Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሞባይል ጌም ሱስ

የሞባይል ጌም ሱስ

ቀን:

ባለትዳርና የሦስት ዓመት ልጅ እናት ነች፡፡ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ትሠራለች፡፡ የተለያዩ የሞባይል ጌሞችን ትጫወታለች፡፡ ከምትጫወታቸው የተየዩ የሞባይል ጌሞች ቴምፕል ረን (Temple Run2) በጣም የምትወደው እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ሲመቸኝና ቁጭ ስል ነው የምጫወተው›› ብትልም ሞባይል ጌም በመጫወት መሥራት ያለባትንና የምትፈልጋቸውን ነገሮች ከመሥራት እንደምትዘናጋ ልደበቀችም፡፡ ለምሳሌ ሕፃኑን ልጇን መጠበቅ እያለባት ወይም የሚሠራ ሥራ እያለ ቁጭ ብላ ጌም የምትጫወትበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ ቆይ አንዴ ቆይ አንዴ እያለች ለሰዓታት ልትቀመጥ ትችላለች፡፡ በዚህ ምንም እንኳ የእሷን ያህል ባይሆንም የሞባይል ጌም የሚጫወተው ባለቤቷ እናቷም ዘወትር ይማረራሉ፡፡

ለረዥም ጊዜአት ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ሞባይል ጌም መጫወቷን እንደ ችግር መገንዘብ አልቻለችም ነበር፡፡ ዘግይታም ቢሆን መጨረሻ ላይ ግን ችግር ውስጥ መሆኗን ተረዳች፡፡ ይህን የተረዳችው ሥራ ገበታዋ ላይ ሁሉ ጌም መጫወቱን ስትያያዘው ነው፡፡ ‹‹እጄ እንደማያርፍ ገባኝ፡፡ ሞባይሌን ካነሳሁኝ ጌም ነው የምጫወተው፡፡ የሰው ሞባይል ካነሳሁኝም ጌም ነው የምከፍተው›› ትላለች፡፡ ቤት፣ መሥሪያ ቤት፣ ታክሲ ላይ አልጫወትም የምትልበት ቦታ አለመኖሩን፤ ከሦስት ወራት በፊት ግን ስልኳ ላይ የነበሩ ጌሞችን ሁሉ በማጥፋት ራሷን እንዳስቆመች ነገረችን

ባላት ትርፍ ጊዜ ሁሉ በሞባይል ስልኳ ጌም እንደምትጫወት የነገረችን ወ/ሮ እመቤት ታደሰም ባለትዳርና የሁለት ሕፃናት እናት ነች፡፡ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ አካውንታንት ነች፡፡ እንቅልፏን አጥታ ወይም ሥራ ትታ ባትጫወትም ታክሲ ውስጥ፣ ቤት፣ ቢሮና በሌሎችም ቦታዎች ከመጫወት ወደ ኋላ አትልም፡፡ ‹‹ስልኬ ባትሪ ሲያልቅና በመብራት አለመኖር ቻርጅ ማድረግ ሲያቅተኝ ጌም መጫወት ባለመቻሌ እበሳጫለሁኝ፡፡ እንቅልፌን እስካጣ ወይም ሥራ ትቼ ባልጫወትም ባገኘሁት ጊዜ ሁሉ የትም ቢሆን መጫወቴ ትንሽም ቢሆን ሱስ የሆነብኝ ይመስለኛል›› ትላለች፡፡ እሷ አብዛኛውን ጊዜ የምትጫወተው ካንዲ ክራሽ (Candy Crush) የሚባለውን ጌም ሲሆን፣ ነጥብ በመጣል አፕልኬሽኑ ለ24 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ እንዳትጫወት ሲያግዳት በዚህ ጊዜ ውስጥ ካርታ በመጫወት እንደምትጠብቅ ትናገራለች፡፡

ሞባይል ጌም መጫወት ሱስ የሆነብኝ በትንሹ ነው የምትለው ራሷን ከጓደኛዋ ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ ጓደኛዋ ምሳ ለመብላት አዝዘው እየተጠባበቁ እንኳ ማረፍ አትፈልግም ትጫወታለች፡፡ ከሰው ጋር ነኝ ወይም ቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር ብላ ከመጫወት ወደኋላ አትልም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አቶ ዳዊት መክብብ በማንኛውም ጊዜ ጌም ይጫወታል፡፡ ቢሮ፣ ታክሲ ውስጥ፣ ቤትና አንድ ሁለት እያለ ለመዝናናት ቁጭ ካለበትም እጁ ከሞባይል አይለይም፡፡ ‹‹ባለቤቴ በጣም ስለምትበሳጭብኝ ሁሌም የሆነ የሆነ ነገር ትናገረኛለች፡፡ እኔ ግን እሺ አንዴ እያልኩኝ መጫወቴን እቀጥላለሁኝ፡፡ አልጋ ውስጥ ገብቼ እንኳ እንቅልፍ እስኪጥለኝ እጫወታለሁኝ›› ይላል፡፡

አሁን ግን ጌም መጫወት ካቆመ ሁለት ወር ሆኖታል፡፡ ላለመጫወት ወስኖ ሳይሆን የሞባይል ቀፎው (BlackBerry) ሁለት በተኖች አልሠራ በማለታቸው ነው፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ግን ቀፎ እንደሚቀይር ይህም በተለይ ጌም ለመጫወት ሲል የሚያደርገው እንደሆነ ይናገራል፡፡ Temple run እና subway surfers የሚባሉትን የሞባይል ጌሞች የሚጫወት ቢሆንም እንደ ወ/ሮ እመቤት አብዛኛውን ጊዜ የሚጫወተው ግን Candy Crush እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ባለቤቱ ብቻ ሳትሆን የሥራ ባልደረቦቹና ጓደኞቹ ዘወትር ስልኩ ላይ በመጠመዱ እንደሚበሳጩ፤ ብዙ ጊዜም ስልኩን በመቀማት ሊያስቆሙት እንደሚሞክሩ ይናገራል፡፡ ብዙ ጊዜ መጫወት ከጀመረ የሚያቆመው የስልኩ ባትሪ ሲያልቅ ብቻ ነው፡፡

ያነጋገርነው ሌላ በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ ወጣት በቀን አንዴ አልያም ሁለት ጊዜ ጌም እንደሚጫወት ገልጾልናል፡፡ እሱም የሚጫወተው Candy Crush የተሰኘውን ሞባይል ጌም ሲሆን፣ የሚጫወተው ታክሲ ሠልፍ ላይ እንዲሁም ብዙም ደስ ከማይሉት ሰዎች ጋር ሲሆን፣ እንደሆነ ይናገራል፡፡

ልጃቸውና ዕድሜአቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ የልጅ ልጆቻቸው ብቻም ሳይሆኑ በቅርብ የዘመድ ለቅሶ ለመድረስ ወደ ዓለም ባንክ አካባቢ ሔደው አንድ አዛውንት በሞባይል ስልካቸው ለቅሶ ቤት ውስጥ ጌም ሲጫወቱ መመልከታቸው በጣም እንዳስገረማቸው በስልሳዎቹ አጋማሽ የሚገኙት ወ/ሮ ዓለም ገብረኪዳን ነግረውናል፡፡ ሴት ልጃቸው ለልጆች ምግብ መሥራት እያለባትና የምትሠራው ብዙ የቤት ሥራ እያለ ስልኳ ላይ እንደምትጠመድ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕፃን ልጅ ምግብ ለማብላት እሺ እሺ እያለች አንድና ሁለት ሰዓት ስልኳ ላይ ትቀመጣለች፡፡ ቤት ውስጥ ሁሉን ነገር ደቃቅና እንኳ ስልኳ ላይ ስትውል ምንም አይመስላትም›› ይላሉ፡፡ ልጃቸው ጉዳዩ እንደ ሱስ እንደሆነባት በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡

መገናኛ ከሚገኝ አንድ ሞባይል ጥገና ቤት በመግባት ምን ያህል ሰዎች የሞባይል ጌሞች ለማስጫን ጐራ እንደሚሉ ጠየቅን፡፡ አንድሮይድና አይፎን ያላቸው ልጅ አዋቂ ሳይባል ሞባይል ጌሞች ያስጭናሉ፡፡ ብዙዎች እንዲጫንላቸው የሚጠይቁት Temple Run 2 የሚባለውን ጌም ሲሆን፣ በዛ ያሉ ጌሞችን አንድ ላይ በመጫን ከሀምሳ እስከ ስልሳ ብር እንደሚያስከፍሉ ገልፀውልናል፡፡ ብዙዎች የሚጫወቷቸው ሌሎች ጌሞች Truck parking parking lot speed car የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ወጣቶች ብቻም ሳይሆኑ ልጆችና ታዳጊዎች ጭምር በሞባይል ጌም መጠመዳቸው የተስተዋለበት ጊዜ ነው፡፡ የትኛውም ቦታ ላይ አጠገብ ካለ ሰው ጋር ከመነጋገር፣ በቤት ውስጥም ከቤተሰብ ጋር አንዳንድ ነገሮችን ከመጨዋወት ይልቅ ሁሉም እጅና ዓይኑን ከሞባይል ስልኩ ላይ አድርጐ ነው የሚታየው፡፡ በዚህ መልኩ በልጆቻቸው፣ በትዳር አጋራቸውና በጓደኞቻቸው የተቸገሩ ብዙዎችን አነጋግረናል፡፡ የማጥናት፣ የመሥራት ኃላፊነታቸውን ለሞባይል ጌም ሲሉ የሚተው፣ መሔድ ካለባቸው ቦታ የሚቀሩና ማድረግ ያለባቸውን ነገር ማድረግ ባለባቸው ሰዓት ማድረግ የተሳናቸውን አግኝተናል፡፡

ብዙዎች ከሚጫወቷቸው የሞባይል ጌሞች በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ Temple Run2 ሁለተኛ ሲሆን፣ Candy Crush ስምንተኛ ነው፡፡ ካንዲ ክራሽ የተሰኘው ሞባይል ጌም በጣም ሱስ የሚያስይዝ ሲሆን፣ በዚህ ጌም ሱስ የተያዙ ሰዎች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ማውጣት፣ የቤት ወይም የቢሮ ሥራ ትተው በጌም እንደሚጠመዱ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ራሳቸው ላይ ከበድ ያለ ችግር የሚያመጡ መኖራቸውም በተለያዩ ሪፖርቶች ተመልክቷል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ይህ የጌም አፕሊኬሽን ከመጣ ጀምሮ 151 ቢሊዮን ጊዜ ሰዎች ተጫውተውታል፡፡ በiOS በአንድሮይድና በፌስቡክ አንደኛ ደረጃን የያዘ የሞባይል ጌምም ነበር፡፡ መቀመጫውን ስቶኮልም ስዊድን ያደረገው የሞባይል ጌሙ ፈጣሪ ኩባንያ ከ23 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አንዱ ካንዲ ክራሽ እንደሚጫወት አስታውቆ ነበር በወቅቱ፡፡

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ትልቁ በሞባይል ጌሞች የመጠመድ አሉታዊ ተፅዕኖ ሰዎችን ከሌሎች ትልቅና ጠቃሚ ተግባራት ማደናቀፉ ነው፡፡ ሰዎች በሥራቸው ትኩረት እንዲያጡና እንዲዘናጉ ያደርጋል፡፡

የእንቅልፍ ችግር፣ ከባድ ራስ ምታት፣ የጀርባ ሕመም፣ የምግብ ፍላጐት ማጣትና ሌሎችም የሞባይል ጌም ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሱሱ የሚያስከትለው ማኅበራዊ ቀውስም ከባድ ነው፡፡ የቀጠሩት ሰው ቢደውል፣ መገኘት ያለብዎ ቦታ ላይ መገኘት ያለብዎ ሰዓት ቢደርስ ወይም ሌላ ጉዳይ ‹‹ቆይ አንዴ ይችን…›› በማለት ነገር ዓለሙን ትቶ ከስልክ ጋር መነጋገር መቀጠል ብዙዎች ላይ እየታየ ያለ ነገር ነው፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሞባይል ጌም ሱስ ከበረታ ሱሰኞች ከእውነታው ዓለም ጓደኛና ዘመድ ወይም ከሞባይል ጌም ዓለም አንዱን ለመምረጥ የሚገደዱበት ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ምርጫቸው የሚሆነው የሞባይል ጌም ዓለም ነው፡፡ ረዥም ጊዜአቸውን ጌም በመጫወት ስለሚያሳልፉ ማኅበራዊ ግንኙነቶቻቸውን ይዘነጓቸዋል ከናካቴውም ሊረሷቸው ይችላሉ፡፡ በሞባይል ጌም ሱስ ከተጠመዱ ባለትዳሮች ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት በሞባይል ጌም መጠመዳቸው በትዳራቸው ውጥረት እንዳስከተለ ተናግረዋል፡፡ ለሞባይል ጌም ቅድሚያ በመስጠት ብዙዎች እያወቁም ይሁን ሳያውቁ በማኅበራዊ ሕይወታቸው አደገኛ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ አንዳንዶች በሞባይል ጌም መጠመድን በሕይወታቸው በኑሮአቸው ከገጠሟቸው ችግሮች እንደማምለጫም ይመለከቷቸዋል፡፡ በሞባይል ጌሞች ከመጠመዳቸው ባለፈ ከሰዎች ጋር በሚነጋገሩባቸው ጥቂት ደቂቃዎች እንኳ ወሬአቸው ሁሉ ሞባይል ጌም በመሆኑ ሰዎች የሚርቋቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡  

የሞባይል ጌም ሱስ የተለያዩ ችግሮችን ሊያስከትል የሚችል አደጋ ነው፡፡ እንደ ሌሎች ሱሶች የሕክምና ዕርዳታ የሚያስፈልገው ነው የሚለው አከራካሪ ቢሆንም ጥቂት ለማይባሉ የሞባይል ጌም ጊዜ ከማሳለፊያነት የዘለለ በመሆኑ ቢያንስ ቤተሰብና ጓደኛ ከዚህ ሱስ እንዲወጡ ማገዝ አለበት የሚለው ብዙዎች የሚስማሙበት የመፍትሔ አቅጣጫ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ