Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅየአዲስ አበባ ቀደምት የጐዳና ላይ ልብስ ሰፊዎች

የአዲስ አበባ ቀደምት የጐዳና ላይ ልብስ ሰፊዎች

ቀን:

የኛ ዕድገት

ዝናብ ያካፋ’ለት – ስቧቸው ሿሿታ

እናት፣ አባታችን – አምሯቸው ጨዋታ

- Advertisement -

‹‹ሂዱ ተጫወቱ፤ አሳድገኝ በሉ፤

ሕፃን ልጅ የሚያድገው

ዝናብ ሲመታው ነው፤ ሲረጥብ አካሉ››

ያሉንን አንግበን

                  ‹‹ዝናቡ አሳድገኝ!

 ዝናቡ አሳድገኝ!››

      ነበር ጨዋታችን፤

      ነበር ዘፈናችን፡፡

እልፍ ዘመን ጠብቶ፣

ብልኮ ደርቦ – ነጠላው ዕድሜያችን

ዜማ ያልለወጠ

                  ‹‹ዝናቡ አሳድገኝ!

 ዝናቡ አሳድገኝ!››

      ዛሬም ዘፈናችን፡፡

  • በአካል ንጉሤ ‹‹ፍላሎት (የነፍስ አሻራዎች)›› (2001)

***************

 

ዓይን ያየውን ገንዘብ ይገዛዋል

ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ሃብታም ነጋዴ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሱቁ በር ላይ ‹‹ዓይኖቼ የሚያዩትን ማንኛውም ነገር መግዛት እችላለሁ፡፡›› የሚል ማስታወቂያ ለጠፈ፡፡ ንጉሡም በከተማዋ ውስጥ እየተዘዋወረ ሳለ የነጋዴውን ሱቅ ሲጎበኝ ማስታወቂያውን አየ፡፡

ከንጉሡ አማካሪዎች አንዱ ንጉሡን ‹‹ይህ ነጋዴ በጣም ባለጌ ነው፡፡ ይህንን ማስታወቂያ የለጠፈው የእርስዎን ልጅም ቢሆን ወደ ቤቱ እንደሚያስመጣት ለማሳየት ስለሆነ እርስዎንም እየተሳደበ ነው፡፡›› አለው፡፡

በዚህ ጊዜ ንጉሡ ወደ ነጋዴው ሱቅ ጎራ ብሎ ነጋዴውን ‹‹የእኔን ልጅ ጨምሮ ሌላ የፈለከውንም ነገር እዚህ ማምጣት እችላለሁ ማለትህ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፡፡

ነጋዴውም ‹‹አዎ፣ እችላለሁ፡፡ አንድ ቀን ቁረጥና በዚያን ዕለት ልጅህን ወደዚህ ሱቅ ካላመጣኋት በስቅላት ልቀጣ፡፡›› አለ፡፡

ንጉሡም በዚህ ተስማማ

ነጋዴውም ወደ አንድ የወርቅ አንጥረኛ በመሄድ ‹‹እኔ በጣም ሃብታም ነኝ፡፡ የቻልኩትን ያህል ወርቅ ልገዛ መጥቻለሁና አንዲት ከወርቅ የተሠራችና ሰው ሊያስቀምጥ የሚችል ትልቅ ሆድ ያላት ግዙፍ ላም አዘጋጅልኝ፡፡›› አለው፡፡
ከዚያም የወርቋን ላም ለሰዎች እያስከፈለ ያሳይ ጀመር፡፡ ይህ ጉዳይ በጣም እየታወቀ ስለሄደ ዜናው በከተማው ውስጥ በሙሉ ተናኘ፡፡ ሰዎች ከሁሉም ቦታዎች መጉረፍ ጀመሩ፡፡

ልዕልቷም ስለዚህ ጉዳይ በሰማች ጊዜ ላሟን ማየት ትችል ዘንድ አባቷ ላሟን ወደ ቤተ መንግሥት እንዲያስመጣላት ጠየቀችው፡፡ ንጉሡም ወታደሮቹ ላሟን ሄደው እንዲያመጧት አዘዛቸው፡፡

ነጋዴውም በላሟ ሆድ ውስጥ ተደብቆ ሳለ ላሟ ተወስዳ ልዕልቷ መኝታ ቤት ውስጥ ተቀመጠች፡፡ ልዕልቷም ወርቃማዋን ላም ባየች ጊዜ ሰዎቹን የትም እንዳይወስዷት አዛቸው ተኛች፡፡

በዚህ ጊዜ ነጋዴው ከላሟ ሆድ ውስጥ ወጥቶ ቀለበቱን ከልዕልቷ ቀለበት ጋር አቀያይሮ ወደ ላሚቷ ሆድ ዕቃ ተመለሰ፡፡ ልዕልቷም ከእንቅልፏ ስትነቃ ቀለበቷ ተቀይሮ ስላየች እንደገና የተኛች በመምሰል የሚሆነውን ነገር ለማየት አንቀላፋች፡፡ ከዚያም ነጋዴው ልዕልቷ እንደገና የተኛች መስሎት ከላሚቷ ውስጥ ተንፏቆ ሲወጣ ልዕልቷ ያዘችው፡፡ ከዚያም እንዳትከዳው ለመናት፡፡ እሷም እሺ ብላ ደንገጡሮቿ ብዙ ምግብ እንዲያመጡላት አዘዘቻቸው፡፡ ንጉሡም ልጁ ጥሩ የምግብ ፍላጎት እንዳላት ሲሰማ ደስ አለው፡፡

ከዚያም ነጋዴውና ልዕልቷ በጣም እየተቀራረቡ ሄደው ብዙ ነገር ከተጨዋወቱ በኋላ ልዕልቲቱ በፍቅሩ ወደቀች፡፡ ነጋዴው ግን ወርቃማዋ ላም ወደ ሱቁ እንድትመለስለት ቢፈልግም ልዕልቲቱ አሻፈረኝ አለች፡፡ በዚህ ዓይነት ለአንድ ወር በልዕልቷ መኝታ ቤት ከቆዩ በኋላ ላሚቷን ለመልቀቅ ተስማማች፡፡ በዚህን ጊዜ የነጋዴው የሞት ቀጠሮ ሁለት ቀናት ብቻ ቀርተውት ነበር፡፡ ንጉሡም ነጋዴውን ወደ ቤተ መንግሥቱ አስጠርቶ ትሰቀላለህ አለው፡፡

ነጋዴውም ‹‹ከተሰቀልኩ መስቀል የምፈልገው እያንዳንዱ የከተማው ዜጋ ባለበት ነው፡፡›› አለ፡፡

በመሰቀያውም ቀን ሁሉም የከተማው ዜጎች በተሰበሰቡበት ነጋዴው የንግሥቲቱን ቀለበት ከኪሱ አውጥቶ ለንጉሡ አሳየው፡፡

‹‹ይህ ቀለበት የማን ነው?›› በማለት ነጋዴው ጠየቀ፡፡

ንጉሡም ቀለበቱን በተመለከተ ጊዜ የልጁ ቀለበት እንደሆነ አወቀ፡፡ ነጋዴውም ‹‹ልጅህ የማንን ልጅ በሆዷ እንደተሸከመች እንድትጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡›› አለ፡፡

በዚህ ጊዜ ልዕልቷ ወደ ነጋዴው መሰቀያ ቦታ ተጠርታ ያረገዘችው የማንን ልጅ እንደሆነ ስትጠየቅ የነጋዴውን ልጅ እንዳረገዘች በከተማዋ ዜጎች ሁሉ ፊት አመነች፡፡

ንጉሡም በሁኔታው አፍሮ ‹‹ቀድሞውኑ ልጄን በሚስትነት ልሰጥህ ይገባ ነበር፡፡›› አለው፡፡

በዚህ ሁኔታ ልዕልቲቱን ለነጋዴው ከዳራት በኋላ ከጥቂት ቆይታ በኋላም ንጉሡ ሲሞት ነጋዴው ከተማዋን ለብዙ፣ ብዙ ዘመናት ገዛ፡፡

በአብዱል ራህማን አብዱላሂ የተተረከ የሐረር ተረት

*****************

‹‹ኧረ ቁጭ ብያለሁ!››

ሰውየው ያጣ የነጣ ድሃ ቢሆንም አንዲት ዶሮ ግን ነበረችው፡፡ ለዶሮይቱ አውራ ባያዘጋጅላቸው ከጎረቤት አውራ ዶሮ ጋር በምታደርገው ግንኙነት በየቀኑ አንድ አንድ እንቁላል ትጥልለታለች፡፡ እርሱ ደግሞ ያቺን ከሥሯ እያነሳ ለሰፈሩ ባለሱቅ ይሸጥና ዳቦ ገዝቶ እየገመጠ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ሲኖር አንድ ምሽት ከቀን ሥራው ሲመለስ ራቱን የምትመግበውን ዶሮ ከቆጧ ላይ ያጣታል፡፡ ምናልባት ጎረቤት ካለው አውራ ዘንድ ሔዳ እንደሆነ ብሎ ቢጠይቅም የለችም፡፡

በጣም አዝኖ ጉዳዩን ለአካባቢያቸው መሪ ይነግራቸዋል፡፡ እሳቸውም ብልህ ነበሩና ሐሳቡን ከሌሎች ጉዳይ ጋር በማያያዝ ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ ከስብሰባው አጀንዳዎች አንዱ የጠፋችው ዶሮ ጉዳይ ነበርና መሪው ስለስርቆት አስከፊነት የተወሰነ መልዕክት አስተላለፉ፡፡ ቀጠሉናም ስለጠፋችው የድሃው ዶሮ ገለጻ ካደረጉ በኋላ የተቀመጠውን ሕዝብ፣ ‹‹በሉ ቁጭ በሉ›› ይላሉ፡፡ ሕዝቡ፤ ‹‹አንድም የቆመ ሰው በሌለበት፣ ‹‹ተቀመጡ›› ማለታቸው ምንድን ነው?›› ብሎ ሲያጉረመርም፣ ሰብሳቢው ጠረጴዛውን መታ መታ አደረጉና፣ ‹‹ያጉረመረማችሁበት ምክንያት ገብቶኛል፡፡ እኔ ‹‹ቁጭ በሉ›› ያልኩት የዶሮዋ ሌባ አለመቀመጡን ስላየሁ ነው፤›› አሉ፡፡ ይኼኔ፣ ድንገት አንድ ወጣት ከተቀመጠበት ተነሥቶ፣ ‹‹ኧረ ቁጭ ብያለሁ!›› ብሎ ራሱን አጋለጠ፡፡

(ዘመን፤ 2001)

*************

‹‹አንድ ጠርሙስ አረቄ . . . !››

በጠጪነቱ የታወቀ የአንድ መሥሪያ ቤት ሠራተኛ ጧት ሥራ ከመግባቱ በፊት ከቤቱ ጀምሮ ባሉ አንድ አራት መጠጥ ቤቶች ጎራ እያለ ፉት ይላል፡፡ ማታም እንዲሁ አትለፍ የተባለ ይመስል የደንቡን ሳያደርስ ቤቱ አይገባም፡፡ ይህ ልምዱ እንደማያዋጣው በብዙ ሰዎች ከተነገረው በኋላ አንድ ጧት ለራሱ ቃል ገባ፣ ሳይጠጣ ቢሮው ገብቶ ሳይጠጣ ቤቱ ለመመለስ፡፡ እናም፣ ምሎና ተገዝቶ እኒያን መጠጥ ቤቶች ጧት ላይ እየገላመጠና እየረገማቸው አልፎ መሥሪያ ቤቱ ደረሰ፡፡ በውሳኔው ተደስቶ በሰላም ሲሠራ ከዋለ በኋላ ማታም ወደ ቤቱ ሲመለስ የጧቱኑ ዕርምጃ ወሰደ፡፡ ሳይቀምስ ውሎ ሳይቀምስ በመግባቱ ተደስቶ፣ ‹‹ጀግና ነኝ! ቆራጥ! ለዚህ ጀግንነቴ አንድ ጠርሙስ አረቄ ይገባኛል በማለት ወደ አረቄ ቤት በረረና አረፈዋ!

(ዘመን፤2001)

*************

ፉዞ! ፉዞ!

በሀያ አምስት ዓመት

ዕድሜው ሽበት ወሮታል፡፡ ወጣት እንጂ አዛውንት አለመሆኑ ግን ከፊቱ ወዝ ይታወቃል፡፡

አይናገርም፤ አይጋገርም፡፡ ብቻውን መንገድ ለመንገድ ሲንከራተት ይውላል፡፡ ሲደክመው ካገኘው ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ ያዛል፡፡ እስመጣለት ድረስ ፊቱን በመዳፉ ያሻሸዋል፡፡ ዓይኖቹን በጣቶቹ ጫፍ ጫን ጫን ይላቸዋል፤ እንቅልፉ መጥቶ ለመንቃት እንደፈለገ ሁሉ፡፡ በእውነቱ ከሆነ ሁልጊዜም ቢሆን በእንቅልፍ መሰል ሰመመን ውስጥ የሚኖር ይመስላል፡፡ ዓይኖቹ ውጫዊ ነገር የሚያዩ ቢመስሉም ውጫዊ ነገር አያዩም፡፡ ዘወትር የሚመለከቱት ወደ ውስጥ ነው፤ ወደ አእምሮው ውስጥ፤ ወደ ሕሊናው ውስጥ፤ በአጠቃላይ ወደ ሕይወቱ ውስጥ፡፡

በሰው መሃል ቢሆንም እንኳ ዘወትር ብቸኛ ነው፡፡ ሻይ ቤት በሚገባበት ጊዜ አሳላፊው ወይም አሳላፊዋ ሲመጡ ‹‹ሻይ›› ከማለት በስተቀር ሌላ ቃል አይተነፍስም፤ በውስጣዊ ሕይወቱ ሰምጦ ስለሚቀር፡፡

ሻይ ቤት ውስጥ ያገኙትና ከሱ ራቅ ብለው የተቀመጡት ሁለት ሰዎች ስለሱ ያወሩ ጀመር፤ አንድ ቀን፤

‹‹ታውቀው የለም?››

‹‹ማንን?››

‹‹ያን ወጣት አዛውንት …. ወይንስ አዛውንቱ ወጣት ልበለው? ለወሬ የማያመች አሳዛኝ ሰው! አሁን ማን ይሙት በሀያ አምስት ዓመት ዕድሜው ሽበት ያበቀለ ሌላ ሰው ታውቃለህ?››

‹‹ኦ! እሱን ማለትህ ነው! ለመሆኑ ስለሱ የሚወራው እውነት ነው እንዴ?››

‹‹ስለሱኮ ብዙ ነገር ይወራል፡፡ የትኛውን ማለትህ ነው?››

‹‹ከዚህ ያደረሰው የሴት ፍቅር ነው የሚባለው፡፡››

‹‹እውነት ነው እንጂ! እኔኮ ደህና አድርጌ አውቀዋለሁ፡፡ መምህር ነበር፡፡ እንዴት ያለ ደስተኛ ሰው ነበር መሰለህ ሳቂታ … ተጫዋች! በዚያ ላይ ለሴት የማይንበረከክ ኩሩ ወጣት ነበር፡፡ በኋላ ጣለበትና አንዷን ተማሪ ወድዶ ቁጭ! እሷ ደሞ የሰይጣን ቁራጭ ነች…. ክልፍልፍ፡፡ አልፈልግህም አለችው፡፡ የወንድ ልጅ ኩራቱን ሰበረችበት፡፡ ከዚያ ወዲያ ሰው ለመሆን አልቻለም፡፡ እምቢ አልፈልግህም ስትለው የዓለም ፍጻሜ የደረሰ መሰለው፡፡››

‹‹ደካማ ሰው መሆን አለበት!››

‹‹እንዴት?››

‹‹አንዲት ሴት ልጅ አልፈልግህም ብትለው ሌላ ሴት ልጅ አይፈልግም ኖሯል? እንዴት የዓለም ፍጻሜ የደረሰ ይመስለዋል? በጣም ደካማ ሰው መሆን አለበት፡፡››

‹‹ኧረ አይጣል በል! ከጣለኮ ይኸው ነው! ፉዞ ሆኖ መቅረት!››

‹‹ፉዞ! ፉዞ!››

  • ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ‹‹ሽኩቻ›› (1987)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...