Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልየእማሆይ ወለተወልድ ‹‹አንክሮ››

  የእማሆይ ወለተወልድ ‹‹አንክሮ››

  ቀን:

  የእማሆይ ድጌማርያም ገብሩ ‹‹ዘ ሆምለስ ዋንደረር›› በዝግታ ተከፍቷል፡፡ ‹‹ዘ ላስት ቲርስ ኦፍ ኤ ዲሲስድ››፣ ‹‹ኤ ያንድ ገርልስ ኮምፕሌንት›› እና ‹‹ዘ ማድ ማንስ ላፍተር›› በቀጣይ የተደመጡ ሙዚቃዎቻቸው ናቸው፡፡ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የሚዘለቁት ሙዚቃዎች ጋለሪውን የተለየ ገጽታ አላብሰውታል፡፡ ቀልብን የሚገዛና መንፈስን የሚያረጋጋ ድባብ ይስተዋላል፡፡ በአስኒ ጋለሪ የሚታዩት ሥዕሎችም ከሙዚቃዎቹ ጋር የተዋህዱ ይመስላል፡፡

  ከሥዕሎቹ አንዱ ‹‹አንቀፀ ብፁአን›› ወደ አንድ ገዳም የሚወስድ ኮረብታማ መንገድን ያሳያል፡፡ በጥቅጥቅ ደን መሀከል የሚገኘው መንገድ ላይ ወደ ገዳሙ መቃረብን የሚያመላክት መስቀልና ጧፍም ይታያል፡፡ በዐውደ ርእዩ የተካተቱት ሌሎች ሥዕሎችም መሰል ይዘት አላቸው፡፡ አብዛኞቹ ገዳማዊ ሕይወትን በተለያየ መንገድ ያንፀባርቃሉ፡፡

  ሠዓሊቷ እማሆይ ወለተወልድ በርታ ይባላሉ፡፡ ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ ማቅረብ አሀዱ ያሉበትን ይህን ዐውደ ርእይ ‹‹አንክሮ›› የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ ከሥዕሎቻቸው አንዱ የዐውደ ርእዩ መጠሪያ ያደረጉት ‹‹አንክሮ›› ነው፡፡ ከዛፍ ጥላ ሥር ሆነው ሩቅ የሚያማትሩ መነኩሴን ያሳያል፡፡ የተለየ ትርጉም ከሚሰጧቸው ሥዕሎቻቸው መሀከል ‹‹አንክሮ›› ተጠቃሽ እንደሆነ የሚናገሩት እማሆይ ወለተወልድ፣ ‹‹የፈጣሪን ጥበብ ማድነቅን የሚያሳይ ሥዕል፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡ ‹‹መልክአ ቁስ›› እና ‹‹ንዋየ ቅድሳት›› ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚሉ ቁሳቁሶችን ያሳያሉ፡፡ በ ‹‹ዕለተ ሰንበት›› ከአንድ ቤተክርስቲያን ደጃፍ የሚያስቀድሱ ምዕመናን ይታያሉ፡፡

  እማሆይ ወለተወልድ 34 ዓመታቸው ሲሆን፣ ተወልደው ያደጉት መካኒሳ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደርጃ ትምህርታቸውን መካኒሳ ትምህርት ቤት ከተከታተሉ በኋላ ትምህርታቸውን ከ9ኛ ክፍል አቋርጠው ወደ ሰበታ ጌቴ ሰማኔ ገዳም አቀኑ፡፡ በገዳሙ ለሁለት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በጉራጌ ዞን ወደሚገኘው ምሑር ገዳመ እየሱስ ገቡ፡፡ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ በዛው ገዳም ይኖራሉ፡፡

  ወደ ምሑር ገዳመ እየሱስ ከመግባታቸው በፊት የሥነ ጥበብ ግንዛቤው አልነበራቸውም፡፡ ሥዕል አይሥሉም፡፡ ሠዐሊት ለመሆን ልባቸው የከጀለበትን ቀንም አያስታውሱም፡፡ ሥዕል የጀመሩት ገዳሙ ውስጥ ሲሆን፣ መነሻቸውመ ወረቀት ላይ በእርሳስ አዋፋትን በመሣል ነበር፡፡ ‹‹ስለ ሥዕል የማውቀው ነገር ባይኖርም በውስጤ ስለነበረ በጊዜው መውጣት ጀምሯል፤›› በማለት ወቅቱን ይገልጹታል፡፡

  ለአእዋፋት የተለየ ፍቅር ያላቸው እማሆይ ወለተወልድ፣ ከጊዜ በኋላ ወፎችን ወረቀት ላይ ከመሣል ወደ ጨርቅ እንደተሸጋገሩ ይናገራሉ፡፡ በገዳሙ ለሥዕል የሚሆን ሸራ ስለማያገኙ በነጠላ አልያም ለልብስ በሚሰጣቸው አቡጀዲ ጨርቅ ላይ ይሥሉ ነበር፡፡ በወቅቱ ለሥዕል የሚውል ቀለም ምን ዓይነት እንደሆነ ስለማያውቁ በገዳሙ የሚገኙ መኖሪያዎች የቀለም እድሳት ተደርጎላቸው የሚተርፈውን መነኩሲቷ ይጠቀሙ ነበር፡፡

  በጨርቅ ላይ መጀመሪያ ያሰፈሩት የማርያምን ሥዕል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ሥዕሉን ሲመለከቱት በርካታ የአሣሣል ስህተቶች እንዳገኙበት ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ በነበራቸው እውቀት የሠሩት ሥዕል እንደ መጀመሪያ ሥራነቱ እንደሚያስደስታቸው ግን አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ከዛ በኋላ ገዳም ውስጥ ሁሌም እሥል ነበር፤ እጄ አያርፍም፤›› ይላሉ፡፡

  በገዳሙ የተጣሉባቸውን ኃላፊነቶች እየተወጡ፣ በሚያገኙትን ክፍተት ሁሉ እየሣሉ ሳለ ከአንድ የሥዕል ችሎታ ያላቸው መነኩሴ ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ መነኩሴውን ሥዕል እንዲያስተምሯቸው ይጠይቃሉ፡፡ መነኩሴውም ፍቃደኛ ሆነው ትምህርት ይሰጧቸው ጀመር፡፡ ችሎታቸው እየዳበረ ሲሄድ በሚኖሩበት ገዳም ለአገልግሎት የሚውሉ ሥዕሎችን መሥራት ጀመሩ፡፡ ከዓመታት በኋላ ደግሞ ገጠራማ አካባቢ ላሉ ቤተክርስቲያኖች ሥዕል ይልኩ ጀመር፡፡ በተለይ ሥዕል ለሌላቸው የገጠር ቤተክርስቲያኖች ሥዕሎችን መስጠት እንደሚያረካቸው ይናገራሉ፡፡

  ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ እየተመላለሱ የሥዕል ቀለምና ሸራ መሸመት እንደጀመሩ መነኩሲቷ ይገልጻሉ፡፡ አዲስ አበባ ከመጡባቸው ዓመታት 2004 ዓ.ም.ን በተለየ ያስታውሱታል፡፡ በዛ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በአንድ የሥነ ጥበብ ተማሪ አማካይነት ከሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ጋር ይተዋወቁና የሠዓሊው ትምህርት ቤት በሆነ ኢንላይትመንት ዓርት አካዳሚ ሥነ ጥበብ መማር ይጀምራሉ፡፡ ለመማር ያቀዱት ለክረምት ብቻ ነበር፡፡ ክረምቱ ሲገባደድ ግን የመማር ፍላጎት ካላቸው ትምህርት ቤቱ ነፃ የትምህርት እድል እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው፡፡ ጊዜ ሳያጠፉ ለገዳሙ አሳወቁ፡፡

  መኖሪያቸውን ወደ ትውልድ አገራቸው አዲስ አበባ መልሰው ለሦስት ዓመታት ተማሩ፡፡ ዘወትር ከሰዓት ክፍል ገብተው እስከ አመሻሽ ይማራሉ፡፡ ሕይወታቸውን በምንኩስና ገዳም ውስጥ ማሳለፍ ከልጅነት ጀምሮ በልባቸው የሰረፀ ሕልማቸው ቢሆንም፣ ሰዓሊት ስለመሆን አሰላስለው እንደማያውቁ የተገነዘቡ ቤተሰቦታቸው ‹‹ምን አመላክቶሽ ነው?›› የሚል ጥያቄ አቅርበውላቸዋል፡፡ ሥዕሎቻቸውን በዓውደ ርእይ እስካሳዩበት ጊዜ ድረስም ብዙዎች ችሎታቸውን ያጠይቁ ነበር፡፡ በአንፃሩ  የሥዕል መምህራን ያበረታቷቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

  ለአንድ መነኩሲት ወጣቶች በሚበዙበት ትምህርት ቤት መማር ቀላል እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ መምህራኖቻቸው ሥዕሎቻቸው ጥሩ አንደሆኑ ባይነግሯቸውና ባይደግፏቸው ለመቀጠል እንደሚያዳግታቸው ያክላሉ፡፡ አስተማሪዎቻቸው ‹‹የሚኖሩበትን ሕይወት ያሳዩን፤›› እያሉ ይጠይቋቸዋል፡፡ የእሳቸውም ዝንባሌ ገዳማዊ ሕይወትን ማንፀባረቅ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት በ‹‹አንክሮ›› ዓውደ ርእይ አኗኗራቸውን እንዳሳዩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሥዕልን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ማዋል እፈልጋለሁ፤›› የሚሉት መነኩሲቷ፣ በሥዕሎቻቸው የመንፈስ ደስታ እንደሚያገኙ በመግለጽ ነው፡፡

  ከሥዕሎቻቸው መካከል ‹‹ፍቅረ እግዚአብሔር›› እና ‹‹በአት›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በገዳም ውስጥ ልዩ ልዩ ሥራ የሚከውኑ መነኮሳትን ያሳያሉ፡፡ እህል የሚለቅሙ፣ የሚወቅጡ፣ ውኃ የሚያመላልሱ እንዲሁም በጎጆአቸው ሆነው ጸሎት የሚያደርሱ መነኮሳት ይታያሉ፡፡ እማሆይ ወለተወልድ እንደሚናገሩት፣ ሥዕሎቹ የመነኮሳትን ሕይወት ያሳያሉ፡፡ ‹‹የገዳምን ሕይወት ለማያውቁ ገዳማዊ ሰው እየሠራም እየጸለየም እንደሚኖር ያሳያሉ፤›› በማለት ሥለ ሥዕሎቻቸው ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹ሥዕል ለኔ አይደለም፤›› ብለው ተስፋ የቆረጡባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በፈለጉት መንገድ ሥዕሎችን ማቅረብ ሲሳናቸው ተስፋ ቢቆርጡም አንዳች ቦታ ለመድረስ የነበራቸው ምኞት ዳግም ተስፋ እንደዘራባቸው ያስረዳሉ፡፡ በፊት በጨርቅ ላይ ከሣሉት የማርያም ሥዕል በእጅጉ የተሻለ እንደሆነ የሚያስረዱትና በዓውደ ርእዩ የሚገኘው በሸራ ላይ የተሣለ የማርያም ሥዕል ‹‹ምሥለ ፍቁር ወልዳ›› የሚል ስያሜ አለው፡፡ በሁለቱ ሥዕሎች መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ዛሬ የደረሱበትን ደረጃ እንደሚያመላክታቸው በሀሴት ተሞልተው ይናገራሉ፡፡ ይህን ሥዕል ለምሑር ገዳመ እየሱስ በስጦታ የሚያበረክቱት ይሆናል፡፡

  መነኩሲቷ የታደሟቸው የሥዕል ዓውደ ርእዮች ጥቂት ሲሆኑ፣ ‹‹ንግስ›› የተሰኘውን የሠዓሊ መዝገቡ ተሰማን ዐውደ ርእይ በይበልጥ ያስታውሳሉ፡፡ በብሔራዊ ሙዝየም በተካሄደው ዐውደ ርዕይ ስለተመለከቷቸውም ሥዕሎች በአድናቆት ይናገራሉ፡፡

  ‹‹በውስጥ ያለ ነገር ጊዜና ሰዓቱን ጠብቆ መውጣቱ አይቀርም፤›› ይላሉ እማሆይ ወለተወልድ፣ እሳቸውም ባለ ተራ ሆነው የሥዕል ዐውደ ርእይ ማዘጋጀታቸውን ሲገልጹ፡፡ ከተመልካች ጥሩ ምላሽ እንዳገኙም ያክላሉ፡፡ ‹‹ሥዕሎቹን መመልከት ገዳም ደርሶ የመመለስ ያህል ነው፤›› በሚል ያገኙት ምላሽ በይበልጥ አስገርሟቸዋል፡፡

  በዐውደ ርእዩ የቀረቡት ሥዕሉች እየተሸጡ ነው፡፡ ከሽያጩ በሚገኘው ገንዘብ ሸራና ቀለም የመግዛት እቅድ አላቸው፡፡ መስከረም ላይ ይኖሩበት ወደነበረው ገዳም ይመለሳሉ፡፡ የሥዕል ሥራቸውን ቀጥለው ሌላ ዐውደ ርእይ እንደሚያዘጋጁ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ አልጋ ባልጋ ባይሆንም ሥዕልና ምንኩስናን ጎን ለጎን ለማስኬድ መነሳታቸውን ያስረዳሉ፡፡

  ዓውደ ርእዩ ሰኔ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከከሰዓት ከተከፈተበት ጊዜ አንስቶ የእማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ ሙዚቃዎች በጋለሪው ይደመጣሉ፡፡ ‹‹ሁለታችንም መነኩሴ መሆናችንና እሳቸውም ሥዕል መሞከራቸው ያመሳስለናል፤›› ይላሉ እማሆይ ወለተ ወልድ፡፡ ዐውደ ርእዩ እስከ ሐምሌ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በአስኒ ጋለሪ ለሕዝብ እይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...