[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው በአስቸኳይ እንዲመጣ ነገሩት]
- ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- በሚገባ መዘጋጀት አለብን፡፡
- የምን ዝግጅት ነው?
- ለውይይቱ ነዋ፡፡
- የትኛው ውይይት ክቡር ሚኒስትር?
- የጂቲፒ 2 ውይይት ነዋ፡፡
- እሱ ላይማ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ አለብን፡፡
- አዎና፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል፤ ወደ ሁለተኛውም እየተሸጋገርን ነው፡፡
- እንግዲህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ለሁለተኛው ዋነኛ ግብዓት ይሆናል፡፡
- ለመሆኑ ከእነማን ጋር ነው ውይይት የምናካሂደው?
- ከወጣቶች ጋር፡፡
- እነሱማ የእኛው ናቸው፡፡
- ከሴቶች ጋር፡፡
- እነሱም የእኛ ደጋፊዎች ናቸው፡፡
- ከምሁራን ጋር፡፡
- እነሱን ፍራ፡፡
- ከግሉ ዘርፍ ጋር፡፡
- እነሱም ሌላ የራስ ምታት ናቸው፡፡
- ለምን ግን ክቡር ሚኒስትር?
- ምሁራንና የግሉ ዘርፍ ቻሌንጅ ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡
- እኮ ለምን?
- በመጀመሪያው ጂቲፒ ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እምብዛም ነበር፡፡
- እሱማ ጥፋታችን ነው፡፡
- ስለዚህ አሳማኝ ሐሳብ ይዘን መቅረብ አለብን፡፡
- የምን አሳማኝ ሐሳብ?
- ለምን በመጀመሪያው ጂቲፒ ትኩረት እንዳልሰጠናቸው ነዋ፡፡
- ለእሱማ ይቅርታ መጠየቅ እንጂ አሳማኝ ሐሳብ ማቅረብ አይጠቅመንም፡፡
- እሷ ነገር እኮ ናት ደስ የማትለኝ፡፡
- የቷ ነገር?
- ይቅርታ የሚሏት፡፡
- እንዲያውም እኛ በዚህ እንጀምረው ብለን ነው እንጂ ያደለው ጋማ ቁንጥጫ አለ፡፡
- የምን ቁንጥጫ?
- ክቡር ሚኒስትር አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፡፡
- እሺ ቀጥል፡፡
- አንድ ዜጋ የኤሌክትሪክ ሒሳቡን ካልከፈለ ምን ይደረጋል?
- ኤሌክትሪክ ይቋረጥበታል በዚያ ላይ ቅጣት ይጣልበታል፡፡
- መንግሥት ኤሌክትሪክ ሲያቋርጥስ ምን ይደረጋል?
- ምንም፤ ደግሞ ምን እንዲደረግ ፈለግክ?
- ይኼን ነው የምልዎት፡፡
- እኮ ምንድነው የምትለኝ?
- ሕዝቡ የኤሌክትሪክ ሒሳቡን ካልከፈለ፣ ይቋረጥበታል ደግሞም ይቀጣል፡፡
- ያ መንግሥትን ኪሳራ ላይ ስለሚጥለው እኮ ነው፡፡
- መንግሥት ግን ኤሌክትሪክ በማቋረጡ ሕዝቡ ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ አይጠየቅም፡፡
- እ…
- ስለዚህ ቁንጥጫ ያልኩዎት ይኼንን ነው፡፡
- እና መንግሥትም መቆንጠጥ አለበት፡፡
- መንግሥት ሲያጠፋ መቆንጠጥ መጀመር አለበት፤ ባህልም ሊሆን ይገባል፡፡
- ጥሩ ነጥብ ነው ያነሳኸው፡፡
- ለምሳሌ ባለፈው የፈጠርነውን ትርምስ ያስታውሳሉ?
- የምን ትርምስ?
- ፕሮቪደንት ፈንድን አስመልክተን ባወጣነው ረቂቅ የተፈጠረው ትርምስ ነዋ፡፡
- ረቂቁን ያወጣነው እኮ ለሕዝቡ አስበን ነው፡፡
- ምን አሉኝ?
- ረቂቁን ያወጣነው ለሕዝቡ አስበን ነው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ሁሉም የግል ድርጅት ሠራተኞች በጡረታ ቢታቀፉ ያዋጣቸዋል፡፡
- እንዴ ለምን?
- ጡረታ ዘለቄታዊ ማኅበራዊ ዋስትና ይሰጣል፡፡
- ፕሮቪደንትስ?
- እሱ ክፍተቶች አሉበት፡፡
- ክፍተቶቹን ማስተካከል ያለብን እኛው ነና፡፡
- ለመሆኑ አንተ የትኛው ይሻላል ትላለህ?
- እኔማ ከጡረታ ውጪ ምን አማራጭ አለኝ?
- እኮ ምረጥ ብትባል የትኛውን ትመርጣለህ?
- ፕሮቪደንትን ነዋ፡፡
- ምን?
- ፕሮቪደንትን ነው የምመርጠው፡፡
- ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ልበል፡፡
- ኪራይ ሰብሳቢ ሆኜ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምን ሆነህ ነው?
- በእርግጥ እንደሚሻል ስለማውቅ ነው፡፡
- እኮ እንዴት?
- ባለፈው ብቸኛ የሆነውን ወንድሜን ማሳከሚያ አጥቼ ሕይወቱ በማለፉ እስካሁን ከውስጤ አልወጣም፡፡
- ይህ ከፕሮቪደንት ጋር ምን አገናኘው?
- ፕሮቪደንት ፈንድ ቢኖረኝማ ወንድሜን አሳክሜ ሕይወቱን ባተረፍኩት ነበር፡፡
- ታክሞም እኮ ላይተርፍ ይችል ነበር?
- ቢያንስ ለእኔ የህሊና ቁስል አይሆንም፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- ከዚያ ውጪ የ40/60 ዕጣ ቢወጣልኝ ከየት እንደማመጣ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው፡፡
- ቤት የለህም እንዴ?
- ያው የመንግሥት ቤት ውስጥ ነው የምኖረው፡፡
- እሱ አይበቃህም ታዲያ?
- ቤቱ የሚኖረው መንግሥትን እስካገለገልኩ ድረስ ነው፡፡ ይህን ሥራዬን ከለቀኩ ቤተሰቤ ያለመጠለያ መቅረቱ ነው፡፡
- ልክ ብለሃል፡፡
- ለዚህ ነው ፕሮቪደንት ይሻላል የምለው፡፡
- ታዲያ ረቂቁ ልክ አይደለም እያልከኝ ነው?
- ረቂቁ መውጣት ካለበት ከጡረታ ሁሉም ወደ ፕሮቪደንት ይዙር ብለን ነው፡፡
- እኛንም ጨምሮ?
- ሠራተኛው ከመረጠው ምን ችግር አለው?
- መንግሥት ገንዘብ አይኖረውማ፡፡
- ቅድሚያ ሊታሰብ የሚገባው ለሕዝብ ነው፡፡
- እሱስ ልክ ብለሃል፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሚኒስትር ደወሉላቸው]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- የጂቲፒ 2 ስብሰባ እንዴት ይዝዎታል?
- ያው ሁሉን ዝግጅት ጨርሰናል፡፡
- እኔም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጌያለሁ፡፡ ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩት ለሌላ ጉዳይ ነው፡፡
- የምን ጉዳይ?
- በቀጣይ አገራችን ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ ታስተናግዳለች፡፡ በዚያ ላይ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል፡፡
- ታዲያ ስንት መሪዎች ተቀብለናል አይደል እንዴ? ምን አዲስ ነገር አለው?
- አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ ይህ አገራችንን ለማስተዋወቅ ወሳኝ አጋጣሚ ነው፡፡
- ያው እንግዲህ እኔ የፕሬዚዳንቱን የአቀባበል ጉዳይ በተመለከተ የተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ስላለሁ በሚገባ እከታተለዋለሁ፡፡
- እኔም ኮሚቴው በአግባቡ ሥራውን እየሠራ አለመሆኑን ሰምቼ ነው የደወልኩት፡፡
- አታስብ እኔ አላሳፍርህም፡፡
- ለማንኛውም አዳዲስ ሱፎችን መግዛት እንዳይረሱ፡፡
- ምን እኔ የፕሮቪደንት ፈንድ የለኝ፤ ከየት አመጣለሁ ብለህ ነው?
- ፕሮቪደንት ፈንድ እኮ ለወሳኝ ነገር እንጂ ለእንደዚህ ዓይነት ነገር መውጣት አይችልም፡፡
- ያው እኛም ቢኖረን ጥሩ ነው ለማለት ነው፡፡
- ምን?
- ፕሮቪደንት ፈንድ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤታቸው እየሄዱ ነው]
- ቀልድ ነው የተያዘው ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ቀልድ አመጣህ?
- ባለፈው ቅዳሜ ጂቲፒ 2 ላይ ለመወያየት ቀበሌ ጠርተውኝ ሄጄ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- የመጀመሪያው ጂቲፒ አፈጻጸም ሪፖርት ተደረገ፡፡
- ከዚያስ?
- ከዚያማ ስለጂቲፒ 2 ተነቦልን ስብሰባው አለቀ፡፡
- በቃ?
- አዎና እኔ እኮ ጂቲፒ 2 ገና እየታቀደ በመሆኑ ለእሱ ግብዓት የሚሆን ነገር ለመስጠት ነው እንጂ የሄድኩት አልሄድም ነበር፡፡
- ምን የምትሄድበት ቦታ አለ ደግሞ?
- ኧረ ስንት ቦታ አለ፡፡ ሌላ ደግሞ፡፡
- ደግሞ ሌላ ምን አለህ?
- ኦባማ ሊመጣ ነው አሉ፡፡
- አሁን ገና መስማትህ ነው?
- እሱማ ቆየሁ፤ ለመሆኑ ምን ሊያደርግ ነው የሚመጣው?
- ያው ልማታችንን ሊያደንቅና ሊያበረታታ ነዋ፡፡
- አሜሪካ የግብረ ሰዶማውያንን መብት በሁሉም ስቴቶቿ ማፅደቋን ሰምተዋል አይደል?
- ያፅድቁዋ፤ እኛ ምን አገባን? ያ የውስጥ ጉዳያቸው ነው፡፡
- አይ የኦባማ ጉብኝት ሌላም ዓላማ አለው እየተባለ ነው፡፡
- የምን ሌላ ዓላማ?
- በአገራችን ያሉ ግብረ ሰዶማውያን መብት እንዲጠበቅ አድቮኬት ለማድረግ ነው ይባላል፡፡
- እኔ በቁሜ እያለሁ?
- መቼም ኦባማ ሲመጣ ይሞታሉ ብዬ አልገምትም፡፡
- ኢትዮጵያ እኮ የእምነት አገር ናት፡፡
- አሁን ክቡር ሚኒስትር እውነት እናውራ ከተባለ የእርስዎ ሃይማኖት አብዮታዊ ዲሞክራሲ አይደለም?
- አብዮት ይብላህ፡፡
- ለማንኛውም የድብቅ ዓላማውን ጉዳይ ነገር አደራ፡፡
- ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
- ሰሞኑን ትልቅ ስብሰባ እንዳለብኝ ታውቂያለሽ?
- የምን ትልቅ ስብሰባ?
- በርካታ መሪዎች ወደ አገራችን ይመጣሉ፡፡
- ምን ሊያደርጉ?
- ኦባማን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ መሪዎች በቅርቡ አገራችንን ይጐበኛሉ፡፡
- ኦባማ ለምንድነው የሚመጣው?
- የአገራችንን ዕድገት ሊያደንቅ ነዋ፡፡
- ለመሆኑ ተቃዋሚዎቹስ ምን ይላሉ?
- አሁን ኢንተርኔት ላይ አላነበብኩም ለማለት ፈልገሽ ነው?
- ምን ዌብሳይቱን ሁሉ ዘግታችሁት የት አነባለሁ ብለህ ነው?
- ምንም ቢሉ ኦባማ መምጣቱ አይቀርም፡፡
- ግን የምር ምን ይላሉ?
- ሁለት አይደለም ገና ሦስት ዓይነት ፀጉር ያበቅላሉ፡፡
- ምን ዓይነት ፀጉር?
- ነጭና ጥቁር…
- ሌላስ?
- ሰማያዊ!