Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የመድኃኒት ያለህ አትሉም ወይ?

ሰላም! ሰላም! ዛሬም እንደ ወትሮው በጆሮ ዳባ ልበስ መዓቱን ‘ኢግኖር’ እያደረግን እዚህ ደርሰናል። ለማም ገለማ ጅማት ከሥጋ ያባጠሰች እያንዳንዷ ስሜት ከታሪካችን አትፋቅም። ምን ይታወቃል? ታሪክ መፋቅ ካርድ እንደ መፋቅ ቀላል የሚመስለው ይኖር ይሆናል እኮ። ‹‹ጉድ›› አለ የፈላበት! አንድ ቱባ ወዳጄ ባለመቶ መቶውን ካርድ እንደ ፈጣን መፈቅፈቅ በለመደ እጁ፣ ሕይወቱም ላይ ብዙ የሚፍቃቸው ነገሮች ሲፈልግ አስተዋልኩላችሁና ነው ይኼን ጨዋታ መጀመሬ። በነገራችን ላይ ፋቂና ጠራቢ መከበር ያለበትን ያህል ሳይከበር፣ እንደሚወራው በተግባር በእኩልነት አንቅልባ ሳይታዘል ካርድ የሚፍቅ ሰው ሲቀናበት ማየቴ ይገርመኛል። አግራሞቴ ሙያን ቁልቁል የማየት ያልተገራ ባህላችን ላይ ብዙ ሳያስለፈልፈኝ በፊት (ለፍልፈንም በሆነልን የሚሉትን እያስታወስን) ይኼው ወዳጄ ምን እንዳለኝ ላጫውታችሁ። ጨዋታም አይደል?!

በሚታየውና በሚዳሰሰው የዓለም ወሬና የፀባይ ለውጧ ስተክዝ (ዓለም በስተርጅና የመፈንዳት ቀጠሮ እንዳላት ሳናውቅ ‘ሎቲ’ አንጠለጠሉ፣ ቀበቶ አላሉ ብለን ስላማናቸው አዛውንት ጎረምሶች ይቅር ይበለንና) ‹‹ወይ ፍዳ እግዚኦ›› ምናምን ስል፣ ‹‹ምንድነው አንተ እዚህ ድረስ የጨለመብህ? ቆይ አንተ ምንህ ተነካ?›› ብሎ ወዳጄ፣ የፍርድና የትዝብት አስተያየት አየኝ። ‹‹አትፍረድ ይፈረድብሃል›› ልለው አሰብኩና የዘመኑን ሰው ወደ ልቡ የሚመልሰው የአምላክ ቃል ሳይሆን የሳይንስና ምርምር  ትንተና መሆኑ ትዝ አለኝ። እናም፣ ‹‹አታይም ይኼን የእርድ ዜና? በየቀኑ እየጨመረ አዕምሯችንን በከለው እኮ። ቀስ በቀስ ከተላመድነው በኋላማ እንጃ የሰው ሥጋ የሚሸጥባቸው ቄራዎች መከፈታቸው ነው፤›› አልኩት። የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እያላችሁ አደራ። በጎደለ መሙላት ከመንግሥት ብቻ ተጠብቆ እንዴት ይኖራል? ወዳጄ ወዲያው ማሽሟጠጡን ትቶ ይደግፈኛል ስል፣ ‹‹ይልቅ እርድ ስትል ባለፈው ስላጫወትከኝ የከባድ መኪኖች ዕቃ ተበልቶ ወደሚሸጥበት ቦታ ደረስ ብለን እንምጣማ። አንደኛው ገልባጭ መኪናዬ ዕቃ ሰብሮ መንገድ ላይ ቆሟል፤›› ብሎ ጨዋታውን ወደ ‘ቻፓ’ ዘረዘረው። ‹‹ምንም ቢሆን ሥር ነው እንጂ ዕጢ አይደማም›› ብዬ እኔም እመራው ጀመር። ግና ሥራችን ሰው መሆን መስሎኝ? እ?

ስንጓዝ አስብ ነበር። ምንም ማሰብ እንደምንችል አምነን የተጠቀምንበት ስንት እንደምንቆጥር ባላውቅ፣ ዓለምን ዓለም አቀፋዊ የሐዘን ሳምንታት እንድታውጅ የሚያስገድዳት ጭካኔ መብዛት ሰላም ሊሰጠኝ አልቻለም። አንዳንዴ ሰላም ተመኝቶ ሰላም ማጣት የጤነኛ ሰው ምልክት ይመስለኛል። መቼም የዘመኑ ሰው እከሌ አለው ካልተባለ አባባልና ጥቅስ ሲነገረው፣ ሽንጥ ሳይዘለዝል ባዶ እንጀራ ባዋዜ ተምትመው እንዳጎረሱት ሁሉ ዓይኑ ይቀላል። ያየሁትን ነው! እናላችሁ የአንዱ ስቃይ ላንዱ ተድላ፣ ያንዱ ዋይታ ለሌላው ጭፈራ ሲሆን ሳይ ዕፍረቴ እየባሰ ነው። በሌላ አባባል ጉበት ታሞ ጥርስ አግጦ ሲስቅ፣ እሾህ በውስጥ እግር ሰርጎ ትከሻ እስክስታ ሲመታ እንደማየት ማለት ነው። ገንዘብ መጣያ ያጡ በየአደባባዩ በረባ ባረባው ወዴትም ለማንም ሲበጥሱ አየን ብለን፣ መንፈቅ ጉድ እያልን አንገት የተረፋቸው በገዛ ቤታችን በየቴሌቪዥን መስኮቶቻችን አንገት ሲበጥሱ እያየን፣ እጅ ካላጨበጨብኩ የሚለው ምን ነክቶት ነው ብለን መጠያየቅ የለብንም እንዴ? መልሱልኛ?!

በበኩሌ ይኼን ያህል ግለኝነት ጢባጢቤ እየተጫወተብን እንዳለ አለማስተዋሌ ከራሴ ጋር ፀብ ይከተኝ ጀምሯል። እንዲያው በቃ ወደ እኛ ያልተወረወረ ድንጋይ ሁሉ ሰብሉን ወፍ እንዳይጨርሰው እንደሚወረወር ጠጠር መቁጠራችን የጤና አይመስለኝም። እንዲህ ከራሴ ጋር በግለ ሂስ ተወጥሬ ሳለሁ ወዳጄ፣ ‹‹ይኼን ዘፈን ሰምተኸዋል?›› ብሎ የሙዚቃውን ድምፅ ከፍ አደረገው። ከራስ ጋር መደማመጥ ቸግሮት ሰው እንዴት ብሎ ቅኝት እንደሚያደምጥ አይገባኝም። እየደነቆርኩ ዘፈኑን ሰማሁለት። ‹‹ይኼ እኮ ታዲያ የድሮ ዘፈን ነው›› ስለው ‘ኖ’ አዲስ ነው። አሁን (እከሌ) አሻሽሎ ተጫውቶት ነው፤›› አለኝ። ምን እላለሁ? ‹‹አሪፍ ነው›› ብዬ ዝም አልኩ። ‘ዓለም ለካ የሰላም እጥረት ብቻ አይደለም ይንጣት የያዘው። የፈጠራ ሥራም ነው’ ብዬ ጭጭ። ‹‹ዝምታ ነው መልሴ›› እንዳለው ዘፋኙ። እኔም ታጠብኩ ስል ጭቃ ነካኝ እንዴ?

የሄድንበትን ጨርሰን ከወዳጄ ጋር ስንለያይ ያሰበልኝን ሸጎጠልኝና ‹‹እንደማይህ ግን እንደ ዘመኑ እያሰብክ አይደለም። በዚህ አያያዝህ እንኳን እንደሚወራብህ ሕንፃ ልታቆም መንነህ ጎጆህን ሳታፈርስ አትቀርም፤›› ብሎ፣ ስቆ መኪናውን እያስጓራ ተለየኝ። ኧረ ዘመን መቼ ነው? ዛሬ ነው? ነገ? ወይስ ትናንት? ሁሉም በኖረበት የዛሬ ዘመን ሰው ሲል ከተረተ የትኛው ጊዜ ነው እሴቱን አክብሮ፣ የሰው ልጅ እንደ ሰው የሚኖርበት ንጋትና ድቅድቅ ያለው? አልኳችሁ በቃ፣ በቆምኩበት ፈዝዤ ሰው አላሳልፍ አልኩ። ኋላ አንዱ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ነፍሱ አንድ መንገዱ አንድ ቀን ሥልጣን ይዘህ እስኪዘጋልህ እንለፍበት። እስከዚያ እንጀራችንን አትዝጋው፤›› ብሎኝ አለፈ። ወዲያው ባሻዬ ‹‹የእብድ ገላጋይ ስለት ያቀብላል›› ብለው የሚተርቷት ተረት ውልብ ብላኝ ፈገግ አልኩ።

ይኼኔ በቅርብ ርቀት ሲታዘበኝ የነበረ ጨርቁን የጣለ የአዕምሮ በሽተኛ ሲሮጥ መጣና (እሱንስ ‹‹የእብድ አጫዋቹ ሙር ነው›› ብለው የሚተርቱ አባቱ ትዝ ብለውት እንደሆን ማን ያውቃል? ትዝታና ታሪክ የእኛ ብቻ የሚመስለን እኮ እያስቸገርን ነው) ‹‹አሌ ቡም እንጫወት?›› ብሎ ቀኝ እጁን ከጀርባው ደበቀ። ስልኬ ይጠራል። የሥራ ስልክ ነው። ለማንሳት እያገነገንኩ በዚያ የአዕምሮ ታማሚ ዓይኖች ውስጥ ሰመጥኩ። እንደ ዘመኑ መኖር አቅቷቸው አስመስለን አንበላም፣ የደም ውርስ ለዘር አናውርስም ብለው ሲገፉና ሲረሱ የሚደርስላቸው ያጡ የአዕምሮ ሕሙማን ተሠልፈው ታዩኝ። መንገድ ከወደቁት፣ ቤት ንብረት ይዘው ቤተሰብ እያስተዳደሩ በታወከ መንፈስ ተስፋ የለሽ ትንፋግ የሚተነፍጉ ዜጎች በዙብኝ። የወደቁትን ከማንሳታችን በፊት ብዙ የምንወድቅ እንዳለን ሳስብ ግን አቃተኝና መንገድ ጀመርኩ። ወይ ሕይወትና አሌ ቡሟ!

አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ መግዛት የሚፈልግ ደንበኛዬን አነጋግሬ ሳበቃ ሳይውል ሳያድር ላሳየው ቀጠርኩት። ያው እንደምታውቁት በአገራችን መቅጠር እንጂ መድረስ ከባድ ነው። ማቀድ እንጂ ማሳካት ህልም ነው። ማፈንዳት እንጂ ማዳፈን እንዴት ጭንቅ እንደሆነ ለኖረ አይነገረውም። ‹‹. . . ዳሩ ትናንትን ዛሬ እያሰከረው ብዙ ነገር የገባን መስሎን ሳይገባን እየዘለለን ነው። ከታሪካችን አስታውሰን ልንማርበት የሚገባንን ሁሉ እንደምንዘለው ለጤናችን አስበን ገመድ እንኳ አንዘልም፤›› ይሉኛል ባሻዬ የሰሞኑን አጥንት ሰርሳሪ ብርድ ቁርጥማት ለቆባቸው ጨምድዶ ቤት እያስቀመጣቸው ልጠይቃቸው ስሄድ። መቼም እሳቸውን ታውቋቸዋላችሁ። ሲያመሩም ሲቀልዱም ወግ ይችሉበታል።

ደግሞ መቼ ዕለት ነው ‹‹አንተ ምነው ወጣት ካልተሆነ በረደኝ ተብሎ ሚስት አይፈለግም እንዴ? እስኪ ሚስት ፈልግልኝ፤›› አሉኝ። ‹‹አይ ባሻዬ በፍለጋ ቢሆን ንፋስ እስከዛሬ ስንት ሚስቶች ይኖሩት ነበር?›› ስላቸው ከት ብለው እየሳቁ፣ ‹‹እኔ እኮ ገለባ ስለማንገዋለል አልጠየቅኩህም? ከአጨዳና ከጉልጓሎ የቱ እንደሚቀድም የተምታታበት ትውልድ በ‘ኢንተርኔት’ የትዳር አጋር ሲጎለጉል ይውላል ሲባል ስለሰማሁ ለምን ይቅርብኝ ብዬ እንጂ። በላ ምን ይጎለኛል?›› ብለው ሳቃቸውን እስኪጨርሱ አጀብኳቸው። ባሻዬ ለቀልድ ነገሩን አነሱት እንጂ እንኳን ትዳር ወገባችንን ታጥቀን የተያያዝነው የአገር ልማት በጎደለ ተሞልቶም አልሞላ ብሏል። እናላችሁ ከሕዝብ ተቀላቅዬ ወደ ደንበኛዬ ስገሰግስ አንዱ፣ ‹‹በቅርቡ ሳተላይት እናመጥቃለን የሚሉን መጀመሪያ መቼ ምድር ለምድር መጠቅን? የታለ ባቡራችን? ራዕይ ከመደራረብ ምናለበት ከሥር ከሥሩ ጫና ብናቀልና የዋልንበትን አረም ባይበላው?›› እያለ ሰውን ሲያስጨንቀው ሰማሁ። ተጨንቆ አስጨናቂ ብቻ ይሙላው መንገዱን?!

በሉ እንሰነባበት። የዋልኩበት ውዬ ከወጪ በቀር ትርፍ የሌላት ገንዘብ ሸቃቅዬ ወደ ቤቴ ስጓዝ ባሻዬ ደወሉልኝና አንድ የምናውቀው የሠፈራችን ሰው በጠና መታመሙን ነገሩኝ። ሠፈር እንደደረስኩም ቤት ገባ ብዬ ስለታመመው ወዳጃችን ለማንጠግቦሽ ነገርኳት። ፍራፍሬ ይዘን ቤቱ ስንሄድ ባሻዬና ምሁሩ ልጃቸው ቀድመውን ኖሮ እዚያው አገኘናቸው። ቢታወቅልንም ባይታወቅልንም እያንዳንዳችን ‘እህህ’ የሚሰኝ ሕመም አናጣም። በሽታ የውስጥ ደዌ ብቻ ነው ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው። እንዲያውም ውዷ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ኧረ እንዲያውም አንዳንዶቻችን ተቀደን የምንሰፋበት ሥፍራው ጠፍቶ እንጂ ‘ሰርጀሪም’ የሚያስፈልገን ነን፤›› ስትለኝ ነበር። አዎ ደግሞ መጠያየቅ መልካም ነገር ነው። ደግሞ በዚህም የሚከራከር አይጠፋም ብዬ እኮ ነው። ምን ይታወቃል? ይኼው በውኃ ቀጠነ ጭቅጭቅና ክርክር ከደባል ሱስና ከሙሰኛው በላይ አገር እያመሰ አስቸግሮናል። ምን ያልተቸገርንበት አመል አለ አትሉም? እንዲያው እኮ!

እና ታማሚውን ዓይን ዓይኑን ስናየው ቆይተን ባሻዬ፣ ‹‹አይ ቋሚ። የቋሚ መከራው ትናንት ጤና የነበረ ሰውዬ እንዲህ ለአንድዜ ይውደቅ፣›› እያሉ ቆያይተን፣ ‹‹ለመሆኑ ምንድነው አሉህ በሽታው?›› አልነው። ወዳጃችን እያቃሰተ፣ ‹‹ምንም የተጨበጠ ነገር የለም፤› ብሎ ብዙ ተነፈሰ። አጥብቆ ጠያቂው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሐኪሙ ምንም አላለህም? ምንም ዓይነት ተጨማሪ ምርመራ አላዘዘልህም?›› ሲለው ወዳጃችን በምጥ፣ ‹‹ኧረ ምንም፡፡ እኔም አጥብቄ አልጠየኩትም። ይኼው መድኃኒት አዞልኛል መዋጥ ነው፤›› ብሎን ዓይኖቹ ሲስለመለሙ ዕረፍት ያድርግ ብለን ምሕረቱን ተመኝተን ወጣን። የባሻዬ ልጅ ግራ ገብቶት፣ ‹‹እንዴት ያለ ነገር ነው በሽታው ሳይታወቅ መድኃኒት የሚታዘዝለት?›› እያለ ሲነዘንዘን አባቱ ቀበል አድርገው፣ ‹‹አንተስ ከመቼ ወዲህ ነው በሽታችን ታውቆ መድኃኒት ሲታዘዝልን ዓይተህ የምታውቀውን ነው የምትጠይቀን?›› ብለው ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት። የባሻዬ ጥያቄን በጥያቄ አመላለስ ፍቺው ብዙ፣ አንደምታው ሰፊ መሆኑ ገብቶኝ እኔም እንደተዘጋሁ ማንጠግቦሽን አስቀድሜ ቤቴ ገባሁ። ግን የቱ ይቀድማል? በሽታችን ሳይታወቅ ኮሶ ከመጋት ማን ይሆን የሚታደገን? አንዱ ነው አሉ፡፡ ይታመምና ሐኪም ዘንድ ይሄዳል፡፡ ያመመው ራሱን ነው፡፡ ሐኪሙ ደግሞ ለሆድ ቁርጠት የሚሆነውን ያዝለታል፡፡ ታማሚው በጣም ገርሞት፣ ‹‹ዶክተር ምነው ራሴ ሊፈነዳ ነው ስልህ የሆድ ቁርጠት መድኃኒት የምታዝልኝ?›› ብሎ ሲጠይቀው፣ ‹‹አዝኜልህ ነው እንጂ በስካር ያሳመምከውን ራስህን በዱላ እተረክክልህ ነበር፤›› አለው አሉ፡፡ ‘መድኃኒቴን የሚያውቅ አስታማሚ ጠፋ’ ማለት ይኼኔ አይደል? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት