በኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ ዘንድሮ የተካሄደው ምርጫ ውጤቱ በቅርቡ በይፋ ተገልጿል፡፡ ኢሕአዴግና አጋሮቹ መቶ በመቶ ማሸነፋቸውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ውጤት ያመለክታል፡፡ ለመራጭነት የተመዘገቡት ጠቅላላ መራጮች ቁጥር 36,851,461 (ሴት 48 በመቶ) ሲሆን፣ 93.2 በመቶ ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዋጋ ካላቸው 33,201,969 ድምፆች ውስጥ 27,347,332 (82.4 በመቶ) ድምፅ በማግኘት ገዥው ፓርቲ በተወዳደረባቸው አምስት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች 500 የፓርላማ መቀመጫዎችን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፉ ተገልጿል፡፡ የተቀሩትን 46 መቀመጫዎች ደግሞ የኢሕአዴግ ስድስት አጋር ፓርቲዎች ያለተቀናቃኝ ማሸነፋቸው ተገልጿል፡፡
በምርጫው በአጠቃላይ 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፡፡ በአጠቃላይ ለተወካዮች ምክር ቤት 1,828፣ ለክልል ምክር ቤቶች ደግሞ 3,991 ዕጩዎች ቀርበዋል፡፡ በግል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶት ዘጠኝ፣ ለክልል ምክር ቤቶች ሦስት በድምሩ 12 ዕጩዎች ተወዳድረዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ከተሰጡ ድምፆች ውስጥ 3.3 በመቶ (1,130,329 ገደማ) ዋጋ አልባ ሲሆኑ፣ ዋጋ ካላቸው ድምፆች ውስጥ (33,222,801) ኢሕአዴግ 27,347,332 (82.4 በመቶ) በአንደኛነት ሲመራ፣ መድረክ (1,092,819)፣ ሰማያዊ (390,105)፣ ቅንጅት (71,111)፣ ኢዴፓ (70,042) ማግኘታቸውን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ውጤት ያሳያል፡፡ የተጠቀሱት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድምር 1,724,077 ድምፅ ማግኘታቸውን ከቦርዱ ውጤት መረዳት ይቻላል፡፡
በተወዳደረባቸው ቦታዎች ሙሉ በሙሉም ቢያሸንፍ መንግሥትን መመሥረት በሚችል ደረጃ (50%+1) ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ ኢሕአዴግ ብቻ ነው፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለተወካዮች ምክር ቤት ኢሕአዴግ 501፣ መድረክ 270፣ ኢዴፓ 160፣ ሰማያዊ ፓርቲ 139 ዕጩዎችን አቅርበው እንደነበር የቦርዱ መረጃ ያመለክታል፡፡