ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የቻይናና የኢትዮጵያ መንግሥታት የፋይናንስና የኢኮኖሚ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ባንክና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችና ኢንቨስተሮች የተገኙበት ፎረም፣ ቻይና በአፍሪካ ስለምታካሂደው የኢንቨስትመንትና የንግድ ልውውጥ እየመከረ ነው፡፡ አዳዲስ ስምምነቶችና የፋይናንስ ድጋፎች ይፋ እንደሚደረጉበት ይጠበቃል፡፡
‹‹ኢንቨስቲንግ ኢን አፍሪካ ፎረም›› በሚል ስያሜ የመጀመሪያውን ጉባዔ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንዳስታወቁት፣ በአፍሪካ ከ2,200 ያላነሱ ኩባንያዎች በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያም ኋጂዬን ግሩፕ የተባለው ጫማ አምራች 3,500 ሠራተኞችን በመቅጠር፣ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ጫማዎችን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከካቻምና ጀምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ካደረጉ የውጭ ኩባንያዎች የሚገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቱርኩ አይካ አዲስን ጨምሮ የታይዋኑ ጆርጅ ሹ ኩባንያና ሌሎችም ሥራዎችን እያስፋፉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ አዳዲሶቹ ፒቪኤችና ኤችኤንድኤም የተባሉ ትልልቅ ኩባንዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውም፣ በዓመት 13 በመቶ እያደገ ለሚገኘው አምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ተስፋ እንደሆነ አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡
የቻይና ምክትል የፋይናንስ ሚኒስትሯ ሊዩ ዢያንሁዋ፣ እንዲሁም የቻይና ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዩዋን ሊ ባደረጉት ንግግር፣ አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ለማጠናከር እንደምትፈልግ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ዩዋን ሊ እንዳሉት፣ ባንካቸው በ34 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በቻይና-አፍሪካ ልማት ፈንድ በኩል እ.ኤ.አ. በ2006 በ82 ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ካደረገው የ3.15 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በተጨማሪ፣ 16 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት የማድረግ ሐሳብ አለው፡፡ ይህም ወደ አፍሪካ የሚመጣውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ፣ የአፍሪካን የወጪ ንግድ በየዓመቱ በሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ፣ እንዲሁም የታክስ ገቢንም በአንድ ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ እስካሁን በቻይና ኩባንያዎች አፍሪካ ውስጥ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አማካይነት የተመዘገበው አራት ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ፣ የሁለትዮሽ ንግዱ ግን 222 ቢሊዮን ዶላር ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ከቻይና ወደ አፍሪካ የሚገቡ ሸቀጦች የሚሸፍኑት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ ቻይናውያን ያስመዘገቡት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በሚመለከት የዓለም ባንክ ካቻምና አካሂዶት በነበረው ጥናት መሠረት፣ እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ኢንቨስትመንት በየዓመቱ በአማካይ የ58 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ቢባል ግን የቻይና ኩባንያዎች በመንግሥት የታክስና ጉምሩክ አስተዳደር የሚታዩ ውጣ ውረዶች፣ በውጭ ምንዛሪ በኩል መንግሥት ግልጽነት አለማሳየቱን፣ በሠራተኛ ሕግ፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦትና በመሳሰሉት መስኮች ላይ ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደሚገኙ የዓለም ባንክ በጥናቱ አሳይቷል፡፡
በሰው ጉልበት ዋጋ መወደድና በማምረቻ ወጪዎች ከፍተኛነት ሳቢያ ከቻይና እየነቀሉ ወደ አፍሪካ የሚመጡ የቻይና ኩባያዎች እንደሚበራከቱ ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲነገር ነበር፡፡ በዚህ መስክ ኢትዮጵያ መጠቀም አለባት በማለት ደጋግመው ሲናገሩ እንደነበር የሚታወሱት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ ሆኖም የተገመተውን ያህል ግን በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ሳይመጡ ቀርተዋል፡፡ ይህንን በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ልዩ ረዳት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አገሪቱ ይህንን ዕድል ለመጠቀም በሚያስችላት ደረጃ ዝግጁ እንዳልነበረች ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካይነት የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችንና ሌሎች እንደ ጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያሉ አገልግሎቶችን በፋብሪካዎቻቸው ደጅ ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡
በአፍሪካ ኢንቨስት ስለማድረግ በዝግ እየመከረ የሚገኘው ጉባዔም መሠረታዊ በሚባሉ ችግሮች ላይ ከመነጋገር ባሻገር፣ በአፍሪካ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ረገድ አዳዲስ ስምምነቶች ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሌሎችም የመሠረተ ልማት መስኮች ላይ የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገሮች የሚደረጉ አዳዲስ ብድሮችንና የፋይናንስ ድጋፎችን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ማክታር ዲዮፕ እንዳስታወቁት፣ በአፍሪካ በየዓመቱ የ90 ቢሊዮን ዶላር የመሠረተ ልማት ግንባታ ፍላጎት ቢኖርም፣ የአፍሪካ አገሮች ኢንቨስት ማድረግ የቻሉት ግን ከ20 ቢሊዮን ዶላር ያልዘለለ ነው፡፡ ይህንን በመንተራስ የቻይና ኩባንያዎች በቋሚ ንብረቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው፣ የቻይና የፋይናንስ ተቋማትም አስፈላጊውን ፋይናንስ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ታውቋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) እንዲሁም የቻይና መንግሥት ያዘጋጁት ይህ ፎረም፣ በየዓመቱ በአፍሪካና በቻይና እየተፈራረቀ በቋሚነት እንዲካሄድ ስምምነት መደረጉን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴ አስታውቀዋል፡፡