Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ዝምድና እንዴት ይመለስ ይሆን?

በልዑል ዘሩ

በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች ታሪክም ሆነ አብሮነትና ጉዳይ ላይ ከጥንት እስከ ዛሬ የተለያዩ ድርሳናት ተጽፈዋል፡፡ ከወቅታዊ የፖለቲካ ክስተት ጋር በማያያዝ የታሪክ ትንተና ቢደረግ እነዚህ ሕዝቦች አብረው የኖሩባቸው ዘመናት ይታሰባሉ፡፡ በእርግጥ ወደ አክሱምና ንግሥተ ሳባ ጊዜ ወይም የቀደመው ሥልጣኔ ዘመን ስንራመድ፣ ዛሬ ባለው የደቡብ ምዕራብና የምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ይልቅ የአሁኑ ኤርትራና የአገራችን ሰሜነኛው ክፍል አንድ ‹‹አቢሲኒያ›› ሆኖ በታሪክ ላይ ሰፍሯል፡፡

በጣም ረዥሙ፣ ዝርዝሩና የታሪክ ውዝግቡ ለዚህ አጭር የጋዜጣ ጽሑፍ አይጠቅመንም፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለት አገር ገጽታ እየያዙ የመጡት በሌሌች የአፍሪካ አገሮች እንደታየው፣ ከአውሮፓ የቅኝ ግዛት ወረራ በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጣሊያን ከመረብ ማዶ ለ40 ዓመታት ባሕረ ነጋሽን ‹‹ኤርትራ›› የሚል ስም ሰጥቶ ሲገዛ፣ ከኢትዮጵያ ምድር በኃይል ተገፍትሮ በመውጣት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ኖረበትም አልኖረበትም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ከፋፋይ የሆኑ ስምምነቶችን በመዋዋል፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙንቱን በጥላቻና በአሉታዊ የፉክክር መንፈስ በማነፅ ግንኙነቱን የድቡሽት ቤት አድርጎታል፡፡

በሒደቱ ቀድሞ የሠለጠነው የፋሽስቱ ወራሪ ኃይል የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያሳዩ (በተለይ ከባህር በር ጥያቄዎች ጋር) ዕርምጃዎችን በመውሰድም በታሪክ የሚወቀስበትን ተግባር ፈጽሟል፡፡ ‹‹ከቀኝ ግዛት ነፃ የመውጣት›› ጉዞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መድረክ እየቀረበ አውሮፓውያን ገዥዎች አፍሪካን እየለቀቁ ሲናወጡና ኤርትራ ወደ እናት ምድሯ ኢትዮጵያ ትቀላቀል ሲባል፣ የተካሄደ እልህ አስጨራሽና የሁለቱም ሕዝቦች ፍላጎት ቢኖርም ውጤቱ የሚያኩራራ አልነበረም፡፡   

በታሪክ በስፋት እንደተተነተነው በአንድ በኩል ጣሊያንና ሌሎች የኢትዮጵያን መጠናከርና አንድነት ብሎም ወደ ቀይ ባህር መቅረብ የሚጠሉ ዓረቦች፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንዳትሆን ግልጽና ስውር ዘመቻ አካሄዱ፡፡ በሌላ በኩል በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች በሕዝብ ለሕዝብ መተማመን ላይ የተመሠረተ አብሮነት ለመፍጠር ከማሰብ ይልቅ፣ የአገር ድንበርና ‹‹የባህር በር ባለቤትነት›› ትኩረትን ግብ አድርገው መንቀሳቀሳቸው ቅቡልነትን ያጣ ድርጊት ሆነ፡፡ በተለይ ‹‹ኢትዮጵያ ወይም ሞት›› በሚሉ አገር ወዳድ ኤርትራውያንና ‹‹ነፃ መውጣት አለብን›› በሚለው ‹‹የባዕዳን ተላላኪው›› ወገን መካከል ገዥዎች ይፈጽሙት የነበረው የፖለቲካ ደባና ሽኩቻ ፍጻሜውን አሰነካክሎታል፡፡ ከዚያ በኋላ ኤርትራን የኢትዮጵያ አካል ለማድረግ ቢሞከርም ጦርነትና እልቂት ብቻ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምድና በፌዴሬሽንም ተባለ መልሶ በአንድ አገር ስም ሊገነባ ቢሞከርም፣ በባዕዳን የተሠራው የጥላቻ አረም ማሳውን ስለሞላው ፍሬ ማፍራት አልቻለም፡፡ በኋላ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ እጁ ላይ የወደቀው ወታደራዊ መንግሥት ደርግም በጀብደኝነትና በኃይል ‹‹አባቶቻችን ያስረከቡንን የአገራችንን አንገት አናስቆርጥም›› እያለ የጦርነቱን አበላ ከማስቀጠል ውጪ ሌላ መፈክር ሊያነሳ አልቻለም፡፡ በ17 ዓመታት ውስጥም በዝቅተኛ ግምት 200 ሺሕ ወታደሮች ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለምርኮ፣ ከ30 ቢሊዮን የማያንስ ገንዘብም ኤርትራ ተራራዎች ላይ በትኗል፡፡

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ወገናቸው ጋር በኅብረትና በዴሞክራሲያዊ አንድነት ቢኖሩ የሚያገኙትን የጋራ ጥቅም ሳያሳዩ፣ ድንበርና ወደብን እየጠቀሱ ያን ሁሉ እልቂት መፈጸም በታሪካችን ውስጥ ጎልቶ የሚኖር አንድ ውርደት ነው፡፡ ከዚያም ከዚህም በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ንፁኃን ዜጎች የተማገዱበት፣ ከሕልፈትና የአካል መጉደል በላይ በዚያ መዘዝ የተበተኑ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ጥላቻና ቂም እንዲዘራም ጦርነቱ የድርሻውን የተወጣ ምዕራፍ ነበር፡፡

በእርግጥ በዚያ ሁሉ አሰቃቂ ወቅት የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተቀራራቢ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ አኗኗር፣ አለባበስ፣ እምነት፣ ወዘተ ውስጥ ኖረዋል፡፡ በጦርነት ውስጥም ሆኖ ተዋልደዋል፣ ተጋብተዋል፣ አብረው ተሰደዋል፡፡ በሐዘንና በደስታም በጋራ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን ገዥዎችም ሆኑ (የነፃነት ታጋዮች ሻዕቢያና ጀበዓ) ለየራሳቸው የፖለቲካ ትርፍ ሲሉ የረጩት ዘረኛና አልባሌ ቅስቀሳ የራሱን ጥቁር ጠባሳ አላሳረፈም ባይባልም እንደ ሰው የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የከፋ ግጭት ነበራቸው ሊባል አይችልም፡፡ ቢያንስ እንደ ደቡብ ሱዳን፣ እንደ ህንድና ካሽሚር ወዘተ በእምነትና በአመለካከት የሚጠራጠሩባት ነገር አልነበረም፡፡

ለኤርትራ አገር መሆን ዕውቅና በመስጠት ረገድ ትልቁንም ሚና የተጫወተው ኢሕአዴግ ሲሆን፣ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት የተሰበሰቡ የፖለቲካ ኃይሎችም በአመዛኙ ሐሳቡን ተቀብለውታል፡፡ በእርግጥ ሻዕቢያ ለ30 ዓመታት የተዋጋበት ‹‹የነፃነት ዓላማ›› መፍቻ መንገድ ‹‹ነፃነት›› ብቻ ካልሆነ ሌላው አማራጭ ዝግ እንደነበር ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡ ቢያንስ ከአሰልቺውና ከረዥሙ ጦርነት በመላቀቅ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ወደ ሰላምና ዕድገት ለመጓዝ፣ ለሁለቱም አገሮች በውጭ ኃይሎችም ሆነ በራሳቸው የቀረበው አማራጭ ‹‹ነፃነት›› (አንዶች መንገጠል የሚሉት) ነበር፡፡

ይህ የፖለቲካ ውሳኔ ቀድሞ ያለቀለት በመሆኑም የኤርትራ ሕዝብ የሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ዕድል ሲፈጠር ‹‹ነፃነት በባርነት›› በሚል ቅንብብ አማራጮች ታጥሮ አንድ ጉዳይ ብቻ እንዲመርጥ ተደርጓል የሚሉ ተቺዎች ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ በወቅቱ የአሁኖቹ የኤርትራ መሪዎችም ሆኑ የአብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎቱ ‹‹ነፃነት›› ለመሆኑ የተለያዩ ማሳያዎች ነበሩ፡፡ በአንድ በኩል ለዓመታት ስቃይና መከራ ካተረፈላቸው ጦርነት በመላቀቅ በአንድ በኩል አጋር በሆኑለት ሽምቅ ተዋጊ መመራት ማንም የሚፈልገው ነው፡፡ በሌላ በኩል በውጭም ሆነ በውስጥ ኃይሎች የኤርትራውያን ጠላት ደርግና ገዥዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢሕአዴግን ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደሆነ የተካሄደው ዘመቻ ቀላል አይደለም፡፡

እዚህ ላይ የተፈጠረው መሠረታዊ ስህተት ግን በግልጽ ሕግና ሥርዓት፣ በታሪክም ሆነ በፖለቲካ ሚዛን የሁለቱንም አገሮችና ሕዝቦች ጥቅም የሚያስከብር ሕዝበ ውሳኔና ስምምነት አለመፈጸሙ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙዎች የተለያዩ ሐሳቦችን ቢሰነዝሩም፣ ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› በሚል የቀድሞው የሕወሓት/ኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ ገብሩ አሥራት ያነሱት ሐሳብ በቂ ማሳያ ያለው መረጃ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

በኢትዮጵያና ነፃ በወጣችው ኤርትራ መካከል በአጭር  ጊዜ የድንበር ወሰን ማበጀት ባይቻል እንኳን፣ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ስምምነት ላይ አለመደረሱ አንዱ ጉድለት ነው፡፡ በወደብ አጠቃቀም ላይ ግልጽ ደንብና መመርያ ሳይኖር ‹‹ኢትዮጵያ በነፃነት እንደፈለገች መጠቀም ትችላለች›› በሚል ጊዜያዊ ውሳኔ መደለሏም ሌላኛው እንቅፋት ነበር፡፡ በሁለቱም አገሮች የሚኖሩ የየአገሮቹ ዜጎች አኗኗርና ሀብት የማፍራት መብት ግልጽ አለመሆን በርካታ የሻዕቢያን ተልዕኮ ያነገቡ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ የመንግሥት ኃላፊነት፣ በኢኮኖሚው ዋነኛ ሞተር በሆኑ ሴክተሮች ላይ በአመራርነት መቀመጥ፣ ለኢትዮጵያውያኑ ግን በኤርትራ የተገደበ (የሁለተኛ ዜግነት) አሠራር መዘርጋት፣ ከግብርና ከቀረጥም ሆነ ከጉምሩክ አሠራር ጋር በተያያዘ በሕግ የተገደበና ግልጽ አሠራር አለመኖር፣ የድንበር ላይ ንግድና የገንዘብ ልውውጥ ቅጥ ያጣ መሆን፣ ወዘተ ከብዙዎቹ መሰናክሎች ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡

በዚህ ላይ ኢሕአዴግ ሰፊውን አገር ይዞ በሰላምና በማረጋጋት ሥራ፣ ከቂምና ቁርሾ ወጥቶ ወደ ኅብረ ብሔራዊነት የሚመጣ ሕዝብ ለመገንባት በውስጥ አቅምና በዜሮ የመንግሥትነት ልምድ ሲባትት፣ የኤርትራ መሪዎች ከደባ ባልፀዳ ፖለቲካ ‹‹እናውቅልሃለን›› ጣጣ ውስ ገብተው እንደነበርም ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ዘግይቶ እንደተጋለጠው ቆይተው ለሚፈጸሙት የኃይል ጥቃት ማዳከሚያ ሥልት ለመዘርጋት የአገሪቱን ሕዝብ የማለያየት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ታሪክን በማዋረድ የሥነ ልቦናና በላይነት ለመያዝ የተኬደው ርቀትም ቀላል አይደለም፡፡

በአደባባይ ታግተው ደብዛቸው የጠፋ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራውያን፣ በየጎዳናው በሻዕቢያ ታጣቂዎች የተገደሉ ኢትዮጵያውያን፣ ትልልቅ ጄኔሬተሮችና ማሽነሪዎች ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ተነቅለው እንዲገቡ መደረግ፣ ኢሕአዴግ ነባር  ታጋዮቹን እንዲበትን ሲመክሩ እነሱ ወደ ማጠናከርና አዲስ ምልመላ መግባታቸው፣ አዲስ የወደብ ኪራይ ታሪፍ ማውጣት፣ በኋላም የኢትዮጵያውያንን ንብረት ከወደብ መዝረፍና የገንዘብ አጠቃቀምን የመለወጥ አሻጥር፣ ወዘተ›› የሻዕቢያ ደባ ውጤቶች ናቸው ብለዋል አቶ ገብሩ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ የሁለቱን አገር ሕዝቦች በቀጠሉበት የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ለመለያየት ተሞክሯል፡፡

ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተከባብሮና ተቻችሎ የሚኖርበትን ጎዳና ከመጥረግ ይልቅ  በጥላቻና በስድብ ድሪቶ የመጀቦኑ ፖለቲካዊ ሒደት ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት በባድመ መዘዝ የተለኮሰው የሁለቱ አገሮች ግጭትና በኋላም አስከፊ ጦርነት መነሻው እነዚህ የጥፋት መንገዶችና ሕግና ሥርዓት ያልገደባቸው አካሄዶች ነበሩ፡፡ ይህን ሀቅ ኢሕአዴግም በተለያዩ የግምገማ ሰነዶቹ እንደ ጉድለት አንስቶታል፡፡ በኤርትራ ነፃነት ጉዳይም ሆነ በወደብ ባለቤትነት ላይ ጥያቄ ቢነሳም በነገ ይስተካከላል ሒሳብ ያልተቋጩ ጉዳዮች ነበሩ ብለዋል፡፡

ከሻዕቢያ በሁለቱም ወገን እስከ 70 ሺሕ ሕዝብ ካለቀበት ጦርነት በኋላ በበረሃ ትግሉም ሆነ በሰባት ዓመቱ (ከ1984 እስከ 1990) የሰላሙ ጊዜ ከሚለው በላይ የኤርትራን ሕዝብ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ለመነጠል እየሠራ ነው፡፡ ለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በብሔራዊ ቴሌቪዥኑም ሆነ በሬዲዮ ጣቢያው ዕለት ተዕለት የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ካለፈው ‹‹የነፃነት›› ትግል ታሪኩ በመነሳት ወራሪ፣ ቅኝ ገዥና ጠላት እያለ የሚገልጸው ደርግን ወይም የአፄ ኃይለ ሥላሴን አገዛዝ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሆኗል፡፡ በልማትና በዴሞክራሲ አልሳካ ያለውን ፎቃቃ ጊዜ በጠላትና በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተሳሳተ ታሪክን ትውልዱ እንዲያመነዥክ በማድረግ እንዳይገናኝ እየቆረጠውም ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያውያን በታሪካችን በጣሊያን ፋሽስት አገዛዝ በተፈጸመብን ወረራ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን አልቀውብናል፡፡ የአካል ጉዳትና የሞራል ድቀት የደረሰበት ትውልድም አልፏል፡፡ የወደመው የአገር ቅርስና ሀብትም ቀላል አይደለም፡፡ የዚያ ያደፈ  ታሪክ ባለቤት ግን ከ60 ዓመታት በፊት የነበረው የጣሊያን አገዛዝ እንጂ፣ የጣሊያን ሕዝብ ነው ብለን አናውቅም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ጣሊያናውያን በአገራችን በሰላምና በክብር የሚኖሩት፡፡ እንዲሁም ያንኑ ያህል ኢትዮጵያውያን በጣሊያን በፍቅር እየኖሩ ያሉት፡፡ አገዛዝና ሕዝብ ፍፁም የተለያዩ ናቸውና፡፡

ሻዕቢያ ግን እየሄደበት ያለው የጥፋት ጉዞ እንደምን በሕዝቦች መካከል መቀራረብና ፍትሐዊ አንድነትን ለመፍጠር ያስችላል? ማለት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶችም ኢሕአዴግ (የኢትዮጵያ መንግሥትስ) ቢሆን ሕዝብን ከሕዝብ ለማቀራረብ ምን የተለየ ዕርምጃ ወሰደ? ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ በእኔ በኩል የኢትዮጵያን መንግሥት ቢያንስ በኤርትራ የነፃነት እጦትና ድህነት አንገሽግሿቸው እየመጡ ያሉ ወጣቶችን (እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 110 ሺሕ ደርሰዋል) ተቀብሎ በአግባቡ ያስተናግዳል፡፡ ከስደተኞቹ ካምፕ ባሻገር በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እንዲኖሩና በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙም እያደረገ መሆኑን እንደ አንድ መልካም ተግባር እወስደዋለሁ፡፡

ከመነሻው ጀምሮ የኤርትራን ሕዝብና ሻዕቢያን ለመነጠል የሚያካሂደው ፕሮፓጋንዳም ቢሆን መስመሩን ያልሳተና ተገቢ ነው፡፡ ሒደቱ ብዙም ተስፋ የሚጣልበት ባይመስልም፣ ሻዕቢያን በነፍጥ እንፋለማን የሚሉ ኤርትራውያን የፖለቲካ ኃይሎችን ለመደገፍ የሚያደርገው ጥረትም አለ፡፡ ያን ያህል የጎላ ዕርምጃ ተወስዶ አመርቂ ውጤት ባይገኝም፣ በኢትዮጵያ የልማትና የሰላም ኢንስቲትዩት በኩል ‹‹የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦችን የሚያቀራርብ መርሐ ግብር›› አለ፡፡ ይህ ጉዳይ ግን ከፖለቲካ ትርፍ ያለፈ ነገር ያለው አልመሰለኝም፡፡

አንድ የነበሩ የሁለቱ አገር ሕዝቦች የባላንጣነት ጉዞ ግን የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ከወደብ፣ ከድንበርም ሆነ ከ‹‹አንድ አገር›› እንፍጠር ቅዠት በፊት ሕዝብ ለሕዝብ ምን ደረጃ ላይ ነን? ማለት ይገባል፡፡ ከወራት በፊት በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደ አንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የሁለቱ አገሮች ዜጎች በዘረኝነት የፖለቲካ የዞረ ድምር ምክንያት ለከፍተኛ ድብድብ በቅተዋል፡፡ በሌላው ዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ሆነውም ታይተዋል፡፡ አልፎ አልፎ በአንዳንድ የጋራ ሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ በሰላማዊና የተቃውሞ ሠልፎች በአንድ ላይ የሚገናኙ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ስደተኞች እንኳ፣ አብረው እንዳይቆሙ የተማማሉ ከመሰሉ መዋል ማደራቸው ነው የሚነገረው፡፡

በአዲስ አበባ የሚኖሩ ብዙዎቹ ወጣት ኤርትራውያን ስደተኞች ከሌላው የአገሬው ሰው ጋር ከመቀራረብና መግባባት ይልቅ፣ መጠራጠራቸው ጎልቶ እንደሚታይ መካድ አይቻልም፡፡ በብዙዎቹ የኮንዶሚኒየም የጋራ መንደሮች ተከራይተው እንደመኖራቸው በራሳቸው የቡናና የሻይ ወይም የምግብና የመጠጥ ቤቶች መጠቀም፣ በተናጠል ብቻ የመሰብሰብ (ከሶማሊያ ስደተኞች በባሰ ሁኔታ) አካሄድ ነው የሚያሳዩት፡፡ ሌላው ቀርቶ ትግርኛ ከሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር እንኳን መግባባትና መቀራረብ ስለመፍጠራቸው ምንም ምልክት የለም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በተፈጠረው ዕድል በመጠቀም ንብረት ሸጦ በፍጥነት ለመውጣት ያለው ሩጫም ያለመተማመን ውጤት ነው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ጉዳይ ፖለቲካም ሆነ በግልግል ኮሚሽኑ ሐሳብ መሠረት መቋጫ እንዳልተገኘለት ይታወቃል፡፡ ሁለቱም መንግሥታት ‹‹ግትር›› በሚመስል አቋም ከአሥራዎቹ ዓመታት በፊት የያዙትን መከራረከሪያ እንደጨበጡና የጎሪጥ እየተያዩ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እየተጠናከረች ስትሆን፣ ኤርትራ በተቃራኒው እየነጎደች ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ550 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞችን አነጋግሮና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መረጃ አገላብጦ ሰሞኑን ባቀረበው ሪፖርት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ኤርትራን ከቀዳሚዎቹ ተርታ አሠልፏታል፡፡ ሕዝብና አገርን በሕግና ሥርዓት ከመምራት ይልቅ በአፈናና በፍርኃት መግዛት የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች መፈጸም በማለት ኤርትራን ቁልጭ አድርጎ አቅርቧል፡፡ በሌላ መረጃም ኤርትራ ከሶሪያ ቀጥላ ከፍተኛ የዜጎች ስደት የሚስተዋልባት (ካላት ስድስት ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ሩብ ያህል ተሰዷል) እንደሆነ በመነገር ላይ ነው፡፡ የሽማግሌና የአሮጊት አገር መስላ ወጣቶቿን ያጣች የእርግማን ምድር መሆኗንም ማስተባባል ያዳግታል፡፡

ከሁሉ በላይ የኤርትራ ሕዝብ እያጋጣመው ላለው መከራና ስቃይ በሥርዓቱ ውስጥ ሳይቀር አመራር የነበሩ ሰዎች እየተሰደዱ ያወጡት መረጃ ማረጋገጫ ነው፡፡ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የተመኘውን ‹‹ነፃነት›› ሳያጣጥም የተገፈፈው የኤርትራ ሕዝብ፣ ተጎሳቁሎና ደስታ ርቆት እየኖረ ለመሆኑ የኤርትራን ቴሌቪዥን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ አገሪቱ ወደብ እያላት ደህይታለች፡፡ ወርቅን በመሰለ የተፈጥሮ ሀብት የምታገኘው ገቢ ቢኖርም፣ ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን በጦረኛው መንግሥት ወታደራዊ አባዜና በአገዛዙ ቁንጮዎች ዙሪያ እንደሚባክንም ይፋ እየሆነ ነው፡፡

በተቃራኒው  ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሻዕቢያ ሰላም በማደፍረሱ እላፊ ዕርምጃ አይውሰድ እንጂ፣ ምስጥ እንደበላው አገዳ በቆመበት እስኪንኮታኮት ዝም እንበለው ያለ ይመስላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሚነድፋቸው የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ኤርትራን እስከ መዘንጋት የደረሰ መስሏል፡፡ ወደብ ሲነሳ ጂቡቲ፣  ፖርት ሱዳን፣ አለፍ ሲልም ሶማሌላንድና በርበራን ሲጠቅስ አሰብና ምፅዋን ‹‹ተከድነው ይብሰሉ›› ብሏል፡፡

ከዚህ ጋር የሚያያይዘው የመንገድና የባቡር መሠረተ ልማትም ኤርትራን እንደ ጎረቤት እየቆጠረ አይደለም፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የአፍሪካ የኃይል ቋት ለመባል በሚከናወኑ ፕሮጀክቶችም ቢሆን በኩራዝ ጭላንጭል ውስጥ ላለችው ኤርትራ ስለመሄዱ ምልክት የለም፡፡ ሻዕቢያን ያህል ጋንግሪን የወደቀባት ኤርትራ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአፍሪካ ኅብረትም ሆነ ከኢጋድ ከመነጠሏም በላይ የኢትዮጵያን ጉርብትና ማጣቷ የሕዝቧን የመከራ ዘመን እያስረዘመ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የኤርትራ ሕዝብ ሸክምና ዕዳ ማን ያቃለው? ማለት ተገቢ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ዕርምጃስ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ አያፈላቅቀው ይሆን? ብሎ መመርመር ብልህነት ነው፡፡

ከዚሁ ሁሉ በላይ በሁለቱ አገሮች የፖለቲካ አቋም ለውጥም ሆነ የሥርዓት መቀየር ቢመጣስ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ፍትሐዊ አንድነትና ዴሞክራሲያዊ እኩልነት፣ ለመገንባት ይቻላቸው ይሆን?! የሚለው ጉዳይ የውይይት ርዕስ ሊሆን ግድ ነው፡፡ የሁለቱም አገሮች ምሁራን ከጥላቻ ቆፈን ሳይላቀቁ፣ ሻዕቢያም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ስለሕዝብ ለሕዝብ ጉዳይ ከፍ ያለ ዕርምጃ ሳይወስዱ፣ በተለይ ሻዕቢያ የጥላቻ መርዙን አጠናክሮ እየረጨ፣ ኢትዮጵያውያኑም መጠራጠርንና ‹‹ተገንጣይ›› ማለትን አሟጠው ሳይቀይሩ እንዴት ያለ መልካም ዝምድና ይመልስ ይሆን?

በጦርነቱ ሰሞን የሁለቱ አገሮች የሃይማኖት መሪዎች ወጣ ገባ ያሉበትን ሽምግልና ካቆሙት አሥር ዓመታት አልፈዋል፡፡ በወታደራዊ መስክም ቢሆን ሸራ በለበሱ ታንኮች ከተፋጠጥን ያንኑ ያህል ዕድሜ ተቆጥሯል፡፡ ሻዕቢያና ኢሕአዴግ  መንግሥታቱን የሚፋለሙትን መደገፍ አላቆሙም፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ዝቅ ያለ ቢሆንም የቃላት ጦርነቱም እየተጧጧፈ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲታይ የሁለቱ ጣጣቸው ያላላቀ አገሮች ሕዝቦች ፍትሐዊ አንድነት ጉዳይ እንዴት ይጠናከር ይሆን? ማለት ተገቢ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles