Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹አንድ የማይታፈን ድምፃችን ፌስቡክ በመሆኑ ሳናበላሸው ልንጠቀምበት ይገባል›› ሕይወት እምሻው

‹‹አንድ የማይታፈን ድምፃችን ፌስቡክ በመሆኑ ሳናበላሸው ልንጠቀምበት ይገባል›› ሕይወት እምሻው

ቀን:

‹‹(መቼም የሁላችንም ቤት፣ 24 ሰዓት ውኃ ከሚያገኘው 75 በመቶ አዲስ አበባ ውጪ ነው መሰለኝ) ላለፉት በርካታ ወራት እንደ ማንኛውም አዲስ አበባዊ በስምንት ወይ በአሥራ አምስት ቀን፤ እንደ ሌባ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ብቅ ትልና ቁ…ር…ር ብላ ወዲያው ከምትጠፋው ውኃ በስተቀር ባንቧ ከፍቼ ውኃ ሲፈስ የማየት ወግ ርቆኛል፡፡

‹‹(እንደውም አሁን ለሥራ ከአገር ወጣ ስል የሚያጓጓኝ ዘመናዊ ሕንፃና ሱፐር ማርኬት ማየት ሳይሆን ቧንቧ ከፍቶ ውኃ ሲፈስ ማየት ሆኗል፡፡ ሆቴል እንደገባሁ ቧንቧውን ክፍት አደርግና፣ ‹‹ፓ…!›› እላለሁ ውኃ ሲወርድ እያየሁ፡፡)

‹‹ይህ እንዲ ሆኖ ሳለ የውኃ ሒሳቤ ግን እየጨመረ ነው፡፡ መቼም መማረር እንጂ ማምረር ያልቻለ ሕዝብ መልስ አያገኝም፤ ግን ውኃ ልማት ውኃ ማቅረብ ቢያቅተው የቧንቧ ኪራዩን እንኳን ባይጨምርብን ምናለ፡፡››

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕይወት እምሻው ‹‹ነቆራና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር›› በተሰኘ የፌስቡክ ገጿ ካሰፈረችው የተቀነጨበ ነው፡፡ ጽሑፎቻቸውን በማኅበረሰብ ድረ ገጽ ከሚያካፍሉ አንዷ ስትሆን፣ ገጿ በርካታ ተከታይ አለው፡፡ ወቅታዊ የሚባሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን ታስነብባለች፡፡ አብዛኛውን የማኅበረሰቡን ክፍል ያማከሉ ሊባሉ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ትችት ትሰነዝራለች፡፡ የግል ምልከታዋን ከሚያንፀባርቁ ሥራዎች በተጨማሪ የፈጠራ ጽሑፎቿም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በቅርቡ ለንባብ ከበቁ የፈጠራ ሥራዎቿ መካከል ‹‹ሸሌ ነኝ›› እና ‹‹ማሂ ድንግሏ›› ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹ቀስቃሹና የተንቀሳቃሹ ምርጫ ቅስቀሳ›› ለአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተካሄደውን ቅስቀሳ ተመርኩዛ ያሰፈረችው ነው፡፡ ሕይወት የኮሙዩኔኬሽንና አድቮኬሲ ባለሙያ ናት፡፡ በአንድ የግል ኮሌጅ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ታስተምራለች፡፡ በትርፍ ጊዜዋ ደግሞ ትጽፋለች፡፡

የተወለደችው መንዝ በሚገኘው መሐል ሜዳ ነው፡፡ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ የአንድ ዓመት ሕፃን ነበረች፡፡ በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ገባች፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች እዛው ግቢ ውስጥ የምትታዘባቸውን ሁነቶች ተንተርሳ በባህል ማዕከል ወጎች ታቀርብ ነበር፡፡ በእውቀቱ ሥዩምና ሌሎችንም ጽሑፎቻቸውን የሚያቀርቡበት ወቅት ነበር፡፡ ባህል ማዕከል ወጣት ጸሐፍት የወጡበት እንደሆነ የምትናገረው ሕይወት፣ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ረቡዕ ዕለትን ‹‹እንደ በዓል በጉጉት እንጠብቀው ነበር›› ስትል ትገልጻለች፡፡ ከዚህ  ዓለም በሞት የተለዩት አባቷ አቶ እምሻው ዓለማየሁ ‹‹ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣልያ የአገዛዝ ዘመናት›› የሚባል የትርጉም መጽሐፍ አላቸው፡፡ አባቷ አዘውትረው መጽሐፍ መግዛታቸው አብዝታ እንድታነብ እንደገፋፋትና ለሥነ ጽሑፍ ዝንባሌዋም አስተዋጽኦ እንዳረገ ትናገራለች፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምትማርበት ወቅት በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቿ በጉልህ ባትታወቅም ጥሩ ጅማሮ ሆኗታል፡፡ አሁን የምትገኝበት ደረጃ ለመድረስ ትልቁን ሚና የተጫወተው ፌስቡክ የከፈተው መድረክ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ወግ ለመጻፍ  መነሻዋ የመስፍን ሀብተማርያም ሥራዎች ናቸው፡፡ በልጅነቷ ያነበበችው ‹‹የቡና ቤት ሥዕሎች›› የተሰኘው መጽሐፍ አጻጻፍ ዘዬ እንደማረካት ትገልጻለች፡፡ ቀለል ባለና እንደ ጨዋታ በሚመስል መልኩ ከተጻፉት ወጎች ብዙ መማሯን ታክላለች፡፡  

ከሌሎች የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች ወግ ይቀላታል፡፡ ‹‹ወግ የምጽፈው በማወራበት መንገድ ነው፤ ወግ በትርፍ ጊዜ በቀላሉ መጻፍም ስለሚቻል መርጨዋለሁ፤›› ትላለች፡፡ በጋዜጣ ላይ ሥራዎቻቸውን የምትከታተላቸው ኤፍሬም እንዳለ፣ በእውቀቱ ሥዩምና በኃይሉ ገብረ እጊዚአብሔር ከመስፍን ቀጥሎ የምትጠቅሳቸው ጸሐፊዎች ናቸው፡፡

የፌስቡክ ገጽ ከከፈተች ወደ ስድስት ዓመት ገደማ ቢሆናትም፣ ጽሑፎች ማስፈር የጀመረችው ከ2005 ዓ.ም. አንስቶ ነው፡፡ የጀመረችው በዕለት ከዕለት ሕይወቷ የምትታዘበውን ‹‹ነቆራ›› በሚል በማስፈር ነበር፡፡ ከአንባቢዎች  አበረታች ምላሽ  ስታገኝ ገጽ ከፍታ በተከታታይ መጻፍ ጀመረች፡፡

‹‹ፌስቡክ ከሌላው ሚዲያ በተሻለ ነፃነት ይሰጣል፡፡ በሌላው ሚዲያ ዕድሉን ያላገኘን ሰዎች ድምፃችንን የምናሰማበት መንገድ ነው፤›› በማለት ታስረዳለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ መደበኛው ሚዲያ በመንግሥት ወይም በግለሰቦች ባለቤትነት የተያዘ ነው፡፡ ሚዲያዎቹ የየባለቤቶቻቸው ሐሳቦች የሚንፀባረቁባቸው ሲሆኑ፣ ድምፅን ማሰማት የሚቻልባቸው ሚዲያዎች ብዙም አይደሉም ትላለች፡፡ ፌስቡክ የመጻፍ ነፃነት ከመስጠቱም ባሻገር ከአንባቢዎች ፈጣን ምላሽ የሚገኝበት ሁነኛ መንገድ እንደሆነ ታክላለች፡፡

እንደ እሷ እምነት፣ ፌስቡክ የሚሰጠው ነፃነት በጸሐፊዎች ላይ ኃላፊነት የሚጥልም ነው፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ለማይችሉ ሚዲያው የማጥፋት ኃይል ያለው መሆኑ አሉታዊ ጎኑ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ፌስቡክ ለጽሑፎች ፈጣን ምላሽ ቢገኝበትም፣ ሁሉም ምላሾች ገንቢ አይደሉም፡፡ የፌስቡክ ጸሐፊዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚሞክሩ ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም ትላለች፡፡

 ሕይወትን ያስለቀሷት፣ ቅስሟን የሰበሯት አስተያየቶችን ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ለምን እንዲህ እየተባልኩ እጽፋለሁ?›› ብላ ራሷን የጠየቀችባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በእሷ እምነት ይህ የሚመነጨው ሰዎችን ከሥራቸው ነጥሎ መተቸት ሲቻል፣ ግላዊ ጥቃት የሚሰነዘሩ ብዙ ስለሆኑ ነው፡፡

ባጠቃላይ ፌስቡክ ብዙዎች ራሳቸውን የሚገልጹበትን መንገድ እንደቀየረ ታምናለች፡፡ ‹‹ድምፄን ማሰማት መቻሌና የማስበውን ማስተላለፌ መታደል ነው፤›› በሚል ትገልጸዋለች፡፡ ፌስቡክን የሚጠቀሙ እንዲሁም የሷን ገጽ የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥር አናሳ ቢሆንም በተወሰነ መልኩም በአንባቢዎቿ ላይ ተፅዕኖ እንደምትፈጥር  ታምናለች፡፡ ከአንባቢዎች በሚሰጧት ምላሾች ላይ በመመርኮዝ የአንዳንድ ግለሰቦችን ምልከታ በአንዳች አቅጣጫ መለወጧን ተገንዝባለች፡፡

የምትመርጣቸው ርእሰ ጉዳዮች በሷ አልያም በሌሎች ብዙ ያልተጻፈባቸው መሆናቸውን ከግምት ታስገባለች፡፡ ‹‹ሚዛን የሚደፉ የምንላቸውን፣ በጣም የወደድኳቸውንና ለአንባቢ ይመጥናል የምለውን አካፍላለሁ፤›› ትላለች፡፡ አብዛኞቹን ምልከታዎች አምናባቸው እንደጻፈቻቸው ትገልጻለች፡፡ ጊዜና ገንዘባቸውን መስዋዕት አድርገው ለሚያነቡ ሰዎች ይመጥናሉ ትላለች፡፡ በብዛት ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ስለምትሰነዝር እያንዳንዱን ክስተት የተመለከተ ትችት እንድትጽፍ የሚጠባበቁ አሉ፡፡ ባሻት ጊዜ መጻፍ ለምትፈልገው ሕይወት፣ ይህ አንባቢዎች የሚያሳድሩባት ተፅዕኖ ነው፡፡

ከጽሑፎቿ መካከል የሴቶችን ጉዳዮች የሚዳስሱ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹የወንዶችና ሴቶችን እኩልነት የማምን ፌምኒስት ነኝ፤›› የምትለው ሕይወት፣ የሴቶችን ሕይወት ለማሳየት ወይም ሴቶችን ለማነሳሳት አልማ ባትፅፍም፤ ጽሑፎቿ ሴቶችን ሲያነቃቁ ስታይ ትደሰታለች፡፡

በአንድ ወቅት ሰሞነኛ መነጋገሪያ የነበሩ ጉዳዮች ላይ የጻፈቻቸው የተወሰኑ አስተያየቶች ይጸጽቷታል፡፡ ማሰላሰያ ጊዜ ሳትሰጣቸው በተጋጋለ መንፈስ ከተጻፉ መካከል ቤተልሔም አበራን ተችታ የጻፈችውን ትጠቅሳለች፡፡ በአብዛኞቹ ጽሑፎቿ ግን ደስተኛ ነች፡፡ በቅርቡ ‹‹የኢትዮጵያዊ ዋጋ ጥንቡን ጥሏል›› በሚል የጻፈችውን ታነሳለች፡፡ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ የተወሰደው እርምጃ ያልተቀናጀ ነው በሚል መንግሥትን የተቸችበት ነው፡፡

አብዛኞቹ ትችት አዘል ጽሑፎቿ መፍትሔ አመላካች እንደሆኑ ታምናለች፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ከኢትዮጵያ ስትወጣ የየአገሩን ተሞክሮ ስታከፍል ብዙዎች እንደሚማሩበት ተስፋ ታደርጋለች፡፡ እንደሷው ፌስቡክ ላይ ከሚጽፉ ግለሰቦች መሀከል የአሌክስ አብርሃምና ኢዮብ ምሕረተአብን ጽሑፎች ታደንቃለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመጡት ውስጥ አሳየ ደርቤና ሜሪ ፈለቀን ትጠቅሳለች፡፡

አዳም ረታ ከምታደንቃቸው ጸሐፊዎች አንዱ ነው፡፡ በጽሑፎቿ ላይ የሱ ዘዬ ተፅዕኖ ስለማሳደሩ እርግጠኛ ባትሆንም፣ ከሱ የተማረቻቸው ነገሮች እንዳሉ ትናገራለች፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን ስለ ጽሑፎቿ አስተያየት ሲሰጣት እንደሚያስደስታትም አልሸሸገችም፡፡ ከጽሑፎቿ ጋር የሚቀራረብ ርእሰ ጉዳይ የሚዳስሱና የምታደንቃቸውን ግለሰቦች ሥራዎች ለአንባቢዎቿ ታጋራለች፡፡ የዳንኤል ክብረትና የጌትነት እንየው ሥራዎች ይጠቅሳሉ፡፡

ሕይወት እንደምትለው፣ የማኅበረሰብ ድረ ገጽ በርካታ ጸሐፊዎችን እያፈራ ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ በመጻፍ የሚታወቁና መጻሕፍት ለማሳተም የበቁ ፀሐፊዎችን ትጠቅሳለች፡፡ ቢሆንም ሚዲያው ጥንቃቄ ያሻዋል ትላለች፡፡ ‹‹አንድ የማይታፈን ድምፃችን ፌስቡክ በመሆኑ ሳናበላሸው ልንጠቀምበት ይገባል፤›› ትላለች፡፡ ሰዎች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹና ሐሳባቸው እንዲከበር ታሳስባለች፡፡

ሕይወት ‹‹ባርቾ›› የተሰኘ መጽሐፏን በሚቀጥለው ሳምንት ታስመርቃለች፡፡ መጽሐፉ የወግና አጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ነው፡፡ ቀድሞ በፌስቡቡክ የቀረቡና መጠነኛ ለውጥ የተደረገላቸው ጽሑፎችም ተካተዋል፡፡ ሥራዎቿን በፌስቡክ የማያውቁ ግለሰቦችን ለመድረስ መጽሐፉ እንደሚረዳት ታምናለች፡፡ ‹‹ሰው እንደሚወደው፣ የመጽሐፍ መደርደሪያው ላይ ለማስቀመጥም ይመጥናል ብሎ እንደሚያስብ እምነት አለኝ፤›› ትላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...