Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎና የባለሙያዎች ግብዓት ያስፈልገዋል!

  የመጀመርያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጠናቆ፣ ሁለተኛው ሊጀመር የዝግጅቱ ምዕራፍ እየተገባደደ ነው፡፡ የመጀመርያው ዕቅድ እንደ ጅማሬ መልካም ተሞክሮዎችና ውጣ ውረዶች የታዩበት ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ግን በርካታ መሰናክሎች ታይተውበታል፡፡ ሆኖም በርካታ ተስፋ ሰጪ ተግባራት መከናወናቸውን በፍፁም መካድ አይቻልም፡፡ አሁን ሁለተኛው ዕቅድ ከመጀመሩ በፊት ግን ከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎና የአገሪቱ ባለሙያዎች ግብዓት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከመጀመርያው በጣም የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ሲፈለግ፣ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎና የባለሙያዎች ርብርብ ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ በመጀመርያው ዕቅድ ያጋጠሙ ችግሮች በርካታ ስለሆኑ፡፡

  ሁለተኛው ዕቅድ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚከናወኑ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ የሚደረጉበትና በአገሪቱ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረውን ድህነት በሚታይ ውጤት እንደሚቀንሱ ይጠበቃል፡፡ ይህ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ከዕቅዱ እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ አገሪቱ አሉኝ የምትላቸው ባለሙያዎችም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዕድሉ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ በዕቅዱ ላይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችና የአካባቢ የልማት ኮሚቴ ተወካዮች በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚገኙ መንግሥት አስታውቋል፡፡ የገጠር ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮችም እንዲሁ፡፡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል፡፡

  በዕቅዱ ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ በመንግሥት ዝግጅት መደረጉ በጣም ጥሩ ነው፡፡ የኅብረተሰቡ ንቁ ተወካዮችና ምሁራን ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በዕቅዱ ላይ ተወያይተው፣ ለዕቅዱ ጠቃሚ የሆኑ ግብዓቶችን እንዲያበረክቱ ማድረግ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ላይ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባው ኅብረተሰቡን ወክለው በንቃት ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብለው የተመረጡት ወይም የሚመረጡት ተሳታፊዎች እነማን ናቸው የሚለው ነው፡፡ በአገሪቱ ታላቅ ብሔራዊ ጉዳይ ላይ የንግዱን ኅብረተሰብም ሆነ ምሁራንን የሚወክሉትስ እነማን ናቸው? ይኼ ሊመለስ ይገባዋል፡፡

  መንግሥት በተዋረድ ባሉት የፓርቲ አደረጃጀቶች ተጠቅሞ የወጣቶችንና የሴቶችን ተሳትፎ በሊጎች ብቻ ከወከለ ችግር አለ፡፡ ሴቶችና ወጣቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች፣ በግል ሥራቸው፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በግብረ ሰናይ ድርጅቶችና በመሳሰሉት ውስጥ በብዛት ስለሚገኙ ተሳታፊዎችን በጥራት መመልመል አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህ በጥራት የተመለመሉ ሴቶችና ወጣቶች በተለያዩ የውይይት ፕሮግራሞች ላይ እጅግ ጠቃሚ ግብዓቶችን ከማቅረባቸውም በላይ፣ እነሱ የሚገኙባቸው ውይይቶች በሥነ አመክንዮ የተደገፉ ክርክሮችና ፍጭቶች ይደረጉባቸዋል፡፡ ከእነዚያ አመርቂ ውይይቶችም ለአገር ዕድገት የሚበጁ በርካታ ለዕቅዱ የሚረዱ ምክረ ሐሳቦች ይፈልቃሉ፡፡ ከዚያ ውጪ በለብ ለብ የሚደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚመስሉ ውይይቶች ከጠቀሜታቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ በስመ ውክልና ተገኝተው አዳዲስ ሐሳቦችን ማመንጨት የማይችሉ አያስፈልጉም፡፡

  ምሁራን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ እንደመሆናቸው መጠን፣ ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚኖራቸው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ምሁራኑ የመጀመርያውን ዕቅድ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እየመዘዙ በምሁራዊ ምልከታዎች በመገምገም፣ ሁለተኛው ዕቅድ በምን ዓይነት አኳኋን ቢመራ የተሻለ አፈጻጸም እንደሚያስመዘግብ፣ መሬት ላይ ያለውንና በወረቀት ላይ የሠፈረውን እንዴት ማጣጣም እንደሚቻል፣ ወዘተ በመተንተን ለውጤት የሚያበቁ አቅጣጫዎችን ያመላክታሉ፡፡ ምሁራኑ የሚደገፈውን ደግፈው፣ የሚነቀፈውን ነቅፈው የተሻለውን መንገድ አመላካች እንዲሆኑ ይኼ ዕድል በፍፁም ሊያመልጣቸው አይገባም፡፡ ጠንካራና የሰላ ትችት የሚያቀርቡና ወደተስተካከለ አቅጣጫ የሚያመሩ ምሁራን ወደ ጎን ተገፍተው፣ የባለሥልጣናትን ዓይንና ግንባር እያዩ የሚልመጠመጡ አድርባዮች ለምንም ነገር አይጠቅሙም፡፡ አድርባይነት የአገር ዕድገት ነቀርሳ ስለሆነ፡፡

  በሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎች አመራረጥ ላይ ተግባራዊ የሚሆነው አሠራርም መፈተሽ አለበት፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የአገሪቱን ሕዝብ ፍላጎቶች የተጣጣሙ እንዲሆኑ የሚፈለግ ከሆነ፣ የቁሳዊው ሀብት ዕድገትና የሕዝቡ አኗኗር ትስስር ሊኖረው ይገባዋል፡፡ ለዚህ ዕቅድ የሚወጣው እጅግ በጣም ግዙፍ የሆነ ሀብት እንዴት ሥራ ላይ ይውላል የሚለው በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ዕድገቱ የሚያመጣው ሀብት እንዴት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ወደ ሕዝቡ እንደሚደርስ አመላካቾች መኖር አለባቸው፡፡ ዕድገቱ በረከት እንጂ እርግማን እንደማይሆን ማሳያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ጥቂት ሚሊዮነሮችን እንጂ በጣም ብዙ ድሆችን እንደማይፈጥር ተስፋ መታየት አለበት፡፡ የክልሎች ዕድገት ይመጣጠናል ወይ? የዜጎች ገቢ እንደ ልፋታቸው መጠን ይቀራረባል ወይ? የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አፈጻጸም ቅደም ተከተል የሕዝቡን ፍላጎት ተንተርሶ ነው ወይ? ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚወሰዱ የመፍትሔ ዕርምጃዎች እንዴት ይቀመጣሉ? ድንገተኛና ያልታሰቡ ጉዳዮች ሲያጋጥሙስ ምን ይደረጋል? የቁጥጥርና የግምገማ ሥርዓቱ እንዴት ይቀናጃል? የመሳሰሉት በጠንካራ ጥያቄዎችና ክርክሮች መታጀብ አለባቸው፡፡

  የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲነደፍ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው የድህነት ማስወገጃ ዘላቂ ፕሮግራም ላይ ተመሥርቶ ነበር፡፡ ዋነኞቹ ተግዳሮቶች ተብለው ከተቀመጡት መካከል ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊፈጠር ስለሚችል የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር፣ ገቢን የመሰብሰብ አቅም አለመኖር፣ ዝቅተኛ መጠን ያለው ብሔራዊ ቁጠባ ለግዙፉ አገራዊ ኢንቨስትመንት ፍላጎ በቂ አለመሆኑ፣ በተዛባ የዝናብ ሥርጭት ምክንያት በግብርና ላይ ለሚደርሰው ተፅዕኖ የመስኖ ልማት ትልቅ ትኩረት እንደሚሻ የቀረቡ መነሻ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ በመንግሥት ርብርብ የዋጋ ግሽበት ነጠላ አኃዝ መውረዱ፣ በታክስ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ በመካሄዱና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች በመወሰዳቸው ችግሮችን ሊቋቋም እንደሚቻል ታምኖበት ዕቅዱ መነደፉ ተገልጿል፡፡ አሁን ከመጀመርያው ዕቅድ አፈጻጸም የተገኙት በርካታ ትምህርቶች አሉ፡፡ በርካታ ማነቆዎች በአፈጻጸሙ ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖ መወገድ የሚችለው ጠንካራ ሕዝባዊ ተሳትፎና የባለሙያዎች ግብዓት ሲኖር ነው፡፡  

  በዚህ ዘመን በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የራስ ምታት ከሆኑ ችግሮች መካከል ዋና ዋና ዋናዎቹ የተቋማት አቅም ደካማነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስና፣ የተሿሚዎች ብቃት ማነስና ደንታ ቢስነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፋ ወደ ሥራ የምትገባ አገር እነዚህን እንከኖች ማፅዳት የምትችለው፣ ገና ከጅምሩ በዕቅዱ ላይ ብሔራዊ መግባባት ሲፈጠር ነው፡፡ በደካማ ተቋማት ምክንያት አገሪቱ መክሰር የለባትም፡፡ እነዚህ ተቋማት ለሥራው በሚመጥን ቁመና ላይ እንዲገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጠንካራ ተቋማት አቅም በሌላቸው ተሿሚዎች መመራት ስለሌለባቸው፣ አቅም ላላቸው መተላለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህም ከፍተኛ የአገር ሀብት ከኪሳራ መዳን አለበት፡፡ ለመልካም አስተዳደር ችግር መፍትሔው ተቋማቱንና ተሿሚዎችን በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ እንዲሠሩ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ሥራ መሥራት የማይችሉ ደካሞች በአግባቡ እንዲገለሉ ተደርጎ አቅም ያላቸው ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለመልካም አስተዳደር መስፈን ፍቱን መፍትሔ ነው፡፡

  ሁለተኛው ዕቅድ የዘራፊዎች ሲሳይ እንዳይሆን ለሙስና ትልቅ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ግዢዎች፣ ጨረታዎች፣ የገንዘብና የንብረት አያያዝና የፋይናንስ ክንዋኔዎች ከሙስና ካልፀዱ በስተቀር አደጋ አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሙስና በመበልፀግ ላይ ያሉ የተደራጁ ቡድኖችና ግለሰቦች የራሳቸውን ኔትወርክ በስፋት ዘርግተዋል፡፡ በየቦታው የሚታየው ዝርፊያ የእነዚህ ሙሰኞች ተግባር ነው፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ የሙስና ሰለባ እንዳይሆን ምን እየተሠራ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ነገር መቀመጥ አለበት፡፡ በደንታ ቢስ የሥራ ኃላፊዎችና መሰሪዎች ምክንያት የሚወድም የአገር ሀብትን እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የመፍትሔ አመላካች መቅረብ አለበት፡፡ ለዚህም ንቁ የሕዝብ ወኪሎችና አገር ወዳድ ምሁራን ተሳትፏዋቸው ይፈለጋል፡፡

  መንግሥት በየደረጃው አካሂዳቸዋለው ባላቸው የሁለተኛው ዕቅድ የውይይት ፕሮግራሞች ላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፎ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የምርጫው ውጤት ከተሰማ በኋላ መንግሥት በተደጋጋሚ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ከእነሱ ጋር መመካከር እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ ከቃል በላይ ተግባር ስለሚፈለግ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ምንም ዓይነት ሐሳብ ይኑራቸው መሰማት አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ ዕቅዱን አንቀበለውም ቢሉ እንኳ መደመጥ አለባቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ይዘውት የሚመጡት ጠቃሚ አጀንዳ ይኖራል ብሎ ማሰብ ነው፡፡ የፓርላማ ወንበር ባያገኙም በርካታ ዜጎች ድምፅ እንደሰጡዋቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ የእነዚያ ዜጎች ድምፅ የሚሰማው በእነሱ በኩል ነው፡፡

  ይህ ሁለተኛ ዕቅድ በነቃ የሕዝብ ተሳትፎና በባለሙያዎች ግብዓት መዳበር አለበት ሲባል፣ በሚደረጉት ውይይቶች አንዱ ተናጋሪ ሌላው አድማጭ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ለዕቅዱ ተጠናክሮ መውጣት የሚያስፈልጉ ጠቃሚ ግብዓቶች በማስፈለጋቸው ነው፡፡ አለበለዚያ የትም የማያደርሱ የተልፈሰፈሱ ሐሳቦችን ተቀብሎ ደካማ ዕቅድ ይዞ መነሳት ውጤቱ ውኃ መውቀጥ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ ተግባራዊ በሚሆንባቸው መጪዎቹ አምስት ዓመታት ከቻይና፣ ከቱርክና ከህንድ በተጨማሪ በርካታ የምዕራባውያን አገሮች ኢንቨስተሮች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የሚያሠሩ ሕጎችን ማውጣት፣ በዘመናዊው ዓለም ተግባራዊ የሚደረጉ ዘመናዊ አሠራሮችን መተግበር፣ የተቋማትን ጥንካሬ ማረጋገጥ፣ ሙሰኝነትን በብቃት መከላከል፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበርና የመሳሰሉት ተግባራት የውይይቱ ጠቃሚ አጀንዳ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ንቁ ተሳትፎ ነበረ የሚባለውም የበቁና የነቁ ሰዎች ሲታደሙ ነው፡፡ በመሆኑም ዕቅዱ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎና የባለሙያዎች ግብዓት ያስፈልገዋል! የግድ ነው!

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

  የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በአክሲዮን ለመደራጀት የሚያስፈልጋቸውን የተሽከርካሪ ብዛት የሚወስን መመርያ ተረቀቀ

  የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ባለንብረቶች ከማኅበርነት ወጥተው አክሲዮን ሲቋቋሙ፣ ከሚጠበቅባቸው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው!

  በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው የሚጨፈጨፉበት ምክንያት ብዙዎችን...

  የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት አካታችነት ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

  በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በሥራ ሥምሪት መካተት እንዳለባቸው የሚገልጽ አዋጅ...

  ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

  በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

  የተቋማት ኃላፊዎች የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ማሳሰቢያ ተሰጠ

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳድርና ቁጥጥር ጉዳዮች...

  ኢዜማ በምሥራቅ ወለጋ ዞን የንፁኃን ጭፍጨፋ አሳስቦኛል አለ

  በግጭት ቀጣና ውስጥ ያሉ ዜጎች ራሳቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ መታጠቅ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው!

  በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው የሚጨፈጨፉበት ምክንያት ብዙዎችን ግራ ከማጋባት አልፎ፣ የአገርና የጠቅላላው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰበ ነው፡፡ መንግሥት...

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...