Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበመገንባት ላይ ባለው የአዲስ አበባ-ሚኤሶ ባቡር መስመር ዘረፋ እየተፈጸመበት መሆኑ ተገለጸ

በመገንባት ላይ ባለው የአዲስ አበባ-ሚኤሶ ባቡር መስመር ዘረፋ እየተፈጸመበት መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

ግንባታው በመገባደድ ላይ ባለው የአዲስ አበባ-ሜኤሶ የባቡር መስመር ላይ በሐዲዶችና በመጋዘን የተከማቹ ንብረተቶች ላይ ተደጋጋሚ የዘረፍ ሙከራ እየተካሄደበት መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ፖሊስ መሠረተ ልማቱንም ሆነ በግንባታ የሚሳተፉ ሠራተኞች ደኅንነት ለማስጠበቅ የተጠናከረ ጥበቃ ማድረጉንና ዘራፊዎችንም ለሕግ ማቅረቡን ገልጿል፡፡

በተለይ በአዳማ ከተማ አካባቢ በመገንባት ላይ ባለው ጣቢያ ተደጋጋሚ ዘረፋ እንደሚፈጽም ተነግሯል፡፡ የጥበቃ ሠራተኞችና ቻይናዊያን ባለሙያዎችም በዘራፊዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው እንደነበር ሪፖርተር ሥፍራው ድረስ በመሄድ ለመገንዘብ ችሏል፡፡

በግንባታ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ዘራፊዎች በጦር መሣሪያ ጭምር በሌሊት ካምፑን ሰብረው በመግባት በመጋዘን የሚገኙ ብረታ ብረቶችንና የግንባታ ግብዓቶችን ለመስረቅ ሙከራ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስ አበባ-ሜኤሶ ባለው አጠቃላይ መስመር ላይ አንድ ሻምበል የተጠናከረ ፌዴራል የፖሊስ ኃይል የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በአዳማ መጋዘኖች በሚገኙ ቦታዎች ግን ዘራፊዎች ከሠራተኞች ጋር በመመሳጠርም ዘረፋ ለማድረግ መሞከራቸው ተገልጿል፡፡

ግንባታውን እያካሄደ ከሚገኘው የቻይናው ሲአርሲሲ የተገኘ መረጃ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ100 ጊዜ በላይ የዘረፋ ሙከራዎች መፈጸማቸውን ያሳያል፡፡

የአዳማ 03 ቀበሌ አስተዳደር ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ተጠርጣሪ ዘራፊዎችን አድነው በመያዝ ለሕግ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምን ያህል የዘረፋ ሙከራ እንደተካሄደ ባይገልጹም፣ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አንድ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ከፖሊስ መረዳት እንደቻለው፣ ዘራፊዎች በምርመራ ወቅት ሲጠየቁ የዘረፉት ንብረት የአገሪቱ ሳይሆን የቻይና እንደሆነም አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

የጥበቃ ሥራውን እያስተባበሩ የሚገኙት ምክትል ኢንስፔክተር እንግዳው ባዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የመሠረተ ልማቱን በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ያለ ቢሆንም፣ በጥቂቶች ዘንድ ያለው ግንዛቤ በተቃራኒው ስለሆነ ሰፊ የግንዛቤ ትምህርት መሰጠት አለበት፡፡

ኩባንያው በበኩሉ በቡድን የተደራጁና የጦር መሣሪያ የታጠቁ ዘራፊዎች በኢትዮጵያውያንና በቻይናውያን ሠራተኞች ላይ በተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ሲፈጽሙ፣ በተለያዩ ካምፖች ግንባታ የሚቆምበት ጊዜ እንደነበር ገልጿል፡፡

የአገር አቀፍ የባቡር ትስስር አካል የሆነው የሰበታ-ሚኤሶ የባቡር መስመር  ግንባታው በቻይናው ሲአርሲሲ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ 329 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይኼ ፕሮጀክት በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለግንባታው 1.8 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደወጣበት ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...