Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ የውጭ አማካሪ ኩባንያ ምርጫና የአራቱ ዓለም አቀፍ አማካሪዎች ፉክክር

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ በመቀላቀል ወደ ሥራ የገባው ከ19 ዓመት በፊት ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ከተቋቋሙ የመጀመሪያዎቹ ሦስት የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ባንኩ ከደርግ ውድቀት በኋላ የመጀመሪያው የግል ባንክ በመሆን ከሚጠቀሰው አዋሽ ባንክም በፊት ቀድሞ ወደ ሥራ ሊገባ የሚችል ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በአቢሲኒያ ባንክ አደራጆችና መሥራቾች መካከል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ከሁሉም ቀድሞ ወደ ሥራ ለመግባት የነበረውን ዕድል አሳልፎ እንዲሰጥ አድርጐታል፡፡ አደራጆቹ እንደአነሳሳቸው ቢቀጥሉ ኖሮ አቢሲኒያ የመጀመሪያው የግል ባንክ ይሆን እንደነበር የቀደሙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ወደ ሥራ ከገባ በኋላም ከሌሎች ባንኮች በተለየ ችግሮች ገጥመውት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በተረጋጋ የሥራ ሒደት በመጓዝ ላይ መሆኑ የባንኩ የሥራ መሪዎች ይገልጻሉ፡፡ አቢሲኒያ ባንክ ባለፉት 19 ዓመታት ከሳምንት በላይ ፕሬዚዳንቶች ለመቀያየሩ ምክንያት ቀድሞ የነበረበትን ችግር አመላካች መሆኑ ይነገራል፡፡   

በ131 ባለአክሲዮኖችና በ18.7 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ የገባው አቢሲኒያ ባንክ በአሁኑ ወቅት በካፒታል፣ በእሴት፣ በደንበኞች ቁጥር፣ በማበደር አቅሙና በሌሎች የባንክ አገልግሎቶች ቀዳሚ ናቸው ከሚባሉት ስድስት የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር አሳድጓል፡፡ 462,000 ደንበኞች ሲኖሩት፣ የተቀማጭ ገንዘቡ ደግሞ 11 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡  

በአሁኑ ወቅት ቀድሞ ይታዩበት የነበሩትን ክፍተቶች በመድፈን የባንኩን አቅም የበለጠ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸውን የባንኩ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡

በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጥሩ ተወዳዳሪና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን አቅም ለመገንባት ያግዘኛል ያለውን አዲስ ስትራቴጂካዊ  ዕቅድ ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግም እየተዘጋጀ ነው፡፡

በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ባንኩ የሚመራበትን መሪ ዕቅድ (Strategic Plan) እንዲቀርጽለት ደግሞ ዲሎይት የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ በመምረጥ ሥራ ማስጀመሩን ባለፈው ሰኞ ይፋ አድርጓል፡፡ የባንኩን መሪ ዕቅድ ለማዘጋጀት አሸናፊ ከሆነው ዲሎይት ጋርም ባለፈው ሰኞ በሒልተን ሆቴል ተፈራርሟል፡፡ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የኮንትራት ስምምነት በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የባንኩን መሪ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ የተመረጠው ኩባንያ ሥራውን ባለፈው ሳምንት በይፋ ጀምሯል፡፡

ዲሎይት የተመረጠው እንዲህ ያሉ ስትራቴጂ ፕላኖችን በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ አራት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በመወዳደር አሸናፊ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ ይፋ አልተደረገም፡፡ የአንዳንድ ወገኖች ግምት ግን ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ነው፡፡  

አማካሪ ድርጅቱ የባንኩን መሪ ዕቅድ በስድስት ወራት አጠናቆ ለባንኩ እንደሚያስረክብ በኮንትራት ውሉ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከመሪ ፕላኑ ዝግጅት ሌላም ለአንድ ዓመት የስትራቴጂውን አፈጻጸም በመከታተልና በመተግበር ሥራ ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡

ባንኩ ለተከታታይ ዓመታት እመራበታለሁ ያለውን መሪ ዕቅድ በውጭ አማካሪዎች እንዲሠራ ከማድረጉ ቀደም ብሎ ሦስት የተለያዩ የስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ሲሠራበት ቆይቷል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሠረት ታዬ እንደገለጹት፣ ባንኩ የተለያዩ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን በመቅረፅ ሲሠራበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የቀደሙት የባንኩ ስትራቴጂክ ዕቅዶች በቅጥር ሠራተኞችና ከአገር ውስጥ አማካሪዎች ጋር በመዋዋል እንዲሠራ ቢደረግም፣ እነዚህ ጉዞዎች በአመቺ ሁኔታ የተጓዙ ስላልነበሩ ባንኩ ወደ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፊቱን ሊያዞር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የቀደሙት ስትራቴጂክ ዕቅዶች በወቅቱ የነበረውን ውድድር ለመወጣት አስችሎናል የሚሉት የባንኩ ኃላፊዎች፣ አሁን ግን የባንኩን መሪ ዕቅድ ዝግጅት ለውጭ አማካሪዎች ግድ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አስማረም በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተቀያየረ የመጣው የባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገት በቴክኖሎጂና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የሚሠራበት ዘርፍ ሆኗል ይላሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት አቢሲኒያ ባንክ በውድድር ተመራጭ እንዲሆንና አትራፊነቱን ለማሳደግ ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያዎች የሙያ እገዛ ጠቀሜታነቱን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከዴሎይት ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

እንደ ባንኩ መረጃ በአሁኑ ወቅት እያደገ ባለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ለማበርከት፣ እየሰፋ የመጣውን የባንክ ተገልጋዮች ለማርካት፣ እየተወሳሰበ የመጣውን በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን ውድድር በብቃት ለመወጣትና የባንኩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር መሥራትን መርጧል፡፡

የመንግሥትን፣ የባንኩን ባለአክሲዮኖች፣ የደንበኞችንና የሠራተኞችን ፍላጐት ጭምር ለማርካት ዘመኑ የሚጠይቀውን የባንክ አሠራር መከተል የግድ በመሆኑ፣ በባንክ አሠራርና ማማከር ሥራ ዓለም አቀፍ ልመድ ያላቸውን ኩባንያዎች ጋር መሥራት ለተሻለ ውጤት ያደርሳልም የሚል እምነት አላቸው፡፡

በቀጣይ ዓመታት ያገለግላል የተባለው መሪ ዕቅድ የሚቀረፀውም የባንኩ ውስጣዊና ውጫዊ ተጨባጭ ሁኔታ፣ የዓለም አቀፍ ሁኔታዎችና ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ባጣጣመ መልክ ነው ተብሏል፡፡

ይህ ዕቅድ ሥራ ላይ ሲውል ባንኩ አሁን ካለበት ደረጃ ያሸጋግረዋል ያሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ይህ ስምምነት አቢሲኒያ ባንክን እ.ኤ.አ. በ2025 መጨረሻ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ብቃት ያለው የንግድ ባንክ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ዲሎይት መመረጡ ደግሞ በተለየ የሚታይ ነው የሚሉት አቶ መሠረት፣ መሪ ዕቅዱን እንዲሠራ ዲሎይት የኢትዮጵያን ገበያ ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ የተፈለገውን ግብ ለማምጣት የሚያስችል ሥራ ይሠራል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ዲሎይት ከ170 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ኩባንያ ነው፡፡ ስለኩባንያው የሚያትቱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ዲሎይት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኔትዎርክ የተገናኙ 47 አባል ኩባንያዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ አባል ኩባንያዎቹ በራሳቸው ነፃ የሆኑና ሕጋዊ ሰውነት የተላበሱ ስለመሆናቸው የኩባንያው መረጃ ያስረዳል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የመንግሥት ድርጅቶች የማማከር አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካም ራሱን የቻለ ተቋም በማደራጀት በስድስት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጽሕፈት ቤት በመክፈት እየሠራ ነው፡፡ የኩባንያው ጽሕፈት ቤት ለሚገኙባቸው አገሮች መካከልም አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡

ጠንካራ የፋይናንስ አቅም አለው የተባለው ይህ ኩባንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩባንያው ሥር ከሚንቀሳቀሱ አባል ኩባንያዎቹ እ.ኤ.አ. በ2014 ብቻ ከ34.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝተዋል፡፡ እነዚህ አባል ድርጅቶች 210 ሺሕ ሠራተኞች አሏቸው፡፡ በአፍሪካ ከአምስት ሺሕ በላይ ሠራተኞችን መቅጠር የቻለ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ቢዝነሱ ገቢ በዓመት ከ600 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያገኘ ነው ተብሏል፡፡

እንደ አቢሲኒያ ባንክ ሁሉ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለፈበት ሳምንት ኤፒኤምጂ ከተባለው ኩባንያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሌሎች የግል ባንኮችም ተመሳሳይ መንገድ ለመጓዝ ውጠን እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ የማማከርና መሪ ዕቅድ በማዘጋጀቱ ሥራ ላይ በመሳተፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ እየገቡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአንድ ሳምንት ልዩነት ለአዋሽና ለአቢሲኒያ ባንኮች መሪ ዕቅድ እንዲዘጋጅላቸው ባወጡት ጨረታ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ተመሳሳይ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ኤፒኤምጂ፣ ኧርነስት ኤንድ ያንግ፣ ዲሎይትና ፕራይስ ወተር ሃውስ ኮፐርስ ናቸው፡፡

አዋሽ ኤፒኤምጂን አሸናፊ ሲያደርግ፣ አቢሲኒያ ደግሞ ዲሎይትን መርጧል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካሪነት የሥራ ዘርፍ የእነዚህ ኩባንያዎች ስም በቀዳሚነት የሚጠራ ነው፡፡

የ2014 የአማካሪዎችን ዓለም አቀፍ ቢዝነስ የተመለከተ ጋትነር የተባለው የመረጃ ምንጭ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ፣ የአማካሪነት አገልግሎት ዘርፍ ቢዝነስ በ2014 በ6.1 በመቶ አድጐ የ125.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡

በዚሁ ሪፖርት መሠረት የመጀመሪያዎቹ አማካሪ ድርጅቶች ናቸው ተብለው የተጠቀሱት አራቱ ኩባንያዎች፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ባንኮች ባወጡዋቸው የማማከር አገልግሎት ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ ላይ ያሉት ዲሎይት፣ ኧርነስት ኢንድ ያንግ፣ ኤፒኤምጂና ፕራይስ ወተር ሃውስ ኮፐርስ ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የአማካሪነት የአገልግሎት ገበያን 40.1 በመቶ መያዛቸውን ይኸው የጋትነር መረጃ አመልክቷል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ኩባንያዎችን በማማከር የሚታወቁ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተፎካከሩ ይገኛሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች