ከኦሎምፒያ ወደ አጎና ሲኒማ በሚወስደው መንገድ ግራና ቀኝ የተለያዩ የንግድና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በብዛት ይታያሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሞቅ ያለ ቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከአነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች ጀምሮ እስከ ባለኮከብ ሆቴሎችና ትላልቅ የሚባሉ የአንዳንድ ኩባንያዎች ዋና መሥሪያ ቤቶች የሚገኙበት ነው፡፡
በአካባቢው ያለውን የቢዝነስ እንቅስቃሴ ተመልክተው ከስድስት በላይ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተዋል፡፡ ማተሚያ ቤቶች፣ ታዋቂ ክትፎ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ የቀበሌ መዝናኛ፣ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎኖች ሳይቀር በዚህ መንገድ ግራና ቀኝ በጉልህ ይታያሉ፡፡ ለተለያዩ አገልግሎት የታነፁ ሕንፃዎች ውስጥም በርካታ ድርጀቶች ተከራይተው ይሠራሉ፡፡ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች መሸጫዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ፋርማሲዎችና የመሳሰሉት የንግድ ድርጅቶች በዚህ መንገድ ይታያሉ፡፡
ቀን ቀን ገርበብ ብለው ምሽት ላይ ሞቅ ያሉ ሙዚቃ የሚሰማባቸው፤ በኅብረ ቀለም በተቆጠቆጡ መብራቶች ብልጭ ድርግም የሚሉባቸው ሌሊቱን ድረስ የሚዘልቁ አነስተኛ ባሮች የዚህ መስመር መለያ ናቸው፡፡
አካባቢው ድብልቅ ቢዝነሶች የሚታዩበት በዋና ጎዳናው ላይ ብቻ ሳይሆን አውራ ጎዳናውን በሚመግቡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዳርቻ ጭምር የደራ ቢዝነስ ያለ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡
ከአምስት ወራት ወዲህ ግን የዚህ አካባቢ ቢዝነስ ተቀዛቅዟል፡፡ ወደ ኪሳራ እያመራንም ነው ያሉ ነጋዴዎችንም ፈጥሯል፡፡ በአካባቢው ያሉ አንዳንድ ነጋዴዎች እንደሚገልጹትም በቢዝነሳቸው መቀዛቀዝ ሥራቸውን ወደ ሌላ ሥፍራ ያዛወሩም አሉ፡፡ በዚህ አካባቢ ከአምስት ወራት ወዲህ የቀድሞ የቢዝነስ እንቅስቃሴው መስተጓጎል ምክንያት ደግሞ ከመስቀል ፍላወር ወደ አጎና ከሚወስደው መንገድ ውስጥ የተወሰነውን ክፍል ለመገንባት የተጀመረው የመንገድ ግንባታ ሥራ ዳር ሊደርስ ባለመቻሉ ነው፡፡
መንገዱን ለመገንባት የተጀመረው ቁፋሮ ወደ ዋናው የመንገድ ግንባታ ሳይገባ መቋረጡ በዚያ አካባቢ ያሉ የንግድ ድርጅቶች ከደንበኞቻቸው ጋር እንዳይገናኙ በማድረግ ለአካባቢው ቢዝነስ መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ መንገዱን ለመገንባት ከአምስት ወራት በፊት የተጀመረው ቁፋሮ ባልታወቀ ሁኔታ ሲቋረጥ፣ የተቆፋፈረውን መንገድ ተሻግሮ ግብይት የሚፈጽምና አገልግሎት ለማግኘት ይመጡ የነበሩ ደንበኞች መቀዛቀዝ ደግሞ ለቢዝነስ ድርጀቶቹ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡
መንገዱ መቆፋፈር ቢዝነሳቸውን ካወከባቸው የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች መካከል አንዱ ያስሚን የሸቀጣ ሸቀጥ ማከፋፈያ ነው፡፡ የመንገዱ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የሞቀ ገበያ የነበረው ይህ መደብር፣ ለመንገዱ ግንባታ ተብሎ የተወሰነ ይዞታው ቢፈርስም በቀሪው ሥፍራ ንግዱን መቀጠሉን የመደብሩ ባለቤት ይገልጻሉ፡፡ ከመደብሩ ፊት ለፊት ለመንገድ ግንባታ ተብሎ የተቆፈረው ሥፍራ ግን ባለመደፈኑ ገበያቸው ቀዝቅዟል፡፡ የቀድሞ ገበያቸውን ለመመለስ እንደ መፍትሔ የወሰዱት ሐሳብ መደብራቸውን ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ነው፡፡ ተለዋጭ መደብሩ እዚያው አካባቢ ካለ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ዳርቻ የተከፈተ ነው፡፡ አድራሻ ለውጡንም በትልቅ ማስታወቂያ ሰቅለው ሥራ ቢጀምሩም፣ አሁንም ይህ የተቆፋፈረው መንገድ ያሰቡትን ገበያ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡
ያስሚን ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ብቻ ሳይሆን ተጀምሮ የተቋረጠው የመንገድ ግንባታ ያወካቸው የንግድ ድርጅት ባለቤቶችም በተመሳሳይ ገበያቸው እንደተበላሸ ተናግረዋል፡፡ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች መሸጫ መደብሮች ደግሞ ገበያ ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን ገበያውን ካገኙ በኋላ ዕቃውን ለማስጫን አለመቻላቸው ነው፡፡
በሦስት ወራት ይጠናቀቃል የተባለው መንገድ እስካሁን ምንም ሳይሠራ ከሦስት ወራት በላይ በመቆየቱ ግራ መጋባታቸውን ይናገራሉ፡፡ እየተጎዳን ነው የሚሉት ነጋዴዎች፣ ቢዝነሳቸው ገበያ በማጣቱ ለአከራይ ለመክፈል የሚያስችል ሥራ እንኳን መሥራት አላስቻላቸውም፡፡
በመኪና አከራይና ሽያጭ ሥራ ላይ የተሰማሩት ነጋዴ ደግሞ የመንገዱ መቆፋፈር ሥራቸውን እንዳቀዘቀዘባቸው ተናግረዋል፡፡ በአንድ ወገን ሌላ በር የከፈቱ ቢሆንም ብዙ ለውጥ አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ በር በመስተናገድ ውስጥ ውስጡን መጓዝ ስለሚያስፈልግ ለደንበኞችም ሆነ ለድርጅቶቻቸው አመቺ አለመሆኑን ገልጸው፣ የመንገዱን መጠናቀው እየጓጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሌላው የውበት ሳሎን ባለቤት ደግሞ ደንበኞችዋ የተቆፋፈረውን መንገድ ተሻግረው ስለማይመጡ እያገኘች ያለችው ገቢ በእጅጉ መቀነሱን ነው፡፡ በቅድሚያ የከፈለችው የስድስት ወር ኪራይ እያለቀ ስለሆነ ቀጣዩ የስድስት ወር ክፍያ እንዴት እከፍለዋለሁ የሚለው ጉዳይ እንዳሳሰባትም ገልጻለች፡፡
የብዙዎችን ቢዝነስ እያስተጓጎለ ያለው የመንገድ ግንባታ ተጀምሮ መቋረጡ ትክክል መሆኑን ያስታወሱት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈቃደ ኃይሌ፣ የተቋረጠው የመንገድ ሥራ ባለፈው ሳምንት መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡
በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች ግን የመንገዱ ሥራ ሰሞኑን የተጀመረ ቢሆንም፣ እንደተባለው በሦስት ወራት ያልቃል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የሥራው ሒደትም እጅግ አዝጋሚ መሆኑን በምሬት በመግለጽ ጉዳታችን ይቀጥላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡
የያስሚን ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ባለቤትም ይህንን ሐሳብ ያጠናክራሉ፡፡ አሁንም መንገዱ በፍጥነት የማይሠራ ከሆነ ብዙዎች እየከሰሩ መዝለቃቸው አይቀርም ይላሉ፡፡ በአካባቢው ካሉ ባለኮከብ ሆቴሎችም እንደ ቀድሞዎቹ እየተንቀሳቀሱ አይደለም፡፡ የቀድሞ ገበያቸው አሁን የለም፡፡ ተሽከርካሪ ይዘው ወደ ሥፍራው ይመጡ የነበሩ ደንበኞች የተቆፈረው መንገድ አሰናክሏቸዋል፡፡ ችግሩን ተረድተው የሚመጡትም ቢሆኑ ውስጥ ለውስጥ መጓዝ አለባቸው፡፡ ይህም ለደንበኞች ያልተመቸ ስለሆነ የመንገዱን መጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
በመኪና ኪራይና ሽያጭ ላይ የተሰማሩት አስተያየት ሰጪ ደግሞ ችግሩ ቀጣይ ይሆናል ብለው የገመቱት በክረምት ዝናብ ሰበብ እንደገና ሥራው ሊቋረጥ ይችላል የሚል ሥጋት አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለብዙዎቹ አደጋ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ካልተገነባ ቀድሞስ ለምን ይጀመራል? የሚል አስተያየት የሰጡም አሉ፡፡ ለመንገዱ ሥራ ተብሎ የተወሰነ ይዞታቸውን በአስቸኳይ እንዲፈርሱ ሲገደዱ መንገዱ በሦስት ወራት ተገንብቶ እንደሚያልቅ ተነግሯቸው፤ ለግንባታው ምቹ ሁኔታዎችን ቢፈጥሩም አለማለቁ አሳስቦናልም ይላሉ፡፡
የመኪና ኪራይና ሻጩ ባለቤት እንደገለጹትም ‹‹ልማት ነውና ሦስት ወራት መታገስ አያቅትም ነበር፡፡ የግንባታው መጠናቀቅ የተሻለ ሥራ ስለሚፈጥርም ልማቱን እንፈልጋለን፤›› ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እንደተባለው እየተሠራ ባለመሆኑ ማዘናቸውን ይገልጻሉ፡፡
በዚህ መንገድ ግንባታ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈቃደ ከወራት በፊት ተጀምሮ የተቋረጠው መንገድ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ችግር ነው፡፡ አሁን ግን ችግሩ በመወገዱ ባለፈው ሳምንት ሥራው የተጀመረ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ሥራው ተጠናቆ መንገዱ ለአገልግሎት ይበቃል የሚል እምነት አላቸው፡፡