የመጀመርያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተገባዷል፡፡ በመሆኑም ተተኪው የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከሕዝቡ አስፈላጊውን ሐሳብ በማሰባሰብ ወደ ሥራ እንደሚገባ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ይገልጻሉ፡፡
በመላ አገሪቱ ከሰኔ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተገልጿል፡፡ አብዛኛዎቹ ክልሎችም ከዚሁ ዕለት ጀምረው ውይይት ያካሂዳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጋምቤላ፣ የደቡብ፣ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ውይይት ደግሞ ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጀምራል፡፡ ትግራይ በቅርቡ የሚጀምር ሲሆን አፋር፣ ሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ሐምሌን አገባደው እንደሚጀምሩ አቶ ሬድዋን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ ውይይቶች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በየራሳቸው ፍላጎት ዙሪያ፣ በሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ዙሪያ ነፃ ሆነው መናገር እንዲችሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ ጉዳዮች ለማወያየት ሐሳብ አለን፤›› በማለት መነሻውን ገልጸዋል፡፡
አርብቶ አደር ያለባቸው ክልሎች በተለይም ኦሮሚያ አርሶ አደርና አርብቶ አደሩን በየራሳቸው የተለያዩ መድረኮች ላይ ለማወያየት መታቀዱንም አስረድተዋል፡፡ የአርብቶ አደር ልማት ላይ በተለይም የሚቀጥለው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንደኛው ትኩረት በእንስሳት ሀብት ላይ እመርታ ማምጣት እንደሆነ፣ ለዚህ ደግሞ አርብቶ አደሩ የእንስሳት ሀብት ምንጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሶማሌና በአፋር ክልል ራሳቸውን ችለው ከሚደረጉት መድረኮች በተጨማሪ፣ አርብቶ አደሮች በዛ ብለው በሚኙባቸው ክልሎች የአርብቶ አደር መድረኮች እንደሚኖሩም ተገልጿል፡፡
የአርሶ አደር መድረኮችም ራሳቸውን ችለው እስካሁን የመጣውን ለውጥ ታሳቢ አድርገው በቀጣይ ዕቅድ መምጣት ያለባቸው መሻሻሎች ላይ ከአርሶ አደሮች ጋር መግባባት እንዲቻል፣ በግብርናው ዘርፍ የሚመጣውን እመርታ ለማስቀጠል አርሶ አደሩ እስካሁን ከነበሩት ልምዶቹና በመንግሥት በኩልም ሲሰጥ ከነበረው ድጋፍ አንፃር በጥንካሬና በጉድለት የሚታዩትን ተወያይቶ የሚቀጥለው የተሳካ እንዲሆን፣ ሰፋ ያሉ መድረኮች እንደሚኖሩና ጠቀሜታቸውም ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ሌላኛው ከወጣቶችና ከሴቶች ጋር የሚደረገው የውይይት መድረክ ነው፡፡ ‹‹እንደሚታወቀው ባለፉት የፈጣን ዕድገታችን ዘመን በአብዛኛው ፍትሐዊ የሆነ ዕድገት ለማስመዝገብ ጥረት ተደርጓል፡፡ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍልም በላቀ ደረጃ በፍትሐዊነት በኢኮኖሚው መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ ለመፍጠር ነው የተሞከረው፤›› ያሉት አቶ ሬድዋን፣ ይህም ሆኖ ሴቶችና ወጣቶች አካባቢ አሁንም ተጨማሪ ጥረቶች እንደሚጠይቁ በግልጽ መለየቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሁለተኛው ዕቅድ የሴቶችና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጠናከርና ከእስካሁኑ አፈጻጸም የነበሩ ድክመትና ጥንካሬዎች በራሳቸው በሴቶችና በወጣቶች ተሳትፎ ለማጎልበት መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድም፣ ‹‹ከመንግሥት የሚጠበቀው ድጋፍ ላይ የተሟላ መግባባት እንዲፈጠር ለማድረግ ራሳቸውን የቻሉ መድረኮች ይካሄዳሉ፤›› በማለት ቀጣይ አቅጣጫን አመላክተዋል፡፡
በከተሞች በሚኖሩ መድረኮች ላይ ደግሞ ዋናው ትኩረት ቀደም ሲል የተጠቀሱት በተለይ የሴቶችና የወጣቶች መድረኮች እንዳሉ ሆነው፣ ጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም መካከለኛ አንቀሳቃሾች ናቸው፡፡ በእነዚህ መድረኮች የሚቀጥለው ዕቅድ አንዱ ማዕከል ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን ከማቀላጠፍ አንፃር ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ እንደሚያተኩሩ ተገልጿል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሰፋ ያለ መሠረት እንዲኖረው ከተፈለገ፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ የሚሸጋገሩትን በስፋት መደገፍና ማጎልበት ጠቃሚ ስለሚሆን በዚህ ረገድ እስካሁን ከነበረው ስኬት ልምዶች መቀመራቸው፣ በሒደቱ ላይ የነበሩ ማነቆዎችን በዝርዝር ከተዋናዮቹ ጋር በመወያየት ቀጣዩን ዕቅድ የተሳካ ለማድረግ የሚቻልባቸው መድረኮች በክልልም በከተማም እንደሚኖሩ ተጠቁሟል፡፡
የክልሎቹ መድረኮች በዚሁ ሁኔታ ከተጠናቀቁ በኋላ የአገር አቀፍ መድረክ እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ አገር አቀፍ መድረኮችም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተመሳሳይ መንገድ በተለያዩ ጊዜያት ያወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሲቪክ ማኅበራትም ራሳቸውን ችለው ውይይት እንደሚያካሂዱ ተገልጿል፡፡ በአገር አቀፉ መድረክ ላይ ትላልቅ ባለሀብቶችና የግሉ ዘርፍም በሚቀጥለው ዕቅድ ላይ እንደሚወያዩ አቶ ሬድዋን ጠቁመዋል፡፡
በሚቀጥለው ዕቅድ የግሉ ዘርፍ ሚና ይበልጥ እንዲጎለብት የሚፈለግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የግል ዘርፍ እስካሁን በነበሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የነበሩ ማነቆዎች ወደ ልማታዊነት እንዲለወጡ በሚደረገው ድጋፍ ውስጥ የነበሩ ጥረቶችም ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተነግሯል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ የነበሩ ማነቆዎችን በዝርዝር በመፈተሽ የሁለተኛው ዕቅድ መዋቅራዊ ሽግግርና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን በተለይ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ለማቀላጠፍ የመንግሥት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የግሉ ዘርፍ ግን እጅግ እየጎለበተ መምጣት ስላለበት በዚህ ረገድ ከግሉ ዘርፍ ጋር ራሱን የቻለ መድረክ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡
የተለያዩ የሲቪክ አደረጃጀቶች የሙያ ማኅበራትም እንደዚሁ በተደራጀ እንቅስቃሴያቸው ልማቱን ለማሳካት የሚያስችል ተግባር ለማከናወንና በተጠቃሚነትም ጉልህ ድርሻ ስላላቸው፣ ለእነዚህም ራሱን የቻለ መድረክ እንደሚፈጠር አስታውቀዋል፡፡
‹‹በተመሳሳይ በፌዴራል ደረጃ በሚኖሩ መድረኮች ላይ በተለያዩ መንገዶች ልማታችን ላይ በሚደረገው እገዛ ሰላማችን ለማስጠበቅ በምናደርገው ጥረት፣ ይበልጥ መግባባትን ከመፍጠር አንፃርም ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ማግባባትና ግልጽነት እንዲፈጠር ራሱን የቻለ መድረክ ተፈጥሮ ውይይት የሚካሄድበት ይሆናል፤›› በማለት አቶ ሬድዋን አብራርተዋል፡፡
በዚህ ረገድ የመጀመርያው ዕቅድ እንደ መነሻ የተዘጋጀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጨምሩት ግብዓት እንደሚኖር ተስፋ አድርገዋል፡፡ በአፈጻጸም ላይ የነበሩ ጉድለቶችን በማንጠርና በሒደቱ ላይ የነበሩ ጥንካሬዎችን አጉልቶ በመያዝም፣ በቀጣይ መጨመር አለባቸው ተብለው ከየማኅበረሰብ ክፍሉ በዕቅድ ውስጥ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች በመጠቆም ረገድም፣ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ጉልህ ድርሻ የሚኖረው በመሆኑ ሰፋ ያለ ተሳትፎ እንደሚኖር ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በእያንዳንዱ መድረክ ከየማኅበረሰቡ ጋር በሚደረገው ውይይት ላይ ከ500 እስከ 600 ተሳታፊዎች እንደሚኖሩ እንደሚጠበቅ፣ በእያንዳንዱ መድረክም በሁለት ቀናት እንዲወሰን ይፈለጋል፡፡ የመጀመርያው ቀን የመጀመርያውን ዕቅድ የሚገመግምበት ሲሆን፣ በዚህ ላይ ድክመትና ጥንካሬዎች ተቀምረው መግባባት ከተደረሰባቸው በኋላ የሁለተኛው ዕቅድ ሐሳቦች ደግሞ በሁለተኛነት ይቀርባሉ፡፡
የሁለተኛው ዕቅድ ሐሳቦች ከመጀመርያው የተወሰደውን ትምህርት በጥንካሬም በድክመትም የተለቀመውን ታሳቢ አድርገው፣ አገሪቱ የጀመረችውን ዕድገት በማስቀጠል የሚኖረውን ፋይዳና አቅም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ውይይቶቹ እንደሚካሄዱም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹የመጀመርያው ዕቅድ ዕቅድ እጅግ የተለጠጠ ግብ እንደነበረው ይታወቃል፤›› ያሉት አቶ ሬድዋን፣ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ አንድ አገር በተከታታይ ሊደርስበት ይችላል ተብሎ የሚገመተውን የመጨረሻውን ጫፍ እንሞክረው በሚል የተቀረፀ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹እንቅልፍ ታጥቶ እያንዳንዱን ማኅበረሰባችን በማንቀሳቀስ መድረስ የምንችለውን ያክል እንሞክረው ከሚል እሳቤ የተቀረፀ ነው፡፡ የቻልነውን ያህል ካሳካን ፈጣን መሆኑ አይቀርም የሚል እምነት ነበረን፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከዚህ ጋር ተያይዞ ከፍተኛው ጣራ ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡ ወለሉ ላይ የተቃረበ ስኬት ነው ማስመዝገብ የተቻለው፤›› ያሉት አቶ ሬድዋን፣ የመጀመሪያው ዕቅድ በርካታ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ገልጸዋል፡፡
ይህም ሆኖ ጉድለቶች ያሉባቸው አካባቢዎች እንደተለዩም አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ መሠረቱ ግብርና መር ኢንዱስትሪያላዜሽን በሒደት በተለይ በመጀመርያው ዕቅድ ወደ ኢንዱስትሪ የማሸጋገሩን ግብ ማፋጠኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሒደት ኢንዱስትሪው እየተፋጠነ ሄዷል፡፡ የኢንዱስትሪ መፋጠኑሰ እንደተጠበቀ ሆኖ ከኢንዱስትሪ ውስጥ ግን ማኑፋክቸሪንግ በስፋት እንዲፈጥን ነበር ይፈለግ የነበረው፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ግን በምንፈልገው ልክ አልሄደም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ማኑፋክቸሪንግ 13 በመቶ እያደገ ሄዷል፡፡ ትልቁ ዕድገት ነው፡፡ ፈጣን ዕድገት ነው፡፡ የእኛን ግብ ግን አላሳካም፡፡ ስለዚህ በ13 በመቶ እያደገ ሄዶም ከአጠቃላይ ዕቅድ አንፃር አምስት በመቶ ብቻ ነው ዘርፉ የያዘው፡፡ ይህን መቀየር አለብን የሚል ግብ ተጥሏል፡፡ በሚቀጥለው ዕቅድ ስምንት በመቶ እያስመዘገበ መቀጠል አለበት፤›› በማለት ቀጣዩን የዕቅድ አቅጣጫ ይፋ አድርገዋል፡፡
‹‹ይህ በጣም ትልቁ አቅም የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ እንዲፈጠር ከተፈለገ ደግሞ ጥቃቅንና አነስተኛ በፍጥነት ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ መካከለኛ ደረጃ የሚወጡ አንቀሳቃሾች መስፋት አለባቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ኢንዱስትሪያሊስቶች በስፋት መጎልበት አለባቸው፡፡ የግል ባለሀብቱ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገባ ጠንካራ ማበረታቻ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን መቀጠል ይገባናል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ይህን በማድረግ ሽግግሩ ግብርና ወደ ኢንዱስትሪ፣ ከኢንዱስትሪ ውስጥም ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በተፋጠነ ፍሰት እንዲሄድ የተጀመረውን በፍጥነት ማስኬድ እንደሚጠይቅም፣ በመንግሥት በኩል አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ረገድ በመጀመርያው ዕቅድ ሰፋ ያሉ ስኬቶች መመዝገባቸውንም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የአገራችንን ገጽታ በመቀየርና የሕዝባችንን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ድርሻዎች አሉት፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን የመጀመሪያው ዕቅድ የነበሩበትን ማነቆዎች በሁለተኛው ዕቅድ ለመፍታት በስፋት የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ የፋይናንስ አቅም ነበር፡፡
‹‹የአገሪቱን የፋይናንስ አቅም በማጎልበት ነው በዋናነት ልማታችንን ማስቀጠል ያለብን፡፡ ስለዚህ ፋይናንስ ማነቆ ይሆናል የሚለው ቀድሞ የተለየ ነው፡፡ በመጀመርያው ዕቅድም ፋይናንስ ማነቆ ነበር፡፡ እሱን እየተቋቋምን ለመሄድ ሞክረናል፡፡ በራሳችን ፋይናንስ ለመደጎም አንዱ አማራጭ ተደርጎ የነበረው በዚያው ዕቅድ ውስጥ ከታቀዱ ፕሮጀክቶቻችን የሚገኘው ገቢ መልሶ ሌሎቹን ፕሮጀክቶች ይደጉማል የሚል ነበር፤›› በማለት የመጀመሪያው ዕቅድ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ታቅዶም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
‹‹የስኳር ፕሮጀክቻችን ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያመነጫሉ ተብሎ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ሁሉም ወደ ማመንጨት አልሄዱም፡፡ ወደ ውጭ መላክ ስላልጀመርን እርሱ ከግብ በታች ወርዷል ማለት ነው፡፡ ያን አድርገን ቢሆንና እርሱን አሳክተን ቢሆን ኖሮ የፋይናንስ ምንጫችን ይጠናከር ነበር፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ስለዚህ የሚቀጥለው ዕቅድ ከመጀመርያው ዕቅድ ያደረ ሒሳብንም ጭምር አካክሶ መሄድን ከግምት ያስገባል፡፡ እነዚህን በድምሩ ከወሰድናቸው ከመጀመርያው ዕቅድ የነበረውን መዋቅራዊ ሽግግርም ኢኮኖሚያዊ ሽግግርም በማጠናከር፣ በሁለተኛው ዕቅድ ላይ አሁንም የተጀመረው ዕድገት ማስቀጠል በዋናነት ታሳቢ ይደረጋል፤›› ሲሉ አቶ ሬድዋን አስረድተዋል፡፡
‹‹የመጀመርያው በግብርናው በራሱ ውስጥ የሚደረግ ትራንስፎርሜሽንን ማጎልበት ሲሆን፣ በራሱ ውስጥ የሚደረገውን ትራንስፎርሜሽን በአንድ በኩል ከተለመዱ ሰብሎች ወጣ ብሎ አርሶ አደሩ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ሰብሎችን ለማምረት እንዲሸጋገር ማድረግ ነው፡፡ በእስካሁን አመጣጣችን ግማሽ የሚሆነው አርሶ አደር ለገበያ ብሎ ምርቶችን ማምረት ጀምሯል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ትራንስፎርሜሽን ነው፡፡ ለቀለብ ብሎ ከማምረት ለገበያ ብሎ ማምረት መሸጋገሩ አንድ እመርታ ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሁለተኛው ዕቅድ የመስኖ ልማት ሥራ ላይም ትኩረት እንዳደረገ አቶ ሬድዋን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ባለው ደረጃ ወደ 2.4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመስኖ ማልማት ተችሏል፡፡ ካለፈው ዕቅድ በፊት ግን የመስኖ ልማት በአርሶ አደሩ ውስጥ ያልተለመደ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
ሌላኛው የሁለተኛው ዕቅድ ገጽታ በእንስሳት ሀብት ያለውን አቅም መጠቀም ነው፡፡ ‹‹አቅማችንን በተገቢው ደረጃ ያልተያዘና ያልተገለገልንበት ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡ ‹‹አንደኛው ከኢንዱስትሪያላይዜሽን ጋር ትኩረት የምንሰጠው ከቆዳና ከቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት በእንስሳት ሀብታችን እመርታ ማምጣት አለብን፡፡ እዚያ ላይ ስንመሠረት ዕድገታችንን ቀጣይነቱን ማረጋገጥ እንችላለን፤›› በማለት የእንስሳት ሀብት በተገቢው ሁኔታ መጠቀም እንዳልተቻለና ይህን ለማሻሻል ዕቅዱ ልዩ አትኩሮት መስጠቱን አስረድተዋል፡፡
‹‹ሁለተኛው የኢኮኖሚ ሽግግሩን ነው፡፡ ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሽግግር መፋጠን አለበት፡፡ ግብርናው የመጀመርያው ዕቅድ አካባቢ ወደ 46 በመቶ ከነበረበት አጠቃላይ፣ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው ድርሻ አሁን ወደ 40 አካባቢ ወርዷል፡፡ በሚቀጥለው ዕቅድ ወደ 36 ማውረድ አለብን፤›› በማለት የግብርናን ድርሻ ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ስለዚህ ኢንዱስትሪው ደግሞ ይህን ተክቶ እንዲሄድ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ ‹‹የመጀመርያውን ዕቅድ በምንጀምርበት ወቅት 12 በመቶ ነበር፡፡ አሁን ወደ 14 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ በሚቀጥለው ዕቅድ 23 በመቶ ማድረስ መቻል አለብን፤›› ሲሉ የመንግሥትን ፍላጐት አስረድተዋል፡፡
በዚህም ለጥቃቅን፣ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
ሁለተኛው ዕቅድ በማኅበራዊ ልማት ላይም ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ ‹‹በማስፋት ረገድ በስፋት ሄደናል፡፡ ተደራሽነት ላይ የተሳካ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ጥራት ላይ ነው ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሁለተኛው ዕቅድ ሊሠሩ ከታቀዱት ሥራዎች አንደኛው የፋይናንስ አቅርቦትን ማጠናከር፣ የብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ማግኘት ነው፡፡ ለዚህ በሁለተኛው ዕቅድ ቢሮክራሲውን ለመቁረጥ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡ እንዲሁም ለዚህ እንዲያመች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡
ለኃይል አቅርቦት አሁን የተጀማመሩትን ፕሮጀክቶች መልክ በማስያዝ የኃይል አቅርቦት ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዘው ሌላው ጉዳይ በየደረጃው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማስወገድ ነው፡፡ ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመጀመርያው ዕቅድ በተለየ ለመፍታት ርብርብ የተደረገበት ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ያልተቀረፈ ነው፡፡ ስለዚህ የሁለተኛው ዕቅድ ትልቁ ትኩረት በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚኖሩ ማነቆዎችን መቁረጥ፣ እነርሱን ማስተካከልና እዚያ ላይ እመርታ ማምጣት ነው፤›› በማለት ጋዜጣዊ መግለጫውን ደምድመዋል፡፡