Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን ያስችለኛል ያለውን የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ስምምነት ተፈራረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ፍኖተ ካርታውን ለማዘጋጀት የስዊዘርላንድ ኩባንያ ተመርጧል

ከደርግ ውድቀት በኋላ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ባንክ በመሆን ወደ ሥራ የገባው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የግል ባንክ ያደርገኛል ያለውን የለውጥ ዕቅድ እንዲያሰናዳለት ኬፒኤምጂ ከተባለ የስዊዘርላንድ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ባንኩ ከኬፒኤምጂ ጋር ያደረገውን ስምምነት አስመልክቶ ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፣ የለውጥ ዕቅዱ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን አቅም ለመገንባት የሚያስችለው ነው፡፡ ኬፒኤምጂ የሚያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በመተግበር፣ እ.ኤ.አ. በ2025 በአጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ ባንኮች አንዱ ለማድረግ ያስችላልም ተብሏል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ፍኖተ ካርታ ታላቅ ለውጥ ያለመ ፕሮጀክት ነው፡፡ ‹‹እንደ ስትራቴጂ ፕላን የሚወሰድ ሳይሆን የረዥም ጊዜ ግብን የያዘ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ባንኩ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ የሚሆነው ፍኖተ ካርታ ከተዘጋጀ በኋላ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ኩባንያው የሚያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ከአራት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ እንደሚያስረክብ ይጠበቃል፡፡

ከዚያ በኋላ አፈጻጸሙን ይከታተላል ተብሏል፡፡ የኬፒኤምጂ ተግባር አጠቃላይ የመዋቅር ለውጥ ጭምር ለማምጣት የሚያስችል በመሆኑ፣ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ የኢኮኖሚ ጥናቶችን አካቶ እንደሚያከናውን ተገልጿል፡፡ የዓለም የቀጣይ ዓመታት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን፤ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጭምር በማጥናት ለባንኩ ቀጣይ ጉዞ አመቺ የሆነ ዕቅድ የማዘጋጀት ኃላፊነት እንደተሰጠውም ተጠቁሟል፡፡

አዋሽ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ቀዳሚ ከሚባሉ የግል ባንኮች አንዱ ለመሆን ያለውን ዕቅድ ለማሳካት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የባንክ ኢንዱስትሪን ይዘት ጭምር በማጥናት ተስማሚ የሆነ ዕቅድ እንደሚያወጣ ይጠበቃልም ተብሏል፡፡

የፍኖተ ካርታው ዝግጅት ታች ካለው የባንኩ አወቃቀር ጀምሮ እያንዳንዱ ዲፓርትመንት ምን ይዘት ሊኖረው ይገባል የሚለውን በዝርዝር እንደሚያቀርብም ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡ ውጥኑ የደንበኞችን ፍላጎት ከማርካት በላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ቦታ በመያዝ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ጥቅምንም ያገናዘበ ይሆናል ተብሏል፡፡ ‹‹Transforming AIB Vision 2025›› የሚል ስያሜ የተሰጠውን የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሥራ ባንኩን በመወከል ፕሬዚዳንቱ አቶ ፀሐዬ ሽፈራው ፈርመዋል፡፡ በኬፒኤምጂ በኩል ደግሞ የኩባንያው የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚስተር ዴቪድ ሊ ፈርመዋል፡፡

ኬፒኤምጂ ይህንን ሥራ የወሰደው ባንኩ ባወጣው ጨረታ ከአምስት ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሮ አሸናፊ በመሆኑ ነው፡፡ ኩባንያው አሸናፊ የሆነበትን ዋጋ ሁለቱም ወገኖች ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚሉት ኩባንያው ያሸነፈበትን ዋጋ ላለመግለጽ ሁለቱም ወገኖች ተስማምተዋል፡፡ ከኬፒምኤጂ ጋር በጨረታው ላይ ከተሳተፉት ኩባንያዎች መካከል ኧርነስት ኤንድ ያንግ ይገኝበታል፡፡ ኬፒኤምጂ በ155 አገሮች የሚሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰቱን 26 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ይነገራል፡፡

አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች በአትራፊነት ከዳሸን ባንክ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከሁሉም የግል ባንኮች በተቀማጭ ገንዘብ አቅሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን ዘንድሮ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ባለፈው ዓመት 861 ሚሊዮን ብር ማትረፍ የቻለው አዋሽ ባንክ፣ በ2007 በጀት ዓመት አሥራ አንድ ወራት ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ አምና በሙሉ በጀት ዓመቱ አግኝቶት ከነበረው ትርፍ ይበልጣል ተብሏል፡፡

ባንኩ በ2007 ዓ.ም. ብቻ 50 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ይህም የባንኩን ቅርንጫፎች ቁጥር 200 አድርሶታል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 26 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የተከፈለ ካፒታሉ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የተጠጋ ሲሆን፣   ባለፈው ዓመት በባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት የተከፈለ ካፒታሉ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ይህም የግል ባንኮች ሊኖረን ይገባል ብለው ከያዙት የተከፈለ ካፒታል መጠን ጋር ሲነፃፀር ብልጫ አለው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች