Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አንድ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተቀራርቦ የመሥራት ችግር አለ››

ዶ/ር ምሕረት አየነው፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር

የአገሪቱ የልማትና የዴሞክራሲ ግቦች ዕውን ለማድረግ ከመንግሥት በተጨማሪ የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) ትኩረቱን በመረጃ የተደገፉ ጥናትና ምርምሮች ላይ አድርጎ እ.ኤ.አ. 1998 ተቋቋመ፡፡ ተቋሙ ነፃ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምርምሮችን የማድረግና በምርምሮቹ ላይም ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሄድን አልሞ የተቋቋመ ነው፡፡ የተቋቋመው በምሁራንና የሲቪል ማኅበራት አቀንቃኞች ሲሆን ከትምህርታዊ ምርምሮች በዘለለ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችን ለውሳኔ ሰጪ የመንግሥት አካላት፣ ሕግ አውጪዎችና ለሕዝብ ውይይት እንዲበቁ ማድረግን ታሳቢ አድርጎ ነው፡፡ የምርምር ተቋሙን እንቅስቃሴ በሚመለከት ምሕረት አስቻለው ከተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት አየነው ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ እስካሁን የሠራቸው ትልልቅ ጥናቶች ምን ላይ ያተኮሩ ናቸው?

ዶ/ር ምሕረት፡-  ለመንግሥት ፖሊሲ ግብዓት መሆን የሚችሉ ብዙ ሐሳቦችን አመንጭቷል ማለት ይቻላል፡፡ በሚያደርጋቸው ጥናቶች ላይ ተመሥርቶም በርካታ ሕዝባዊ ውይይቶችን አካሂዷል፡፡ በሕዝባዊ ውይይቶቹ ተመራማሪዎች፣ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰቦች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ መሰል የጥናትና ምርምር ተቋማት በአንድ ላይ በተለየዩ ጉዳዮች መወያየት ችለዋል፡፡ ይህ የመንግሥት ፖሊሲዎችንና ሕዝብን ያቀረርባል ብለን እናምናለን፡፡ በኢኮኖሚ ልማት፣ በምግብ ዋስትና፣ በአካባቢ ጥበቃና ድህነት ቅነሳ የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ምርምሮች ተሠርተዋል፡፡ ጥናቶቹ ታትመው ለመንግሥት ለክልል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለመሰል ምርምር ተቋማትና ለሌሎችም ተሠራጭተዋል፡፡ እንደሁኔታው ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል በተባሉ ጉዳዮች ላይም ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህ ረገድ የከሰል አመራረትና ደን ጭፍጨፋ፣ የአረቄ ምርትና ግብይት ላይ ያተኮሩት ጥናቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ቀደም ያሉት ሲሆኑ ጥናቶቹ ለፖሊሲ አውጪዎች ተሠራጭተዋል፡፡ በቅርቡ በቴሌቪዥን እንዲሠራጭ ያቀድነው በአረቄና በከሰል አመራረት ላይ የተሠራ ዘጋቢ ፊልም አለ፡፡ በቅርብ ከተሠሩትና አሁንም እየሠራንበት ካለው የጫት አመራረትና ኢኮኖሚያዊ አንድምታው እንዲሁም አሉታዊ ተፅዕኖው ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች ቅድሚያ የተሰጣቸው ትኩረታችን አንገብጋቢ የሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ውጪ ትኩረት የምታደርጉባቸው ጉዳዮች?

ዶ/ር ምሕረት፡- የጨመርናቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የገጠር መሬት አስተዳደር፣ ልማትና ድህነት ቅነሳ ላይ ሰፋ ያለ በሰሜን፣ በኦሮሚያና በደቡብ ጥናት እየሠራን ነው፡፡ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (IGAD) የሚደግፍና በአርብቶ አደር አካባቢዎች የመሬት ሥርዓትና አጠቃቀም ላይ የሚያተኩር ጥናት እያካሄድን ነው፡፡ እነዚህ ጥናቶች ሲጠናቀቁ በማስረጃ ተደግፈው በባለሙያ ለሕዝብ ይቀርባሉ በውይይትም ይዳብራሉ፡፡ የምሁራን ስብስብ እንደመሆኑ ተቋሙ የሚሠራው ሌላ ነገር መንግሥታዊ ላልሆኑና የአቅም ውስንነት ላለባቸው የልማት ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ ይህ የድርጅቶቹን የሥራ አመራርና ፕሮጀክቶችን የመቅረፅና የመተግበር አቅም መገንባት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የሠራቸው ጥናቶች ምን ያህል ለፖሊሲ ግብዓት መሆን ችለዋል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ምሕረት፡- ተቋሙ ብዙ ዕውቀት ከሚያመነጩ ተቋማት አንዱ ነው፡፡ የፖሊሲ ሐሳብ የሚያመነጩ፣ ግብዓት የሚሆኑ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ብዙ አሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ጋር በመሆን ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል እንጂ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ለብቻው ይህን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል ብሎ መናገር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ዓላማውም በሌሎች የሚደረገውን ጥረት ማገዝና የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት፣ እንደ አገር የሚደረገውን ነገር መደገፍ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ምን ያህል አግዟል ብለውስ ያምናሉ?

ዶ/ር ምሕረት፡- እገዛው በመረጃ የተደገፈ ዕውቀት በማበርከት ረገድ እንደ አንድ የኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚታይ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የተጫወተው ሚና አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ ሕዝባዊ ውይይቶች አሉ?

ዶ/ር ምሕረት፡- እያካሄድናቸው ያሉ ሁለት ሕዝባዊ ውይይቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላት ድህነትን ለመቅረፍ ከመንግሥት ጋር በመሆን ምን ዓይነት ሚና መጫወት አለባቸው? የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጥረትስ እንዴት ይቀናጃል? በሚሉት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ሁለተኛው ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ሲሆን የከተማ የሕዝብ አገልግሎቶች ትራንስፖርት፣ ጤና፣ የመኖሪያ ቤትና የመሳሰሉት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ይህ ሕዝባዊ ውይይት ለመጠናቀቅ ሁለት ወይም ሦስት ዙር ይቀረዋል፡፡ እነዚህ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙን ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ካሉ?

ዶ/ር ምሕረት፡- አንዱ ችግራችን ውስጣዊ ነው፡፡ በማኅበራዊና በልማት ጉዳዮች ላይ የምናስባቸውን ጥናቶች በምንፈልገው ደረጃ ለማካሄድ የአቅም ውስንነት አለብን፡፡ ይህ በአንድ በኩል በምንፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በምናስበው መጠን እንዳንሠራ አድርጎናል፡፡ በሌላ በኩል ይኸው ችግር የሰው ኃይልን ጨምሮ በብዙ መልኩ ራሳችንን እንዳናጠናክር አድርጎናል፡፡ ሌላው ያጋጠመን ችግር የኔትወርኪንግ ነው፡፡ በራሳችን እንደተመለከትነው በአገራችን አንድ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተቀራርቦ የመሥራት ችግር አለ፡፡ እኛ የምንፈልገው ጥናትና ምርምር ስናደርግ የሚመለከታቸው ሁሉ አብረውን እንዲሠሩና እንዲሳተፉ ነው፡፡ ነገር ግን በጥናቶቻችን አጋር እንዲሆኑን የምንፈልጋቸው ተቋማት አብርውን እየሠሩ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የምትሠሯቸው ጥናቶች ጉዳዩ በሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትስ እንዴት ነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- በመጀመሪያ የጥናቱ ይዘት ምን መሆን አለበት? በመጨረሻስ ከጥናቱ የምንጠብቀው ምንድነው? በሚሉና በመሰል ጉዳዮች እኛ ተወያይተንና ተከራክረን ነው የምንወስነው፡፡ ጥናቱን ይፋ ስናደርግ ባለሥልጣናትን ጨምሮ እስከታች ያሉ ባለሙያዎችን በውይይት ላይ ተገኝተው የተሠሩት ጥናቶች ግኝቶች መሬት ላይ ካለው ሁኔታ ጋር አብረው ይሄዳሉ? ትርጉምስ ይሰጣሉ በሚለው ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ እንጋብዛለን፡፡ በተለይም የጥናቱ ተግባራዊነት ላይ የእነሱ አስተያየት ትልቅ ቦታ አለው ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ቅር የሚያሰኘን የእነዚህ የምንጋብዛቸው አካላት አለመገኘት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቶቻችሁ ትምህርታዊ ሳይሆን ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን የምታረጋግጡት እንዴት ነው?  

ዶ/ር ምሕረት፡- የጥናቱን ንድፈ ሐሳብ ስንቀርጽ መጀመሪያ ለፖሊሲ ተግባራዊ ግብዓት መሆን እንዲችል እናደርጋለን የጥናቶች ጥያቄዎችም በዚህ መልኩ ነው የሚቀረጹት፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣይ ትኩረታችሁ ምንድነው?

ዶ/ር ምሕረት፡- በአገር ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ማኅበራዊና የልማት ጉዳዮች ላይ እስከዛሬ ስናደርግ እንደነበረው በመረጃ የተደገፈ ጥናትና ምርምር መሥራታችንን በሰፊው መቀጠልና ዕውቀት ማምረት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...