በርካታ የግል ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረቡ፡፡
የምክር ቤቱ የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማሻሻያውን አስመልክቶ ባዘጋጀው የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ላይ የተጋበዙ ከ300 በላይ የሚሆኑ የግል ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት፣ ማሻሻያውን ያረቀቀው የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ባለድርሻ አካላትን ሳያነጋግር ወይም ሳያወያይ ይህንን ረቂቅ ማሻሻያ ለፓርላማ ማቅረቡ ፍፁም ተገቢ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በዋናነት ከተካተቱት ማሻሻያዎች መካከል በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 ቀደም ሲል የፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓት በፈቃደኝነት እንዲቀጥል ቢወሰንም፣ በማሻሻያው ግን ወደ ግል ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ይዞራል የሚለው ይገኝበታል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ከቀረበ በኋላ ግን አርቃቂው አካል የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ኤጀንሲ ማሻሻያውን በድጋሚ በማየት ፕሮቪደንት ፈንዱ በቀጥታ ይዞራል ወይም የተጠራቀመው ገንዘብ ወደ ጡረታ ፈንድ ይገባል የሚለው እንዲስተካከል ማድረጉን የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በውይይቱ መጀመርያ ላይ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ እንዲገኙ የተጋበዙት ድርጅቶች በሙሉ ሠራተኞቻቸውን በፕሮቪደንት ፈንድ ዋስትና የሚያስተዳድሩ በመሆናቸው፣ በመጀመርያ እፎይታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ይገኙበታል፡፡
‹‹ይህንን ማሻሻያ በመስማቴ ደስ ብሎኛል፤›› ያሉት ዶ/ር አረጋ መንግሥት ስለ ግል ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ማሰብ ከመጀመሩ በርካታ ዓመታት ቀደም ብሎ፣ የግል አሠሪዎችና ሠራተኞቻቸው ተነጋግረው ፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓትን መፍጠራቸውን አስታውሰዋል፡፡
‹‹ስለዚህ ፕሮቪደንት ፈንድ የአሠሪና የሠራተኛው የግላቸው ነው፡፡ ማንም ሌላ ሰው ሊወስንበት አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም መልክ መወሰኑን ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
ሲአርዲኤ የተባለው የሲቪክ ማኅበራት ጥላ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋ፣ በተመሳሳይ የማሻሻያ አዋጁ አርቃቂዎች ባለድርሻ አካላትን አወያይተናል በማለት ያቀረቡት ሪፖርት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በሲአርዲኤ ሥር ከ350 በላይ ሲቪክ ማኅበራት የሚገኙ መሆኑንና ኢትዮጵያ ከዚህ ዘርፍ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታገኝ አስታውሰው፣ ይህንን ዘርፍ እንደ ባለድርሻ አካል ሳያወያዩ ሪፖርት ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአዋጁ አርቃቂዎች ባለድርሻ አካላትን አወያይተናል የሚሉት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንና የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ነው፡፡
‹‹ዛሬ በድፍረት መናገር ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ተቋማት እንደማይወክሉን ታውቃላችሁ፡፡ እንዲያውም ለመንግሥት ነው የሚሠሩት፤›› ሲሉ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ተችተዋል፡፡
ዶ/ር መሸሻ ፕሮቪደንት ፈንድን በቀጥታ ወደ ጡረታ እንዳይዞር በመጨረሻ መወሰኑን ተቀብለዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ፕሮቪደንት ፈንድ ምንም እንዳልሠራ መቆጠር የለበትም፡፡ በ2003 ዓ.ም. እንደተፈቀደው ሁሉ አሁንም በሠራተኞች ምርጫ ሊቀጥል ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
የሲቪክ ማኅበራት ፀባይ ከሌሎቹ ስለሚለይ ሠራተኞች የሚቆዩት ፕሮጀክቶች እስካሉ ድረስ ብቻ ስለሆነ፣ ፕሮጀክቶች ሲያበቁ እንደሚሰናበቱ አስታውሰዋል፡፡
ዶ/ር መሸሻ ሠራተኞች በሚሰናበቱበት ጊዜ ለሥራ መፈለጊያም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደሪያ ሆኖ የሚያገለግለው ፕሮቪደንት ፈንድ በመሆኑ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ ሌላው አገር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ‹ኢምፕሎይመንት ፈንድ› ወይም ሥራ አጥ በሚኮንበት ወቅት የኑሮ ዋስትና አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እኛ አገር ይህ ባለመኖሩ ፕሮቪደንት ፈንድን ይዞ መቀጠል ምን ችግር አለው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲስ ዴቨሎፕመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ በበኩላቸው፣ ‹‹የፕሮቪደንት ፈንድ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ምክንያቱም በተለይ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወጣቶች እስከ 60 ዓመት ዕድሜያቸው በተቀጣሪነት ቆይተው የጡረታ ተከፋይ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትን ወክለው የተገኙት የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ ‹‹የፕሮቪደንት ፈንድ ማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት የራሱ ደካማ ጎኖች አሉት፡፡ እነዚህ ደካማ ጎኖች ግን መንግሥት ለፕሮቪደንት ፈንድ ጥበቃ ለመስጠት ኃላፊነት ባለመውሰዱ የተከሰቱ ችግሮች እንጂ የግሉ ዘርፍ የፈጠረው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፕሮቪደንት ፈንድ ለግሉ ዘርፍ ትልቅ ዋስትና ነው፡፡ አሠሪው ለሠራተኛው ዋስትና እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፣ ኮንፌዴሬሽኑ ከኤጀንሲው ጋር በተወያየበት ወቅት ፕሮቪደንት ፈንድን በተመለከተ ኮንፌዴሬሽኑ ያቀረበው ሐሳብ የጡረታ ዐቅድ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ፕሮቪደንት ፈንድ እየተዋጠ እንደሚሄድ፣ በመሆኑም በራሱ ጊዜ ሊሞት ስለሚችል መነካካት አያስፈልግም የሚል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ፕሮቪደንት ፈንድን የማይፈልጉ ድርጅቶች ብቻ ወደ ጡረታ በምርጫቸው እንዲመጡ መደረግ እንዳለበት ኢሠማኮ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችም ፓርላማው ይህንን አዋጅ በዚህ ዓመት ሊያፀድቀው እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡
ይህንን ያሉበት ምክንያት የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 19 ላይ የተደረገው ማሻሻያን በመቃወም ነው፡፡ አንቀጹ ‹‹በተቀጠረ ሦስት ዓመት ወይም ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በጡረታ የሚገለል ሠራተኛ፣ በጡረታ ከሚገለልበት ወር ሦስት ዓመት አስቀድሞ ባለው ወር ሲከፈለው ከነበረው መደበኛ የወር ደመወዝ በ25 በመቶ የሚበልጥ ዓመታዊ አማካይ የደመወዝ ጭማሪ ያገኘ እንደሆነ፣ በየዓመቱ 25 በመቶ ያለው የደመወዝ ጭማሪ ብቻ በደመወዙ ላይ ተደምሮ የሦስት ዓመት አማካይ የወር ደመወዙ ተይዞ ይታሰባል፤›› ይላል፡፡
ይህንን የተቃወሙት የድርጅት ተወካዮቹ አገሩን በዝቅተኛ ደመወዝ ሲያገለግሉ የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ወታደሮችንና የመሳሰሉትን የሚጎዳ ነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ በዕድሜው መጨረሻ ላይ የተሻለ ገንዘብ ቢያገኝ ለአገሩ ያበረከተውን በገንዘብ የማይለካ አስተዋጽኦ ወደጎን በመተው፣ 25 በመቶ ጭማሪውን ብቻ ማሰብ ተገቢ አይደለም በማለት ተቃውመዋል፡፡
የኤጀንሲው የሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሲሳይ ፕሮቪደንት ፈንድን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ ፕሮቪደንት ፈንድ ዘለቄታዊ ማኅበራዊ ዋስትና መሆን አይችልም ብለዋል፡፡
‹‹የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘብን የወሰደ ሠራተኛ ገንዘቡ ካለቀበት አለቀበት ነው፡፡ በማኅበራዊ ዋስትና (በግል ጡረታ) ቢታቀፍ ግን አሥር ዓመት ብቻ አገልግሎ ዕድሜ ልኩን እስከነ ተተኪዎቹ ሚስቱንም ጨምሮ ዕድሜው ስልሳ ዓመት ከደረሰ በኋላ ማግኘት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
አንቀጽ 19 ላይ የተደረገውን ማሻሻያ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ አንድ ሠራተኛ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከ25 ዓመት በላይ ያገለግልና በ25/55 የጡረታ መብት መሠረት በአምስት ሺሕ ብር ጡረታውን አስከብሮ፣ ቀሪውን ዕድሜ ማለትም አምስት ዓመቱን በግል ድርጅት በወር እስከ 30 ሺሕ ብር ቢቀጠር አጠቃላይ የጡረታ አበሉ የሚሰላው በ30 ሺሕ ብር ደመወዝ ተመን ነው፡፡ ያላዋጣውን በመብላት ፈንዱን የሚያደርቀው በመሆኑ ገደብ ሊጣልበት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው፣ ማኅበራዊ ዋስትናን በተመለከተ በየትም አገር ስምምነት ኖሮ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡ በኋላ ላይ የኅብረተሰቡን ዋስትና ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
የፓርላማው የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ፣ ከውይይቱ በርካታ ቁም ነገሮችን መገኘታቸውን፣ ለፓርላማ የቀረበ ነገር ሁሉ እንደማይፀድቅ፣ በተደረገው ውይይት ላይ በድጋሚ በመነጋገር ተጨማሪ የሕዝብ ውይይት ካስፈለገም ሊጠራ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡