መንግሥት የዜጐችን የማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ሲል፣ በተለይ በአገሪቱ ያሉ የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ አዋጅ ቁጥር 715/2003 አውጥቷል፡፡ በወቅቱ መንግሥት ይህን አዋጅ ሲያወጣ ከዚህ በፊት የማኅበራዊ ዋስትና ያልነበራቸው ዜጐች በማኅበራዊ ዋስትና እንዲታቀፉ በማድረጉ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 90(1) ላይ የተደነገገው መብት ተግባራዊ እንዲሆን አድርጓል፡፡
መንግሥት ይህን አዋጅ ባፀደቀበት ወቅት በተለይ የግል ድርጅት ሠራተኞች በፕሮቪደንት ፈንድ ወይስ በጡረታ ፈንድ ዐቅድ ውስጥ ይካተቱ በሚለው ሐሳብ ላይ፣ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑ ዜጐች መወሰናቸው ይታወቃል፡፡ በወቅቱ በፕሮቪደንት መቀጠል የፈለጉት በዚያው ሲቀጥሉ፣ በጡረታ ዐቅድ ውስጥ መካተት የፈለጉትም በዚያ ውስጥ ተካተዋል፡፡ በእርግጥ ይህ የዜጐችን በተለይም የእያንዳንዱን ግለሰብ መብት ያስከበረ አካሄድ ስለነበር እጅግ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል፡፡
ከወር በፊት ግን ሥራ ላይ ያለውን የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ለማሻሻል አንድ ረቂቅ አዋጅ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ ይህ አዋጅ በበርካታ የግል ድርጅት ሠራተኞች መካከል ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮ መቆየቱም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የግል ድርጅት ሠራተኞች ያጠራቀሙትን የፕሮቪደንት ፈንድ መንግሥት ሊወስደው ነው በሚል የተነዛው ሥጋት፣ በበርካታ ዜጐች ላይ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ በወቅቱ ይህ ረቂቅ አዋጅ ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ ባለመሆኑ፣ ተገቢው ውይይት ባለመካሄዱና አማራጭ ሐሳቦች ስላልቀረቡበት ረቂቁ እንዳይፀድቅ ብለናል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቁን ለማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡ የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በረቂቅ አዋጁ ላይ የሕዝብ ውይይት አድርጓል፡፡ ረቂቅ አዋጁ የሚመለከታቸው የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ኃላፊዎች፣ የግል ድርጅቶች ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተውም ነበር፡፡ በውይይቱ ላይም ረቂቁ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ስለረቂቁ ምንም ሳይሰሙ፣ ስለጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃን በመስማታቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፡፡ ረቂቁን ያዘጋጀው የመንግሥት አካልም የባለድርሻ አካላቱን ቅሬታ ተቀብሎታል፡፡
በዚህ የሕዝብ ውይይት ላይ በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦች የተነሱ ሲሆን፣ አሁንም የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ከሥር በተጠቀሱት ምክንያቶች ማሻሻያ አያስፈልገውም እንላለን፡፡
- ሕጎች ሲወጡ ተገቢው ጥናት ይደረግ!
መንግሥት የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ካፀደቀ በኋላ፣ በርካታ ሠራተኞች በፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ውስጥ መጠቃለልን መርጠዋል፡፡ እንደሚታወቀው የፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ አንዱ የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን አካል ነው፡፡ በዓለማችን ላይ በርካታ አገሮች ለዜጐቻቸው ይህን የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ይሰጣሉ፡፡ በአገራችንም ቢሆን ይህ የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን በተለይ በበጐ አድራጐት ድርጅቶች በሰፊው ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ከአንዳንድ የግል ድርጅቶች ባሻገር አብዛኞቹ የበጐ አድራጐት ድርጀቶች፣ በፕሮቪደንት ፈንድ ሠራተኞቻቸው እንዲታቀፉ በማድረግ ፈር ቀዳጆች ናቸው፡፡ በዚህም ዐቅድ በርካታ የበጐ አድራጐት ሠራተኞች ሕይወት መቀየሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በእነዚህ ድርጀቶች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የሚያጠራቅሙትን ገንዘብ ቤት ለመሥራት፣ መኪና ለመግዛት፣ ለወሳኝ ሕክምና ወይም ለወሳኝ የሕይወት ሁነቶች በመጠቀም ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
መንግሥት የማኅበራዊ ዋስትና ፈንድን አስገዳጅ ካደረገ በኋላ በርካታ የግል ድርጅት ሠራተኞች በዚህ ዐቅድ ታቅፈዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕድል የወጣላቸው ዜጐች ይህን ፈንድ በመጠቀም የቤት ባለቤቶች ሲሆኑ ታይቷል፡፡ ይህ በእርግጥ አንደኛው የማኅበራዊ ዋስትና መገለጫ ነው፡፡
ዜጐች እንደ ቤት ያሉ መሠረታዊ ነገሮች እንዲያገኙ ያስቻለው ይህ የፕሮቪደንት ፈንድ፣ ለዜጐች ማኅበራዊ ዋስትና መረጋገጡ ሁነኛ አመላካች ነው፡፡ ከፕሮቪደንት ፈንድ ጠቃሚነት የተነሳም ዜጐች ከመንግሥት ይልቅ በግል ድርጅቶች ይቀጠሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በቅርቡ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ግን ያለበቂ ጥናት የፕሮቪደንት ተጠቃሚ የነበሩ የግል ድርጅት ሠራተኞች በጅምላ ወደ ጡረታ ዐቅድ እንዲገቡ ያስገድዳል፡፡ ሕጐች ሲወጡ ዜጐችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ በመሆኑ፣ የግል ድርጅት ሠራተኞች በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ሲወጣ የፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድን የመረጡት እንደሚጠቅማቸው ተገንዝበው ነበር፡፡ አሁን ግን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ተገቢው ጥናት የተደረገበት ባለመሆኑ፣ አዋጁ መሻሻል አያስፈልገውም፡፡
- ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣም!
አገራችን በዕድገት ጐዳና ላይ ትገኛለች፡፡ መንግሥትም ይህን ዕድገት ለማቀላጠፍ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይህ ዕድገት ለዜጐች ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ የሚበረታታና የሚደገፍ ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማስፈጸም ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ይህንንም በሚያደርግበት ወቅት በርካታ ገንዘብ ያለበትን ቦታ ማየቱ አይቀርም፡፡ የግል ድርጅት ሠራተኞች የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘብም ቀላል የማይባል በመሆኑ፣ የመንግሥትን ዓይን ሊስብ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ዜጐች የኑሮ ውድነትን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን ተሸክመው ባለበት በዚህ ወቅት፣ ሌላ ጫና ሊያድርባቸው አይገባም፡፡ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ እንደማይወጣ ሁሉ፣ መንግሥትም አንዳንድ የተለጠጡ ፕሮጀክቶችን በማቀዛቀዝ በዜጐች ላይ ያለውን ጫና ያቃል፡፡
- መንግሥት የራሱን የቤት ሥራ ይሥራ!
አንዳንድ የግል ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን የፕሮቪደንት ፈንድ በአግባቡ እንደማያስገቡ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ይህን የሚያደርጉት የፕሮቪደንት ፈንዱ ባንክ ከሚቀመጥ እኛ ሠርተንበት ብናተርፍበት ይሻላል በሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ አስተሳሰብ ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ምናልባት ድርጀቱ ኪሳራ ውስጥ ቢገባ ለሠራተኞቹ የሚሆን የፕሮቪደንት ፈንድም አይኖርም፡፡ ይህ ደግሞ ሠራተኞቹን ያለማኅበራዊ ዋስትና ያስቀራል፡፡ ይህ በምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም፡፡
አንዳንድ ድርጅቶች እንደዚህ ዓይነት ስግብግብ አሠራር የሚከተሉት ግን መንግሥት ራሱ የፕሮቪደንት ፈንድ ሕጉን ክፍተት እንዲኖረው በማድረጉ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ያልተገባ አሠራር የሚከተሉ ድርጅቶችንም ለመቆጣጠር እጅግ ቀላል መሆኑ መቼም መንግሥት አይጠፋውም፡፡ ምክንያቱም በእነዚሁ ድርጅቶች ያሉና በጡረታ ዐቅድ ውስጥ የታቀፉ ሠራተኞች የጡረታ ፈንዳቸው መግባቱን በየወሩ ያረጋግጣልና፡፡ በተመሳሳይም በፕሮቪደንት የታቀፉት ሠራተኞች ተገቢው ፈንድ በየወሩ ድርጅቶች ማስገባታቸውን የሚያረጋግጡበት አሠራር መዘርጋት ይችላል፡፡ መንግሥት ግን የራሱን የቤት ሥራ ባለመሥራቱ ምክንያት፣ ዜጐች በፕሮቪደንት ፈንድ መታቀፋቸው የማኅበራዊ ዋስትናቸውን አያረጋግጥም ለማለት ስለማያስችለው የራሱን የቤት ሥራ በሚገባ ይሥራ፡፡
- ለዜጐች ጠቃሚ አማራጭ ይቅረብ!
መንግሥት አዋጅ ቁጥር 715/2003 በሥራ ላይ ሲያውል የግል ድርጅት ሠራተኞች በጡረታ ወይስ በፕሮቪደንት ይታቀፉ በሚለው አሠራር ላይ መርጠዋል፡፡ እንደሚታወቀውም በአብዛኛው ሠራተኞችም በፕሮቪደንት ዐቅድ ታቅፈዋል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሠራተኞች በወቅቱ ተገቢ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ፕሮቪደንት ፈንድን መርጠዋል ሲሉ የመንግሥት አካላት ይናገራሉ፡፡ ከፕሮቪደንት ፈንድ ይልቅ ለዜጐች ጠቃሚ የሆነው የጡረታ ፈንድ መሆኑን እነዚሁ የመንግሥት አካላት ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥ ዜጐች ያለበቂ ግንዛቤ የፕሮቪደንት ፈንድን መርጠው ከሆነና አሁን ደግሞ ወደ ጡረታ ፈንድ መሸጋገር ከፈለጉ ይኼ ዕድል በድጋሚ ሊሰጣቸው ይገባል እንጂ፣ ለሁሉም የሚጠቅመው ጡረታ ነው ማለቱ ‹‹ከባለቤቱ ያወቀ…›› የሚለውን ብሂል ያስታውሳል፡፡ ስለዚህ ረቂቁ ይህ ጠቃሚ አማራጭ ሊቀርብበት ይገባል፡፡
በስተመጨረሻ ግን ልናነሳው የምንፈልገው ሐሳብ በእርግጥ መሻሻል ካስፈለገው በመጀመሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታው የባለድርሻ አካላት ጋር በቂ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሕጐችን አርቅቆ ለውይይት ከማቅረብ ይልቅ ሕጉ ከመረቀቁ በፊት ከሕዝብ ጋር አስፈላጊውን ውይይት ማድረግ ያሻል፡፡ ይህን ማድረግም በመንግሥትና በዜጐች መካከል ቅራኔ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ይህ የግል ድርጅት ሠራተኞች ረቂቅ ማሻሻያም ከመቅረቡ በፊት ውይይት ያልተደረገበት በመሆኑ፣ የተለያዩ ቅራኔዎችንና ሥጋቶችን መፍጠሩ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ይህ የጡረታ አዋጅ ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች ማሻሻያ አያስፈልገውም!