Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያገኘነው መልዕክት የአውሮፓ ኅብረት ምርጫውን እንዲታዘብ ኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሌላት ነው››

ግሬግ ዶሪ፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ሲሆኑ፣ በተጨማሪም በጂቡቲ የእንግሊዝ አምባሳደር ናቸው፡፡ በአፍሪካ ኅብረትና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ቋሚ ተወካይም ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በሃንጋሪ የእንግሊዝ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1989 እስከ 1992 ድረስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች አንደኛ ጸሐፊ በመሆንም በሃንጋሪ ታሪክ ብዙ እንቅስቃሴ የተደረገባቸውን ዓመታት በቅርበት ተከታትለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1996 እስከ 2000 ድረስ በፓኪስታን፣ እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ በሆንግ ኮንግ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አምባሳደር ዶሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እ.ኤ.አ. በ2011 ነው፡፡ አሥራት ስዩም በቅርቡ የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መያዝና የእስር ሁኔታ፣ እንዲሁም የእንግሊዝ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አምባሳደር ግሬግ ዶሪን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በኢትዮጵያ የተካሄደውንና ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፓርላማውን ሁሉንም ወንበሮች ያሸነፉበትን ምርጫ እንዴት አዩት? ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ነው ብለው ይገልጹታል?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- በቅድሚያ ምርጫውን መታዘብ አለመቻላችን አሳዛኝ ነው፡፡ በምርጫ 97 እና በምርጫ 2002 ታዛቢ የነበረው የአውሮፓ ኅብረት ምርጫ 2007ን እንዲታዘብ አልተጋበዘም፡፡ የታዛቢ ልዑካን መላክ ከነበረብን ግብዣ ሊደርሰንና መንግሥት እንደሚተባበረን ማሳየት ነበረበት፡፡ መንግሥት የአውሮፓ ኅብረት ምርጫውን እንዳይታዘብ እንደሚፈልግ በግልጽ አሳይቷል፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ዲፕሎማቶችም ምርጫውን እንዳይታዘቡ ተከልክለዋል፡፡ ይሁንና የአፍሪካ ኅብረት የታዛቢዎች ልዑክ ውስጥ ዲፕሎማቶች እንዲካተቱ መደረጉን እናውቃለን፡፡ እኔ በግሌ በተለያዩ ቦታዎች ምርጫዎችን ታዝቤያለሁ፡፡ ከእነዚህም አንዱ በፓኪስታን ሩቅና ገጠራማ አካባቢ የተደረገው አንዱ ነው፡፡ አሁን ግን ባለመታዘባችን በምርጫው ምን እንደተከሰተ በቀጥታ መረጃው የለኝም፡፡ ውጤቱ በይፋ ሲገለጽ ጠብቀን አስተያየታችንን እንሰጣለን (ቃለ ምልልሱ ሲደረግ ውጤቱ በይፋ አልተገለጸም ነበር)፡፡ ከዚህ ውጪ ከምርጫው አስቀድሞ በነበረው የፖለቲካ ምኅዳር መጣበብ ላይ ግን ሥጋት ነበረን፡፡ አሁን ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ መቶ በመቶ ፓርላማውን እንደሚቆጣጠሩ እየተሰማን ነው፡፡ በእኔ አስተያየት ይኼ ለዴሞክራሲ ጥሩ ነገር አይደለም፡፡ ይኼ እንደ ሰሜን ኮሪያ ባሉ አገሮች የሚከሰት ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፓርላማ የተለያዩ አመለካከቶች ቢንሸራሸሩ ጥሩ ነበር፡፡

ይህ ማለት ግን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ልማትን በተመለከተ እየሠራ ያለው ነገር መጥፎ ነው ማለት አይደለም፡፡ ልማት ላይ በአጠቃላይ ጥሩ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ግን ጤናማ የሚሆነው የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦች ሲቀርቡ ነው፡፡ ባለፈው ፓርላማም ቢሆን ከ547 ወንበሮች ተቃዋሚዎች የተወከሉት በአንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑ በቂ አይደለም፡፡ ወደፊት ፓርላማው ብዛት ያላቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ቢያቅፍ ኢትዮጵያ እያደገችና የዓለም አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አባል ለመሆኗ ምልክት ይሆናል፡፡ በምርጫ ታዛቢ ስላልነበርን ስለተከሰቱ ግድፈቶች አስተያየት ለመስጠት አልችልም፡፡ ገዥው ፓርቲ መቶ በመቶ የፓርላማውን መቀመጫ የሚያሸንፍ ከሆነ፣ ድምፃቸውን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የሰጡ ዜጎች አገሪቱ እየሄደች ባለችበት አቅጣጫ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ሊሰማ ይገባል፡፡ በርካታ ዜጎች ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፃቸውን እንደሰጡ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ድምፃቸው እስከ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካላት ድረስ ሊሰማ ይገባል፡፡ ይኼ በአገሪቱ ዘላቂ መረጋጋት ለማምጣት ጠቃሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት የሚለው የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ልዑክ እንዲልክ ግብዣ ያልላከው ኅብረቱ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት በመግለጹ ነው፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- በዚህ ዓመት በአፍሪካ ብቻ 17 ወይም 18 ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በትክክልም ሁሉንም ምርጫዎች ለመታዘብ የገንዘብ እጥረት አለብን፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህን ለመወሰን ግብዣ ስላልደረሰን ዕድሉንም አላገኘንም፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማቀድ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያገኘነው መልዕክት የአውሮፓ ኅብረት ምርጫውን እንዲታዘብ ኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሌላት ነው፡፡ ለዚህም ነው ያለንን ሀብት ለሌሎች ምርጫዎች ለማዋል ያቀድነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ መንግሥት በጣም አቅሎ በሚያምታታ ሁኔታ እንደገለጸው አይደለም፡፡ የተወሳሰበ ነው፡፡ ውሳኔያችን የተመሠረተው በገንዘብ እጥረት አልነበረም፡፡ ከምርጫ 97 እና ከምርጫ 2002 በኋላ የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የተለያዩ የማሻሻያ ሐሳቦችን ሰጥቶ ነበር፡፡ መንግሥት በጠቅላላ ሐሳቦቹን ውድቅ አድርጓል፡፡ እርግጥ ነው ምርጫ ያካሄደው አገር ሐሳቦችህን የማይቀበል ሲሆን፣ ከሌሎች የአውሮፓ ኅብረትን መታዘብ ጠቃሚነት የተቀበሉ አገሮች ጋር ለመሥራት ማሰብ አይቀርም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት ለመቀየር ያደረጉትን አስተዋጽኦ እንዴት አዩት? የፖለቲካ ተንታኞች ከምርጫ 97 ጋር ሲነፃፀር ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተከፋፈሉና ደካማ በመሆናቸው ለተገኘው ውጤት ተጠያቂ እንደሆኑ ይከራከራሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት እንዴት ነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- ይኼ በትክክልም የችግሩ አንድ አካል ነው፡፡ ሌላው ችግር የምርጫ ሥርዓቱ የሚከተለው የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡ እርግጥ ይህ ሥርዓት በእንግሊዝም ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ለተቃዋሚዎች የተሰጡ በርካታ ድምፆች ወደ ፓርላማ መቀመጫ አይቀየሩም፡፡ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ግን ይህን ያስችል ነበር፡፡ ነገር ግን እንደተባለው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተከፋፈሉ መሆናቸውንም ተመልክቻለሁ፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ዓመታት ጉዳዩን እንደገና ሊመለከቱትና አብረው መሥራታቸው ውጤቱን የሚያሻሽለው ከሆነ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ፓርቲዎች በበዙ ቁጥር የመራጮችን ድምፅ ስለሚቀራመቱ የተሻለ ውጤት የማግኘት ዕድላቸውን ያጠባል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተስማሚ አይደለም እያሉ ነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- የትኛው ሥርዓት ይሻላል የሚለውን የመወሰን ሥልጣን የአገሮቹ ነው፡፡ ሥርዓቱን እስከመረጥክ ድረስ አክብሮ መሥራትም ይጠበቅብሃል፡፡ አንድን ቡድን ተጠቃሚ ለማድረግ ሥርዓት መቀየር የለብህም፡፡ ይሁንና በአንድም ሆነ በሌላ የተለያዩ ሐሳቦች እንዲሰሙ ግን ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልተፈጠረ ለአገር አለመረጋጋት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ይኼን የምርጫ ሥርዓት ትቀበል ለማለት አልችልም፡፡ መንግሥት የተለያዩ ሐሳቦችንና አመለካከቶችን ለማስተናገድ መንገድ መፈለግ ግን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት መንግሥትዎ ለደኅንነትና ለአስተዳደር መድቦት የነበረውን የገንዘብ ዕርዳታ ወደ ሌሎች ፕሮግራሞች አዘዋውሯል፡፡ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር መሥሪያ ቤት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያ ላይ ባቀረበው ሪፖርትና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታሰር ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር መሥሪያ ቤት ፕሮግራሞች የሚመሠረቱት ሰብዓዊ መብትን ጨምሮ ከአገሮቹ ጋር ባለን የሁለትዮሽ የአጋርነት ግንኙነት መርህ እንጂ፣ በግለሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ከመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ፕሮግራም በመውጣት ይበልጥ ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ያተኮሩ እንቅስቃሴዎችን የመደገፍ የቆየ ሐሳብ ነበረው፡፡ ምክንያቱም ይኼ ዘለቄታዊ ለውጥ ለማምጣት ይበልጥ ዋጋ አለው፡፡ ውሳኔው ከዚህ ሐሳብ የመነጨ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባለው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች አፈጻጸም ላይ ያለን ሥጋት እዚህ ውሳኔ ላይ እንድንደርስ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን ውሳኔያችንን ያፋጠኑ ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ አንዳርጋቸው የእንግሊዝ ዜጋ በመሆናቸው መንግሥትዎ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የግለሰቡን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲያደርግ ነበር፡፡ አሁን አቶ አንዳርጋቸው በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- በመጀመሪያ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ላይ ለመናገር በጣም የተገደብኩ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ለአቶ አንዳርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ዕርዳታ እያደረግን ሲሆን፣ ከቤተሰባቸውም ጋር ቅርብ ግንኙነት አለን፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ዕርዳታችን ላይ ስላሉ ዝርዝር ጉዳዮች አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ለቤተሰቡ ያልተገለጸን ነገር ለሌላ አካል መናገር ስለማያስፈልግ ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ከተያዙ በኋላ ሦስት ጊዜ አይቻቸዋለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ምን ማለት እችላለሁ? በተገቢው ሁኔታ ስለመያዛቸው ለማረጋገጥ አልቻልንም፡፡ የዲፕሎማሲያዊ ጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማም ይኼው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የሚገዛውን የቪየና ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ አይደለችም፡፡ ለምን እንዳልፈረመች ባይገባኝም አንድ ቀን ፈራሚ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሁንና የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ፈራሚ በመሆኗ፣ የእስረኞች አያያዝን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ደረጃ የማሟላት ግዴታ አለባት፡፡  

ሪፖርተር፡- ነገር ግን አቶ አንዳርጋቸው የእንግሊዝ ዜጋ በመሆናቸው እንግሊዝ በእሳቸው አያያዝ ላይ ልዩ ፍላጎት የላትም?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- አንድ የእንግሊዝ ዜጋ ውጭ አገር ሲታሰር ሥጋቶችና ልዩ ግዴታዎች አሉብን፡፡ የእንግሊዝ ሕዝብ እነዚህ ዜጎች በአግባቡና ዓለም አቀፍ መሥፈርቱን በጠበቀ መንገድ መያዛቸውን እንድናረጋግጥ ይጠብቃል፡፡ ከዚህ ውጪ በአጠቃላይ በሰብዓዊ መብት ላይ ሥጋት አለኝ፡፡ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት እንቅስቃሴ ላይ እንሳተፋለን፡፡ ስለዚህ በሌላ አገር ዜጎች የእስር አያያዝ ላይ ችግር ካለ እሱም ቢሆን ያሠጋናል፡፡ ሥጋቶቻችን የምንገልጸው መሠረታዊ መሥፈርቶች እንዳልተሟሉ ስናስብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለአቶ አንዳርጋቸው እነዚህ መሠረታዊ መሥፈርቶች እንደተሟሉላቸው መናገር ይቻላል? በተገቢው ሁኔታ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ለመናገር ገደብ ስላለብኝ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንግሊዝ ለዜጋዋ ያልታገለችው አቶ አንዳርጋቸው በነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ የተነሳ አማራጭ ስላልነበራት ነው ይላሉ፡፡ የአቶ አንዳርጋቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ፈጥሮባችኋል?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- በአጠቃላይ አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ከመያዛቸው በፊት ምን እየሠሩ እንደነበር አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ይኼ ጉዳይ ወደ ችሎት ሊያመራ ስለሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት አቶ አንዳርጋቸው ይሠሩ ከነበረው ነገር ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ምንም አደረጉ ምንም ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት አይነፈጉም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ዜጎቻችሁ በከባድ የወንጀል ድርጊት የሽብር እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ መጠርጠራቸው በአቀራረባችሁ ላይ ምንም ልዩነት አያመጣም እያሉኝ ነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡-ዜጋውን ከመጎብኘት፣ የጤና ሁኔታውን ከመከታተልና ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ፍላጎቶች መሟላታቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ግለሰቡ የሠራው ሥራ ቅንጣት ልዩነት አያመጣም፡፡ ከዚያ በተረፈ በየትኛውም ሁኔታ የሞት ቅጣትን እንቃወማለን፡፡ የሞት ቅጣት ተግባራዊ የሚያደርጉ አገሮችን እንቃወማለን፡፡ የሞት ቅጣት ምንም ዓይነት ጥሩ የሆነ የሚያሳካው ዓላማ አለው ብለን አናምንም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ አሜሪካ በኢትዮጵያ ፓርላማ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ቡድኖችን እንደምትቃወም በአደባባይ ገልጻለች፡፡ ከእነዚህ አንዱ አቶ አንዳርጋቸው አባል የነበሩበት ግንቦት ሰባት ነው፡፡ በእነዚህ ድርጅቶች ላይ የእንግሊዝ አቋም ምንድን ነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- አባባሉን በትክክል ስለማየቴ እርግጠኛ አይደለሁም….

ሪፖርተር፡- ይኼንን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ዊንዲ ሼርማን በቅርቡ ከሰጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል ብዬ ነው…

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- ዊንዲ ሼርማን አሜሪካ ግንቦት ሰባትን አትደግፍም ነው ያሉት፡፡ ይኼን እኔም አረጋግጥልሃለሁ፡፡ ግንቦት ሰባትንም ሆነ መሰል ቡድኖችን እንግሊዝ አትደግፍም፡፡ ነገር ግን እንግሊዝ ግንቦት ሰባትን በሽብርተኝነት አልፈረጀችም፡፡ ምክንያቱም በእንግሊዝ ዓውድ አንድን ቡድን ሽብርተኛ ብሎ ለመፈረጅ የሚያስችል ማስረጃ አላየንም፡፡ ቢሆንም ሕጋዊ መንግሥትን ለመገርሰስ የሚሠራ ማንኛውንም ቡድን አንደግፍም፡፡ የዊንዲ ሼርማን መግለጫ በተለያዩ ሚዲያዎች በትክክል እንዳልተንፀባረቀ ግን እረዳለሁ፡፡ በትክክል ምን እንዳሉ አላውቅም፡፡ በጉዳዩ ላይ አሜሪካ ያላት ፖሊሲ ግን ከእንግሊዝ ፖሊሲ መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለው ግን አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት እንግሊዝ ለኢትዮጵያ በሰጠችው የዕርዳታ መጠን ተቀዳሚዋ አገር ነች፡፡ ነገር ግን ይኼ እያደጉ ያሉ እንደ ቻይናና ቱርክ ካሉ ኢኮኖሚዎች ጋር ሲነፃፀር በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች በሚደረግ ተሳትፎ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ይህን ያላደረገችው ለምንድነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- በመጀመርያ ደረጃ የልማት ድጋፍ የምናደርገው ሌሎቹ አገሮች እንደሚያደርጉት የእንግሊዝን ቢዝነስ ለማስፋፋት አይደለም፡፡ ዕርዳታውን በሚቀበሉ አገሮች የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታው በአጠቃላይ እንዲሻሻል ለማገዝ እንጥራለን፡፡ ይሁንና እኛ በምናደርገው ዕርዳታ የተነሳ የእንግሊዝ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ መንግሥት የፕሮጀክት ኮንትራቶች እንዲያገኙ አናደርግም፡፡ እርግጥ አንዳንድ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ጋር ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከአምስትና ከስድስት ዓመት በፊት ግን እንግሊዝ በኢትዮጵያ የነበራት የኢንቨስትመንት መጠን አነስተኛ በመሆኑ ላይ እስማማለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን በከፍተኛ መጠን ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡ አሁን እንደ ዲያጆና ዩኒሊቨር ያሉ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ገበያ ተቀላቅለዋል፡፡ አስፈላጊው የሕግ ማዕቀፍ ከተጠናቀቀ በታዳሽ ኢነርጂ ላይ የመሥራት ፍላጎት ያላቸው በርካታ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡

በነዳጅ ፍለጋና በማዕድን ማውጣት ዘርፎች ላይ ብዙ ካፒታል ፈሰስ ያደጉ የእንግሊዝ ኩባንያዎችም ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስኬት እንደሚያስመዘግቡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቡናና የምግብ ምርቶችን ከኢትዮጵያ የሚገዙ ታዋቂ የእንግሊዝ ኩባንያዎችም ይመጣሉ፡፡ ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎችም እንዲመጡ ለመሳብ እየጣርን ነው፡፡ እርግጥ እነዚህ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን በአፅንኦት ማየትና አስቀድመው ገበያው ውስጥ የገቡ ኩባንያዎች እንዴት እየተስተናገዱ እንደሆነ ይገመግማሉ፡፡ አስቀድመው ገበያው ውስጥ የገቡ የእንግሊዝ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብሩህ ተስፋ አለው ብለው ያምናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ገበያ በዓለም ላይ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ቢገነዘቡም፣ በትዕግሥት በረዥም ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ዝግጁ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የእንግሊዝ ኢንቨስትመንት ወደፊት እያደገ እንደሚመጣ ታያላችሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የእንግሊዝ ኩባንያዎች እያደገ የመጣውን የአፍሪካ ገበያ እንዴት ያዩታል? በርካታ ተሳታፊዎች ስላሉ ይህ የአፍሪካ ገበያ ቀጣዩ የውድድር ቀጣና ይሆናል ብለው ይወስዱታል?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- አዎ በዚያ ደረጃ መረዳት ይቻላል፡፡ በታሪክም ከታየ እንግሊዝ በአፍሪካ አኅጉር ቀዳሚ ኢንቨስተር ነች፡፡ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ከተመለከትን ግን ከአዳዲሶቹ ኢንቨስተሮች ከነ ቻይና፣ ቱርክና ህንድ ጋር ሲነፃፀር የእንግሊዝ ድርሻ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ አፍሪካ የወደፊቱ የዕድገት ማዕከል ስለሚሆን ፍላጎት አለን፡፡ አንዳንዴ ከሌሎች አገሮች ጋር እንደምንወዳደር ይታየናል፡፡ በሌላ በኩል ግን ከሌሎች አገሮችና ከኩባንያዎቻቸው ጋር አብረን እንደምንሠራ እናስባለን፡፡ በኢትዮጵያ ግን ለውድድር አልደረስንም፡፡ በቂ ዕድሎች አሁንም አሉ፡፡ ከሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ጋር በትብብር ለመሥራት እያሰብን ነው፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ እንደሚሳካ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ ቁጥጥርን በተመለከተና በሌሎችም ጉዳዮች ለውጥና መሻሻል የሚያስፈልጋቸው የትኞቹ ናቸው ብላችሁ ታስባላችሁ?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- የእንግሊዝ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኩባንያዎች ቢሮክራሲውን ለማለፍ ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ፡፡ ይኼ ውድ ጊዜ ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለማስፋትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማቀላጠፍ ጥቅም ቢውል መልካም ነበር፡፡ ኢኮኖሚው ጤነኛ እንዲሆን የሕግ ቁጥጥር መደረጉ ተገቢ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይኼ ቁጥጥር ሁሉም በቀላሉ የሚረዳው ግልጽ የሆነ ሥርዓት ለመፍጠር ይረዳል፡፡ ነገር ግን የቁጥጥር ሥርዓቱ በተቻለ መጠን ቀላል ቢሆን ይመረጣል፡፡ በእኔ አረዳድ የኢትዮጵያ የቁጥጥር ሥርዓት ከመጠን ያለፈ ነው፡፡ አንዳንድ ድንጋጌዎች መንግሥትንም፣ ኢንቨስትመንትንም ሆነ ሕዝቡን በአጠቃላይ የሚጠቅሙ አይደሉም፡፡ አንድ አካል እነዚህን ድንጋጌዎች በድጋሚ በማየት የትኞቹ ጠቃሚ እንደሆኑና የትኞቹ እንደማያስፈልጉ የመለየት ሥራ የሚያከናውን ይመስለኛል፡፡ አዳዲስ ድንጋጌዎች ሲወጡም በቢዝነስ ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ተፅዕኖ የግድ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ አንዳንድ ደንቦች በቢዝነስ ዕድገት ላይ ጫና እየፈጠሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቪዛና የጉዞ ደንቦች እዚህ ውስጥ ይካተታሉ? በቅርቡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት ኃላፊዎች ቅሬታ ማቅረብዎ ተዘግቧል፡፡

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- የእንግሊዝ የቪዛ ሒደት በዓለም ላይ ቀላሉ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ግልጽነት ያለው መሆኑ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በሒደቱ ላይ ለውጥ የምናደርግ ከሆነ ለውጡን አስቀድመን የምናስተዋውቅ ሲሆን፣ ሰዎችም ተረድተው በአዲሱ አሠራር እንዲስተናገዱ እናደርጋለን፡፡ ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ቪዛ የሚጠይቁ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ማመልከቻውን በትክክል የሞሉና ትክክለኛ መረጃ ያቀረቡ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ሌሎች በርካታ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንግሊዝ ከሄዱ በኋላ ስለማይመለሱ ቪዛ የማያገኙ ሰዎችም አሉ፡፡ ሰነዶቻቸውን አጥፍተው ከተፈቀደው ጊዜ በላይ የሚቆዩ አሉ፡፡ ስለዚህ ቪዛ ከመስጠታችን በፊት ጠንካራ ቁጥጥር ማድረጋችን ፖለቲካዊ ተቀባይነት አለው፡፡ ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ነገር በድንገት የቪዛ ሒደቱ የሚያስወጣው ወጪ ከመጨመሩ ይጀምራል፡፡ ወጪው በመጨመሩ ላይ ይኼን ያህል ችግር የለብኝም፡፡

ነገር ግን አዳዲሶቹ ደንቦችና መመርያዎች ግልጽ ስላልነበሩ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ዜጎቻችን በተለያዩ መንገዶች ነው የተረዷቸው፡፡ በድንገት ለቢዝነስ ሰዎች ይሰጥ የነበረው የሦስት ወራት ቪዛ ወደ አንድ ወር ቪዛ ተቀየረ፡፡ በተጨማሪ የቪዛ ማመልከቻው ቀን የቪዛ ቀን ተደርጎም ተወሰደ፡፡ በመሆኑም እዚህ በመጡ በቀናት ጊዜ ውስጥ መመለስ አለባቸው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ለምትጥር አገር ይኼ ችግር ፈጣሪ ነው፡፡ በዚህ ላይ እንግሊዝ ዲፕሎማሲያዊ ፓስፖርት ለእያንዳንዱ ሰው የምትሰጥ አገር አይደለችም፡፡ ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻችንና የፓርላማ አባሎቻችን ዲፕሎማሲያዊ ፓስፖርት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ባለሥልጣኖቻችንም ለሥራ ሲመጡ በእነዚህ ግራ አጋቢ የቪዛ ደንቦች የተነሳ ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይኼ ችግር እንደሚቀረፍና ወደፊት ለቢዝነስ በተመቸ አኳኋን እንደሚስተካከል ቃል ገብተውልናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባትም በአፍሪካ አኅጉር የመጀመሪያው ኤምባሲ የሆነው የእንግሊዝ ኤምባሲ የቪዛ ማዕከሉን ወደ ደቡብ አፍሪካ አዛውሯል፡፡ የውሳኔው አመክዮ ምንድነው?

አምባሳደር ግሬግ ዶሪ፡- በከፊል ከወጪና ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቪዛ ሒደቱን በየአገሮች ከማድረግ በማዕከል ለመሥራት ወስነናል፡፡ በአፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ብቻ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በኢንተርኔት ማመልከቻ የሞሉ ሰዎች ፓስፖርት የሚሰጡበት ማዕከል አለን፡፡ ነገር ግን ፓስፖርቱ ፕሪቶሪያ ሄዶ መመለስ አለበት፡፡ በመደበኛው አሠራር ይኼ እስከ ሦስት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል፡፡ ይኼ የአሠራር ለውጥ ከኢትዮጵያ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ በመላው ዓለም አሠራራችንን በማዕከል ለማድረግ ስለወሰንን ብቻ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...