Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአምበርብር ጎሹ ሞት - የዴሞክራሲ እጦት

የአምበርብር ጎሹ ሞት – የዴሞክራሲ እጦት

ቀን:

እኛ ያለፈው ዘመን ቅሪት፣ የአሁኑ አካል፣ የወደፊቱ ደግሞ የመሸጋገሪያ ድልድዮች ነን፡፡ ያለፈው ዘመን ቅሪቶች በመሆናችን የጥፋቱም፣ የልማቱም፣ የክፉውም የደጉም፣ የምሥጋናውም እርግማኑም እባሽ ከላያችን ላይ ተፍቆ የማይጠፋ፣ በማንኛውም ሳሙና ብንፈገፍገው ለቆን የማይሄድ ቁርኝት ነው፡፡ አዕምሯችን ጥልቀት ያለው የትውስታ ጎጆ በመሆኑም አሁን የምናደርገውና ወደፊት የምናከናውነው ሁሉ፣ እኛ ባንወድም እሱ ራሱ ሰርፆ እየወጣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማንነታችንን በይፋ ያሳውቃል፡፡ ያሳብቃል፡፡ በተራ አባባል ያጋልጠናል፡፡

እና ከድሮ ትውስታ፣ ከድሮ ትዝታ፣ በበአዕምሯችን ጎጆ ውስጥ ከተከማቸው የመንፈስ ጥሪት፡-

‹‹ኧረ ስንቱ ስንቱ ናቸው የሞቱቱ

ለንጉሣቸው ክብር ለባንዲራይቱ››

የሚለውን የሟቹ ባለቅኔ መንግሥቱ ለማን ግጥም እናገኘዋለን፡፡ ታሪኩን እስቲ ከ40 ዓመታት በኋላ መለስ ብለን እንቃኘው? አንበርብር ጎሹ የተባለው ሰው፣ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ ብቻዋን ትሆናለች ይልና አመሻሽ ላይ ወደ አንዲት ወዳጁ ቤት ይሄዳል፡፡ ቤቷ እንደደረሰም ጥርቅም አድርጋ የዘጋችውን በር እንድትከፍት ይቆረቁራል፡፡ ዝምታ በመጀመሪያ ይሰፍናል፡፡ ደጋግሞ የመሰበር ያህል ሲቆረቁር ‹‹ሰው አለኝ፣ በሕግ አምላክ፣ በንጉሥ አምላክ፣ በሬን ሊሰብርብኝ ነው፤›› ትላላች፡፡ ያኔ አምበርብር ጎሹ ይናደድና ‹‹ለንጉሡ ይመኛታል››፡፡ በዚህ የተነሳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲገረፍ ይሞታል፡፡ ሞቱም ሴተኛ አዳሪ ወዳጁን ለንጉሡ በምኞቱ ሳይሆን በፖለቲካ ሆነና ባለቅኔው፣

‹‹ኧረ ስንቱ ስንቱ ናቸው የሞቱት

ለንጉሣቸው ክብር ለባንዲራይቱ››

በማለት ጽፈው አቆዩን፡፡

ስንኞቹ እንኳንስ ንጉሡን መቃወም አንዷን ወዳጅ ‹‹በንጉሥ አምላክ›› ብትል ‹‹ንጉሥ ይገናኝሽ›› ብሎ መልስ መስጠት ምን ያህል ከባድ እንደነበረ ያመለክታሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አካሂዶ በተነሳው ሕዝብ ስም በመነሳት ደርግ፣ ‹‹አይዞህ አታልቅስ፣ አይዞህ አትገፋ፣ አይዞህ አትጨቆን፣ እኛ ልጆችህ ደርሰንልሃል፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊት ከጎንህ ነን፡፡ በዚች ለብዙ ሺሕ ዓመታት ዴሞክራሲ ነጥፎባት በነበረች አገር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ዘር ለመዝራት፣ የዴሞክራሲን አዝመራ ለማምረት፣ በምታደርገው ጥረት ከግንባር እንጂ ከኋላህ አንገኝም፡፡ ሠራዊቱ ሕዝባዊ መንግሥት አቋቁሞ ወደ ጦር ሠፈሩ ይመለሳል፡፡ ላላማዬ ለነፃነቴ ለዓርማዬ፣ ወደፊት፣ ወደፊት ይላል ጉዞዬ…›› በማለት በጦር ሠራዊቱ ዘምሮና አዘምሮ ነበር፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ለታገሉትም ‹‹ጉሮ ወሸባዬ፣ ጉሮ ወሸባ፣ ጉሮ ወሸባዬ… እንዲያ እንዲያ ሲል ነው ግዳዬ›› በማለት አስዘፍኗል፡፡ በእርግጥም የዚያን ጊዜ የተዘመሩ፣ የዚያን ጊዜ የተነገሩ፣ የዚያን ጊዜ ቃል የተገቡ… ነገሮችን ዛሬም ቢሆን ማንም ሰው ከዘመኑ ጋዜጦች፣ የሬዲዮ ቴፖች፣ የቴሌቪዥን ፊልሞች፣ መጽሔቶች ማየትና መስማት ይችላል፡፡

ከገድለ ደርግ እንደምንማረው አፍታ ሳይቆይ የገባውን ቃል ለማጠፍ በልዩ ልዩ ምክንያቶችን መደርደር ጀመረ፡፡ ጎን ለጎንም ከጦር ሠራዊቱ እየመለመለ በየመንግሥታዊ ተቋማት ‹‹የለውጥ ሐዋሪያት›› እያለ መመደብ፣ ከጦር ሠራዊቱ አባላት መደበኛና መደበኛ ያልሆነ ሥልጠና እየሰጠ የተማሩ ሰዎች አለቃ አደረገ፡፡ ከእነዚህም አለቆች አንዳንዶቹ የሚያደርጉትን አያውቁም ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዱ ባለሥልጣን አንድ ጥያቄ፣ ወይም ጥናት ወይም ሌላ ሲመጣለት ‹‹ጓድ እኬሌ ብቻ በማለት ለሚቀጥለው ኃላፊ ይመራል፡፡ ሰውየው የልብ አውቃ ስለነበር እንዳመጡቱ፣ እንደሁኔታው እያየ አስተያየት ይሰጥ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ግን አስተያየቱን የሚሰጥበት ነገር ሆኖ ስላገኘው ‹‹ጓድ እከሌ›› ተብሎ በስሙ ለተመራለት ‹‹አቤት›› ብሎ መለሰ ይባላል፡፡ ይህንንም ለማለት የደፈረው ከአለቃው አለቃ ጋር በመወዳጀቱ ነበር፡፡

ሌላው ትልቅ ባለሥልጣን ደግሞ በየዓመቱ ‹‹ኢኮኖሚያችን አሥር በመቶ አደገ፣ ዘጠኝ በመቶ አደገ፣ …›› እያለ ለሕዝብ ዓመታዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡ ይኸው ባለሥልጣን ከዓመታት በኋላ ነገሩ ይከነክነውና ‹‹ጓድ እከሌ፣ የአሜሪካ ኢኮኖሚ፣ የብሪታንያ ኢኮኖሚ፣ የፈረንሳይ ኢኮኖሚ የሚያድገው አንድና ከአንድ በታች በሆነ መቶኛ ነው፡፡ እኛ እንዴት ከልመናና ከችግር ሳንወጣ፣ ይኸው እንደምታየው ረሃብ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የእኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ከበለፀጉት አገሮች የበለጠው?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሥልጣኑ (ሚኒስትሩም) ‹‹አየ ጌታዬ የእነሱ ጠሪ ከቆጣሪው ይበልጣል፡፡ የእኛ ቆጣሪ ደግሞ ከጠሪው ይበልጣል፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት የእኛ ከእነሱ በበለጠ ፍጥነት እያደገ መሄዱን ያመለክታል፡፡ ዋናው ነገር ሕዝብ የሚፈልገው ዕድገትን ነው፤›› በማለት መለሰለት ይባላል፡፡ ትልቁ ባለሥልጣንም ዓመታዊ ሪፖርቱን ለመንግሥት ምክር ቤት አቅርቦ በጭብጨባ ተቀባይነት አገኘ፡፡ ‹‹ብራቮ! ብራቮ! ብራቮ! ኢትዮጵያ በእርግጥም የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት እናደርጋታለን…›› ተባለ፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሰዎች አንዳች ክንውን ሲያዩ ‹‹ወንዳታ!›› እንደሚሉት ማለት ነው፡፡

ሆኖም በደርግ ጊዜ በረሃብ ያለቀው ሕዝብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነበር፡፡ ደመወዝ 30 ብር ሆኖ ጤፍ በኩንታል 60 ብር የገባበት ጊዜ መጣ፡፡ የበቆሎ ዋጋ ከአሥር ብር እስከ 40 ብር ደረሰ፡፡ ቤንዚን በሊትር ከአንድ ብር ወደ ሁለትና ሦስት ብር ገባ፡፡ የ25 ሳንቲም ታክሲ 50 ሳንቲም ሆነ፡፡ የአውቶቡስ ከአንድ ጣቢያ ወደሌላ ጣቢያ ከ25 ሳንቲም በመጀመሪያ ወደ 30 ቀስ ብሎ ወደ 50 ሳንቲም ገባና አረፈው፡፡

በዚህ ጊዜ አንዳንድ ምሁራን ‹‹ኧረ የለም፣ የዴሞክራሲ አካሄዱ እንደዚያ አይደለም፣ ከመንገዱ ወጣ ብላችኋል፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት የገባችሁትን ቃል እየናዳችሁት ነውና ሳታፈርሱ ፈጽሙት፡፡ ኧረ በሕግ አምላክ፣ ኧረ በደርጉ አምላክ…›› አላሉትም ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥም ታሪክን መለስ ብሎ መመልከት ወደፊት ለመራመድ ይጠቅማልና መለስ ብለን ስንመለከተው፣ ከ1967 እስከ 1971 ዓ.ም. ድረስ ደርግ በገባው ቃል መሠረት ወደ ጦር ሠፈሩ እንዲመለስና ሥልጣኑን ለሕዝቡ እንዲያስረክብ ሲጠየቅ፣ ‹‹ትቀልዳላችሁ እንዴ? ኧረ ለመሆኑ ሥልጣኑን የምሰጠው ለማንኛችሁ ነው? ለኢሕአፓ ነው? ለመኢሶን ነው? ለኢኮፓ ነው? ለኢጫት ነው?›› ሲል፣ ‹‹ኧረ ተው ክቡር እምክቡራን ደርግ፣ ሥልጣኑን የሚረከበው በምርጫ ተወዳድሮ የሚያሸንፈው ይሆናል፡፡ አንድም ተመራጩ ፓርቲ ይሠራል፡፡ ካለበለዚያም ከሌሎች አነስተኛ ድምፅ ካገኙት ጋር ግንባር ፈጥሮ ይሠራል፤›› ሲባልም፣ እርሱ ራሱም በወታደራዊ ክንፍ ሰበብ ወዝ ሊግና አብዮታዊ ሰደድ አቋቋመና ከቆየ በኋላ፣ ‹‹እኛም አለን!›› የሚል ሆነ፡፡ በአደባባይም፣ ‹‹እኛስ ምንስ ካኪ ለባሽ ብንሆን፣ ጥይት ተኳሽ ብንሆን ኢትዮጵያውያን አይደለምን? ሲቪሉ ይግዛ፣ ጦር ሠራዊቱ ሎሌ ሆኖ ይኑር የሚል ማን ነው? ደግሞስ አሁን ሥልጣኑን ለሲቪል ብንሰጥ ለሶማሊያ ወራሪ እጅ መስጠት አይደለምን? ለሻዕቢያና ለጀብሃ አገር ቆርሶ የመውሰድ ህልም (ምኞት) ዕውን ማድረግ አይደለምን? የሕዝቡን የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ ለፀረ-አብዮታውያን አሳልፎ መስጠት አይደለምን? በሉ አርፋችሁ ቁጭ በሉ፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ነንና እንገዛለን፤›› የሚል ዓይነት መልስ ሰጠ፡፡

በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ዝቅተኛ ንቃተ ሕሊና የነበራቸውን፣ በፋብሪካዎችና በመኖሪያ ሥፍራዎች በደባል በባህሪያቸው (በስርቆት፣ በማጅራት መቺነት፣ በሰካራምነት) የሚታወቁትን ግንባር ቀደም አብዮተኞች አድርጎ ምሁራንን አገለለ፡፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት፣ ሥዩመ እግዚአብሔር፣ ሞአ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩነቨርሲቲና የሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ምትክ፣ የጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም የኢሕድሪ (በመጀመሪያ የጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) ፕሬዚዳንት፣ በፊት የኢሠፓአኮ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን) በኋላም የኢሠፓ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ) ዋና ጸሐፊ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዘዥ የግለሰብ አምልኮ ተተካ፡፡

ያኔ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት፣ ሥዩመ እግዚአብሔር ለሕዝባቸው ሲሉ እንደ በረዶ በቀዘቀዘ ውኃ ውስጥ በርሜል ውስጥ ሲፀልዩ ያድራሉ እየተባለ ሲነገረን እንደነበረው ሁሉ፣ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምም ለሕዝባቸው የተሻለ ማኅበራዊ ሕይወት፣ ለአገራቸው አንድነትና ነፃነት ሲሉ በክኒን እንደሚኖሩ ተነገረን፡፡ የሚለበስ አጥተው የነተበ ካናቴራ እንደሚለብሱ ሰማን፡፡ ለዘበኛና ለቤት ሠራተኛ እንኳን ተቆርቋሪ መሆናቸው ተነገረን፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንታቸው በፈቃድ ወደ ኩባ ከመሄዳቸው በፊት ‹‹ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምን ብፁዕ ወቅዱስ›› በሚያሰኝ አነጋገር ያፈሰሱትን ቃል የምናስታውስ ሁሉ እስከ ዛሬ ሊገርመን ይችላል፡፡ ካስፈለገም ፊልሙ በቴሌቪዥን፣ ድምፁ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ጽሑፉ በሠርቶ አደር፣ በአዲስ ዘመን፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በአብዮታዊ ፖሊስ (ጋዜጦች)፣ በመስከረም፣ በየካቲትና  መጽሔት ስለሚገኝ ማየት፣ መስማትና ማንበብ ያቻላል፡፡  እግዚአብሔር ይይለትና ‹‹የቄሳር እንባ!›› በሚል ርዕስ የእሳቸውን ጉዳይ በትልቅ መጽሐፍ ባያወጣ ይህ ጸሐፊ እውነት ባልተባለ ነበር፡፡  

ዳሩ ግን የዴሞክራሲያዊ መብትን በማፈን ለዘመናት አቆያለሁ ብለው አስበው የነበሩት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የትየለሌ የአፍ መቆጣጠሪያ ኬላዎችን እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት አቋቋሙ፡፡ የሩሲያ፣ የኩባ፣ የቻይናና የቬትናም አብዮቶችን እየጠቃቀሱ ሕዝቡን የተስፋ ምግብ ይመግቡ ነበር፡፡ መስከረም 2 ቀን በመጣ ቁጥር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጓል፡፡ መስከረም 2 ቀን በመጣ ቁጥር የታንታለም ማዕድን፣ የወርቅ ማዕድን፣ የብረት ማዕድን፣ የድንጋይ ከሰል ማዕድን፣ የነዳጅ ማዕድን፣ የጋዝ ማዕድን… ወዘተ እንደሚወጣ በክቡር ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም፣ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አንደኛ ጸሐፊ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ይነገር ነበር፡፡ በኢሠፓ ጠቅላላ ጉባዔም ከውጭ አገር ይመጡ የነበሩ ታላላቅ ባለሥልጣናት፣ የአገር መሪዎች፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የዲፕሎማሲ አባላት ባሉበት ኢትዮጵያ ትንግርት የተሞላበት ሥራ እያከናወነች እንደምትገኝ በሙሉ ዕውቀት ሳይሆን በሙሉ ልብ ተነግሮ ነበር፡፡ ይህም የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሃብ ቸነፈር እየተገረፈና ቁምስቅሉን እያየ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡

‹‹የአስተዳደር በደልን፣ ጭቆናንና ብዝበዛን፣ ብኩንነትና ምዝበራን ይቆጣጠራል…›› ተብሎ ተቋቁሞ የነበረው አካል እንኳን ሳይቀር በርዕሰ ብሔሩ ላይ የሚወረወሩ ቃላትን፣ የጦር መሣሪያ አንጋች ያህል እንዲጠብቃቸው ታስቦ መቋቋሙ አዋጁ ራሱ ይጠቅማል፡፡ ዳሩ ግን ሕዝባዊነት የጎደለው ስለነበረ ጥቆማዎቹም ሆነ በጥቆማ ተነስቶ የሚደረገው ክትትል ከሚገባው በላይ ደካማ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ የፕሬዚዳንቱ አገርን የሚያጠፋ ተግባር መቃወም ፈጣሪን እንደመቃወም ተቆጥሮ ብዙዎች ወህኒ እንደማቀቁ፣ እየማቀቁም የፍዳ ዘመናቸውን ጨርሰው የሞቱ እንዳሉ ትዝታው ገና ከልቦናችን አልተፋቀም፡፡ የቀይና የነጭ ሽብር የበላቸውንም ታሪክ አይዘነጋቸውም፡፡

የአምበርብር ጎሹ ሞትንና የዴሞክራሲ ጥማትን አንስተን በቅርበት ስናስተውልና በዚህ የማስተዋያ መነፅር ተመሳሳይ ድርጊቶችን ስንቃኝበት፣ በሕዝቡ ስም የነገደው የደርግ መንግሥት ‹‹ወሸኔ ዴሞክራሲ›› እንዲባልለት ከፍተኛ የአፍ ድለላና ሽንገላ ቅስቀሳ አካሂዷል፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ ሕይወት ውሏን ባለመሳቷ የሐሰት ዴሞክራሲና ሕዝባዊ ተቆርቋሪነታቸው ሕዝቡን ተመልሶ በረሃብ፣ በእርዛት፣ በበሽታና በጦርነት እንዲኖርና እንዲያልቅ መደረጉን መሰከረች፡፡

ከዚያ መድረክ የሥልጣን ዘመን ልምድ አዕምሯችን መዝግቦት እንደሚገኘው፣ በሕዝቦች ብሶት የተነሳው የደርግ መንግሥት በዴሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በእኩልነት፣ በወንድማማችነትና በነፃነት ስም ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደር በደል ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ በደሉን እየፈጸመም እስከ መጨረሻው በበደል ላይ በደል መፈጸም አልታከተውም፡፡ እስከ ግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. መጀመሪያ ድረስ እንኳን ከየአንዳንዱ የአስተዳደር አካባቢ ከ25 ሺሕ ያላነሰ ሠራዊት ለመመልመልና የጦርነት ሰለባ ለማድረግ ሲዘጋጅ ነበር፡፡ ለዚህ ዝግጅት ግብ ማድረሻ ከእያንዳንዱ የአስተዳደር አካባቢ ከሦስት ሚሊዮን ብር ያላነሰ መዋጮ ይጠበቅ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ በአገሪቱ ነፃነት፣ አንድነትና ህልውና ስም ከመማልና ከመገዘት በስተቀር እርባና ያለውን ተግባር ሲያከናውኑ አልታየም፡፡ እነሱ ከቶ ምን በወጣቸው? ሌላው ቀርቶ ከደሃው ገበሬ ለእርድ የቀረበውን ወጣት አሠለጠንን ብለው ሲያስመርቁ እንኳን ‹‹ተወው የቁም ተስካሩን ይብላ›› ሲሉ አፋቸውን አይዛቸውም ነበር፡፡

ይሁንና  ወዳጁን ለንጉሡን የተመኛት አምበርብር ጎሹን አሁንም በዓይነ ህሊናችን እያስታወስን፣ አገሪቱን ለዚህ ሁሉ እልቂት ዳርጓት የሄደውን የመንግሥቱን ከኢ-ሰብዓዊ ግፉ ጋር ለአፍታ ብናስበው አምበርብር ጎሹ አርባ ተገርፎ በአሰቃቂ ሁኔታ ከሞተበት ቅጣት የከፋ እብሪት አረመኔነት የተመላ ግፍ በዴሞክራሲ ስም ግድያ፣ በዴሞክራሲ ስም የሀብትና የንብረት ዝርፊያ፣ በዴሞክራሲ ስም የራሱን ህልውና ለማጠናከር ሌላውን የመግደል ደባም ይፈጸም እንደነበረ ሥዕሉ በዓይነ ህሊናችን ተስተካክሎ ይመጣል፡፡

ይህም ሆኖኮ ዘውዳዊው ሥርዓትም ሆነ የአረመኔው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንደ ፋሽስት  አገዛዝ ሁሉ አጫፋሪ አልነበረውም ማለት ደግሞ አይደለም፡፡ ይኼ ግን የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንጂ የእኛ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በዚች ምድር ላይ የተፈጠሩትን ዕቡይ አምባገነን መሪዎችን ሁሉ መጥራት አስቸጋሪ ቢሆንም ፈረንሣዊው ናፖሊዮን፣ ጀርመናዊው ሂትለር፣ ሶቪየታዊው ስታሊን፣ ኢጣሊያዊው ሞሶሎኒ መጥቀስ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እነዚህ ዕውቅ የዓለማችን አምባገነኖችም ‹‹ዴሞክራሲን፣ ፍትሕን፣ እኩልነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ነፃነትን እንቁልልጬ›› ብለው ከማለፋቸው በፊት የዴሞክራሲ ውበትን በማሳየት ሕዝብን አጭበርብረዋል፡፡ የሰውን ኅሊና በሚያሳምን አንደበታቸውም ከእነሱ ጎን እንዲሠለፉ አድርገዋቸዋል፡፡ እነዚህ አምባገነኖች ግን በአውሮፓ ለዚያውም ዴሞክራሲ ተወልዶ ባደገባቸው አገሮች የተገኙ፣ ንቃተ ኅሊናቸው ከኢኮኖሚ፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂና ከባህሉ ዕድገት ጋር የዳበረ አመለካከት ያላቸው ሳይንቲስቶችን ከጎናቸው ያሠለፉ፣ አገርን ሳይሆን ዓለምን ሊለውጡ ይችላሉ ተብለው የተገመቱ መሆናቸውን ማጤን ይገባል፡፡

ስለትናንቱ የተዛባ የዴሞክራሲ ትርጉም ስናወሳ ደግሞ ዛሬስ በእርግጥ ዴሞክራሲ አለ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ የሚጠብቀን ያፈጠጠ እውነት ይኸው ነው፡፡ በእውነት ጠያቂ ሲመጣ፣ ይህ እውነት ያፈጠጠ ብቻ ሳይሆን ያገጠጠም ጭምር ይሆናል፡፡ ጥያቄው ‹‹ዛሬ በምድረ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሚባል ነገርስ የለም?›› ብሎ ከመጠየቅ ጋር እኩል ነው፡፡

‹‹ኧረ ስንቱ ስንቱ ናቸው የሞቱቱ

ለንጉሣቸው ክብር ለባንዲራይቱ››

የሚለው የባለቅኔው መንግሥቱ ለማ ግጥም በተቀዳሚነት የቀረበውም፣ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ያላንዳች ቁጥጥርና ሥጋት ሕዝብ በአደባባይም ይሁን በአዳራሽ እየሰበሰቡ ዓላማቸውንና የፖለቲካ መስመራቸውን እንዲያስረዱ ፈቃደኛ የሆነ ሁሉ ከእነሱ ጋር ተባብሮ እንዲሠራና የወደፊቷን ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር እንዲገነባ ማስቻል ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ በአንድ ድርጅት የሚሠራም ሆነ የሚመራ አለመሆኑን ማጤን ይገባል፡፡ የኢኮኖሚ ግንባታ፣ ልማትና ዕድገት ማለት የፖለቲካ ነፃነት፣ ፍትሕ የሞላበት ማኅበራዊ ሕይወት፣ የሰብዓዊ መብት መከበር፣ መሆኑን ረስቶ ወይም ቀርቶ በደመነፍስ መጓዝ፣ ወይም እኔ ራሴም በማላውቀው መንገድ ተጓዝ ማለት ትርፉ የዴሞክራሲን ደብዛ ማጥፋት ነው፡፡ ወደ ኃይል ዕርምጃ ማዘንበልም የሚስከትለው ነገር ቢኖር ሕዝቡ የማይፈልገውን የኃይል ዕርምጃ ለመፈጸም ማስገደድ ይሆናል፡፡ ዴሞክራሲ እኮ በሁሉም የሥራ መስክ በሁሉም የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ሥፍራ፣ የፖለቲካ ድርጅት ነፃ እንቅስቃሴ ማድረግ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ደግሞስ የዕድገት እንቅፋት በየአጋጣሚውና በየቦታው እየተደነቀረ ከርሃብ፣ ከእርዛት፣ ከጭንቀት ያልዳነ ሕዝብ እንደምን አድርጎ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ሊከበርለትም ሆነ ሊያስከብር ይችላል?

በጸሐፊው እምነት ዴሞክራሲው መጎልበት ያለበት በአንድ በኩል አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ህልውናውን ‹‹ዴሞክራት ነኝ›› ብሎ ያስታወቀ ድርጅት በወረቀት ሳይሆን (ለነገሩ አንዳንዱ ወረቀት የለውም) አመራር አባላቱ ዴሞክራሲን በአገሪቱ ለማስፈን ራሳቸው በገዛ እጃቸው ዴሞክራት ሆነው መገኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ መብትን ለማስከበር የሚቻለው የሌላውን መብት ሲያስከብሩና ሲያውቁ እንደሆነ መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡

አንድን ኢትዮጵያዊ በተወለደበት ክልል፣ በቋንቋው፣ በባህሉ እየጠሩ በጠላትነት መፈረጅ እጅግ አስቀያሚና የለየለት ዘረኛነት ነው፡፡ ‹‹እከሌ የተመረጠው በኢትዮጵያዊነቱ ነውና ሊያስተዳድረን ይገባል›› መባል ሲገባው፣ ‹‹ከሌላ ነውና የመጣን አይመራንም›› ማለትን የሚያህል ፋሽስታዊ አመለካከት የለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚለው አንድ ሰው የአካባቢውን ቋንቋ ካወቀና በአካባቢው ሁለት ዓመታት ያህል ከኖረ ተመርጦ እንደሚያገለግል ሲያስታውቅ፣ የብሔር ብሔረሰብ አከላለል የማይቀበሉ ነገር ግን የመልከዓ ምድራዊ አከላለል እንዲኖር የሚፈልጉ እንዲህ ዓይነቱ ዘረኝነትና መድልኦ የተሞላበት አስተሳሰብ ሲያራምዱ ማየት በእጅጉ የሚያሳፍር ነው፡፡ የአስተሳሰብ ነፃነትና የእምነት ነፃነት እንዲኖር የሚታገሉ መሆናቸውን በአንደበታቸው እየገለጹ በተግባር ግን የራሳቸው አመለካከትና እምነት ብቻ እንዲጎላ የሚጥሩ ሰዎችን ማየት የሚያሳፍር ነው፡፡ እነርሱ ራሳቸው፣ ለስውርና ለግልጽ አመጽ ምክንያት ሆነው ሌሎች ጭራሹኑ ያላሰቡትና በሰላም የሚኖሩትን ወደ ፍቅርና መከባበር ከማምጣት ይልቅ፣ ያለ ስማቸው ስም እየሰጡ ማስደንበር ከአደገኞች ሁሉ የበለጠ አደገኛ ነው፡፡  ይህም አሳፋሪና አደገኛ ድርጊት ዴሞክራቶች ነን ብለው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ከሚያከናውኑት እንደሚብስና አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህም በዚህ ጋዜጣ በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው ሁሉ፣ ለአገሪቱ ዕድገት በርካታ የግል ጋዜጦችንና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች እንዲኖሩ ማድረግ፣ እነዚህም የፕሬስ ውጤቶች ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመሩ ማድረግ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አሠራር ለሕዝብ አገልግሎት ማዋል ያስፈልጋሉ፡፡ ‹‹ሮም የተገነባችው በአንድ ሌሊት አይደለምና ዝግ በሉ…›› ማለትን ጨምሮ የሚያስጽፉ ብቻ ሳይሆኑ የሚጽፉ  የፖለቲካ መሪዎች ያስፈልጉናል፡፡ እነዚህም መሪዎች ፖለቲካን በፖለቲካ ለመመለስ ፍልስፍናቸውን፣ አመለካከታቸውን፣ ርዕዮታቸውን፣ እምነተቸውን በጋዜጦች የመጻፍና የመፋለም ልምድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተባ ብዕርም የጥላቻ ፖለቲካ ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ የአሜሪካም፣ የእንግሊዝም፣ የፈረንሣይም መሪዎች ተቃዋሚዎቻቸውን ሲፋለሙ የምናውቀው በብዕርተኝታቸው ነው፡፡

ዋናው ቁም ነገር የሕዝቡ ጥያቄዎች በመሪዎቻቸውና በባንዲራቸው ስም የሚሞቱ ሰዎች እንዳይኖሩ ምን መደረግ ይኖርበታል? ሰላማዊ ሕዝብ ሲፈልግ የሚሾመው ሳይፈልግ የሚሽረው መንግሥት እንደምን ሊመሠረት ይችላል? የመንግሥት መሪዎች ሕዝባዊ እንዲሆኑ ምን መላ ይፈጠር? የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ዘለዓለም መታመስ አያስፈልግም፡፡ ዴሞክራሲና ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም፣ ዴሞክራሲና ተከባብሮና ተዋዶ መኖር የአንድ ሳንቲም ግልባጮች ሲሆኑ፣ አንዱ ያለሌላው እያየናቸው ዴሞክራትነት ልንለው አንችልም፡፡ በጠመንጃ አፈሙዝ እየነዱ ለመኖር ማሰብም ፍፁም አያዋጣም፡፡ ወደምንፈልገው የልማት ግብ ለመድረስ የዴሞክራሲ አቅጣጫውን በትክክል ይዘን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሕዝብ መካከል ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች መካከል ቅራኔ ሊፈጠር የሚችልና ቅራኔውም በውይይት በማሳመን ወይም በድምፅ ብልጫ ሊወሰን እንደሚችል መገንዘብ ነው፡፡       

 ‹‹ኧረ ስንቱ ስንቱ ናቸው የሞቱቱ

ለንጉሣቸው ክብር ለባንዲራይቱ››

የተባለውም ግለሰቦችን አትቃረኑኝና አትቃወሙኝ፣ ሐሳባችሁን አትግለጹልኝ፣ አትጠይቁኝ፣ ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ወይም ከእሱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ድርጅቶች ሁሉ ዓላማቸውን በሕዝብ መካከል ሲያሰራጩ የሕዝቡን የአስተሳሰብ አድማስ በእነሱ አስተሳሰብ እንዳይቀነብቡት ሕዝቡም መንፈሳዊ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ መንግሥት ባለው አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀመ በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲመራ ወሳኝ ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ ሕዝባዊ የሆነ ዴሞክራሲም በቀላሉ ሊናጋ የማይችለው ለዚሁ ነው፡፡ ምዕራባውያን ‹‹ዴሞክራሲ ማለት ከሕዝብ ለሕዝብ በሕዝብ›› የሚሉት ሚስጥሩ ይኼው ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...