Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእስራኤሉ ኩባንያ የአላና ፖታሽ የግዥ ስምምነት ተጠናቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የኩባንያው አሻሻጥ አሁንም አነጋጋሪ እንደሆነ ነው

እስራኤል ኬሚካልስ የተባለው ኩባንያ የአላና ፖታሽ የግዥ ሒደትን ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቁንና የኩባንያው የኢትዮጵያ ፕሮጀክት መጠሪያ አላና ፖታሽ ሆኖ እንዲቀጥል መወሰኑ ተገለጸ፡፡

በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተፈጸመው የግዥና የሽያጭ ስምምነት መጠናቀቅን በማስመልከት የእስራኤሉ ኩባንያ በላከው መረጃ የአላና ፖታሽ 83.78 ከመቶ ድርሻ በመግዛት 137 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ክፍያ መፈጸሙን ይገልጻል፡፡

እንደ ኩባንያው መረጃ ባለፈው መጋቢት 2007 ዓ.ም. ከአላና የአክሲዮን ድርሻ 16.22 ከመቶውን በ25 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር መግዛቱን በማስታወስ አሁን ደግሞ ቀሪውን 83.78 በመቶ በመግዛት የአላና ኩባንያ የነበሩትን ሁሉንም አክሲዮኖች ገዝቷል፡፡

በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ይፋዊ ይሁንታ ያለማግኘቱ እየተገለጸ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነት ስምምነቶች ሲደረጉ የማዕድን ሚኒስቴር ሊያውቅ እንደሚገባ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ እስካለፈው ሳምንት ድረስ የማዕድን ሚኒስቴር በይፋ የደረሰው መረጃ ባይኖርም፣ የአላና ፖታሽ አደራጅና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጅብ አባብያ ስለጉዳዩ እንዳሳወቁ ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ ነጅብ ገለጻ የኩባንያው የሽያጭ ሒደት በተለየ ተከናወነ ነው፡፡ አላና ኩባንያውን ሳይሆን የሸጠው የኩባንያው ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን ለእስራኤሉ ኩባንያ እንዲሸጡ ነው የተደረገው በማለት አላና ኩባንያ አሁንም ያለ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

አንድ ኩባንያ ለሌላ ኩባንያ ሲተላለፍ ስለአጠቃላይ ዝውውሩ ሊፈጽሙ የሚገባቸው ሒደቶች ቢኖሩም፣ የእስራኤሉ ኩባንያ የገዛው አክሲዮኖችን በመሆኑ የአላና ፖታሽ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት እስካሁን ባለው ሒደት የሚቀጥል ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት ያነጋገርናቸው አንድ የማዕድን ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ እንደገለጹት፣ የኩባንያው ዝውውር ሕጋዊ መንገድ መከተል ይኖርበታል የሚል ነበር፡፡ አቶ ነጅብ ደግሞ የኩባንያው ዝውውር የተመሠረተው የአክሲዮን ባለቤቶች ባደረጉት የአክሲዮን ሽያጭ በመሆኑ ሕጋዊ ስምምነት ተፈጽሟል ይላሉ፡፡ ስለ ኩባንያው ዝውውር ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ነጅብ፣ የእስራኤሉ ኩባንያ መጀመሪያም ቢሆን 16 በመቶ አካባቢ ድርሻ ሊይዝ የሚያስችለውን አክሲዮኖች ገዝቶ ነበር፡፡ ይህንንም በ26 ሚሊዮን ዶላር እንደገዛው አቶ ነጅብ ይናገራሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉንም አክሲዮኖች ልግዛ በማለቱ ባለአክሲዮኖችም አላና እየከሰረ ነውና አክሲዮኖቻችንን እንሽጥ በማለታቸው እያንዳንዱ ባለአክሲዮን አክሲዮኑን ለእስራኤሉ ኩባንያ ሸጧል ይላሉ፡፡

ባለአክሲዮኖቹ ያላቸውን አክሲዮን የሸጡትም በተለያዩ ዋጋዎች እንደሆነ የገለጹት አቶ ነጅብ፣ አንዳንዱ አክሲዮን በ2.40፣ በ1.50፣ 2.00፣ በ0.50 የካናዳ ዶላር ጭምር መሸጡን ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ባለ በተለያየ አጠቃላይ ዋጋ የገዛቸውን አክሲዮኖች ዋጋ ከ130 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ ነው፡፡ የአላና ባለአክሲዮኖችም እንደየድርሻቸው አክሲዮን በሸጡበት ዋጋ ልክ ገንዘባቸውን እንደወሰዱ አቶ ነጅብ ተናግረዋል፡፡

አላና ኩባንያውን የሸጠው በካናዳ ያለው የፖታሽ የአክሲዮን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመውረዱና የዓለም የፖታሽ ምርት ዋጋ በእጅጉ በመቀነሱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህንን የገበያ ሒደት ተሸክሞ ለመቆየት አቅም ስለሌለ አሁን ያለውን ገበያና የወደፊቱን በማየት የእስራኤሉ ኩባንያ የተሻለ አቅም ስላለው የአላና ፖታሽ አክሲዮኖችን ሊገዛ መቻሉን የአቶ ነጅብ ገለጻ ያስረዳል፡፡

በዚህ የኩባንያ ዝውውርም የአላና ፖታሽ በአፋር ክልል ደንከል ያለውን ፕሮጀክቱ መጠሪያ ስም አላና ፖታሽ ሆኖ እንዲቀጥልም ተደርጓል፡፡ አዲሱ የአላና ፖታሽ ባለቤትም አዳዲስ ቦርድ አባላትን የሰየመ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ያሉ ሠራተኞችንም እንዳለ ይዞ ለመቀጠል ተስማምቷል፡፡ በቀድሞው የኩባንያው ባለይዞታ (አላና ፖታሽ) በአካባቢው የአዋጭነት ጥናት ያደረገ ቢሆንም፣ የእስራኤሉ ኩባንያ ተጨማሪ የአዋጭነት ጥናት እንደሚያደርግ ባለፈው ሳምንት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡

በዚህ ምክንያት የሎጂስቲክ፣ የመሠረተ ልማት፣ የምርት ፍላጎትና የምርቱን መጠን ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን ያካሂዳል፡፡ በቀድሞ ጥናት በአካባቢው ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ ፖታሽ በዓመት መመረት የሚችል መሆኑን ያሳያል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የእስራኤሉ ኩባንያ በደንከል የፖታሽ ክምችትን በማሳደግ ተጨማሪ የምርት ይዞታዎችን የመያዝ ዕቅድ አለው፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ኩባንያው የላከው መግለጫ ላይ የእስራኤል ኬሚካልስ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቴፈን ቦርጋስ እንደተናገሩት፣ የአላና ፖታሽ ኩባንያን ድርሻ ሙሉ በሙሉ በመያዛቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል፡፡ ‹‹የአላና ግዢ በዋናነት ኩባንያችን የያዝነውን ስትራቴጂ የሚያስፈጽምና በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የምናቀርበውን የጥሬ ማቴሪያል ሽፋን ያሳድጋል፤›› ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያም ጭምር በከፍተኛ መጠን እያደገ ያለውን የማዳበሪያ ፍላጎትም የመሸፈን አቅም ይፈጥርልናል ያሉት ስቴፋን፣ ከዚህም በላይ ገበያችንን ወደ እስያ ገበያ የሚያሳድግና በአሁኑ ወቅት በስፔን፣ በእስራኤልና በእንግሊዝ ውስጥ በፊት ያለንን ገበያ ወደ ሌሎች አገሮች ያሰፋልናል ብለዋል፡፡

የአላና ኩባንያ ሽያጭ የበለጠ ጠቀሜታ ይሰጣል ያሉት አቶ ነጅብ ደግሞ፣ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ተወስኖ የአላናን ኩባንያዎች የእስራኤሉ ኩባንያ ባይገዛ ኖሮ ይህ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት በጅምር ይቀር ነበር ይላሉ፡፡ አሁን ግን የአላናን ጅምር የእስራኤሉ ኩባንያ የሚቀጥለው በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች