Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊአጋጣሚ የፈጠረው ማዕከል

  አጋጣሚ የፈጠረው ማዕከል

  ቀን:

  ገና ድክድክ ሲል ያሳይ የነበረው ባህሪ ከሌሎች ሕፃናት የተለየ ነበር፡፡ በወቅቱ የአንድ ዓመት ከሁለት ወር ሕፃን ነበር፡፡ ያለመታከት ለረጅም ሰዓት የመጫወቻ ቁሳቁሶቹን ይደረድራል፡፡ ሲበሳጭ እጁን ይነክሳል፡፡ ጤናውን በመጠራጠራቸው በተለያዩ የሕክምና መስጫ ቦታዎች ወስደውታል፡፡ ያገኙት ምላሽ ግን ምንም ዓይነት የጤና ችግር እንደሌለበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የልጃቸው ሁኔታ የጤና አለመሆኑ ታውቋቸዋል፡፡ በሚያገኙት ምላሽም ተደላድለው አልተቀመጡም፡፡

  በአንድ አጋጣሚ ግን ጥርጣሬያቸውን አረጋገጡ፡፡ ‹‹በዓረብ ቻናል የሚተላለፍ ፕሮግራም ነበር፡፡ ፕሮግራሙ የኦቲዝም ሕፃናት ሁኔታን የሚያሳይ ነው፡፡ ሕፃናት አውሮፕላን ሲደረድሩ፣ ሲበሳጩ ራሳቸውን ሲጐዱ ይታይ ነበር፡፡ ሁኔታቸው ከኔ ልጅ ጋር ስለተመሳሰለብኝ አትኩሬ እከታተል ጀመር፤›› የሚሉት ወ/ሮ ራሔል ዓባይነህ ልጃቸው የኦቲዝም ተጠቂ መሆኑን ተረዱ፡፡

  እውነታውን መቀበል አቅቷቸው ብዙ ተቸግረው ነበር፡፡ ‹‹አለቅስ ነበር፡፡ ‹ብዙዎችም ገና ዕድሜ ልክሽን ታለቅሽ› ይሉኝ ነበር፤›› በማለት ተስፋ ያስቆረጧቸው ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ራሔል የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ ልጆቹን ለማሳደግ ከሥራ ገበታቸው ከቀሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የኦቲዝም ተጠቂ የሆነው ሁለተኛው ልጅ ዛሬ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ነው፡፡

  የኦቲዝም ተጠቂ መሆኑን ባወቁበት ወቅት በጊዜው ብቸኛ ወደ ሆነው ጆይ የኦቲዝም ማዕከል ወስደውት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ቦታ አልተገኘለትም፡፡ ‹‹በተጠባባቂ መዝገብ ላይ ተመዘገበ፡፡ ከእሱ በፊት 459 ተጠባባቂ ተመዝጋቢዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ዓይነት መቼም አይደርሰውም ብዬ አለቀስኩ፤›› በማለት ሌሎች አማራጮችን ማፈላለግ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡

  የተለያዩ መንገዶችን ቢሞክሩም አልተሳካም፡፡ በመሆኑም የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ያላቸውን ወላጆች በማነጋገር የኦቲዝም የሕፃናት ማቆያ ለማቋቋም ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ ወሎ ሠፈር አካባቢ ነህምያ የሚባል የኦቲዝም ሕፃናት ማቆያ አቋቋሙ፡፡ በወቅቱ የረዷቸው የተለያዩ አካላት ነበሩ፡፡ ማዕከሉን ያቋቋሙት ከስድስት ወላጆች ጋር ሲሆን፣ ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ስድስት የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ነበሩት፡፡ ልጆች የሚማሩበት ሰባት ክፍሎች ነበሩ፡፡ ሦስት አስተማሪዎችን መቅጠር ችለውም ነበር፡፡ ራሱን የቻለ ገቢ ስላልነበራቸው የአቅም እጥረት ነበረባቸው፡፡ የቤት ኪራይ ለመክፈልም ብዙ ይቸገሩ ነበር፡፡

  የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ገንዘብ ለማሰባሰብ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ ስለዚህም በተለያዩ ተቋማት በመዘዋወር ተቋሙን በማስተዋወቅ ዕርዳታ መጠየቅ ጀመሩ፡፡ በዚህም የተሻለ ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡ ከበፊቱ የተሻለ መሄድ ቢችሉም አሁንም የገቢ እጥረት ማነቆ ነው፡፡ አሁን ላይ የተማሪዎች ቁጥር 40 የደረሰ ሲሆን፣ 10 የመማሪያ ክፍሎችና 22 አስተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ ከልጆች ማቆያነትም ወደ ማዕከልነት ተሸጋግሯል፡፡

  ወ/ሮ ራሔል እንደሚናገሩት፣ በኦቲዝም ረገድ አሁንም ችግሮች አሉ፡፡ ድርጅቶች ኦቲዝምን በተመለከተ በጀት የላቸውም፡፡ ተማሪዎችን በበቂ ለማስተማርም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሳይማሩ ዕድሜያቸው እየሄደ ይገኛል፡፡ ‹‹ኦቲዝም ከዕድሜ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሕፃንነታቸው ከደረስንላቸው በቀላሉ መግራት ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ በአገር ውስጥ ከ300,000 እስከ 600,000 የሚሆኑ የኦቲዝም ተጠቂዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ትምህርት ያገኙት በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹እኛ ብቻ 250 በተጠባባቂነት የተመዘገቡ ታዳጊዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ራሔልን ያገኘናቸው አምቦ ጠበል ለሦስት ወራት ያደረገውን የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አስመልክቶ፣ ሐሙስ ሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በቢርጋርደን በተዘጋጀ የምስጋና ምሽት ላይ ነበር፡፡

  ወ/ሮ ኢየሩሳሌም ታዬ የአምቦ ጠበል ማርኬቲንግ ማናጀር እንደሚሉት፣ አምቦ ጠበል የማኅበራዊ ግዴታ ለመወጣት ነህምያ የኦቲዝም ማዕከልን የጐበኘው ከሦስት ወራት በፊት ነበር፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም ሠርቷል፡፡ በከተማው ውስጥ በሚገኙ በርካታ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ከአምቦ ውኃ ጠርሙስ ጋር ስለኦቲዝም መረጃ የሚሰጡ ካርዶችን በማዘጋጀት ለሦስት ወራት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሠርቷል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በቢርጋርደን ባዘጋጀው የምስጋና ምሽት፣ ለነህምያ የኦቲዝም ማዕከል የ100,000 ብር ስጦታ አበርክቷል፡፡

  የነህምያ መሥራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ራሔል፣ መሰል ዝግጅቶች ቢበራከቱ በርካታ ሕፃናትን መታደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img