Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮንዶሚኒየም ዕጣ የደረሳቸው አራት ሺሕ ዕድለኞች ክፍያ ካላጠናቀቁ ቤቶቹን እንደማያገኙ ተነገረ

የኮንዶሚኒየም ዕጣ የደረሳቸው አራት ሺሕ ዕድለኞች ክፍያ ካላጠናቀቁ ቤቶቹን እንደማያገኙ ተነገረ

ቀን:

  • ኤጀንሲው 31 ሺሕ ያህሉ ከፍለው መዋዋላቸውን አስታውቋል
  • የተዋዋሉት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍለዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአሥረኛ ጊዜ ባወጣው የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ዕድለኛ ከሆኑ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አራት ሺሕ ተመዝጋቢዎች ለክፍያ ይጠበቃሉ፡፡ ክፍያቸውን በሁለት ሳምንት ውስጥ ካላጠናቀቁ ቤቶቹን እንደማያገኙ ተገለጸ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዕጣ ከወጣላቸው 35 ሺሕ ዕድለኞች ውስጥ 31 ሺሕ ያህሉ ውል መፈጸማቸውን አስታውቋል፡፡

ዕጣው ከደረሳቸው መካከል 31 ሺሕ ያህሉ ውል ተዋውለው መጨረሳቸውንና ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ቅድመ ክፍያ መፈጸሙን አስታውቋል፡፡ ቀሪዎቹ ዕድለኞችም እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ውላቸውን ፈጽመው መጨረስ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ ውል የመፈጸሚያ ጊዜው ካለፋቸው ቤቱን እንደማያገኙም አስታውቋል፡፡

መክፈል ያልቻሉ ዕጣው የወጣላቸው ዕድለኞች ደግሞ ቅድመ ክፍያ (ሃያ በመቶውን) ለመክፈል ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ በብድርና በተለያዩ ወገኖች ድጋፍ ሊከፍሉ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ኪራይ እየከፈሉ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ለደረሳቸው ኮንዶሚኒየምና ለሚኖሩበት የቤት ኪራይ በየወሩ መክፈል ስለማይችሉ፣ ክፍያውን በሁለት ሳምንት አጠናቁ በመባላቸው ከወዲሁ ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡

አራት ኪሎ፣ ልደታና ለመሀል ከተማው ቀርበው በተሠሩ ኮንዶሚንየም ቤቶች የደረሳቸው ዕድለኞች፣ ኮንዶሚኒየም ቤቱ ባይፀዳ እንኳን ገብተው ለኪራይ የሚከፍሉትን እየከፈሉ እንደሚኖሩ የገለጹት ዕድለኞቹ፣ ከመሀል ከተማው በ10 እና በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደረሳቸው ግን ግራ እንደተጋቡ ተናግረዋል፡፡

ቤቶቹ የተገነቡት አገር ውስጥ በተመረቱ የግንባታ ግብዓቶች በመሆኑ ቅናሽ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁት ነዋሪዎቹ፣ የመሠረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች ዕጣ የደረሳቸው በኮንዶሚኒየም ቤቶቹ አካባቢ ትምህርት ቤቶች እስከሚከፈቱና ትራንስፖርት ተሟልቶ እስከሚገባ ድረስ፣ የባንክ ክፍያ መጀመሪያው ጊዜ እንዲያራዝምላቸው ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ያለፉና በመሰናዶ ትምህርት ቤት የተመደቡ ልጆቻቸውን እንዴት አጓጉዘው ማስተማር እንደሚችሉ ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ዕጣ የወጣላቸው የተወሰኑ ዕድለኞች ቅድሚያ ክፍያ የሚከፍሉት አጥተው በየመሥሪያ ቤቱ፣ በካፌ፣ በሬስቶራንትና በመዝናኛ ቦታዎች በመገኘት እውነቱን እየተናገሩ ዕርዳታ እየጠየቁ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንዶቹ ዕድለኞች ከአሥር ዓመታት ቆይታ በኋላ የደረሳቸው ዕድል መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ዕድል ካመለጣቸው ዳግመኛ ስለማያገኙት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ዕርዳታ በመጠየቅ ለማሟላት እየተሯሯጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በልመና ምን ያህሉን መሸፈን እንደሚችሉ አለማወቃቸውን የሚናገሩት ዕድለኞቹ፣ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ የቻሉትን ጥረት አድርገው ካልሞላላቸው ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ሳይወዱ በግድ እንደሚተውት ተናግረዋል፡፡

የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ግን ቤቶቹን ለማዋዋል የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ስለሚያበቃ፣ በአስቸኳይ መዋዋሉን እንዲያጠናቅቁ አስታውቋል፡፡ የዕጣ ዕድለኞች የሆኑት አራት ሺሕ ያህል ግለሰቦች በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ የማያጠናቅቁ ከሆነ ቤቶቹን እንደማያገኙ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በተለይ በአሥረኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋ በመጋነኑ ምክንያት፣ ልዩ ኮሚቴ አቋቁሞ የዋጋውን ሁኔታ ማጥናት መጀመሩ የታወቀ ቢሆንም፣ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...