Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርአባ ቃኘው የጅማ ከተማ ዕድገት

አባ ቃኘው የጅማ ከተማ ዕድገት

ቀን:

ስለጅማ ከተማ አጠቃላይ ገጽታም ሆነ ስለዕድገቱ ወይም ስለታሪካዊ አመሠራረቱ ለመጻፍና ለመናገር ያነሳሳኝ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሚያዝያና በግንቦት ወራት በተከታታይ በጅማ ዞን አስተዳዳሪና በጅማ ከተማ ከንቲባ የተሰጠውን ቃለ ምልልስ በማንበቤ ነው፡፡ አልደብቃችሁም፡፡ የጅማ ከተማ ፍቅርና ትዝታ አለብኝ፡፡ ለምን ብትሉኝ ተወልጄ ያደኩት በጊንጆ ጉሩ ቀበሌ ክልል ውስጥ ጅማ ከተማ ስለሆነ ነው፡፡ እንደማንኛውም ተወላጅ እኔም መልካሙን ሁሉ ለከተማው ነዋሪ ዕድገትና ብልፅግናን እመኛለሁ፡፡ በዚሁ በግንቦት ወር የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር በከተማው የተገነባውን ዘመናዊ አየር ማረፊያ መመረቃቸውን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አንብቤያለሁ፡፡ ሌሎችም ሥራዎች እንዲሠሩ ዝግጅት እንደተደረገ፣ ስለመሆኑም ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሰምቻለሁ፡፡ እንግዲህ እኔም በብዕሬ ስለከተማይቱ አጠቃላይ ገጽታ እውነታውን መጻፍ አሰኝቶኛልና ይህችን ጀባ ልበላችሁ፡፡

ስለጅማ ከተማ ለማውራትም ሆነ ለመጻፍ ብቁ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለጅማ ሲወራ፣ ሲጻፍም ሆነ ሲዘፈን አልፎ አልፎም ቢሆን ሰምቻለሁ፡፡ የጅማ ከተማ መሥራችና አስተዳዳሪ የነበሩት አባጅፋር እንደሆኑ ከታሪክ ተረድተናል፡፡ አባጅፋር መጠርያ ስማቸው ‹‹መሐመድ›› እንደሆነም በቅርቡ ከሬዲዮ መስማት ችያለሁ፡፡ ስለከተማዋ ጥንታዊነት ብዙ ተወርቷል፡፡ እኔ የምጨምረው የለኝም፡፡ እኔ የፈከሉት ግን እውነታውን በእኔ ምልከታ ለማስቀመጥ ነው፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ይተባበሩኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የጅማ ከተማ ምሥረታዋ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ዘመን ከምን ላይ ደርሳለች? የሚለውን በእኔ በኩል እንዲህ ለማለት ወድጃለሁ፡፡

ከተወለድኩባት መንደር ጊንጆ ጉድሩ ቀበሌ ልጀምርና የቀበሌው አስተዳደር ቀደም ባሉት ዓመታት ማለትም በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ጊዜ እንደነበረው ያለ ነው የቀበሌው አስተዳደር ቅጥር፡፡ ይኸውም የቀበሌው ነዋሪ የሚሰበሰብበት አዳራሽና የሠራተኞች ቢሮዎች ቀደም ሲል እንደነበሩት ናቸው፡፡ በቀሌው ግቢ ውስጥ 1970ዎቹ ጀምሮ የመዋዕለ ሕፃናት መማሪያ ቦታ አለው፡፡ እኔም እዚያው ግቢ ውስጥ ነው ፊደል የተማርኩት፡፡ እንደውም የፊደል መምህሮች መምህር አሉላና እማትርፌ እንደሚባሉም አስታውሳለሁኝ፡፡

- Advertisement -

ከዚህ መነሳቴ ምልከታዬን ግልጽ ያደርገዋል ብዬ ነው፡፡ አንባቢዎችም በደንብ ሊረዱኝ ይችላሉ በሚል እምነት ነው፡፡ በእርግጥ የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት በቀሌው ቦርድ አባላት የሚመራ ሲሆን፣ የውጭ ዕርዳታ ድጋፍ እንዳለውም ለመስማት ችያለሁ፡፡ ከዚህ የተነሳም ይመስላል ለውጦች ይታያሉ፡፡ ይህ ለልጆቻችን መልካም ነገር ነው፡፡ እንዲሁም በቀበሌው አካባቢ ባሉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የኮብል ስቶን የማንጠፍ ሥራ ጅምሮች እንዳሉም ተመልከቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ ቀበሌ መነሻነት ወደ ከተማዋ ዕድገትና ለውጦች እንዲሁም ከነዋሪዎቿ ስለሚነሳው የመልካም አስተዳደር ችግርና በእኔም በኩል ያጤንኩትን ለውጦች እንደሚከተለው ላቅርብ፡፡

‹‹ኩኒስ ጀለላ መጋላ ጂማ ናኖ ኦሮሚያ›› በሚለው ቅኝት በከተማዋ መግባቢያ ቋንቋ ጀምሬ ሐሳቤን ልግለጸው፡፡ በእርግጥ በከተማዋ ቀደም ሲል ከነበረው አስተዳደር የተሻሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም የከተማው ነዋሪዎች የሚዳኙበት ፍርድ ቤት ሥርዓት በኦሮምኛ ቋንቋ ሆኖ ቋንቋውን የማይችሉ ሰዎችም አስተርጓሚ በማቅረብ እንደሚዳኙ ለማጤን ችያለሁ፡፡ በዕድገት ላይ ያለ ዳኝነት በመሆኑ ከመልካም አስተዳደር አንዱ ትሩፋት ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ ልምጣና በተለያዩ ጽሑፎች ላይ ያነበብኩትን ወይም ከግለሰቦች በአፈ ታሪክ የሰማሁትን አሁን ላይ ባለሁበት አርባዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ ደግሞ የታዘብኩትን ላውጋችሁ፡፡ ተወላጅና ነዋሪ የነበርኩና በአሁኑ ወቅት በሥራ ምክንያት አዲስ አበባ የምገኝ መሆኑንም ልግለጽ፡፡  

ጅማ አባጅፋር የከተማዋ መሥራችና አስተዳዳሪ የነበሩት ዲፕሎማሲያዊ ጥበብን ይጠቀሙ እንደነበርና ከሌሎች መንግሥታትም ጭምር መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው ከታሪክ ለማወቅ ችያለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው አስተዳደር ካለፈው የአባጅፋር አስተዳደር ብዙ መማር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ነዋሪውን ለልማት ማነሳሳት የሚችልበትን ጥበብ ከአባጅፋር ታሪክ መውሰድ ይችላል፡፡ ሌላው ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመተለከተ ከነዋሪዎቹ የሚሰጠውን አስታየየት እንደ ግብዓት በመቀበል ለከተማዋ ዕድገትና ካላት የረዥም ጊዜ ታሪክ አንፃር መነሻችንን ማግኘት ይቻላል፡፡

እንግዲህ የከተማው አስተዳደር እንዳለ ሆኖ ግለሰቦች ባላቸው አቅም በመነሳሳት ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ሆነ ኢንቨስት ለማድረግ የሚደረጉ ሥራዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ በእኔ ቅኝት ደግሞ የታየኝን የመልካም አስተዳደር ጥቆማዎች ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡

ይኸውም በከተማዋ መተማመንን በመፍጠር ለነዋሪዎቿ ምቹ አስተዳደር እንዲሰፍን በማድረግ የከተማዋን የቀድሞ ፍቅር፣ አንድነትና ለሥራ አብሮ መነሳሳት የሚያስችለውን ወኔ ዳግም ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚህም ተጠቃሚው ሁሉም ሰው ነውና በዚህ አስተሳሰብ ጅማሬነት የከተማው አስተዳደር የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥርዓትን በመዘርጋት ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን እንዲያከናውን ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በግሌ በከተማዋ በሚከናወኑ አያሌ ሥራዎች ውስጥ ባለኝ አቅም እንደምሳተፍ ከወዲሁ ቃል በመግባት፣ ቃሌን በተግባር ለመፈጸም ይኸው በጋዜጣም ይሁን በሬዲዮ በተገኘው ሚዲያ በመጠቀም አስተዋጽኦዬን አበረክታለሁ፡፡ አብሮ አደጎቼንም ለዚሁ የብልጽግና ሥራ እንዲነሳሱና የየግላቸውን ክህሎቶች በመጠቀም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ፡፡

(መስፍን አራጋው፣ ከመጋላ ፊንፊኔ)

*********

አየር መንገዱ የአገልግሎት ክፍያን የሚከለከልበት የሕግ አግባብ

 አለውን?

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በቋሚ ሠራተኝነት ሳገለግል የቆየሁ ቢሆንም በአንድ ወቅት በሥራ እንቅስቃሴ ላይ ሳለሁ በፖሊስ ከሥራ ገበታዬ ላይ ተይዤ በሙስና ክስ ወንጀል ተጠርጥረሃል ተብዬ፣ በፀረ ሙስና ኮሚሽን በዓቃቤ ሕግ በኩል ክስ ከተመሠረተብኝ በኋላ ጉዳዩን ሲመለከተው የነበረው ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ በማድረግ መከላከል ሳያስፈልገኝ ከክሱ በነፃ አሰናብቶኛል፡፡

ወደ መሥሪያ ቤት በመሄድ ወደ ሥራ ገበታዬ እንድመለስ ውሳኔ ካገኘሁበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ለኮርፖሬት የሰው ኃይል አስተዳደር አቤቱታዬን ባቀርብም፣ ከተደጋጋሚ ጥያቄያዎቼ በኋላ በሐምሌ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ተጽፎ በተሰጠኝ ደበዳቤ ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገልጾልኛል፡፡ በመቀጠልም በመስከረም 15 ቀን 2007 ዓ.ም የአገልግሎት ክፍያና መልቀቂያዬን ከዚህ በፊት ዕንባ ጠባቂ በወሰነው መሠረት ብጠይቅም፣ አሁንም በመሥሪያ ቤቱ በኩል ፈቃደኛነት ያለበት ምላሽ አላገኘሁም፡፡ ይህንንም በመስከረም 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጽፎ በተሰጠኝ ደብዳቤ ገልጸውልኛል፡፡

ለ14 ዓመታት ድርጅቱን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገልኩና ምንም ዓይነት ክስ ከዚያ በፊት ያልነበረብኝ በመሆኔ ቢያንስ የዕንባ ጠባቂው የመፍትሔ ሐሳብ ሊፈጸምልኝ በተገባ ነበር፡፡

ውድ አንባቢዎች ወደ ዋና ፍሬ ነገሩ ልመለስና፣ ከሥራ ገበታዬ ላይ እጄ ከተያዘበት ከሚያዝያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ፍትሕ እስካገኘሁበት እስከ የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ በፍርድ ቤት በክርክር ሳለሁ ከእስር በዋስ ተፈትቼ በነበረበት ወቅት ወደ ሥራ ክርክር ችሎት በመሄድ ክስ ባቀርብም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሙስና የተጠረጠረ ሠራተኛ ከፍርድ ቤት ወደ ሥራ ቢመለስ በሌሎች ሠራተኞች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያመጣ ወደ ሥራ መመለስ የለበትም ብሎ በመከራከሩ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከዳመጠ በኋላ የእኔን ወደ ሥራ አለመመለስ ወሰነ፡፡

ይሁንና ፍርድ ያገኘሁበትን ደብዳቤ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን እስካገኘሁበት ጊዜ እስከ የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ በመታገስ ከቆየሁ በኋላ ማስረጃዬንና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመያዝ ወደ መሥሪያ ቤት በመሄድ በድጋሚ አቤት ብልም፤ አቤቱታዬ ለረዥም ጊዜ በኮሚቴ እየታየ ነው ጠብቅ በመባሌ በተስፋ ስጠብቅ ቆየሁ፡፡ ነገር ግን ምንም ምላሽ ስላጣሁ ጉዳዩን በግንቦት 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ወደ እንባ ጠባቂ ተቋም ይዤ በመሄድ የደረሰብኝን በደል ለማስረዳት ችያለሁ፡፡ የእንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 211/92 በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት በመርማሪ አማካይነት በደብዳቤ መሥሪያ ቤቱን በመጠየቅ ከአምስት ያላነሱ ደብዳቤዎችን ከተለዋወጠ በኋላ፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዳለ ሆኖ በጥር 29 ቀን 2005 ዓ.ም. የመፍትሔ ሐሳብ ሰጥቶበታል፡፡

ይሁንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመፍትሔ ሐሳቡን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ላለመፈጸም እንደምክንያት የሚያቀርበው ጥቅማ ጥቅምህን በወቅቱ አልጠየቅክም የሚል ሲሆን፣ እኔ ግን ጥቅማ ጥቅሜን ለመጠየቅ ይርጋ እንደማያግደኝና በጊዜውም አግባብ ባለው ፍርድ ቤት ጥያቄ ጠይቄ እንደነበር የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሰጠው የመፍትሔ ሐሳብ ላይ በዝርዝር በስፋት ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው የእንባ ጠባቂ ተቋም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ የአገልግሎትና የሥራ ልምዴን እንዲሰጠኝ በማለት የመፍትሔ ሐሳቡን ያስቀመጠው፡፡ እኔም ከዚህ በኋላ ከእንባ ጠባቂ ያገኘሁት መልስ ባለመኖሩ ወደ ሚዲያ ለመምጣት ተገድጃለሁ፡፡ ከሁሉም የሚገርመኝ ግን የመሥሪያ ቤቱ መልስ በተደጋጋሚ ‹‹ጊዜው ረዘመ›› የሚል መሆኑ ነው፡፡ እኔ ነኝ እንዴ ጊዜውን ያረዘመኩት ብዬ ስጠይቃቸው ግን መልስ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም እኔ ከመጠየቅ የቦዘንኩበት አንዳችም ጊዜ የለምና፡፡

 (ግርማቸው ገብረንጉሥ፣ ከአዲስ አበባ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...