ከሥነ ቃል ዓይነቶች አንዱ ተረት ነው፡፡ ተራቹ ‹‹ተረት ተረት›› ሲል መላሹ ‹‹የላም በረት›› ወይም ‹‹የመሠረት›› እያለ መመለሱ፣ አድማጭ ተረቱን ለማዳመጥ መስማማቱን መግለጹ ነው፡፡ ተራቹ በዚህ ብቻ አይቆምም፣ ወደ ተረቱ የሚዘልቀው ‹‹ላሙን ለኛ በረቱን ለእረኛ›› በማለት ነው፡፡
ተረት በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ቢኖርም አካሔዱ ግን እንደየብሔረሰቡ ትውፊት ይለያል፡፡ ይህ የተረት መንደርደርያ የተገኘው ከአዲስ አበባ ሰሜን ምሥራቅ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው አንኮበር ነው፡፡ አንኮበሮች ተረትን እንደ ቁም ነገር ማስተላለፊያ ማስተማሪያ /መማማሪያ፣ ይቅርታን ማስተማሪያ ብልሃት አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
‹‹ነገር በምሳሌ፣ ጠጅ በብርሌ፣ መዝሙር በሃሌ›› እንዲሉ አንኮበሮች ፍየልን በለፍላፊነት፣ ጦጣን በብልጠት፣ ዝንጀሮን በቂልነት፣ ኤሊን በአዝጋሚነት፣ በግን በየዋህነት፣ ጅብን በሆዳምነት፣ አንበሳን በጀግንነት፣ ዶሮን በረባሽነት በመጠቀም ቤተሰቦቻቸውን ልጆቻቸውን ያስተምሩበታል፡፡