Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

አወዛጋቢው ከኮንዶም የተሠራ ምስለ አካል

ትኩስ ፅሁፎች

ሚልዋኬ አርት ሙዚየም በቅርቡ ለዕይታ ሊያቀርበው ያሰበው ሥዕል ውዝግብ አስነስቷል፡፡ ሥዕሉ የፖፕ ቤነዲክትን ምስለ አካል የሚያሳይ ነው፡፡ ተቃውሞው የተነሳው ምስሉ በሙዚየሙ በመታየቱ ሳይሆን፣ ምስሉ የተሠራው ከኮንዶም በመሆኑ ነው፡፡

ወደ 17,000 የሚደርሱ ባለቀለም ኮንዶሞች ተለጥጠው የተሠራው ሥዕሉ የጳጳሱን ፊት ያሳያል፡፡ ሥዕሉን በሙዚየሙ ለመስቀል የወሰኑት ኤችአይቪ ኤድስን መወያያ አጀንዳ ለማድረግ ፈልገው መሆኑን የሙዚየሙ ዳይሬክተር ዳን ኪጋን ተናግረዋል፡፡ ሥነ ጥበብ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ ለማሳየትም ሥዕሉ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ይህን ቢሉም የጳጳሱ ምስል ከኮንዶም መሠራቱ በርካታ የካቶሊክ እምነት ተከታዮችን አስቆጥቷል፡፡ ሥዕሉ ኒኪ ጆሃንሰን በተባለች አርቲስት የተሠራ ሲሆን፣ ‹‹ኤግስ ቤነዲክት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የሙዚየሙ ድረ ገጽ እንደሚያሳየው፣ እስካሁን ወደ 200 ቅሬታዎች ለሙዚየሙ ቀርበዋል፡፡ ሙዚየሙን ከሚደጉሙ ባለሀብቶች አንዱ ለሙዚየሙ ከዚህ በኋላ ዕርዳታ እንደማይሰጡም አሳውቀዋል፡፡ በተቃራኒው የሥዕሉን መታየት የሚደግፉ ጥቂት አይደሉም፡፡

የሙዚየሙ ዳይሬክተር ‹‹ቅርጹ ማንንም ለማስቆጣት ያለመ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ አርቲስቷ በበኩሏ ቅርጹን የሠራችው ከሁለት ዓመት በፊት ጳጳሱ ኮንዶም መጠቀምን የሚቃወም አስተያየት በሰጡበት ወቅት እንደሆነ ገልጻለች፡፡ ጳጳሱ በአሁን ወቅት ኮንዶምን ስለመጠቀም የተለሳለሰ አቋም መያዛቸውን ድረ ገፁ ያመላክታል፡፡

* * *

የታዳኝ መድኃኒት

እኔማ!

ከአዳኞቹ ወንጭፍ አቅሜ ‘ማያድነኝ፤

ሞቼ ሰው የማኖር ምስኪንዬ ወፍ ነኝ፡፡

‘‘ረግፎ ያደምቀናል ኅብራዊ ላባዋ፤

ቢበሉት ያድናል መድህን ነው ስጋዋ፡፡

የደሟ ጠብታ፣

የአጥንቷ ሽራፊ – ከደዌ ይፈውሳል፤

ዕንቁላሏን ቢያቅፈው ያረጀ ይታደሳል!…’’

ምናምን እያለ፤

ጀማሪ አዳኝ ሳይቀር ቀስቱን ለእኔ ሳለ፡፡

ትልቁም ትንሹም!

ነፍሴን ዒላማ አርጎ አደን ይጀምራል፤

ፈሪው ተኳሽ እንኳን ዘሬን ገድሎ ያድራል፡፡

እነሆ! በሆነች ድንቅ ቀን!

‘በፍተሻ ጥበብ’ ስሟገት ከነፍሴ፤

‘‘ንስር ነህ!’’ አልኩና ነገርኩት ለራሴ፤

‘‘ከአዳኝነት ላቅ!’’ አልኩት ለታዳኝ መንፈሴ፡፡

መከርኩት!

‘‘የቀስቱን አመጣጥ በደማቁ እንድታይ፤

ለነፍስህ አውስና የክንፍህን ሲሳይ፤

በነፃነት ብረር ከከፍታው ሰማይ!’’

ሲገርም!!

በንስር መንፈሴ ልቀዝፍ ብነሳ፤

አንዲት ቀስት ወደቀች ግራ ክንፌን ዳብሳ፤

ሌላዋም ከሸፈች መስመሯን ቀልብሳ፡፡

ይኼ ኃያል ዳኛ!

የአዳኝ ታዳኝ ኑሮን በፍትሕ ሲያቋቁም፤

ከሟች ጥበብ ሠራው የገዳይን አቅም፡፡

– በረከት በላይነህ፣ የመንፈስ ከፍታ፣ 2005 ዓ.ም.

* * *

ሌባን በመጥረጊያ ያባረሩት አዛውንት

ጀርመን፣ በርሊን ውስጥ ነው፡፡ በአንድ መደብር የሚሠሩ ሠራተኛ የተለመደ ሥራቸውን እያከናወኑ ነበር፡፡ እኩለ ለሊት ላይ መደብሩን ማፅዳት ይጀምራሉ፡፡ መሣሪያ የታጠቁ ሁለት ሌቦች ሱቁ ውስጥ መግባታቸውን ያወቁት ዘግይተው ነበር፡፡ ሌቦቹ በመሣሪያቸው እያስፈራሩ በመደብሩ ያለውን ገንዘብ እንዲሰጧቸው ያዛሉ፡፡ ሠራተኛዋ ተርበትብተው ትዕዛዛቸውን በመፈጸም ፈንታ ሱቁን ያፀዱበት የነበረውን ቫኪዩም ክሊነር አንስተው ሌቦቹን ያስፈራሩአቸው ጀመር፡፡ ይህን ምላሽ ያልጠበቁት ሌቦች ሱቁን ጥለው ፈረጠጡ፡፡ ሮይተርስ የበርሊን ከተማ ፖሊስን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የ59 ዓመቷ የመደብሩ ሠራተኛ ሌቦቹን በቫኪዩም ክሊነሩ አስፈራርተው ካስወጧቸው በኋላ በፍጥነት ከአካባቢው ተሰውረዋል፡፡

* * *

በደብዳቤ ውሰጂ ሰበብ የተጀመረ ሦስት ጉልቻ

አዳም የትናንቱ

የጥንት የጠዋቱ

ሳይለፋ ሳይታክት ተኝቶ ባደረ

ውሎ አጣጭ አቻውን ከጐኑ ተቸረ፤

የምርጡ ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም ጅምር ግጥም ናት፤ አላለቀችም፡፡ ለአሁኖቹ ‹ምስኪን› አዳሞች ‹‹ይብላኝ ለሱ›› የሚል ‹‹ያሳዝናል›› ባይ ሐሳብ ያላቸው ስንኞች ይቀራሉ፡፡ ለጋሽ ሰውነት የግራ ጐን አይሆኑምና ተቆርጠው ቀሩ፡፡ (ገጣሚውን ታላቅ ይቅርታ በመጠየቅ፡፡) ጋሽ ሰውነት አሳቢ አቻውን የተቸረው የትናንት አዳም ስለሆነ፡፡

አሠልጣኙ በ1970 ዓ.ም. ወጣት አስተማሪ ነበር፡፡ ለዚያውም ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋች፡፡ ወቅቱ ደግሞ የኢሕአፓ አባላት በአዳኝ ወጥመድ ውስጥ እየገቡ የሚያልቁበት፡፡ እሱም ታድኖ ታሰረ፡፡ ታስሮ ተመረመረ፤ ነገር ግን አንዳች ፍንጭ አልተገኘበትም፡፡ ከወር በላይ እስር በኋላ በነፃ ተፈታ፡፡ በመፈታቱ ጠቁመው ያሳሰሩት ፍርኃት ውስጥ ገቡ፡፡ ‹‹ይገለናል›› አሉ፡፡ ‹‹እሱ ለምን ይጓጓል፡፡ ትዳር የለው፣ ልጅ የለው ገድሎን ወደ አንዱ ቢሄድ ዋስትናችን ምንድነው?›› ጠቋሚዎች ተጨነቁ፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ጓደኞቹ አንድ መላ ዘየዱ፡፡ ‹‹ለምን አታገባም?›› ‹‹ማንን?›› ጠየቀ ጋሽ ሰውነት ‹‹ከአዲስ አበባ መጥታ እዚህ ባህር ዳር የምትኖር፣ አጐቷ መሀንዲስ የሆነ ጥሩ ልጅ አለች እሷን ብታገባ ጥሩ ነው፡፡›› ተባለ፡፡

የኛ መጽሔት፡- ታዲያ እንዴት ተገናኛችሁ?

አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው፡- ደብዳቤ ይዤልሽ መጥቻለሁ እዚህ ቦታ መጥተሽ ውሰጂ ብዬ ደወልኩላት፡፡ መጣችና የታለ አለችኝ፡፡ አይ ደብዳቤ አልያዝኩም እንድታገቢኝ ነው አልኳት፡፡ ተናዳ ሄደች፡፡ ከዚያ በየቀኑ ደጅ ጠናሁ፡፡ በስተመጨረሻ እሽታዋን ሰጠችኝና በ1970 ዓ.ም. ተጋባን፡፡ አሁን 35 ዓመት አልፎናል፡፡   

  • የኛ መጽሔት ቁጥር 1፣ 2006 ዓ.ም.
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች