣውን ጥፋትና አጥፊ (መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢ ይለዋል) በግልጽ መርህ መመከት ካልተቻለ፣ ከዕድገቱ እኩል ባልተናነሰ ቱባ ሌቦችን ከማፍራት መዳን አይቻልም፡፡ ሄዶ ሄዶ ዕድገቱም ኢፍትሐዊነትን ያሰፍንና ጥገኝነት የበላይነት ሊያገኝ ይችላል፡፡ ስለሆነም ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) ሲታሰብ የፀረ ሙስና ትግሉም አንድና ሁለት ደረጃ ከፍ ማለት አለበት ለማለት እወዳለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...